ክፍለ ዘመኑን ለሚመጥን የሠለጠነ የሠላም ግንባታ ዋናው መንገድ ምክክር ነው

ሆሳዕና:- የ21ኛውን ክፍለ ዘመን የሚመጥን የሠለጠነ የሠላም ግንባታ ለማካሄድ ዋናው መንገድ ምክክር ነው ሲሉ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ተናገሩ። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚያካሂደው የአጀንዳ ማሰባሰቢያ የምክክር መድረክ ዛሬ ይጀመራል።

ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በክልሉ የሚካሄደውን የአጀንዳ ማሰባሰቢያ የምክክር መድረክ አስመልክተው ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ሁሉም አሸናፊ ሆኖ ሊወጣ የሚችልበትን መንገድ ለመቀየስ ተፎካካሪም ሆኑ ታጣቂ ወገኖች ወደ ምክክር ሊመጡ ይገባል።

ኮሚሽነሩ እንደተናገሩት፤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሚደረገው የአጀንዳ ማሰባሰብ መርሐግብር 82 ወረዳዎች፣ ከሦስት ልዩ ወረዳዎችና ከሰባት ዞኖች የተመረጡ የሕዝብ ተወካዮች ይዘዋቸው በመጧቸው አጀንዳዎች ላይ ምክክር ያደርጋሉ።

የሀገራዊ ምክክር ዋናው ዓላማ ቅራኔን በምክክር የመፍታት ልምድ እንዲዳብር፣ በሕዝብና በመንግሥት እንዲሁም በሕዝቦች መካከል መተማመን እንዲፈጠር ማድረግ ነው ብለዋል።

ኮሚሽነሩ እንዳመለከቱት፤ በክልል ደረጃ በአጀንዳና በተሳታፊ መረጣ የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት ከኅብረተሰብ ክፍሎቻቸው ያሰባሰቧቸው አጀንዳዎች ላይ በቀጣይ ቀናት የጋራ ውይይት ያደርጋሉ።

በመድረኩ የተለያዩ ሃሳቦችን በማዳበር የማጠቃለያ አጀንዳ የሚሰጡበት ሂደት መኖሩን ጠቁመው፤ በክልሉ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ማኅበራትና የመንግሥት አካላት፣ የተለያዩ ተቋማትና ማኅበራት ተወካዮች እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንደሚሳተፉ ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

መድረኩ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን አጀንዳዎችን ለይተው ለሀገራዊ ምክክር የሚውሉ አጀንዳዎችንና ተሳታፊዎችን የሚመርጡበት መሆኑን ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።

እንደ ዮናስ (ዶ/ር) ማብራሪያ፤ የምክክር መድረኩ ዋና ዓላማ የአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታ፣ ፖለቲካውን፣ ማኅበራዊውንና ባሕላዊውን ሁኔታዎች የሚያንፀባርቁ ጉዳዮች ላይ በመከባበርና በመደማመጥ ስሜት ጠለቅ ያሉ ምክክሮችን እንዲካሄዱ ማድረግ ነው።

በተጨማሪም አንኳር ጉዳዮች ናቸው ተብለው የተለዩ ሀገራዊና ክልላዊ ችግሮቻችን ላይ በዘላቂነት መግባባት ለመፍጠር ዓላማ ያደረገው ዋናው የምክክር መድረክ ግብዓት የሚወስበት የአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት እየተከናወነ መሆኑን አስንተዋል።

በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ተፎካካሪ ወገኖቻችን የሚሳተፉበትን መንገድ ለማመቻቸት ኮሚሽኑ በየጊዜው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ለመገናኘት ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። በቀጣይም በአማራ ክልልና በትግራይ ክልል የተሳታፊ ልየታ ለማድረግ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ችግሮች በተፈጠሩ ቁጥር ወደ ጫካ ከመግባት ተመካክሮ ችግሮቻችን የመፍታት ባሕል ለማዳበር ምክክሩ መሠረት የሚጥል ነው፤ ይህ ሲሆን አዲስ የፖለቲካ ባሕል እንዲፈጠር ማድረግ ያስችላል ብለዋል።

የሀገራዊ ምክክር ዋናው ዓላማም ሀገራዊ መግባባትን መፍጠር ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ምክክርን ባሕል የማድረግ ልምድ እንዲዳብር እየተሠራ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

በሆሳዕና ከተማ የሚደረገው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ከዛሬ ጀምሮ ለስድስት ተከታታይ ቀናት ይቆያል። በሂደቱም ከክልሉ የተውጣጡ ከአንድ ሺህ 500 በላይ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ታውቋል።

ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You