‹‹ለሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ማሟያ የሚካሄዱ ጥናቶች በአማካሪውና በፈታኙ መካከል ያለው ግንኙነት መጥፎ ከሆነ አማካሪው በደንብ ቢያማክረውም የተማሪው የምርምር ሥራና ግኝት ምንም ሳይታይ በጭፍን ጥላቻ ውጤቱ እንዲበላሽ ይደረጋል፡፡›› ያሉት ስማቸው እንዳይገለፅ የጠየቁን የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህር ናቸው፡፡
እኚሁ መምህር የሚናገሩት ከአማካሪውና ከፈታኙ ጋር በመነጋገርና በመስማማት ብቻ በደንብ ባልተሰራ ሥራ የማይገባ ከፍተኛ ውጤት እንደሚያገኝ፤ በእርግጠኛነትም በጉዳዩ ላይ ጥናት በማካሄድ በቁጥር ላይ የተመሰረተ መረጃ ማቅረብ ቢያዳግትም በብዙ ዩኒቨርሲቲዎች ፍትሃዊነት የጎደለው የውጤት አሰጣጥ እንዳለ ፤ ይህ ጉዳይ የተማሪዎችን ህይወት ከማበላሸቱም ባሻገር ጉዳቱ እስከ አገር የሚዘልቅ መሆኑን ነው፡፡
መምህሩ ውጤት አሰጣጡ ፍትሃዊና ሳይንሳዊ አለመሆኑ የሚያስከትለውን ጉዳት ሲያብራሩ፤‹‹ ተማሪ በሳይንሳዊ መንገድ በትክክል ካልተመዘነ በህክምና ውስጥ ታማሚውን በሽተኛ አይደለም፤ በሽተኛውን ደግሞ ጤነኛ ነው ይላል፤ ይህ ማለት በአገሪቷ ታሞ መዳን አይቻልም፡፡ በሌሎች ዘርፎችም እንደዚያው የሚሰራው ስራ ትክክል አይሆንም ፤ ጉዳቱ በጠቅላላ የአገሪቷን የኢኮኖሚ፣የሚያዛባ ይሆናል፡፡
በእርግጥ በስምምነትና በተቃርኖ የተማሪ ውጤት ላይ ከመፍረድ ባሻገር የፈታኝ እጥረት ስለሚኖር ከውጭ ፈታኝ እንዲመጣ ሲደረግ ለሙያው የቀረበ ሰው ብቻ ስለማይመደብ የሌላውን ጥናት የሚያይበት መነፅር የተለየ ይሆናል፡፡
በሶሽዮሎጂ ዘርፍ የተሰራን ጥናት በህግ የተመረቀ ሰው ሲመዝነው የሚያይበት መነፅር ከህግ አንፃር በመሆኑ ውጤቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ በዚህ ምክንያትና አንዳንዴም ፈታኙ በደንብ አንብቦና ተዘጋጅቶ ባለመምጣት የተማሪው ውጤት ከሚገባው በታች የሚሆንበት አጋጣሚ መኖሩንም መምህሩ ይናገራሉ፡፡
የሁለተኛም ሆነ የሶስተኛ ዲግሪ የትምህርት ስርዓት አካሄዱ ያልተስተካከለ ከመሆኑ ባሻገር ዋነኛው ችግር ተማሪው ምን አወቀ? ሳይሆን ተማሪው ምንም አያውቅም? በሚል አቃቂር ማውጣት ላይ ትኩረት ይደረጋል የሚል ምልከታ እንዳላቸው በመጠቆም፤ ያለውን ማወቅ ሳይሆን የጎደለውን በጣም አግዝፎ አውጥቶ ተማሪን መጉዳት ተገቢ ያልሆነ ተግባር መሆኑንም ነው የሚያብራሩት፡፡
ይህ መነሻው ራሱ ትክክል እንዳልሆነና በሌሎች አገሮች ግን በትምህርት ሂደት ተማሪው ምን አለው? እንጂ ምን ጎደለው ብሎ ስህተት መፈለግ ላይ ትኩረት እንደማይሰጥ አመልክተው፤ በኢትዮጵያም ይህ ቢሆን የተሻለ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
የአማካሪዎችና የፈታኞች አመዳደብ ላይ በብዙ ዩኒቨርሲቲዎች በትውውቅ ወይም በጥቅም ግንኙነት (በኔት ወርክ) መሆኑ ይታወቃል የሚሉት መምህሩ፤ የሚተዋወቁ ሰዎች የሚጠራሩበት ሁኔታ እንዳለ ገልጸው፣ በዚህም ያልተገባ ውጤት ይሰጣል ብለዋል፡፡
መሆን ያለበት ግን አንድ ሰው በደረጃው ምን ያህል የሚመጥን ጥሩ ሥራ ሰርቷል? በሚል የሙያ ብቃቱና ተወዳዳሪነቱ ታይቶ ቢገመገም ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ አገር ትድናለች፤ ተማሪዎችም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን ይችላሉ ብለዋል፡፡ አሁን ግን በተቃራኒው ማደግ የሚችሉና ትልቅ አቅም ያላቸው ሰዎች የማይሆን ውጤት ተሰጥቷቸው እንዳያድጉ የሚደረግ በመሆኑ ጉዳዩ ትኩረት ያሻዋል ይላሉ፡፡
‹‹አማካሪው(adviser) በትክክል ሳያማክር፤ ፈታኙም (examiner) የተማሪውን ምርምር የሚያይበት መንገድ የተዛባ ሲሆን፤ ተማሪው ቢሰራም ይጎዳል ፤በተማሪነትም ሆነ በአስተማሪነት ህይወቴ በዚህ ጉዳይ ተጠቅቻለሁ›› በማለት የሚያስከትለውን ችግር ይጠቅሳሉ፡፡
ሌላው የጉዳቱ ገፈት ቀማሽ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮ የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂው ተማሪ እንግዳወርቅ ነጋሽ እንደሚናገረው፤ ጥናቱን ያካሄደው ለሁለት ዓመታት ለፍቶ ቢሆንም ፈታኞቹ ያካሄደውን ጥናት በትክክል መመዘን የማይችሉና ዘርፋቸውም ከጥናቱ የራቀ በመሆኑ ግኝቱ ላይ ከማተኮር ይልቅ የመግቢያ ፅሁፉ ላይ ያለ ውስን የፊደል ስህተትን በመጥቀስ በግዴለሽነት የሰጡት ውጤት እጅግ ያሳዘነው መሆኑን ይናገራል፡፡
‹‹ ጭራሽ ያቀረብኩትን መረጃና የሰራሁትን ስራ ፈታኞቹ ያዩት አይመስለኝም›› የሚለው እንግዳወርቅ፤ ውጤቱ ዝቅተኛ እንዲሆን ያደረገው በፈታኙና አማካሪው መካከል ያለው ግንኙነት ሸካራ በመሆኑ ነው የሚል ግምት እንዳለው ይናገራል፡፡ አንድ ፈታኝ ጎበዝ ነው የሚባለው ጥሩ ውጤት ባለመስጠቱ በመሆኑ ብዙዎች ለተማሪዎች ጥሩ ነጥብ ካለመስጠታቸውም ባሻገር፤ በአግባቡ ማየት ያለባቸውን የጥናት ፅሁፍ ሳያዩ አንድ ሰዓት በማይሞላ ግምገማ ውጤት የሚሰጡበት ሁኔታ መኖሩንም ነው ያመለከተው፡፡
‹‹ለኢንጂነሪንግ ትምህርት ከሂሳብ ወይም ከፊዚክስ ዲፓርትመንት ሰው በመመደብ በጉዳዩ ላይ ያላቸው ዕውቀት ውስን ሆኖ እንደፈታኝ መቀመጣቸው ችግር ነው›› የሚለው ተማሪ እንግዳወርቅ፤ ፈታኞቹ ብዙ ተማሪ የሚፈትኑ በመሆኑ ምንም ያክል ተማሪው ቢሰራም በመሰላቸት የሰራውን ከ20 እስከ 30 ደቂቃ አብራራ ተብሎ መድረክ ላይ በጠየቁት ያልተገባ ጥያቄ በሰጠው ምላሽ ብቻ ውጤቱን መወሰናቸው የብዙ ተማሪዎችን ህይወት እያበላሸው መሆኑን ተናግሯል፡፡
‹‹ሶስተኛ ዲግሪ ያላቸው ሰዎች ብቻ የሚጠሩበት ሁኔታም አለ፡፡ ተቆጣጣሪ አለ ቢባልም አይቆጣጠሩም፡፡ ተማሪው በሚፈተንበት ቦታ ላይ አማካሪው መኖር ሲገባው አይኖርም፡፡ ተማሪው መክሰስ አይችልም፤ ልክሰስ ቢል ፈታኙን ላቀረበው ትምህርት ክፍል በመሆኑ፣ ‹አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ› ሆኖ መክሰስ ዋጋ ስለሌለው ብዙዎች እየተቸገሩ ነው›› ይላሉ፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት በጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል አማካሪዎች በአግባቡ አያማክሩም ነበር የሚሉት ደግሞ አቶ ሄኖክ ጌታቸው ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ አንዳንዶቹ ምንም አያማክሩም፤ እንዲያውም ፍላጎታቸው ሳያማክሩ አማከሩ ተብሎ ክፍያ እንዲፈፀምላቸው ብቻ ነው፡፡
ተማሪው ጥናቱን ሲያቀርብ ጭራሽ የተማሪውን ጥናት ስለማያውቁ ለሚቀርበው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እንደሚያዳግታቸውም ይናገራሉ፡፡ በተለይ አሁን አሁን በኔት ወርክ ከመመዳደብ ባሻገር በተማሪውም ሆነ በመምህራን ላይ የራስን ብሔር የመፈለግና የመጠቃቀም ሁኔታም መኖሩን ያመለክታሉ፡፡
በዲላ ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካ ሳይንስ የሚያስተምሩት ዶክተር ቴዎድሮስ ሃይለማርያም፤ ቀደም ሲል በሰፈር ልጅነት፣ በአብሮ አደግነት፣ በፆታ ግንኙነትና በትውውቅ ይሰጥ የነበሩ ፍትሃዊነት የጎደላቸው የውጤት አሰጣጦች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሌላ መልክ ይዘው በብሔር እና በሃይማኖት ውጤት የመስጠት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን እንዲህ አይነት ተግባራት በድብቅ የሚሰሩ በመሆናቸው መረጃ ለማግኘት እንደሚቸግር ይናገራሉ፡፡
‹‹ተፅዕኖ የሚያደርጉ አማካሪዎች ያጋጥማሉ፤ አንዳንዴ ሰው እየታየ ለሰው ሲባል በደንብ ላልተሰራ ጥናት ትልቅ ውጤት ይሰጣል›› ያሉት ዶክተር ቴዎድሮስ ፤በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተማሪዎች የመምህራን የብቀላ መሳሪያ ሆነው ለጉዳት እየተጋለጡ መሆኑንም ያመላክታሉ፡፡
‹‹አማካሪዎችም በደንብ ስለማናማክር ፈታኞችም በደንብ ፅሁፉን አንብበን ስለማንመጣ በደፈናው ውጤት የመስጠቱ ሁኔታ በጣም እየተለመደ መጥቷል፡፡ ጥናቶቹን የማቅረብ ሁኔታዎች በማብራሪያ ውስጥ የሚቀርቡ ጥያቄዎችና የሚሰጡ ምላሾች ለይስሙላ ሆኗል፡፡ ጥሩ የሰራው መጥፎ ውጤት፣ መጥፎ የሰራው ደግሞ ጥሩ ውጤት ሲያመጣ በተደጋጋሚ እየታየ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ ተማሪዎች ህይወታቸው የሚመሰቃቀልበት ሁኔታ ተፈጥሯል›› ይላሉ፡፡
አንድ መምህር ማማከር ያለበት ከአራት በላይ ተማሪ ሊሆን እንደማይገባ ቢታወቅም፤አንድ ሰው እስከ ሃያ ሰው ያማክራል ያሉት ዶክተር ቴዎድሮስ፣ መታለፍ የሌለባቸው ደንቦች ይታለፋሉ፣ መፈተን ላይም እርስ በእርስ ለመጠቃቀም አንድ ሰው አስር ተማሪ ይፈትናል፡፡ ይህንን ሁሉ ሰው የሚፈትነው ደግሞ በአንድ ሳምንት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለትምህርት የሚሰጠው ትኩረት መውረዱን ያመላክታሉ ፡፡
እንደ ዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ዶክተር ቴዎድሮስ ገለፃ፤ ይህንን አስቸጋሪ ጉዳይ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ያለው ችግር የፈጠረው ነው፡፡ በህግና በሥርዓት መመራት ከተቻለ ግን ተማሪዎችም ያልሰሩትን የሚፈልጉበትና ያልሰሩትን የሚያገኙበት ሁኔታ ይቀራል፡፡ በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲ አካባቢ ላሉ አስተዳደሮችም ሆኑ አመራሮች የሚሰጠው ሹመት በፖለቲካ ሳይሆን በችሎታ የሚመደቡበት ሁኔታ ከተፈጠረ ትልቅ ለውጥ ይመጣል ብለው እንደሚያምኑም ይናገራሉ፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 28/2011
ምህረት ሞገስ