‹‹የመንግስት አሰራር ለህዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት›› የሚለው ዓረፍተ ነገር በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ (1) ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ በንዑስ አንቀጽ (2)ትም ‹‹ማንኛውም ኃላፊና የህዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ ይሆናል›› በማለት ይደነግጋል፡፡
ነገር ግን መንግሥት በተደጋጋሚ የእርምትና የተጠያቂነት ዕርምጃ ለመውሰድ ሲምልና ሲገዘት ከመስማት ውጪ፣ ይህ ነው የሚባል ዕርምጃ ሲወስድ እምብዛም እንደማይታይ ይነገራል፡፡ መንግሥት ለሕዝብ የሚያሳየው ኃላፊነትና ታማኝነት ከሚለኩባቸው መንገዶች አንዱና ዋናው በሆነው
የሀብት አጠቃቀም ላይ ተጠያቂነቱ ልል በመሆኑ በየጊዜው የኦዲት ጉድለት እንደሚታይም የሚናገሩት የመንግስት ወጭ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጀንበሩ ሞላ ናቸው፡፡
በየዓመቱ በሚመጡ የኦዲት ግኝቶች ላይ ጉድለቱ እየጨመረ እንጂ የመሻሻል አዝማሚያ ብዙም የማይታይ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ጀንበር፤ እስካሁን በቋሚ ኮሚቴው በተካሄደው ይፋዊ መድረክና የመስክ ምልከታ ክትትልና ቁጥጥር ከ176 ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ከችግር ነጻ መሆን የቻሉት 25 ብቻ መሆናቸውን ይጠቁማሉ፡፡
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ተጠያቂነትን በማረጋገጥ በኩል መሠረታዊ ውስንነቶች ነበሩ፡፡ ጉድለቶች የታዩት መሠረታዊ በሆነው የተጠያቂነት ችግር ነው፡፡ በኦዲት ግኝቱ ላይ ምክር ቤቱ የአስፈጻሚ አካላት ተጠያቂነትን ሊያረጋግጥ የሚችል የማሻሻያ እርምጃዎች መወሰድ መቻል እንዳለበት ያምናል፡፡
ተጠያቂነትን ሊያረጋግጥ የሚችሉ ተቋማትን በመፍጠር በኩል መሠረታዊ ክፍተቶች ነበሩ፡፡ የኦዲት ግኝቶች እንዳይታረሙ እያደረጋቸው የመጣው ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በኦዲት ግኝት ጉድለት ዙሪያ ችግር ያለባቸውን አካላት ለይቶ እርምጃ እየወሰዱ ባለመሆኑ ነው፡፡
አቶ ጀንበር፤ ኦዲት ተደራጊ ተቋማት አልፎ አልፎ በተያዘላቸው ይፋዊ የህዝብ ውይይት መድረክ ላይ ሚኒስቴሮች ትኩረት ሰጥተው እንደማይገኙ ለአብነት የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር፤ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠቅሰዋል፡፡ አሁን ላይ በምክር ቤቱ የተዘጋጀው የተጠያቂነት ውሳኔ ሀሳብ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ያስችላል ብለዋል፡፡
የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ንዑስ ሰብሳቢ ወይዘሪት ወይንሸት ገለሶ፤ ምክር ቤቱ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ (11) መሠረት የፌዴራል መንግስትን በጀት የማጽደቅና በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (17) መሠረት ደግሞ የህግ አስፈጻሚውን አካል አሰራር የመመርመር ሥልጣን ያለው መሆኑን በመጠቆም፤ ይህ ደግሞ የተመደበው ዓመታዊ በጀት፣ በበጀት ዓመቱ ለተሰሩት ሥራዎች በሚገባ መዋሉን ጭምር በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መመርመርን ቢያካትትም ህጉን ተግባራዊ በማድረግ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ የማደረግ ክፍተት መኖሩን ገልጸዋል፡፡
ከአሰራር ሥርዓት ውጭ ለብክነት የተጋለጡ አሰራሮች እንዲታረሙ ላሉፉት በርካታ ዓመታት በዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ሲሰጡ የነበሩት የማስተካከያ እርምጃዎች እንዳልተወሰዱ፤ ለችግሩ አለመቀረፍ መንስኤው ደግሞ የኦዲት ግኝቱን ተከትሎ የማስተካከያ እርምጃዎችን በማይወስዱ ኃላፊዎች ላይ የተጠያቂነት እርምጃ አለመውሰድ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡
ይህ ደግሞ ከህገ መንግስቱ ጋር የማይጣጣምና የምክር ቤቱንና የመንግስትን ተዓማኒነት የሚጎዳ በመሆኑ እርምጃዎች በመንግስት በኩል እንዲወሰዱ የውሳኔ ሀሳብ ቀርቦ መጽደቅ መቻሉን ወይዘሪት ወይንሸት ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይ ቀደም ባሉት ዓመታት የተፈጸሙ የሀብት ብክነትና ምዝበራ የአሰራና የህግ ጥሰትን በተመለከተ በህግ አግባብ እርምጃ ተወስዶ የህዝብና የመንግስት ገንዘብ እንዲመለስ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ወይዘሪት ወይንሸት የኦዲት ግኝቶችን ተከትሎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ሲያብራሩ፤ ህግና አሰራር የጣሱ በየደረጃው የሚገኙ ኃላፊዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ተወስዶ ተጠያቂነት የሚረጋገጥ መሆኑንም አክለዋል፡፡
በገንዘብ ሚኒስቴር የኢንስፔክሽን ዳይሬክተሩ አቶ ፈቃዱ አጎናፍር በበኩላቸው፤ በየጊዜው በሚደረጉት የተቋማት ኃላፊ ሹመቶች ምክንያትኃላፊዎች ለቦታው አዲስ ሲሆኑ ለመጠየቅም አስቸጋሪ ሁኔታን መፍጠሩን ይናገራሉ፡፡ ምክር ቤቱም ቢሆን ባለሥልጣናት በሚሾሙበት ወቅት የኦዲት ግብዓት እንደ አንድ መሳሪያ መታየት እንዳለበት መገንዘብ ይገባል ይላሉ፡፡
በኦዲቱ የሚታዩት ጉዳዮች ከህዝብ ጥቅም ጋር ስለሚያያዙ በህግ ባለመመራት የህዝብ ሀብት እንዲባክን ያደርገዋል፡፡ በተለይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ተያይዞ ተጠያቂነቱ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ፤ በተለይ የኦዲት ችግሮች ሲፈጠሩ በሥራ ድልድል ምክንያት በአንዳንድ መስሪያ ቤቶች የሚመደቡ ኃላፊዎች ተጠያቂነትን ከራስ ለማውረድ ‹‹ለቦታው አዲስ ነኝ›› የሚል ምክንያት ማቅረባቸው ተገቢ አለመሆኑን፤ በሁሉም ዘንድ ተጠያቂነቱን በማረጋገጥ የህግ ጥሰት የሚፈጽሙት አካላት ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ህጉን ተከትሎ ከተሰራ ‹‹እጠየቃለሁ›› የሚል ውሳኔ ላይ ስለሚደርስ ጥፋትን ማስቀረት የሚቻለውም ሥር የሰደደውን የተጠያቂነት ችግር ከስሩ በአፋጣኝ በመግታት እንደሆነና፤ የደረሰውን ጥፋት ሊቋቋም የሚችል የህግ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ለነገ የማይባል ሥራ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 28/2011
አዲሱ ገረመው