በኢትዮጵያ በዓመቱ እስከ ሁለት ሚልዮን የሚጠጉ ወጣቶች ወደ ሥራው ዓለም ይቀላቀላሉ ወይም ሥራ ፈላጊ ይሆናሉ። ለዚህ ከፍተኛ ቁጥር ላለው ዜጋ በመንግሥት ወይም በግል ተቋማት እና ድርጅቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ባለመቻሉ አብዛኛው ቁጥር ያለው ወጣት ለስራ አጥነት ይዳረጋል። ይህንን ችግር ለመፍታት ደግሞ ሥራ ጠባቂ ከመሆን ይልቅ ሥራ ፈጣሪ ሆኖ መገኘት ይገባል።
ሆኖም በኢትዮጵያ በርካታ ወጣቶች የስራ ፈጠራ ባለሙያዎች ቢሆኑም የፈጠራ ሀሳባቸውን ወደ ተግባር ለማዋል የመስሪያ ቦታ እጥረት፣ የብድር አቅርቦት አለመመቻቸት፣ የገበያ ትስስር አለመኖር እና የክህሎት ክፍተቶችና መሰል ችግሮች እንቅፋት ሆኖ ሲገጥማቸው ይስተዋላል።
አንድ ሰው የተሳካለት ሥራ ፈጣሪ ወይም ኧንተርፕረነር ለመሆን አዲስ የፈጠራ ሃሳብ ወሳኝ ነው። ከዚያ ሲቀጥል ደግሞ ሃሳቡን ተግባራዊ ማድረጊያ ገንዘብ ወሳኝ መሆናቸው አይጠረጠርም። ሆኖም፣ እነዚህ ሁለቱ ብቻ ሥራ ፈጣሪው የተሳካለት የቢዝነስ ሰው እንዲሆን አያስችሉትም። ሥራ ፈጣሪው፣ ስኬትን መቀዳጀት እንዲችል ወይም ጉዞው ወደ ስኬት የሚገሰግስ እንዲሆን፣ ዓይነተኛ የሆኑ የስብዕና መገለጫዎች ያስፈልጉታል። ታታሪነት፤ አርቆ አሳቢነትና ተስፋ አለመቁረጥ የመሳሰሉት የስብእና ባለቤት ሊሆን ይገባል። እንደ ሥራ ፈጣሪ፣ እነዚህ የስብዕና መገለጫዎች ወይም ጠባዮች ካሉት ሊያዳብራቸው፣ ከሌሉት ደግሞ እንደ አዲስ በውስጡ ኮትኩቶ ሊያሳድጋቸው ይገባል።
በቅርቡ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ወጣቶች በዲጅታል ቴክኖሎጂ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግና ለማጠናከር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ24ኛ ጊዜ “From Clicks to Progress: Youth Digital Pathways for Sustainable Development” (በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ደግሞ ለ21 ጊዜ “ወጣቶችን በቴክኖሎጂ ማብቃት ለዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት” በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀንን አክብሯል።
በበዓሉም በአገር አቀፍ ደረጃ በወጣቶች አማካኝነት የተፈጠሩ የዲጂታል ውጤቶች የሆኑ የፈጠራ ሥራዎችን የያዘ ኤግዚብሽን ቀርቧል።
ወጣት ኦብሳ ሃምዛ በዚህ አውደ ርእይ ሥራዎቻቸውን ይዘው ከቀረቡ ወጣቶች መካከል አንዱ ነው። (አምራች ዶትኮም) የሚል መጠሪያ የተሰጠው የቴክኖሎጂ ኩባንያ መሥራች የሆነው ወጣቱ የቴክኖሎጂ ድርጅቱ በዋናነት ምን አይነት ሥራዎችን እንደሚሰራ ስናገር፤ የግብርና ምርቶችን ከአምራቾች ተቀብሎ በችርቻሮ ንግድ ላይ ለተሰማሩ ግለሰቦች እንደሚያቀርብ ይናገራል።
አንድ ምርት ተመርቶ ከፋብሪካ ወጥቶ ተጠቃሚው ጋር እስኪደርስ ድረስ በመሃል ከሰባት እስከ አስር ሰው እየገባ የራሱን ትርፍ ለማግኘት ጥረት ያደርጋል የሚለው ወጣት ኦብሳ፤ ይህ ጉዳቱ ለአብነት አንድ ምርት በአንድ መቶ ብር ከተገዛ በኋላ አንድ መንደር ላይ ወዳለ ሱቅ ሲደርስ 180 ብር ይሆናል። ባለሱቁ ደግሞ ሁለት መቶ ብር አድርጎ ለመጨረሻ ተጠቃሚው ይሸጣል። ይህ ጤናማ አካሄድ አይደለም ይላል።
‹‹ለዚህ ችግር መፍትሄ የሚሆን ቴክኖሎጂ ነው ይዘን የመጣነው›› የሚለው ኦብሳ፤ ዲጂታል የገበያ ማዕከል በመዘጋጀት አምራችና ገዥ በቴክኖሎጂው እንዲመዘገብና ገዥ የሚፈልገውን የምርት አይነትና ፍላጎት እንዲገልጽ በማድረግ ሶስተኛ ወገን ሳይኖር ለአብነት በፊት 200 ብር ይገዛ የነበረውን እቃ በ100 ብር እንዲያገኝ የሚያስችል አሰራር መሆኑን ይናገራል። ይህ ደግሞ ለኅብረተሰቡ እፎይታን የሚሰጥ መሆኑን ይገልጻል።
በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነት መባባስ አንዱ ምክንያት ምርት ከማሳ እስከ ገበታ ባለው ሂደት ተሳታፊ የሆኑ አካላት የራሳቸውን ጥቅም ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት በሚፈጠር የንግድ ሰንሰለት መርዘም ምክንያት ነው የሚለው ወጣት ኦብሳ፤ ይህ ቴክኖሎጂ ግን አላስፈላጊ የደላሎች ጣልቃ ገብነትን በማስወገድ ለኑሮ መረጋጋቱ የራሱም አወንታዊ ሚና እንደሚጫወት ይናገራል።
የቴክኖሎጂ ፋይዳው ለአምራቾችም ትልቅ ነው የሚለው ወጣት ኦብሳ፤ ማንኛውም አምራች የሰውን ፍላጎት ባገናዘበ መልኩ ምርት ማምራት ከቻለ ምርቱ ሳይበላሽ ተጠቃሚው ጋር እንዲደርስ ይረዳዋል። በተጨማሪም ተደራሽነቱን በማስፋት ተጨማሪ የገበያ ትስስር መፍጠር እንዲቻል መንገድ እንደሚሆን ይገልጻል።
ይህንን ቴክኖሎጂ ለመፍጠር መነሻ ምክንያት ስለሆነው ነገር ወጣት ኦብሳ ሲናገር፤ `‹‹በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት ለመግዛት የምንፈልጋቸው እቃዎች ነበሩ። ነገር ግን የተለያዩ ቦታዎች ብንፈልግም ማግኘት አልቻልንም። እቃው አለ የተባለበት ስንሄድም በትክክል ጥረቱን የጠበቀ ምርት አልነበረም። ስለዚህ ለምን ይህንን ችግር ለመፍታት ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው የሚፈልጉትንና ጥረቱን የጠበቀ አገልግሎት ማግኘት አይችሉም በሚል መነሻ ይህንን ቴክኖሎጂ ለመሥራት ተነስተናል ›› ሲል ሀሳቡ የመነጨበትን መንገድ ያብራራል።
ምርት በሚደበቅበት፣ አላግባብ ዋጋ ጭማሪ በሚደርግበት፣ አለመተማመን በበዛበትና የሰለጠነ አካሄድ በሌላው የኢትዮጵያ የገበያ ስርዓት በዚህ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ችግሩን በማቃለል ሰዎች የሚፈልጉትን ምርት ከተለያዩ አምራቾች በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ እያደረጉ እንዳለ ይናገራል።
ማንኛውም ሰው (Kamrach.com) በተሰኘ ድህረገጽ አማካኝነት የአማርኛ፣ ኦሮሚኛ፣ ትግረኛና ሶማልኛ ቋንቋ በመጠቀም በቀላሉ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችል የሚናገረው ወጣት ኦብሳ፤ የክፍያ ስርዓቱም ቀላልና ማንኛውም ሰው ሊረዳው በሚችለው መልኩ የተዘጋጀ ስለመሆኑ ይናገራል።
‹‹በአሁኑ ወቅት ከአንድ መቶ ሺህ በላይ አገልገሎት ፈላጊዎች ድረገጸችንን ጎብኝተዋል›› የሚለው ወጣት ኦብሳ፤ የአገልግሎት ፈላጊው ቁጥሩ ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ መምጣቱ በርካቶች በቴክኖሎጂው የመጠቀም ፍላጐት እንዳለቸው የሚያሳይ እንደሆነ ይገልጻል።
መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ለቴክኖሎጂና ፈጠራ የሰጠው ትኩረት ይበል የሚያሰኝ ነው የሚለው ኦብሳ፤ ይህ የዓለም ወጣቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው ዓውደ ርዕይም ሀሳብና በጅምር ያለ የፈጠራ ሥራ ያላቸው ወጣቶች የተገኙበት ነው። በጅምር ያለ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራ ደግሞ ከፍተኛ ፋይናንስ የሚጠይቅ በመሆኑ የተለያዩ ባለሃብቶች አብረው እንዲሰሩ ለማድረግ ሥራዎችን ማሳየት የሚቻልበት አጋጣሚ መፈጠሩ በጎ ጅምር ስለመሆኑ ይናገራል።
ወጣት አበበ ነጋሽ ሌላኛው በዚህ አውደርእይ ሥራዎቻቸውን ይዘው ከቀረቡ ወጣቶች መካከል አንዱ ነው። የተለያዩ የዕደ ጥበብ ሥራዎችን የሚሰራው ወጣቱ በአይነስውርነት ያልተገደበ የብዙዎች ምሳሌ ነው።
ለንፅህና አገልግሎት የሚውሉ መጥረጊያና መወልወያ እንዲሁም የቤት ውስጥ ምንጣፎዎችን የሚሠራው አበበ ለዚህ ሁሉ ሥራ ምክንያት የሆነው በትውልድ አካባቢውም ሆነ በሀገሪቱ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ያለው አመለካከት እራስን ካለመቻል እና ከልመና ጋር የተያያዘ በመሆኑ አካል ጉደተኛም እንደማንኛውም ሰው መሥራት የሚችል መሆኑን ለማሳየት ነው ይላል።
“ምንጣፍና መወልወያ መሥራት ከባድ አይደለም። ከዚህ በላይ የኤሌክትሪክ ሁሉ ብልሽት ሲገጥመኝ እንደማንኛውም አይናማ ሰው በቀላሉ ማስተካከል እችላለሁ’’ የሚለው አበበ በተጨማሪም በትውልድ አካባቢው የእንጀራ ምጣድ፣ ስቶቭ ጥገና የመሥራት ልምድ ስላዳበረ በርካታ ስራዎችን የመስራት ክህሎት እንዳዳበረ ይናገራል።
ሥራችንን በተመለከተ ብዙዎች የሚሰጡት አስተያየት አበረታች ነው የሚለው አበበ፤ ከዚህ የበለጠ ጠንካሮች እንድንሆን የሚያበረታታ አስተያት ይደርሰናል ይህ ከዚህ ቀደም አካል ጉዳተኞች ከሰው በታች እንደሆኑ ተደርጎ የሚወሰደው አመለካከት ከግዜ ወደ ጌዜ እየተሻሻለ ስለመምጣቱ የሚያመለክት ነው ይላል።
የመንግሥት ድጋፍ በተመለከተ አበበ ሲናገር፤ ‹‹አካል ጉዳተኞች መበረታታት አለባቸው ምክንያቱም መንግሥትም የሚፈልገው ሥራ ፈት ወጣት እንዳይኖር ነው። ከዚህ አኳያ መንግሥት በተለያዩ ድጋፎች ከጎናችን ቢሆን ማንኛውም ሰው መሥራት እንደሚችል ምሳሌ ከመሆን ባለፈ ይበልጥ ተጠቃሚ እንድንሆን ያግዛል›› ይላል።
“ሰው ሥራ አጣሁ፤ ይላል ግን ሥራ ፈጣሪ መሆን ያለበት እራሱ’’ ነው የሚለው አበበ ‹‹መንግሥትን መጠየቅ የሚቻለው የመስሪያ ቦታ፣ የድጋፍ አገልግሎት ነው። ሥራ ፍጠሩልን ብሎ መንግሥትን መጨቅጨቅ ልክ ነው ብዬ አላምንም። ከመንግሥትም ቢሆን ድጋፍ ለማግኘት የሚታይ ነገር መሥራት ይጠይቃል። ስለዚህ ተቀምጦ ማማረር ሳይሆን መፍትሄው እራስን ለሥራ ዝግጁ ማድረግ ነው›› ይላል።
‹‹ሰዎች ምርታችንን በብዛት እየተጠቀሙ ነው›› የሚለው አበበ፤ በተለያዩ መልኩ ምርቶቻቸው የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሰሩ በዚህም ሕብረተሰብ ከተመሳሳይ ምርት ጋር አነፃጽሮ የእነሱን ምርት እንደሚገዛ ይናገራል። በጥራት እና በተመጣጣኝ ዋጋ መስራት ከተቻለም የገበያ ችግር እንደማያጋጥም ያስረዳል።
አሁንም የገበያ ትስስሩ አነስተኛ ስለሆነ ገበያ ያለበት አካባቢ የመሸጫ ሼዶች በመንግሥት ተመቻችተው ቢሰጡን የበለጠ ምርታማ ሆነን መውጣት እንችላለን የሚለው አበበ፤ የመሸጫ ሼዶች መኖር በስፋት ወደ ገበያ ለመግባት እንደሚያስችል ይናገራል።
‹‹የፕላስቲክ ደረቅ ቆሻሻ መጥረጊያ ቶሎ የሚሰበር በመሆኑና በአንፃሩ የእኛ ምርት በጥንካሬው የሚታወቅ በመሆኑ ሕብረተሰቡ በስፋት ጥቅም ላይ እያዋለ ነው የሚለው›› አበበ፤ መጥረጊያው ቢሰበር መልሰው አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ እድሳት ስለሚደረግለት የበለጠ በሕብረተሰቡ ዘንድ ተመራጭ ለመሆን እንዳበቃው ይናገራል።
‹‹አይነስውር ብሆንም ሥራውን በብቃት መሥራት እንደሚችል ለሁሉም ማሳየት ችያለሁ›› የሚለው ወጣት አበበ፤ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያለውን አቅም ለማሳደግና ተጨማሪ አቅም ለመገንባት በትምህርት እራሱን ለማሻሻል መደበኛ ትምህርቱን እየተከታተለ እንደሚገኝ ተናግሮ በተለይ ለኤሌክትሪክ ጥገና የሚያስፈለገውን መስፈርት ለማሟላት ጥረት እያደረገ ስለመሆኑ ይናገራል።
ወደፊት የአካል ጉዳተኞች የሙያ ማሰልጠኛ ተቋም መመስረት እፈልጋለሁ የሚለው አበበ፤ ለዚህ እቅድ መሳካት ራሱን በተለያየ መልኩ ለማሳደግ ጥረት እያደረገ ስለመሆኑ ተናግሮ፤ የሚመለከታቸው አካላት በሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ከጎኑ ቆመው ለብዙዎች ብርሃን የመሆን ሕልሙን እንዲደግፉ ጥሪውን ያቀርባል።
ስኬታማ ኧንተርፕረነሮች ከዛሬው እንቅፋት፣ ውጣ ውረድ ወይም ጊዜያዊ ድል ይልቅ የወደፊቱ ጊዜና የሚደርሱበት ከፍታ የሚታያቸው ናቸው የሚሉት ወጣቶቹ፤ ሁልጊዜም ከወራት፣ ከዓመታት በኋላ ሥራችን የት እንደሚደርስ በማሰብ ታትረው መስራት እንደሚገባቸው ይመክራሉ።
ወጣቶች ዛሬ በሚያጋጥማቸው እንቅፋት ሳይሰናከሉ ነገን ወደፊት አሻግረው በማየት በአሸናፊነት መንፈስ ሊጓዙ እንደሚገባም ስራ ፈጣሪ ወጣቶቹ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 24 ቀን 2016 ዓ.ም