አዲስ አበባ፡- በመንግስት ተቋማት የበጀት አጠቃቀም ችግሮች መኖራቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጠቆሙ፡፡
የህዝብ ተወካች ምክር ቤት በ4ኛ የስራ ዘመን 9ኛ ልዩ ስብሰባ የ2012 ዓ.ም ረቂቅ በጀት ላይ ውይይት ባደረገበት ወቅት በምክር ቤቱ አባላት የመንግስት ተቋማት ውስጥ በጀት በአግባቡ የመጠቀም ችግር እንዳለና የወጪ ቁጠባ አሰራር ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት እንደገለፁት፤ በመንግስት ተቋማት ውስጥ የሚመደበው በጀት ለስራ አስፈላጊ ከሆኑ ቁሳቁሶች ይልቅ የተቋማቱ አመራሮች እና ሃላፊዎች የሚጠቀሙበት የቅንጦት እቃ መግዛት ላይ እንደሚያተኩሩና የበጀት አጠቃቀማቸውም ችግር የሚስተዋልበት ነው፡፡
የምክር ቤቱ አባል የሆኑት ወይዘሮ አገሬ ምናለ በውይይቱ ወቅት እንደገለፁት፤ ሀብትን በቁጠባ ከመጠቀም አንፃር የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከፍተኛ የአሰራር ችግር አለባቸው፡፡
ወይዘሮ አገሬ አክለውም ከፕሮጀክት የሚመለሰው ሀብት በአግባቡ ለመንግስት ገቢ መሆኑን በቂ ክትትል ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ወጪያቸው ከፍተኛ በመሆኑ ምክንያት በመንግስት ተቋማት ለተወሰኑ ተግባራት ብቻ እንዲውሉ የታገዱ መኪኖች መስሪያ ቤቶቹ በፍቃዳቸው እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ ገልፀው ፤ መስሪያ ቤቶቹ መመሪያው ተግባራዊ አለመደረጉ ጥያቄ ያስነሳል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ሌላኛዋ የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ ሰናይት አንዳርጌ፤ የመንግስት ተቋማት የበጀት አጠቃቀማቸው ችግር እንዳለበትና የመንግስት መመሪያና ህግን የተከተለ ላለመሆኑ ብዙ ማሳያዎችን ያነሳሉ፡፡
ለባለስልጣናቱና ለሀለፊዎቹ የተጋነነ ዋጋ ያላቸው የመጠቀሚያ ቁሳቁሶች ይገዛሉ፣ ለወጪ ቅነሳ ብሎ መንግስት ያወጣቸው መመሪያዎች አይተገበሩም፣ በየተቋማቱ ያገለገሉ ንብረቶች አያያዝ ማሳያ ነው፡፡ በማለት የመንግስ መስሪያ ቤቶቹ የሚታይባቸው ችግር ዘርዝረዋል፡፡
በዕለቱ ምክር ቤቱ በመገኘት በጉዳዩ ላይ ለተነሱ አስተያየትና ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር የበጀት ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ ደመቀ እንደተናገሩት፤ መስሪያ ቤታቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች የበጀት አጠቃቀም ላይ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደረግ ገልፀው፤ ከ2009 ጀምሮ የወጪ ቁጠባ ስልት መመሪያ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ቢደረግም በአንዳንድ መስሪያ ቤቶች የሚታዩ ችግሮች የሚገዙት መገልገያ እቃዎች ግዢ መስፈርት የተቀመጠላቸው ባለመሆኑ ለቁጥጥር አስቸጋሪ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም፤ መስሪያ ቤታቸው ለዚህ መፍትሄ እያፈላለገ መሆኑንና ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀው፤ የመንግስት ተቋማት አመራሮች የተጣለባቸውን ሃላፊነት በትክክል እንዲወጡና የህዝብና የመንግስት ንብረት በሃላፊነት ስሜት እንዲመሩ አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 28/2011
ተገኝ ብሩ