አዲስ አበባ:- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተጨማሪ እሴት ታክስ ማሻሻያ አዋጅን እና የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ረቂቅ አዋጅን አጸደቀ።
ምክር ቤቱ ትናንት ባደረገው አራተኛ አመት የስራ ዘመን 48ኛ መደበኛ ስብሰባ የተጨማሪ እሴት ታክስ ማሻሻያ አዋጅን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። አዋጁ ለገቢ አሰባሰቡ ከፍተኛ ችግር አስከትለዋል የተባሉትን የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ድንጋጌዎችን በማሻሻል የንግድ ስራን በተቀላጠፈ ሁኔታ በማካሄድ የንግድ ስራ እንቅስቃሴን ለማገዝ የሚያስችል እንደሚሆን ተገልጿል።
የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ለምለም ሀድጎ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ስራ ላይ ከዋለ አስራ ሰባት አመታትን ያስቆጠረ በመሆኑ ረቂቅ አዋጁ አሁን ካለው ነባራዊ የኢኮኖሚ የእድገት ደረጃ ጋር በማጣጣም የንግድ ስራና አስተዳደርን ቀላል፣ ቀልጣፋና የግብር ከፋዩን ግዜ ለመቆጠብ ይረዳል።
በተጨማሪም የታክስ ባለሰልጣን የተመላሽ ጥያቄዎችን በስጋት ስራ አመራር መርህ ላይ በተመሰረተ የአሰራር ስርዓት እንዲያስተናግድ የሚፈቅድ ይሆናል።
የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/1994 በጥናት ላይ ተመስርቶ ሙሉ ለሙሉ ለማሻሻል ዝግጅት እየተደረገ ቢሆንም በአጭር ግዜ ሊደርስ ባለመቻሉ ለገቢ አሰባሰቡ ማነቆ የሆኑ አንቀጾች ለይቶ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱንም ሰብሳቢዋ አስረድተዋል።
ምክር ቤቱ በአራተኛ አመት የስራ ዘመን 48ኛ መደበኛ ስብሰባው የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ረቂቅ አዋጅንም አፅድቋል። የኢንዱስትሪ ሰላም በማስፈን የምርታማነትና የገበያ ተወዳዳሪነትን አቅም ለመፍጠር ያስችላል ያለውን የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምጽ ያፀደቀ ሲሆን፤ በምክር ቤቱ የሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አባባ ዮሴፍ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ማብራሪያ እንደተናገሩት፤ ረቂቅ አዋጁ ከኢትዮጵያ አሰሪዎችና ሰራተኛ ማህበራት ፌዴሬሽኖችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ሲደረግበት ቆይቷል።
ከውይይቱ በመነሳት በተደረሰው የጋራ መግባባት የአሰሪውንና የሰራተኛውን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ አዋጁ የተዘጋጀ ሲሆን፤ የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት ከሽኩቻ የጸዳ ሰላማዊ እንዲሆን ያደርጋል። ሰራተኛውም ሙሉ አቅሙን በመጠቀም ምርትና ምርታማነት ላይ አውሎ ትርፋማ እንዲሆን ያስችላል። በተጨማሪም ከዚህ ቀደም በነበሩ አዋጅና መመሪያዎች ላይ ያጋጥሙ የነበሩ የአፈጻጸም ችግሮችንም ለመቅረፍ የሚያስችል እንደሆነ ጠቁመዋል።
ረቂቅ አዋጁ በሰራተኞች መካከል ልዩነት አለማድረግን፤ በስራ ቦታ አእምሮን የሚያደነዝዙ ነገሮችን መከልከልን፣ የስራ ውልን ስለማቋረጥ ስለሰራተኛ ቅነሳና የወሊድና ውርጃ ሲያጋጥም የሚሰጥ ፈቃድን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ያካተተ ነው ያሉት ሰበሳቢዋ፤ አዋጁ መሰረታዊ የስራ ላይና የሰብአዊ መብቶችና ግዴታዎች ለማስጠበቅ እንዲሁም የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት የሚመራበትን መሰረታዊ የስራ ደረጃዎች የህግ ተፈጻሚነት የሚያረጋግጥ እንደሚሆን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 28/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ