አዲስ አበባ:- 250ሺ ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች በኢትዮጵያ በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ አስታወቀ።
የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) አባል አገራት ትናንት በአዲስ አበባ አምስተኛውን አመታዊ የኤክስፐርቶች ጉባኤ ባካሄዱበት ወቅት፤ ስደተኞችንና ከስደት ተመላሾችን የትምህርት እድልን ተደራሽ ለማድረግ ታስቦ በተደረገው ውይይት ላይ 250ሺ ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች በኢትዮጵያ በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ተጠቁሟል።
በጉባኤው ላይ የተሳተፉት የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ተወካይ አቶ ዳንኤል ዳርጫ እንደገለጹት፤ ከሁለት አመት በፊት አባል አገራቱ በጂቡቲ ስደተኞችን እና ከስደት ተመላሾችን የትምህርት እድል ተጠቃሚ ለማድረግ፤ የስደተኞችን ክህሎት ለማሳደግ በአጠቃላይ አምስት ዋና ዋና የስደተኞችን ጥቅም የሚያስጠብቅ ጉዳዮችን የያዘውን ስምምነት አባል አገራቱ ሲያጸድቁ ኢትዮጵያ እንደ ኢጋድ ሊቀመንበርነቷ ስምምነቱ ሲጸድቅ ከፍተኛ ሚና ነበራት።
ኢትዮጵያም ስምምነቱን ከፈረሙ አገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ ሲሆን፤ ስምምነቱን በከፍተኛ ቁርጠኝነት ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል።
ከስደተኞች አንጻር አገሪቱ በርካታ እርምጃዎችን የተጓዘች ሲሆን፤ ከዚህ በፊት የነበረው የኢትዮጵያ የስደተኞች አዋጅ ስደተኞች ትምህርታቸውን ቀጥታ በአገሪቱ በሚገኙ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ላይ ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅሎ የመማርና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን የሚነፍግ እንደነበር አስታውሰዋል። አሁን ግን የጂቡቲውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የነበረውን በመቀየር ኢትዮጵያ የስደተኞችን አዋጅ አሻሽላለች ብለዋል።
በተሻሻለው አዋጅ የስደተኞች የትምህርት እድል ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን፤ መንግስት ስደተኞች በኢትዮጵያ ከቅድመ መደበኛ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ መማር እንደሚችሉ አረጋግጧል። በመሆኑም አሁን በአገሪቱ ከቅድመ መደበኛ እስከ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት እርከን ድረስ 250ሺ ስደተኛ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ መገኘታቸውን አቶ ዳንኤል ገልጸዋል።
አገሪቷ ስደተኛ ተማሪዎች ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ለማድረግ የተለያዩ አጋር አካላትን በማስተባበር የተለያዩ ስራዎችን እየሰራች የምትገኝ ሲሆን፤ ስደተኛ መምህራኖችን ማሰልጠን መቻሉንና አስፈላጊ ግብዓቶችን የማሟላት ስራ መሰራቱን አቶ ዳንኤል ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብለው የሚያስተናግዱ ክልሎችንና የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አዋጅ ማጽደቋን የጠቆሙት በትምህርት ሚኒስቴር በእቅድ ዝግጅትና ሀብት ማፈላለግ ዳይሬክቶሬት ስር የስደተኞች ትምህርትን በተመለከተ የሚሰሩት አቶ ጌታቸው አድማሱ በበኩላቸው፤ በአገሪቱ ስደተኞችን ተቀብለው የሚያስተናግዱ አምስት ክልሎች አሉ።
እነዚህ ክልሎች ስደተኞችን ተቀብለው በሚያስተናግዱበት ወቅት በማህበረሰቡ ላይ የሚፈጠር ጫና ስላለ ስደተኞችን የሚያስተናግዱ ክልሎች ከትምህርት እድሉና ከተለያዩ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሰራር ይፈጠራል ብለዋል።
ከሁለት አመት በፊት ጅቡቲ ላይ የተደረሰው ስምምነት በኢጋድ አባል አገሮች የሚገኙ ስደተኛ ተማሪዎች ለብቻ ተነጥለው በካምፕ ሳይማሩ ከማንኛውም አስጠጊ አገራት ትምህርት ቤቶች ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው የሚማሩበት፣ ጥራት ያለው ትምህርት የሚያገኙበት እንዲሁም የተማሩት ትምህርት በየትኛውም የአባል አገራት ተቀባይነት ሊኖረው እንዲችል ስምምነት መደረሱን ያስታወሱት የኢጋድ የትምህርት ፕሮግራም አስተባባሪ ዶክተር ከበደ ካሳ፤ ለሶስት ዓመታት የሚቆየው ይህ ስምምነት በሚቀጥለው አመት ቢያንስ የስደተኞች ትምህርት በእያንዳንዱ አባል አገራት የትምህርት ፕሮግራም ውስጥ ተካቶ በትምህርት መረጃ ቋት ውስጥ ገብቶ አንድ ወጥ የትምህርት ስርዓትና መረጃ ይኖራል በሚል ታሳቢ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም ማንኛውም በአባል አገራቱ የሚገኙ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ ስደተኞች ከትምህርት ገበታ እንዳይገለሉ በሁሉም አባል አገራት ውስጥ እንደሚተገበር ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 28/2011
ሶሎሞን በየነ