ጡረታ ባህላዊ እና ሕጋዊ (ዘመናዊ) ትርጓሜ አለው። በባህላዊ ትርጉሙ አንድ ሰው ተጧሪ (ጡረተኛ) የሚባለው በዕድሜ መግፋት ምክንያት፤ እንደበፊቱ መውጣትና መውረድ፣ መሯሯጥ፣ በአጠቃላይ ሥራ መሥራት የማይችል ሆኖ በልጆቹ ወይም በሌላ የቤተሰብ አባል ሲጦር ማለት ነው። ለዚህም ነው እናቶችና አባቶች ሲጸልዩ ‹‹ጧሪ ቀባሪ አታሳጣኝ›› የሚሉት። በእርጅና ወቅት ተሯሩጦ መሥራት ስለማይቻል ደጋፊ ያስፈልጋል ማለት ነው።
ታዲያ እነዚህ ተጧሪ እናቶችና አባቶች ምንም አይሠሩም ማለት አይደለም። በአካባቢያቸው ለብዙ ማህበራዊ አገልግሎቶች ያስፈልጋሉ። አስታራቂ ሽማግሌዎች ናቸው፣ ወጣቶችንና ጎልማሶችን መካሪ ናቸው፣ ያሳለፏቸውን ዘመናት በመተረክ የጊዜ መስታወት ሆነው ያወጋሉ። በተለይም በሽምግልና ከፍተኛ ሚና ይወጣሉ። ሽምግልና የሚለው ቃል ዕድሜን ብቻ የሚገልጽ አይደለም፤ ማስታረቅ የሚል ተደራቢ ትርጉም እንዲይዝ ተደርጓል።
ወደ ዘመናዊው (ሕጋዊ) ስንመጣ ከባህላዊው የተቀዳ ነው። ጡረታ መውጣት ማለት አንድ ተቀጣሪ ከነበረበት የሥራ ዘርፍ በዕድሜ መግፋት ምክንያት የሚገባው ክፍያ ተጠብቆለት ከመደበኛው የቅጥር ሥራ መሰናበት ማለት ነው። እዚህ ላይ ነው ብዙ ነገሮች የሚነሱት። ለመሆኑ ጡረታ እና የሥራ ልምድ ኢትዮጵያ ዓውድ ምን እና ምን ናቸው?
ከስድስት ዓመታት በፊት በቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን አዳራሽ የኢትዮጵያን ሚዲያዎችና ጋዜጠኝነት የተመለከተ ውይይት ተዘጋጅቶ ነበር። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር) ለውይይት መነሻ የሚሆን ጥናታዊ ጽሑፍ አቀረቡ። በጽሑፋቸው እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ሚዲያዎች ውስጥ የሚገኙ ጋዜጠኞች ዕድሜያቸው በ30ዎቹ ውስጥ የሚገኝ ነው። ልምድ የላቸውም። በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ውስጥ የሚገኙት ግን ከጡረታ ዕድሜ በላይ የሚገኙ ሁሉ አሉበት። ተንታኝ ናቸው፤ ብዙ ነገር ያውቃሉ።
የጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር) ጽሑፍ በአንድ ዘርፍ ላይ የታየ ነው። እንደ ምሳሌ መውሰድ የሚቻልበት ምክንያት ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በብዙ የሙያ ዘርፎች እንዲህ አይነት ነገር መኖሩ ነው። አንድ ሰው በተቀጠረበት የሙያ ዘርፍ እና በተቀጠረበት ተቋም ውስጥ እስከ ጡረታ ዕድሜው ድረስ አይሠራም፤ አለ ከተባለም ምናልባት በመብራት ተፈልጎ የሚገኝ ካለ ነው። በሠለጠኑት ሀገራት ግን በአንድ ሙያ እና በአንድ ተቋም ውስጥ ብዙ ይቆያሉ።
እንዲህ እንዲህ እያለ አንድ ባለሙያ ተቋም እና የሥራ ዘርፍ እያቀያየረ የጡረታ ዕድሜው ይደርሳል። አንድ ባለሙያ ከተቋም ተቋም መቀያየሩን የሚያቆመው በጡረታ ዕድሜው አካባቢ ነው። ከዚህ በኋላ ነው በአንድ ዘርፍ ውስጥ የተሻለ ልምድ የሚኖረው። ስለዚህ ጡረታ እና የሥራ ልምድ በኢትዮጵያ ዓውድ የተለየ መልክ አለው ማለት ነው። በኢትዮጵያ የጡረታ ዕድሜ 60 ዓመት ነው፤ አንድ ባለሙያ አንድ ተቋም እና አንድ ዘርፍ ውስጥ የሚቆየው ምናልባትም ከ50 ዓመቱ በኋላ ነው። ስለዚህ ይህ ሰው በዚያ ዘርፍ ውስጥ የ 10 ዓመት ልምድ ብቻ ነው ያለው ማለት ነው። መሆን የነበረበት ግን ቢያንስ ከ30 ዓመት በላይ ነበር ማለት ነው።
የጡረታ መውጫ ዕድሜ እንደየሀገራቱ ይለያያል። ከፍተኛው የጡረታ ዕድሜ 70 ዓመት ሲሆን በብዛት የሚጠቀሙት የአውሮፓ ሀገራት ናቸው። ከአፍሪካ ሀገራት የሊቢያ 70 ዓመት ነው። ዝቅተኛው የቱርክዬ ሲሆን 45 ዓመት ነው።
የጡረታ የዕድሜ ጣሪያ እንደየሀገራቱ ብቻ ሳይሆን እንደየ ሁኔታውም ይለያያል። በሁሉም ሀገራት ወጥ አይደለም፤ አስቻይ ሁኔታዎች አሉት። ከሠራተኛው ጋር የሚደረጉ ስምምነቶች አሉት። ከሙያ ሙያ እና ከተቋም ተቋም ይለያያል። አንዳንድ ሀገራት (በተለይ የአሜሪካና የአውሮፓ ሀገራት) ከጡረታ በኋላ የሙሉ ጊዜና ክፍያ ቅጥር የሚቀጥሩም አሉ። ይህ የሚሆነው ግን በባለሙያውና በተቋሙ ስምምነት ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥም በቅርቡ በጸደቀው አዋጅ በተቋሙና በባለሙያው ስምምነት ቅድመ ሁኔታዎች እንዳሉት አይተናል። መቀጠልም ይቻላል፤ ባለሙያው ካልፈለገ ጡረታውን መውጣትም ይችላል ማለት ነው።
እዚህ ላይ ግን ልብ መባል ያለበት ነገር የአንዳንድ ሙያዎች ጉዳይ ነው። አንዳንድ ሙያዎች በባህሪያቸው የረጅም ዓመታት ልምድ የሚፈልጉ ናቸው። ባለሙያው ብዙ ልምድ ሲኖረው፣ በንባብም ሆነ በሕይወት ተሞክሮ ብዙ ነገር ሲያውቅ… የጡረታ መውጫ ጊዜው ይደርሳል ማለት ነው። በኢትዮጵያ ዓውድ ያልኩበትን ሌላ ምሳሌ ልጥቀስ።
ለምሳሌ፤ አንድ የ60 ዓመት ባለሙያ አለ እንበል። ከዛሬ 30 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ የትምህርትና የቴክኖሎጂ ሁኔታ ምን ላይ ነበር? ይህ ሰው ለብዙ ነገሮች ተደራሽ ነበር ወይ? የንባብ እና የሚዲያ ዕድሎች ነበሩት ወይ?
ይህ የ60 ዓመት ሰው አፍላ ዕድሜው የሚባለው ምናልባትም ከ40 እና ከ50 ዓመቱ በኋላ ያሉት ናቸው። ከዚያ በፊት በውስን አካባቢ የተወሰነ የነበረ ሊሆን ይችላል። ይህ ሰው በ60 ዓመቱ ጡረታ ቢወጣ ምን ያሳጣናል?
ይህ ሰው 60 ዓመት እዚች ሀገር ላይ ኖሯል። ይህ ሰው ለአንድ የ30 ዓመት ወጣት ቤተ መጽሐፍ ነው ማለት ነው። ያንን ዘመን ከዚህኛው ዘመን ጋር የሚያገናኝ ድልድይ ነው ማለት ነው። የ30 ዓመቱ ወጣት ለዚህ ዘመን ቴክኖሎጂ ቅርብ ነው፤ የ60 ዓመቱ ሰውየ ደግሞ ያ ዘመን ምን አይነት ሕይወት ይኖርበት እንደነበር ይናገራል ማለት ነው። ስለዚህ ወጣቱና አዛውንቱ አብረው ቢሠሩ ዘመንን ከዘመን የሚያገናኙ ይሆናሉ ማለት ነው።
በኢትዮጵያ ዓውድ የጡረታ ዕድሜ ቢያንስ 70 ዓመት መሆን ነበረበት። ምክንያቱም ከዛሬ 60 ዓመት በፊት በነበረው ሁኔታ ትምህርት በልጅነት የሚጀመርበት ዕድል አልነበረም። ምናልባትም ከአሥር ዓመት በላይ ሆኖ ሊጀምር ይችላል። የዚህ ሰው የትምህርትና የሥራ ዘመን ትንሽ ይሆናል ማለት ነው። ችግሩ ግን በኢትዮጵያ ዓውድ ዕድሜን በትክክል ማወቅም አስቸጋሪ ነው። ከዛሬ 70 ዓመት በፊት በጥቂት የባለሥልጣናት ቤት ካልሆነ በስተቀር የልደት ቀን የሚጻፍበት ባህልና ልምድ አልነበረም። ወላጆችም መጻፍና ማንበብ የማይችሉ ሊሆኑ ይችላሉ።
ምናልባት ሌላው ችግር ግን የጤና ሁኔታ ነው። ሕጉ 70 ዓመት ይሁን ቢባል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ የ70 ዓመት ሰው በሙሉ ጤንነት ላይ ላይሆን ይችላል። አንዳንድ የሥራ ዘርፎች ደግሞ ውጣ ውረድ የሚጠይቁ ሊሆኑ ይችላሉ። የጉልበት ሥራ እንኳን ባይሆን እንቅስቃሴ ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ።
ያም ሆነ ይህ ግን ልብ መባል ያለበት ነገር፤ በኢትዮጵያ ዓውድ አንድ ባለሙያ አንድ ተቋም እና አንድ ዘርፍ ውስጥ የተሻለ የሥራ ልምድ የሚኖረው በጡረታ ዕድሜው አካባቢ መሆኑን ነው። ስለዚህ በተቀመጠው የጡረታ ዕድሜ (60 ዓመት) ይውጣ ቢባል ያ ተቋም ወይም ዘርፍ የረጅም ዘመን ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች አይኖሩትም ማለት ነው። ተቋሙ ባለሙያ ሲቀያይር ይኖራል ማለት ነው። ምንም እንኳን ከተቋም ተቋም እና ከዘርፍ ዘርፍ የሚደረገውን የሠራተኛ ዝውውር የሚከለክል አዋጅ ይውጣ ባይባልም የብዙ ዓመት ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች ግን መጠቀም ይገባል!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም