ጅማሬዋ በጋዜጠኝነት ሙያ ነበር። ሕይወቴን የምመራው ውስጤ ባሉ ሀሳቦች በሚፈጠሩብኝ ጥያቄዎች ነው የሚል እምነት አላት። ከልጅነቷ ጀምሮ በደብተሮቿ ላይ የምትጽፈውን ጽሁፍ፤ የማንበብ ፍቅሯን ወደ መጽሀፍ እንድታሳድገው አደረጋት። የመጀመርያውንም መጽሀፏን አሳተመች። ከእነዚህ በተረፈ ጊዜዋ ደግሞ ወደ ንግዱ ዓለም በመግባት የተለያዩ ስራዎችን ትፈጥራለች። አሁን ላይ አራት ድርጅቶችን እያስተዳደረች ትገኛለች -ዮርዳኖስ ጉዕሽ።
የመጀመርያው ድርጅቷ ‹‹ ቑሩህ ማስታወቂያ እና ሁነት›› ዮርዳኖስ ገና የ17 ዓመት ልጅ እያለች የመሰረተችው ነው። ቑሩህ የሚለው ቃል ሶማሊኛ ሲሆን ቆንጆ ማለት ነው። ይህ ድርጅትም የተለያዩ ማስታወቂያዎችን መስራት የተለያዩ ሁነቶች ማዘጋጀት በዚህ ተቋም ውስጥ የሚሰሩ ናቸው። ሁለተኛው በስራ ላይ የሚገኘው ድርጅት ደግሞ ‹‹ ኢኤስቢ ሰክሬት ›› የሚሰኝ ሲሆን የተለያዩ የውበት መጠበቂያ ምርቶችን ለቆዳም ሆነ ለጸጉር የሚሆኑ ምርቶችን የሚያቀርብ ነው። እነዚህ ምርቶችም ራሱ ተቋሙ በሚፈጥራቸው የራሱ መሸጫ ሱቆች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ቅርንጫፉን ከፍቶ ለገበያ ያቀርባል። ዮርዳኖስ ሌላኛው የተሳተፈችበት ዘርፍ ደግሞ ሬስቶራንት ሲሆን መላይካ አፍሪካን ግሪልስ ይሰኛል የምዕራብ አፍሪካ ባህል፣ አመጋገብ የሚያስተዋውቅ ሲሆን የተለያዩ ግብዓቶችን እንዲሁ በማምጣት ለገበያ ያቀርባል።
ትውልድና እድገቷ በአዲስ አበባ አውቶቢስ ተራ ተብሎ በሚጠራበት ሰፈር ሲሆን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰቦች የተገኘች ናት። እሷ የተወለደችበት እና የነበረችበት የልጅነት ጊዜ እኔ እና መሰሎቼ የፊውዳል ርዝራዥ ተብለን የምንጠራበት ወቅት ነበር ብላ ታስታውሳለች። ዮርዳኖስ ዛሬ ላይ ደፋር ከሚባሉ እንስቶች ውስጥ አንዷ ሆኗ የተለያዩ የሕይወት ፈተናዎችን እየተጋፈጠች እና በከሰረችባቸው የንግድ ስራዎች ሳትሸነፍ እንደ አዲስ የምትጀምር ብርቱ ሴት ናት።
ታዲያ ዮርዳኖስ ለዚህ ሁሉ የሕይወት ጉዞዎቿ ዋነኛው ምክንያት ወላጅ አባቷን በልጅነቷ መነጠቋ መሆኑን ታነሳለች። ‹‹ አባቴን ባጣሁበት ጊዜ እናቴ የቤት እመቤት ስለነበረች ምንም ገንዘብ በእጇ ላይ አልነበረም፤ የገቢ ምንጫችን የነበረው አባታችን ነበር። ›› የምትለው ዮርዳኖስ በጊዜው እናታቸው ማድረግ የምትችለው አንድ ነገር የነበራቸው ቤት ሸንሽና በጊዜው ወደ ኢትዮጵያ በብዛት ይመጡ ለነበሩት ሶማሊያውያን ማከራየት ነበር።
የዮርዳኖስ አሁን ያለችበት የስራ ፈጠራ በንግድ ላይ በንቃት መሳተፍ እና በልጅነቷ የነበራትን ቅልጥፍና የሚያሳድግ ሕይወት እንድትመራ ያደረጋት ክስተት የተጀመረው በዚህ ወቅት ነበር ። ‹‹ ከሶማሊያውያኑ ጋር በመኖሬ ቋንቋቸውን አወቅሁ፣ ባህላቸውን ተማርኩ እናም እነሱ ያሏቸውን ክህሎቶች ለመማር ችያለሁ። ›› ከተማረቻቸው ክህሎቶች ውስጥም የተለያዩ ግብቶችን በመጠቀም እጣን መስራት፣ ሽቶ መቀመም፣ ሳሙና መስራት ለቆዳ ተስማሚ የሆኑ ውህዶችን ማዘጋጀት የሚሉ እውቀቶችን ማግኘት ቻለች። ከዚህም በተጨማሪ የሶማሌ ሴቶች የሚሰሯቸው ስራዎች ለገበያ አውጥተው ሽጠው ራሳቸውን የማስተዳደር ጥሩ ብቃት ያላቸው ሲሆን ዮርዳኖስ ይህንን ድፍረት ከእነሱ መማር እንደቻለች ትገልጻለች።
በልጅነቷ ፈጣን የነበረችው ታዳጊዋ ዮርዳኖስ በማኅበረሰቡ ካለው እይታ እና አመለካከት ትምህርታቸውን እንዲጨርሱ በስነምግባር እንዲያድጉ በሚል ከብዙ ነገሮች ታቅበው በጣም ቁጥጥር በነበረበት ቤተሰብ ውስጥ ማደጓን ታስታውሳለች።
የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ስትገባ የነበረውን ነጻነት የማስተናገድ ችግር ገጥሟት እንደነበር ታስታውሳለች። ከልጅነቷ ጀምሮ ማንበብ እና መጻፍ የምትወደው ተግባር መሆኑን የምታነሳው ዮርዳኖስ ጸሀፊ እና ደራሲ የመሆን ሕልሟን ለማሳካት በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ስነ-ጽሁፍን ስታጠና ጋዜጠኛ የመሆን ፍላጎትም ነበራት። ‹‹ እኔ ባደጉበት ወቅት የነበረው ውዥንብር፣ ሁከትና ውጥረት ብዙም ስለማልወደው ራሴን በንባብ እና በፊልም ውስጥ ነበር የምደብቀው፤ በዛ ወደ ኪነጥበብ ልሳብ ችያለሁ። ››ትላለች።
ዮርዳኖስ ሌላ ከንባብ እና ከስራ ፈጠራ ጋር የተቆራኘችበት አጋጣሚን ስታስታውስ አያቷን ታስታውሳለች። ‹‹ አያቴ ማንበብ ስለማትችል በጊዜው የነበረው የተቋዋሚ እና የገዢ ፓርቲ ሀሳብ የሚንጸባረቅባቸውን ጋዜጦች አምጥቼ ዜና አነብላትና ገንዘብ እሰራለሁ። ›› ይህ አጋጣሚም ከ13 ዓመቷ ጀምሮ ስራ መስራት ገንዘብ ማምጣት ጀምራለች።
ዮርዳኖስ የሰው ልጅ ሲያጣ የሚኖረውን ባህሪ አልወደውም። ከሰውነት በታች የሆነ ተግባር ውስጥ ሊገኝ ይችላል። ይህንንም አባቴን በሞት ባጣሁበት ወቅት በነበሩት ክስተቶች አይቻቸዋለሁ። ስለዚህ ማጣትና ችግር በፍጹም የማልወድ ሰው ነኝ ትላለች።
አባቷ ሹፌር በመሆናቸው ለልጆቻቸው እና ለቤተሰባቸው ሕይወት መልካም እና ችግር የሌለበት ቤተሰብ ይመሩ ነበር። እርግጥ አባታቸው ካለፈ በኋላም ችግር አላየሁም የምትለው ዮርዳኖስ በሕይወት እያሉ ደግ እና ለሰዎች ደራሽ የነበሩት አባቷ በዙርያቸው በሰዎች የተከበቡ ነበሩ። ሕይወታቸውን ያጡት በመኪና አደጋ ሲሆን በወቅቱ ከአሰብ የተለቀቁ መኪኖች መኖራቸውን ሰምተው ለመግዛት ያጠራቀሙትን ገንዘብ ይዘው አቀኑ፤ ነገር ግን በተፈጠረው አደጋ ብራቸው ተሰረቀ። በወቅቱ የዮርዳኖስ እናት ባለቤታቸው ያበደሩትን ገንዘብ ለማስመለስ የወዳጆቻቸውን በር ቢያንኳኩም ምላሽ የሚሰጣቸው ታማኝ የሆኑ ሰዎች ግን አልነበሩም። ይህ አጋጣሚ ለዮርዳኖስ በሕይወቷ ብዙ ጥያቄዎችን እንድትጠይቅ ራሷን እንድትመረምር ራሷን እንድትፈልግ አደረጋት።
‹‹ በልጅነቴ አይቻልም፣ አይሆንም፣ አትችይም አትደርሺም የሚሉ መልሶችን እያስተናገድኩ ነው ያደግሁት እኔ ደግሞ የምጥረው ይቻላል፣ ይሆናል፣ ይደረጋል የሚለውን በሕይወቴ ውስጥ ለማረጋገጥ ከችግር እና ከድህነት ለመውጣት ነው ። ›› ትላለች።
ዮርዳኖስ ምንም እንኳን ልጅ ብትሆንም ብዙ ሕልም ነበራትና ለመጀመርያ ጊዜ ስራ የጀመረችው የ17 ዓመት ታዳጊ እያለች ነበር። እሱም ቑሩህ የማስታወቂያ ድርጅት የተመሰረተው በዚያን ጊዜ ነበር። ዮርዳኖስ ይህንን ድፍረት ያገኘችው በልጅነቷ ፈጣን የነበረች ሲሆን ከእናቷ ተደብቃ የተለያዩ ስራዎችን በመስራት እና እቃዎችን በመሸጥ ነው።
በልጅነቷ ወደዩኒቨርሲቲ የገባችው ዮርዳኖስ ትምህርቷን የተማረችው በአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ ነው። እየተማረች በደጃች ውቤ ሰፈር ትንሽ ቢሮ በመከራየት ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመሆን የግጥም ምሽቶችን ማዘጋጀት፤ የማስታወቂያ ስራዎችን መስራት በጊዜው ትልልቅ የሚባሉ ፕሮጀክቶችን ተቀብላ መስራትን ተያያዘችው።
‹‹ የዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ አይኔን ለዓለም እንድገልጥ ሰዎችን እንዳውቅ የሀገሪቱን ማኅበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ነባራዊ ሁኔታ እንዳውቅ አድርጎኛል። ›› የምትለው ዮርዳኖስ በአንድ ወቅት የገጠማትን ስራ ታስታውሳለች ‹‹ የአሜሪካን ኤምባሲ በወቅቱ የጸረሽብር መጽሄትን በመላው ሀገሪቱ የሚያሰራጭ ሰው እፈልጋለሁ ብሎ ጨረታ ሲያወጣ በቑሩህ የማስታወቂያ ድርጅት አማካኝነት ተቀብዬ ለመስራት ተስማማው። ›› በማለት ከዚያም አብረዋት የሚማሩ ተማሪዎችን ገንዘቡ ከተከፈለኝ በኋላ ነው የምከፍላችሁ ብላ 230 ሰው አሰማርታ ስራውን ለመስራት ችላለች። ትልልቅ ድርጅቶች ቢሮዋን ለማየት ጥያቄ በሚቀያርቡበት ወቅት ቢሮዋ ደረጃውን የጠበቀ ባለመሆኑ ወደቤትዋ ይዛቸው ትሄድ ነበር።
ከተመረቀች በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ስራዋን የጀመረችው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በጊዜው ባወጣው ማስታወቂያ ተወዳድራ ለመቀጠር ቻለች። ‹‹ መጀመርያ ስገባ የተሰጠኝ ኃላፊነት ዜና ማንበብ ነበር። ነገር ግን ብዙም ደስተኛ አልነበርኩም። ›› የምትለው ዮርዳኖስ የሰዎች ታሪክ አልያም ሰው ሰው የሚሸት ፕሮግራም ለመስራት ከመፈለግ የሴቶች ፕሮግራምን ለማዘጋጀት ጥያቄ አቅርባ ተሳካላት። ‹‹ ፕሮግራሙን ሳዘጋጅ ያስተዋልኩት ነገር አብዛኛዎቹ ሴቶች በችግር ውስጥ የሚገኙ እና ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ውስጥ ያሉ ናቸው። ይህ ደግሞ ለእኔ ልቆይበት የማልችለው ስራ ሆነ። ››ትላለች።
ዮርዳኖስ በስራዋ ሴቶች ራሳቸውን በኢኮኖሚ የቻሉ አለመሆናቸው በዛ ላይ ደግሞ የሚያሳድጓቸው ልጆች መኖራቸው በችግር ውስጥ መኖራቸው ይከነክናት ነበር። የአብዛኛው ሴቶችም ከችግር ጋር የተያያዘ መሆኑ ጠንካራ ታሪክ ያላቸውን ስኬታማ ሴቶች ማግኘት ከባድ ነበር ትላለች።
በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የነበራትን ስራ ካቆመች በኋላ በነበራት ጊዜ ደራሲ የመሆን ሕልሟን የመጀመርያ መጽሀፍ አሳተመች ‹‹ልቡሰ ጥላ ›› የመጽሀፉ ርዕስ ሲሆን ስለ ሕይወት የሚሰማኝን ፍልስፍና ለማስፈር የሞከርኩበት መጽሀፍ ነው ካለች በኋላ ፍልስፍናም እንደሚመስጣት ትናገራለች።
በጊዜው በአሜሪካ ለሴቶች ነጻ የትምህርት እድል ለመስጠት የሚያስችል እድል በማግኘት ለሁለት ዓመት ያክል በስራ ላይ ከቆየች በኋላ ወደ አሜሪካን ሀገር አቀናች። በአሜሪካ በነበራት ቆይታ ጥሩ እድል እና እዛው እንድትቀር ጥሪ ቢቀርብላትም ለዮርዳኖስ ግን ምቹ አልነበረም
‹‹ እኔ ሰው በጣም እወዳለሁ፤ መጣር መስራት ነበር ምፈልገው፤ በአሜሪካ ደግሞ የተዘረጋ ሲስተም በመኖሩ ማንኛውም ሰው በዛ ሲስተም ውስጥ ሰርቶ ተመሳሳይ የሆነ ሕይወትን ነው የሚመራው፤ ያ ደግሞ ለእኔ አሰልቺ ነበር ። ›› ስትል ሁኔታውን ታስረዳለች።
ዮርዳኖስ አዳዲስ ነገሮችን በመፈለግ ለመፍጠር የተዘጋጀች በመሆኗ በአሜሪካ የቀረበላትን ጥሪ ትታ ወደ ጋና ሄደች። በዚያ የነበረው የስራ እንቅስቃሴም ሆነ ሕይወትን በዚያ በቆየችባቸው ጊዜያት ምቹ ሆኖ አግኝታዋለች። በጋና በነበረችበት ወቅት ሕይወቴን በንግድ መምራት የምችልበትን እውቀትና ክህሎት እንዳዳብር ረድቶኛል የምትለው ዮርዳኖስ በልጅነቷ ከሶማሊያ ጎረቤቶቿ የተማረችውን ለቆዳ መንከባከቢያ የሚረዱ ምርቶች በሀገር ውስጥ የሚገኘውን ቀሲል ጨምሮ ከኢትዮጵያ ኤክስፖርት በማድረግ መስራቷን ቀጠለች። ከዚያም የቆዳ መጠበቂያ ምርቶችን ወዳለቀላቸው ምርቶች የመቀየር ጥያቄ ሲቀርብላት የኮስሞቲክስ ምሮችን ማምረት እና መቀመም ላይ በትምህርት ቤት ውስጥ ከተማረች በኋላ ሙሉ ለሙሉ ወደ ኢትዮጵያ መጣች።
ወደ ኢትዮጵያ ከመጣች በኋላ የጀመረችውን የንግድ ስራዋን ለማስቀጠል ስራ ስትጀምር ያለው ሲስተም እጅግ በጣም ከባድ ሆኖ አገኘችው። ስራዎችን ከጅምሩ መስራት ለሚፈልጉ አዳዲስ እሳቤዎችን እና የስራ ሀሳቦችን ይዘው ለሚመጡ ያለው ሲስተም እንዲያድጉ ሳይሆን በቶሎ ግብር እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ነበር። ይህ ደግሞ አዳዲስ ቢዝነሶች እንዲዳከም ያደርጋል። በመሆኑም አዳዲስ የስራ ሀሳብ ይዘው ወደ ገበያው የሚመጡ የስራ ፈጣሪዎች የሚበረታቱበት እና የሚደገፉበት መንገድ ቢኖር የሚል ሃሳብ ታነሳለችለ።
ዮርዳኖስ ኢትዮጵያ ከመጣች በኋላ ኢኤስቢ የተሰኘ የተለያዩ ለጸጉር እና ለቆዳ የሚሆኑ ምርቶችን ወደ ገበያው የሚያቀርብ ድርጅት መሰረተች። ወደፊትም ይህ ምርት በኢትዮጵያ የተመረተ ሆኖ በሌሎች ሀገራት እውቅና ያለው እና ለጥቁር ሴቶች ቆዳ እና ጸጉር ተስማሚ የሚሆን ነው። ዮርዳኖስ ባለትዳር እና የሁለት ልጆች እናት ስትሆን የኢኤስቢ ብራንድ ወደፊት ልጆቼ የሚያስቀጥሉት እና ቀጣዩ ትውልድ ሊጠቀምበት የሚችል ነው ስትልም ሕልሟን አካፍላናለች።
ዮርዳኖስ በስራዋ አራት የሚያህሉ የስራ ፈጠራዎችን ወደ ገበያው ለማውጣት በተጓዘችበት ሂደት ውስጥ ሲስተሙ ለሴቶች አልተሰራም ወደ ስራ ለመግባት ለሚፈልጉ እንስቶች ምቹ እንዳልሆነ ተረድታለች። ‹‹ ለምሳሌ የስራ ሀሳብ ላላቸው ሰዎች ባንኮች ብድር ሲያመቻቹ የማስያዣ ኮላተራል ንብረትን ይጠይቃሉ። አብዛኛዎቹ የሀገራችን ሴቶች ከእናታቸው ቤት ወጥተው ንብረት ሳያፈሩ ትዳር ለሚመሰርቱ ሴቶች ይህ ሲስተም ከኢኮኖሚው እንድትገለል የሚያደርግ ነው። ስለዚህ ሴቶችን የትልልቅ ንግድ አካል ለማድረግ ከተፈለገ የሆነ ያህል ርቀት መጥቶ ለሴቶች እድል መስጠት፤ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ልዩ ድጋፍና የተለየ ስርዓት መዘርጋት አለበት። ›› ትላለች።
በሀገራችንም ሆነ በዓለማችን ላይ ከሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች ሴቶች በሚያውቋቸውና በማያውቋቸው ሰዎች በይበልጥ ጥቃት ይደርስባቸዋል። የሴቶች መብት ለማስከበር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚሰሩ እንቅስቃሴዎችም ሆኑ ተቋማት በዓለም ላይ ይገኛሉ። ነገር ግን እነዚህ ጥቃቶች አሁንም ድረስ ባደጉትም ሆኑ ባላደጉ ሀገራት ሪፖርት ይደረጋሉ። ‹‹ ሴቶችን ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ጅማሮዎች ቢታዩም የማኅበረሰባችን ግማሹ ክፍል ሴት በሆነበት ሀገር አንድ ተቋም ብቻውን በቂ ሊሆን አይችልም። ሴቶች ላይ መሰረት ያደረጉ ተቋማት በሴቶች መብት እና ጥቃት ጉዳይ የተለያዩ ስብሰባዎችን ቢያደርጉም ውጤት ሲያመጡ ግን አይታይም። በመሆኑም ማብቃት ላይ መስራት ይገባቸዋል። ›› የምትለው ዮርዳኖስ ሴቶች የልማቱ አካል መሆን ይገባቸዋል የሚለውን አክላለች።
ዮርዳኖስ ባላት የማህበራዊ ገጽ ያሏትን ሀሳቦች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ታጋራለች። በዚህም ሀገር ያላት ትልቁ አቅም ሰው መሆኑን አንስታ ሕዝባችንን ማሰልጠን እና ከዓለም እኩል ማድረግ ላይ በይበልጥ መስራት ይገባልም ትላለች።
በንግዱ ዓለም ላይ ሰዎች በተለያዩ አጋጣሚ ከስረው ከገበያ የሚወጡበት አልያም የጀመሩትን መቀጠል ሳይችሉ የሚቀሩበት ፈተና ይገጥማቸዋል። ዮርዳኖስ ካሳለፈችው ለዚህ የምትለው አላት። ‹‹ በንግድ ዓለም ላይ ከስሮ ሙሉ ለሙሉ መውጣት የሚባል እሳቤ ትንሽ ነው። ምክንያቱም በየቀኑ ፈተናዎችን ማስተናገድ ያለ በመሆኑ አዕምሮ የተለያዩ ውሳኔዎችን እየወሰነ እና መፍትሄ የሚሆኑ መንገዶችን እያሰበ ስራው እንዲቀጥል ያደርጋል እንጂ ተስፋ መቁረጥ መታሰብ የለበትም። ምክንያቱም በንግድ ውስጥ መውደቅ መነሳት ያለ ነው። ›› ትላለች
ለዚህም አሁን ላይ በስራ የሚገኘው መላይካ ሬስቶራንትን ለመክፈት ያነሳሳት ሀሳብ የኮቪድ ወረርሺኝ በዓለም ስጋት ሆኖ የስራ እንቅስቃሴዎች በተዘጉበት ወቅት በውበት መጠበቂያ ምርቶች ላይ ያሉ ሰራተኞቿ በቤት ውስጥ ሆነው ለረጅም ጊዜ ደሞዝ መክፈል ይጠበቅባት ነበር፤ ዮርዳኖስም ይህንን ለተወሰኑ ወራት ካደረገች በኋላ ደሞዝ ለመክፈል በተቸገረችበት ወቅት ግን ተጨማሪ ስራ እንደሚስፈልጋት በማሰብ ያሏትን ሰዎች እና ግንኙነቶች ተጠቅማ ሌላ ስራ መፍጠር እና ለሰዎችም የስራ እድል ለመስጠት ችላለች።
በመሰረተቻቸው የፈጠራ ስራዎች ሴቶች በኢኮኖሚ ውስጥ እንዴት ገንዘብ ማንቀሳቀስ እና ገንዘብ መስራት ይቻላል የሚለውን እንዲያውቁ እና ራሳቸውን እንዲችሉ እንዲሁም ድምጻቸውን ማሰማት እንዲችሉ ነው። ‹‹ የፌሜኒዝም አልያም የሴቶች መብት ጥያቄ ምግብ የማብሰል እና ያለማብሰል ወንዶች ከሴቶች ይበልጣሉ የሚለው ክርክር ሳይሆን የሴቶችን ምርጫ በማክበር ትክክለኛ ኑሮ እንድትኖር ማድረግ ነው ። ›› ትላለች።
ዮርዳኖስ አሁን ላይ ከዚህ ቀደም ትሰራው የነበረውን የጋዜጠኝነት ስራ መመለስ እና ያለፈበችትን የሕይወት መንገድ ለሌሎች በመጽሀፍ መልክ የማጋራት ሕልም እንዲሁ አላት።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 21 ቀን 2016 ዓ.ም