አዲስ አበባ፡- ዳኞች በመጪው የክረምት ወቅት የዕረፍት ሰዓታቸውን በመጠቀም በዓመቱ ለተጠራቀሙ መዝገቦች እልባት ለመስጠት የሚያስችላቸውን ዝግጅት እንደጨረሱ የ“ጀስቲስ ፎር ኦል ፌሎው ሺፕ ኢትዮጵያ” አስታወቀ። የተሻሻለው የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት የዳኞች ስነምግባርና የዲሲፕሊን ደንብም ተመርቋል።
የ“ጀስቲስ ፎር ኦል ፌሎው ሺፕ ኢትዮጵያ” ፕሬዚዳንት ፓስተር ዳንኤል ገብረስላሴ እንዳስታወቁት ዳኞች ለበርካታ ዓመታት መፍትሔ ያልተሰጠባቸውን ውዝፍ የክስ መዝገቦች በዕረፍት ሰዓታቸው እልባት ለመስጠት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል። በተለያዩ ክልሎች ዳኞች ሲያጠፉ የሚቀጡበትን የሥነ-ሥርአት ደንብ ለማሳተም እየተሠራ ነው።
በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ከ20 እስከ 30 ሺህ የክስ መዝገቦች ይቀንሳሉ ብለው እንደሚያስቡ የጠቀሱት ፓስተር ዳንኤል ባለፈው ተመሳሳይ ወቅት 23 ሺህ መዝገብ እልባት በመሰጠቱ 23 ሺህ ዜጎች ፍትሕ አግኝተዋል።
እንደ ፓሰተር ዳንኤል ድርጅታቸው በፍትሕ ዘርፍ ከክልሎች ጋር በመሥራት ላይ ሲሆን በአራቱ ክልሎች ማለትም የአማራ፣ የትግራይ፣ የደቡብ እና የኦሮሚያ ክልሎች ጋር እየሠራ ነው፤ በትናንትናው ዕለትም የተሻሻለው የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት የዳኞች ስነምግባርና የዲሲፕሊን ደንብ ተመርቋል።
የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሙሉጌታ አጎ በበኩላቸው ዳኞች በክረምት ወራት ውዝፍ መዝገቦችን እልባት መስጠታቸው በፍትህ ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ ፋይዳ አለው።
በርካታ ሰዎች በሚንከባለሉ ፋይሎች ምክንያት እስር ቤት የሚቆዩበት አግባብ አለ ያሉት አቶ ሙሉጌታ ይህንንም በተፋጠነ ሁኔታ ውሳኔ በመስጠት በርካታ ሰዎች ፍትህ የሚያገኙበት፤ ከእስር የሚፈቱ ካሉ እንዲፈቱ የሚደረግበት ሌሎችም ደግሞ በፍትሐ ብሄር ጉዳዮች ላይ በተፋጠነ ሁኔታ ውሳኔ እንዲሰጣቸው የሚረዳ ነው የሚል ሃሳብ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2011
ዳግማዊት ግርማ