ሰበታ፡- በሰበታ ከተማ ከ700 የሚበልጡ ኢንቨስትመንቶች ከ60 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደፈጠሩላቸው የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ።
የሰበታ ከተማ ከንቲባ አቶ ብርሃኑ በቀለ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት ከተማዋ ለኢን ቨስትመንት ባላት ተመራጭነት መዋዕለ ንዋያቸውን የሚያፈሱ ባለሀብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ከተማዋን ወደ የኢንዱስትሪ መንደርነት እያሸጋገራት ነው።
ሰበታ የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደረግባት፣ ፈጣን የከተማ መስፋፋትና ዕድገት የሚታይባት፣ ነዋሪዎቿም በተለያዩ ፋብሪካዎች ውስጥ ተቀጥረው በመሥራት የሥራ ጊዜን ጥቅም ላይ ማዋልን የተለማመዱባት ከተማ እንደሆነች አቶ ብርሃኑ አስታውቀዋል።
ኢንቨስትመንት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከማንቀሳቀስ አንጻር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንዳለ የጠቀሱት ከንቲባው ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠርም ትልቁን ሚና የሚጫወት ዘርፍ ነው ብለዋል። ሰበታ የኢንዱስትሪ መንደር እየሆነች መምጣቷ በአካባቢው ለሚገኙም ሆነ ከአካባቢ ውጪ ለሚመጡ በርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው አስችሏል።
ሰበታን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ካደረጓት ነገሮች መካከል የአካባቢው ማህበረሰብ ለኢንቨስትመንት ያለው ጉጉትና አቀባበል፣ ለሥራ ያለው የተነቃቃ መንፈስ፣ ከተማዋ ጥሬ ዕቃን ለማግኘትና ምርትን ወደ ተፈለገው አቅጣጫ ለማሰራጨት አመቺ መሆኗ፣ ባለሀብቱ ማግኘት የሚገባውን መንግሥታዊ አገልግሎት በሚገባ ማግኘቱ ፣ በቂ የሰው ኃይል መኖሩና የአካባቢውም የጸጥታ ሁኔታ አስተማማኝነት ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ እንደሆኑ ተናግረዋል።
በፋብሪካ ውስጥ ተቀጥረው ከመሥራት ባሻገር ፋብሪካዎቹ የሚያመርቷቸውን ምርቶች ለገበያ በማቅረብ በተፈጠረ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ለበርካታ ተጨማሪ ዜጎችም የሥራ ዕድል እንደተፈጠረ ገልጸዋል። በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው የፋብሪካዎቹን ውጤት ለገበያ በማቅረብ ሥራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶችም እንዳሉ ጠቁመዋል።
በከተማዋ ካለው የኢንቨስትመንት ፍሰት ጋር ተያይዞ የተሟላ የመሰረተ ልማት እጥረት እንዳለ የተናገሩት ከንቲባው የከተማዋን የመንገድ ችግር ለመፍታት እየተሠራ ነው ብለዋል። በከተማዋ ትላልቅ ፋብሪካዎች ያሉ እንደመሆኑ በድንገት የሚፈጠር የእሳት አደጋን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በቀጣይ የህዝቡን ፍላጎት ማዕከል ያደረገ ሥራ ለመሥራት ታስቧል ያሉት ከንቲባው የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ከግል ባለሀብቶች ጋር እየተሠራ እንዳለ ገልጸዋል። በቅርቡም በከተማው የሚገኙ ባለሀብቶች ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር 29 ሚሊየን ብር በማውጣት ለከተማው ነዋሪዎች የመጠጥ ውሃ ጉድጓዶችን እንዳስቆፈሩ አስታውቀዋል።
አሁንም ቢሆን በከተማው ሙሉ ለሙሉ የሥራ አጥነት ችግር ተቀርፏል ማለት እንደማይቻል እና በየጊዜው የሚመጣውን ሥራ ፈላጊ ለማስተናገድ እንዲያስችል ባለሀብቶችን ወደ ከተማዋ የመጋበዝና ነባሮቹም የማስፋፋት ሥራ በመሥራት ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር እየተሠራ እንዳለ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2011
እያሱ መሰለ