አዲስአበባ፡- ኢትዮጵያ በአገራዊ የቡና ፍጆታዋ የተሻለ ብትሆንም በአፍሪካ ደረጃ ግን ዝቅተኛ መሆኑ ገቢን ለማሳደግም ሆነ በዓለም ገበያ ያጋጠመውን የቡና ገበያ የዋጋ መውረድ ለመቋቋም እንዳላስቻለ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ። በዓለም ላይ የቡና ዋጋ እየወረደ መምጣት በቡና አምራች አርሶአደሮች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩ ተጠቆመ።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ትናንት በኢሊሌ ሆቴል ከተለያዩ አፍሪካ ሀገራት ከተውጣጡ ልዑካን ቡድን ጋር በአፍሪካ የቡና ፍጆታ ያለበትን ደረጃ አስመልክቶ ለሁለት ቀናት ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ እንደገለጹት ኢትዮጵያ አገር ውስጥ የቡና ፍጆታዋ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተሻለ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ተጠቃሚነቷም 50 መቶ ያህል ድርሻ ይዟል።
እንደ ዶክተር አዱኛ ገለፃ አፍሪካ እንደ ቡና አምራችነቷ በሀገር ውስጥ የቡና ፍጆታዋን በማሳደግ ወደ ገንዘብ መቀየር ባለመቻሏ ተጠቃሚ አልሆነችም፤ በዓለም ላይ የወደቀውን የቡና ዋጋም ለመቋቋም ባለማስቻሉ አፍሪካን ጎድቷታል ብለዋል።
እንደ ዶክተር አዱኛ አስተያየት የውይይቱ ዓላማ የአፍሪካ ሀገራት በሀገር ውስጥ የቡና ፍጆታን በማሳደግ ከዘርፉ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አቅጣጫ ማስቀመጥ ነው። በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ ተሞክሮዋን በማካፈል የሚኖራት ድርሻ ከፍተኛ ነው። ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ የቡና ፍጆታዋ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት ብቻ ሳይሆን፣ ማኅበረሰቡ በቡና ሥነሥርዓት ላይ በማህበራዊ ችግሮቻቸው ዙሪያ እንደሚነጋገርና የግንኙነት እሴቶቹንም የሚያጠናክርበት እንደሆነ ለተሳታፊዎቹ ገልጸዋል።
ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በዓለም ላይ የቡና ዋጋ እየወደቀ መምጣት የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንዲቀንስ ከማድረጉ በተጨማሪ ቡና አምራች አርሶአደሮችን ተስፋ እያስቆረጠ መምጣቱንና የማምረት ሂደቱ ላይም ተጽዕኖ ማሳደሩን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ የአፍሪካውያን የገበያ ትስስር ተስፋ እንደሚሰጥ አመልክተዋል።
የዓለምአቀፍ ቡና ድርጅት ዋና ፀሐፊ ዶክተር ፍሬድ ካውማ በበኩላቸው ቡና ለአፍሪካ ወሳኝ የኢኮኖሚ ምንጭ መሆኑን አስታውሰው፣ ከዚህ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ምንጭ ተጠቃሚነትን እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል ምክክር መደረጉ አንድ ዕርምጃ እንደሆነ ገልጸዋል።
አፍሪካ ጥሬ ቡና ለተለያዩ ዓለም ሀገራት በመላክ መልሳ በውድ ዋጋ መግዛቷ በተጠቃሚነቷ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑንም አመልክተዋል። እሴት ጨምሮ ተጠቃሚነትን በማሳደግ ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበትም ጠቁመዋል። በሀገር ውስጥ የቡና ፍጆታን ለማሳደግ በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት የተጀመሩት እንቅስቃሴዎችም መጠናከር እንዳለባቸው አስታውቀዋል።
በሀገር ውስጥ የቡና ፍጆታን ለማሳደግ መልካም ተሞክሮ ካላቸው ሀገሮች መካከል ኮሜሩን ዓመታዊ የቡና ሥነሥርዓት ፌስቲቫል በማዘጋጀት ተጠቃሚነቷን በማሳደግ ላይ መሆኗን ጠቁመው፣ ኮትዲቯር ወጣቶችን በማሳተፍ ኬኒያም በፕሮጀክት ደረጃ፣ ዩጋንዳም በቤትና በቢሮ ውስጥ የቡና ተጠቃሚዎችን ቁጥር በማሳደግ ተጠቃሽ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በምክክሩ ተሳታፊ ከሆኑት መካከልም የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ሚኒልክ ሀብቱ በሰጡት አስተያየት በሀገር ደረጃ የአፍሪካን የእርስ በርስ ገበያ ለማጠናከር የተዘጋጀው መድረክ ቡና ላኪውንም አምራቹንም እንደሚያነቃቃ ገልጸዋል። በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ፍጆታው ሲጨምር ኢትዮጵያ በገቢ ይበልጥ ተጠቃሚ እንደምትሆንና ጥሩ ዕድል እንደሆነ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በዓመት ወደ 280 ሺ ሜትሪክ ቶን ቡና እንደምታመርት እና የቡና መገኛ ሆና ከብራዚል፣ ቬትናም፣ኮሎቢያ እና ኢንዶኔዥያ ቀጥሎ ከፍተኛ ቡና አምራች መሆኗ ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2011
ለምለም መንግሥቱ