አዲስ አበባ፡- በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት በሀገሪቱ በሚከናወኑ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ትናንት በ5ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ ልዩ ስብሰባ 2012 ዓ.ም ረቂቅ በጀት ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡ ሚኒስትሩ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንዳመለከቱት በሀገሪቱ የፕሮጀክቶች መጓተት ለአላስፈላጊ ወጪ በመዳረግ በበጀት ላይ ጫና ያሳድራል።
ሀገሪቱ በመንገድ፣ በመስኖና በዩኒቨርሲቲዎች ላይ ከፍተኛ በጀት የሚመደብ በመሆኑ አፈጻጸ ሙን በጥንቃቄ ለመከታተል እየተሠራ ነው ያሉት ሚኒስትሩ የህዝብ ሀብትን በአግባቡ ከመጠበቅና የልማት ተጠቃሚነትን በፍጥነት ከማረጋገጥ አንጻር ታላላቅ ፕሮጀክቶች በዕቅዳቸው መሰ ረት መጠናቀቅ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ፕሮጀክቶችን በሚያዘገዩ ኮንትራክተሮችም ላይ ዕርምጃ በመውሰድ የተመደበው በጀት የመንግ ሥትን ሚና በአግባቡ ለመወጣት እንዲያስችል ይደረጋልም ብለዋል።
በጀቱን በተመለከተ የምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የገጠር ኤሌክትሪክ ድጎማን፣ ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነትን፣ የበጀት ጉድለትን፣ የግዢ ስርዓቱ የጥራትና የዋጋ ግነት የሚታይበት መሆኑ፣ በየተቋማቱ የቅንጦት ቁሳቁስ ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን፣ የገቢና ወጪ የንግድ ሚዛን ያለመጣጣሙ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን የመሳሰሉትን ጥያቄዎች አቅርበዋል። ለተነሱት ጥያቄዎችም ሚኒስትሩ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል።
በጀቱ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል አብዛኛው ኃላፊነት የወደቀው ሥራ አስፈጻሚዎች ላይ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሩ ከባለፉት ዓመታት ተሞክሮዎች በመነሳት በበርካታ ጉዳዮች ላይ ማስተካከያዎች እንደተደረጉም አስረድ ተዋል። በአጠቃላይ ረቂቅ በጀቱ አሁን የተያዘውን ልማት የበለጠ በሚደግፍ መልኩ የተበጀተ መሆኑን በመግለጽ በልማት ጉዞ ላይ ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑ ታሳቢ እንዲደረግ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2011
ኢያሱ መሰለ