የዓለማችንንም የሀገራችንንም ክብረ ወሰን የሰበረ የትውልዶች ገድል፤

በዛሬው እለት 30 ሚሊየን ሕዝብ በአንድ ጀንበር 600 ሚሊየን ችግኞችን በ325 ሺህ ሄክታር ላይ ለመትከል መዘጋጀቱን፤ ችግኞቹ በ5 ሺህ 456 ተፋሰሶች ላይ እንደሚተከሉ እና የካርታ ዝግጅት ሥራውም መጠናቀቁን ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል። ባለፈው ዓመትም 34 ሚሊየን ሕዝብ በተሳተፈበት በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ 550 ሚሊየን ችግኞች መተከላችንም ይታወሳል።

በእርግጥ ከሌለ ጥሪታችን ዝቀን ዳር እስከ ዳር፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከነፍሰ ጡር እስከ አራስ፣ ከጉዳት አልባው እስከ አካል ጉዳተኛ፣ ወጥተን ችግኝ የምንተክለው መጀመሪያ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ነው። ትሩፋቱ ድንበርና ዘር የተሻገረ ነው። ዛሬ በአየር ንብረት ለውጥ ቁም ስቅሏን እያየችና የምትይዝ የምትጨብጠው ላጣችው እናት ዓለም ጭምር የሚተርፍ ነው። በነገራችን ላይ ትሩፋቱ ለእኛም ከክልል ወሰንና ከጎሳ ግድግዳ የተሻገረ ነው። እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የብሔራዊ ሰንደቃችን ፕሮጀክት ነው።

ዓለማችን በአማዞንና በኮንጎ ደኖች ብቻ ተንፍሳ በጤና ውላ እንደማታድር እየታዘብን ነው። ትንፋሽ እያጠራት፣ ሰደድ እሳት እየለበለባትና በውሃ ጥም ጉሮሮዋ እየደረቀ ነው። በዓለም ላይ ተመዝግቦ የማያውቅ እጅግ ከፍተኛ ሙቀት፣ ጎርፍና ሰደድ እሳት እየተከሰተ ነው። ይህን የአየር ንብረት መዛባት ሌት ተቀን እየዘገበ ያለው ዓለም አቀፍ ተብዬው ብዙኀን መገናኛ ባለፈው ዓመት ከ34 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በአንድ ጀንበር ወደ 567 ሚሊዮን የሚጠጋ ችግኝ መትከላቸውን ግን ባላየ ባልሰማ አልፎታል ማለት ይቻላል።

በሶሪያ ኢድሊብ የሰፈራ ካምፕ ተፈናቃይ ወላጆች ልጆቻቸውን እየተንበለበለ ካለው ሀሩርና ሙቀት ለመታደግ ለመጠጥ እንኳ ውድ ከሆነው ውሃ ቀንሰው በልብስ ማጠቢያ ሳፋ ውሃ ጨምረው እስከ ማስቀመጥ መድረሳቸውን የዘገበልን “CNN” በአንድ ጀምበር 567 ሚሊዮን ችግኝ መተከል ጉዳይ ግን በዓይኑ አልሞላም። የምዕራባውያን ሚዲያ አጀንዳ ይሰጥሃል እንጂ አጀንዳ ለመቀበል ይተናነቀዋል። እንዲህ ነው አሠራሩ።

ባለፉት 50 ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥ ያደረሳቸውን ጉዳቶች አስመልክቶ ያስጠናውን ጥናት ይፋ ሲያደርግ፤ የአየር ንብረት ለውጥ ባለፉት 50 ዓመታት ከ4 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ዶላር በላይ የኢኮኖሚ ኪሳራ ሲያደርስ 2 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል። የሚያሳዝነው የበለጸጉ ሀገራት ባመጡት ጦስ ዋጋ እየከፈሉ ያሉት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ቢሆኑም እነሱም በአየር ንብረት ፍዳቸውን መብላታቸው አልቀረም።

ሰሞነኛውን የአሜሪካና የአውሮፓ ከፍተኛ ሙቀት ልብ ይላል። ሆኖም የከፋውን ዋጋ እየከፈሉ ያሉት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ናቸው። በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሕይወታቸውን ከሚያጡ 10 ሰዎች ውስጥ ዘጠኙ በታዳጊ ሀገራት የሚኖሩ ናቸው። ከፈረንጆቹ 1970 እስከ 2021 ድረስ ባሉት ዓመታት ውስጥ ከ12 ሺህ በላይ አስከፊ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች ተከስተዋል። በምሥራቅ አፍሪካ ብቻ በ10 ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን አፈናቅሏል። አስከፊ ድርቅ፣ ከፍተኛ ሙቀት፣ በጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የአውሎ ነፋስ እና የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ የደረሱ የአየር ንብረት አደጋዎች ናቸው።

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በአህጉራችን 1800 አስከፊ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች ተከስተው 755 ሺህ ሕዝብ ሲሞት ከ185 ቢሊዮን በላይ ዶላር ደግሞ የኢኮኖሚ ጉዳት ደርሷል። አሜሪካ ብቻዋን በዚሁ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የአንድ ነጥብ ሰባት ትሪሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ ጉዳት ጎብኝቷታል። የእስያ አህጉር ከሁሉም አህጉራት በበለጠ በአየር ንብረት ለውጥ የተጠቃ ሲሆን በነዚህ አደጋዎች ምክንያት የአንድ ነጥብ አራት ትሪሊየን ዶላር ጉዳት ደርሶበታል።

ሌላ የዓለም ባንክ ጥናት ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ በምሥራቅ አፍሪካ ብቻ እስከ 2050 ድረስ ከ38 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሊፈናቀሉ እንደሚችል ይተነብያል። የአየር ንብረት ለውጥ ሰለባ ሆነው የሚፈናቀሉት፤ በድርቅ ሳቢያ ሌላ የእርሻ መሬት አሊያም ለየት ያለ ሥራ ለመፈለግ ወደ ከተማ እና ሌሎች አካባቢዎች የሚፈልሱ አርሶ አደሮች እንዲሁም ንጹሕ የመጠጥ ውሃ ፍለጋ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ይገኙበታል።

‹‹በእንቅርት ላይ…›› እንዲሉ የበለጸጉ ሀገራት ለአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል ቃል የገቡትን የ100 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ድጋፍ አለመፈጸማቸው አህጉሩ አካባቢ ጥበቃ ላይ ሊሠራቸው ያቀዳቸውን ተግባራት ማስተጓጎሉን የአፍሪካ ኅብረት መግለጹ አይረሳም። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባይደን የአየር ንብረት ልዩ መልዕክተኛ ጆን ኬሪ ሰሞኑን አሜሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ምንም አይነት ካሣ እንደማትከፍል መናገራቸው ዓለምን እያስገረመ ነው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ 5 የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ማለትም ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ዑጋንዳ እና ብሩንዲ በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ እየተጎዱ መሆኑን ሪፖርቱ ያመለክታል። በዓለም ባንክ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ምክትል ፕሬዚዳንት ሃፌዝ ግሃኔም፤ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ መጠነ ሰፊ ርምጃ በአፋጣኝ ካልተወሰደ እስከ 2050 ድረስ በርካታ ሚሊዮኖች ሊፈናቀሉ ይችላሉ ብለዋል። የካርቦን ልቀት መቀነስን ጨምሮ ሌሎች የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚረዱ ርምጃዎችን በአፋጣኝ መውሰድ ከተቻለ የተፈናቃዮችን ቁጥር በ30 በመቶ መቀነስ እንደሚቻልም አስታውቀዋል።

ሀገራት የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ካልተስማሙ ከኢንዱስትሪ አብዮት ወዲህ የከባቢ አየር ሙቀት በ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይጨምር ይሆናል ሲል ስጋቱን ያጋራው የTIME ዘገባ በበኩሉ እስከ አውሮፓውያኑ 2030 ዓ.ም 350 ሚሊዮን ሕዝብ ለድርቅ፣ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ለከፋ ድህነት ሊጋለጥ ይችላል ሲል አበክሮ ያስጠነቅቃል። የዓለም ሙቀት በሽርፍራፊ ሴንትግሬዶች በጨመረ ቁጥር የአየር ንብረት ለውጡ እየተባባሰ ይሄዳል። ይህ ፍርሃትን ለማንገስ ሳይሆን በሳይንቲስቶች የተረጋገጠ ጥሬ ሐቅ ነው። የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች፣ የዘርፉ ተመራማሪዎች ላለፉት አስርት ዓመታት ፖለቲከኞች ለአሳሳቢው የአየር ንብረት መዛባት ፖለቲከኞች ትኩረት እንዲሰጡት ነጋ ጠባ ቢወተውቱም ሰሚ ሳያገኙ በመቅረታቸው ዛሬ ላይ ደርሰናል።

ችግኝ ተከላ የአየር ንብረት ለውጥን፣ የዓለም ሙቀት መጨመርንና የአካባቢ ጥበቃ ችግሮቻችንም ሆነ ድህነትን፣ የምግብ ዋስትና ጉድለትን፣ የምርታማነት ተግዳሮትን፣ ድርቅን፣ ረሀብን፣ የዝናብ መቆራረጥንና መቅረት፣ የውሃ እጥረትን፣ የኑሮ ውድነትን፣ በፈጣን የሕዝብ ቁጥር እድገትና በምርት አቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተትን፣ ሥራ አጥነት፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰትን፣ የፀጥታና የደህንነት ችግርን፣ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር በማሳለጥ እና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማለም መስፈንጠሪያ በመሆን ያገለግላል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ደጋ የነበሩ ወይና ደጋ፣ ወይና ደጋ የነበሩ ቆላ፣ ቆላ የነበሩ በረሀ፣ በረሃ የነበሩ አካባቢዎች እንደ ሳሃራ እጅግ በረሃማ እየሆኑ ነው። ዓመት እስከ ዓመት ይገማሸሩ የነበሩ ወንዞች፣ በየገመገሙ፣ በየጋራና በየሸንተረሩ ይንፎለፎሉ የነበሩ ምንጮች ደርቀዋል። ወደ 60 በመቶና ከዚያ በላይ የነበረው የደን ሽፋን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከሦስት በመቶ የማይበልጥ ነበር። አሁን በተደረገ ርብርብ የደን ሽፋኑን ወደ 17 በመቶ ከፍ ብሏል።

በአየር ንብረት ለውጡ የተነሳ በየአስር ዓመቱ ይከሰት የነበረው ድርቅ በየዓመቱ ከመመላለሱ ባሻገር በበልግና በመኸርም መከሰት ጀምሯል። ከዓመት ዓመት ይከሰት በነበረ የዝናብ እጥረት የተነሳ የከርሰና የገጸ ምድር ውሃ እጥረት ተከስቷል። እየተቆራረጠና እየተዛባ የሚጥለውን ዝናብ ቢሆንም ደኖች በመራቆታቸው የተነሳ አፈሩ ውሃ መያዝ ባለመቻሉ ጠብ ባለቁጥር ስለሚሸረሸር የአፈር መከላትን እያባባሰ ግብርናውን አደጋ ላይ ጥሎታል።

በዚህ የተነሳ ከሕዝብ ብዛቷ አንጻር ተመጣጣኝ ምርት ማምረት አልቻለችም። የግብርና ቴክኖሎጂ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ፀረ አረምና ተባይ ኬሚካል በመጠቀም ምርትን ለማሳደግ የተደረገው ጥረት አይደለም አግሮ ኢንዱስትሪውን ዜጋውን መመገብ እንደተሳነው ከመንገድ ቀርቷል። በቅርብ የወጡ ጥናቶች 47 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የከፋ የምግብ እጥረት እንዳለባቸው ያትታሉ ።

የዓለም ሙቀት መጨመርን ተከትሎ የመጣው የአየር ንብረት ለውጥ ለሀገራችንም ሆነ ለአፍሪካ ጥሩ ዜና የለውም። እየታረሰ የነበረው መሬት ለምነቱን በማጣቱና በመራቆቱ የተነሳ እየቀነስና እየተራቆተ ይገኛል። የከፋ የምግብ እህል እጥረት፣ ድህነትና የበዛ ሥራ አጥ ባለበት ሀገር መታረስ የሚገባው አብዛኛው መሬት ዛሬም ጦም ያድራል። አበው ‹‹የወለፈንዲ ስልቻ ጤፍ ይቋጥራል፣ ባቄላ ያፈሳል›› እንዲሉ።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሀገራችንን ጨምሮ በዓለማችን እያየናቸው ያሉ የደን ቃጠሎዎች፣ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ውሽንፍር፣ የበረሀ መስፋፋት፣ የወቅቶች መዛነፍ፣ ወዘተረፈ የዓለም ሙቀት መጨመር እነ ትራምፕ እንደሚሉት የደባ ኀልዮት ሳይሆን የእለት ተእለት የሕይወት ገጠመኝ ከሆነ ውሎ አድሯል። ሰሞኑን እንኳ 63 ሚሊዮን አሜሪካውያን ለከፍተኛ ሙቀት አደጋ ተጋልጠዋል።

የበለጸጉ ሀገራት ዛሬ ድሃ ሀገራትን ዋጋ እያስከፈለ ባለው የኢንዱስትሪ አብዮት ባካበቱት ሀብት እየተቋቋሙት ሲሆን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ግን በዓለም ሙቀት መጨመር ያለ እዳቸው ውድ ዋጋ እየከፈሉ ነው። በግብርናችን ያለ መዋቅራዊና ተቋማዊ ችግር የራሱ ድርሻ ቢኖረውም የዓለም ሙቀት መጨመር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ጋሬጣ እየሆነ ይገኛል ።

ዛሬም በቀን ሦስት ጊዜ መመገብ አልቻልንም። ይሁንና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኩታ ገጠም ግብርናን፣ በተወሰነ ደረጃ ሥነ ምህዳርን ታሳቢ ያደረገ የቴክኖሎጂ እገዛ፣ የከርሰና የገጸ ውሃን አሟጦ የመጠቀም፣ ፍራፍሬና አትክልት ላይ ለመሥራት፣ በተለይ የከተማ ግብርና ትኩረት ማግኘቱ፤ በአርብቶ አደሩ የሚገኙ ጦም ያደሩ ሰፋፊ መሬቶችን በመስኖ ለማልማት አበረታች ጥረትና ርብርብ መደረጉ እና ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ማስቀረት መቻሉ የአተያይ ለውጥ በማምጣቱ ተስፋ ያስቆረጠን ግን ደግሞ ብቸኛ ሊባል በሚችለው ግብርና ከምግብ ዋስትና ባሻገር ተስፋችንን እንድናድስ አድርጎናል።

ደጋግሜ እንደምለው ችግሮቻችንን ሁሉ ፈታተን፣ በታትነንና አገላብጠን ብንመረምራቸው አብዛኛዎቹ ከአንድ ቅርጫት የሚገኙ ናቸው። የተፈጥሮ ሀብታችንን በአግባቡ ካለመንከባከብ፣ ካለመጠበቅና ካለማልማት ቅርጫት። የዓለም ሙቀት መጨመርን ተከትሎ በመጣ የአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ የተፈጥሮ ሀብታችን እየተጎሳቆለ በመምጣቱ ማለትም መሬታችን የተራቆተ፣ ዝናባችን የአጠረና የተቆራረጠ በመሆኑ የከርሰና የገጸ ምድር ውሃችን በመመናመኑ ግብርናው ውጤታማ ሊሆን አልቻለም።

በዚህ የተነሳ በግብርና ላይ የተመሠረተው የዜጋው ሕይወት፤ የሀገሪቱ ልማት ችግር ላይ ወድቋል። ይህ የሀብት ውስንነትን ፈጥሯል። በዚህ የተነሳ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ከዓመት ዓመት እየተባባሱ መጡ። እነዚህን ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ደግሞ የተፈጥሮ ሀብታችን እንዲያገግም ሌት ተቀን መሠራት አለበት። መሬት ማገገም፣ ውሃ መያዝ አለበት። ይህ ደግሞ እውን ሊሆን የሚችለው ችግኝ በመትከልና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን በስፋት በማከናወን ነው።

“አረንጓዴ ዐሻራ” የበሽታውን ምልክት ከማከም ይልቅ መነሻውን በማያዳግም ሁኔታ የመፈወስ አቅም እንዳለው በማመን ተግባራዊ የሆነ የሰንደቅ ዓላማ ፕሮጀክት ነው። በዚህ ዓመት ሰባት ቢሊየን ችግኝ ለመትከል የተጣለው ግብ ሲፈጸም ባለፉት ስድስት ዓመታት የተተከሉት ችግኞች ወደ 40 ቢሊዮን ይደርሳሉ። እነዚህ ችግኞች በሚቀጥሉት ዓመታት ለነገዋ ኢትዮጵያና ለመጭው ትውልዶች ይዘውት ከሚመጡ በረከቶች የተወሰኑትን ላነሳሳ።

1ኛ. ካርቦንን ከከባቢ አየር መቀነስ፤ እነዚህ ችግኞች ምግባቸውን በፎቶሴንቴሲስ አማካኝነት ለማዘጋጀት ካርበን ዳይኦክሳይድ ከከባቢ አየር ስለሚጠቀሙ የካርበን መጠንን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል። በዚህም የግሪንሀውስ ጋዝን ወይም ሜቴንና ካርበን በመቀነስ የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል ይቻላል።

2ኛ. ብዝሀ ሕይወትን መጠበቅ፤ እንዲህ በአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን፣ በስድስት ዓመት ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ሲተከል ብዝሀ ሕይወትን ለመጠበቅና እንዲያገግም ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው እሙን ነው። የሀረማያንና የአሰላን ሐይቆች፤ እያገገሙ ያሉ ወንዞችንና ምንጮችን ልብ ይላል። ዛፎች ለዱር እንስሳት መኖሪያና የምግብ ምንጭ ይሆናሉ። በመጥፋት ላይ ያሉ የዛፍም ሆነ የእንስሳት ዝርያዎችን ለመታደግ ያገለግላል።

3ኛ. የአፈር መከላትን ማስቀረት፤ ችግኞችን መትከል በሥራቸው አማካኝነት አፈርን እንዲይዙ በማድረግ የአፈር መሸርሸርን፣ መከላትንና የመሬት መንሸራተትን ከመከላከሉ ባሻገር የአፈርን ለምነት ይጨምራል።

4ኛ. ውሃ ጥበቃ፤ ዛፎችና ሌሎች አትክልቶች የውሃን ዑደት ለመቆጣጠር የማይተካ ሚና አላቸው። ጎርፍን በመቀነስ የከርሰ ምድር ውሃ ክምችትን በመጨምር አቅርቦቱን አስተማማኝ ያደርጋል።

5ኛ. የአየርን ጥራት ያሻሽላል፤ ዛፎች በተፈጥሮ አየርን ከበካይ ነገሮችና ባዕድ ብናኞች ያጣራሉ። በቢሊየኖች የሚቆጠር ችግኝ መትከል የዛኑ ያህል የምንተነፍሰውን አየር ጥራት በእጅጉ ያሻሽለዋል። የመተንፈሻ አካላት ሕመምን ለመቀነስ ያግዛል።

6ኛ. የሥራ ዕድል መፍጠር፤ ከችግኝ ማፍላት እስከ መንከባከብ በመቶ ሺዎች ወይም በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። በዚህ ላይ ወደፊት በግብርናውና በኢንዱስትሪው ዘርፍ ላይ የሚፈጥረው የሥራ ዕድል የትየለሌ ይሆናል።

7ኛ. የአየር ንብረትን ለማመጣጠን፤ እንዲህ እንደ ሀገራችን በቢሊዮን የሚቆጠር ችግኝ ሲተከል የአየር ንብረት ሚዛንን ይጠብቃል። ዛፎች የሚፈጥሩት ጥላ ከተሞችን ሳይቀር ለኑሮ ተስማሚና ነፋሻ ያደርጓቸዋል። ይህ እንዲሆን ግን ችግኞች እንደየሥነ ምሕዳሩ ባሕሪ ተመርጠው መተከል፤ ከተተከሉ በኋላ ደግሞ ተገቢው ጥበቃና ክትትል ሊደረግላቸው ይገባል።

ሻሎም ! አሜን ።

አዲስ ዘመን ዓርብ ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You