ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል እየተነሱ ያሉ የክልል እንሁንም ጥያቄዎች ህገ መንግሥታዊ መሆናቸውንና ነገር ጥያቄውን ከህግ ውጪ ለማስፈጸም የሚደረግ እንቅስቃሴ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉዳዩ ዙርያ የሰጡት ማብራሪያ መንታ ስሜትን ፈጥሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2011 በጀት ዓመት የአፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ከምክርቤቱ አባላት ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል እየተነሱ ያሉ የክልልነት ጥያቄን የሚመለከተው ይገኛል።
ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ በክልል መደራጀት ህገ መንግሥታዊ መብት ነው፤ በመሆኑም በክልሉ ከሚኖሩ ህዝቦች የተነሱትን የክልል እንሁን ጥያቄዎችን መንግሥት በክብር ተቀብሏል።
ክልሉን እያስተዳደረ ያለው ደኢህዴንም ጥያቄውን ተቀብሎ በህግ እየመረመረ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ደኢህዴን የመጨረሻ ውጤቱን እስከሚያሳውቅና ምርጫ ቦርድ ዝግጅቱን እስከሚያጠናቅቅ በደቡብ ክልል ውስጥ ክልል የመሆን ጥያቄ ያቀረቡ ህዝቦች በትዕግስት እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል። በህጋዊ መንገድ የቀረበውን ጥያቄ ከህጋዊ መንገድ ውጪ ለማስፈጸም የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን መንግሥት አይታገሳቸውም ሲሉም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልሉ እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎችን አስመልክተው በሰጡት ምላሽ ዙሪያ ለአዲስ ዘመን አስተያየታቸውን የሰጡት በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አክቲቪስት ሁለት ዓይነት ሃሳብ ያንጸባርቃሉ፤ አንዳንዶቹ ህዝቡ ያነሰው ህገ መንግሥታዊ ጥያቄ ህገ መንግሥታዊ ምላሽ እስኪሰጠው በትዕግስት እንዲጠብቅ ማሳሰባቸውን በበጎ ጎኑ እንደሚመለከቱት አንስተዋል። በሌላ በኩል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀይለ ቃል በተሞላበት ንግግር ደስተኛ እንዳልሆኑ ገልጸዋል።
የወላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ወህዴግ) ሊቀመንበር አቶ ተክሌ ቦረና እንደተናገሩት፤ ህገ መንግሥታዊ መስመርን ተከትሎ መደረግ ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ተከናውነው አግባብ ባለው መልኩ ተፈጻሚ እስኪሆን ድረስ ጠያቂው ወገን በትዕግስት መጠበቅ እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉትን መልዕክት ፓርቲያቸውም ይጋራል። ፓርቲያቸው የወላይታ የክልልነት ጥያቄ ከህግና ስርዓት ውጪ በሆነ መልኩ ምላሽ እንዲያገኝ አይሻም። ምክንያቱም ህግና ስርዓትን ባልተከተለ መንገድ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ለህዝብም ስለማይጠቅም መኖር አለባቸው ብሎ አያምንም።
የወላይታ የክልልነት ጥያቄ በህገ መንግሥቱ መሰረት የክልልነት ጥያቄው በቅድሚያ በዞኑ ምክር ቤት ቀርቦ ጸድቆ ለክልሉ ምክር ቤት መቅረቡን የሚናገሩት አቶ ተክሌ፤ የክልሉ መንግሥት ግን በህገ መንግሥቱ መሰረት የቀረበውን ጥያቄ ወደ ጎን በማድረግ የህግ ምርመራ መጀመሩ ተገቢ አይደለም ብለዋል።
ህገ መንግሥታዊ ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ያለበት በምርመራ ሳይሆን ህገ መንግሥቱ በሚያዘው መሰረት ምላሽ መሰጠት አለበት ብለዋል። በተለይም የክልሉ ምክር ቤት አንዳንድ የክልልነት ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ሲያደርግ አይታይም የሚሉት አቶ ተክሌ፤ የክልሉ መንግሥት ለጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እንቅስቃሴ ሳይጀምር መቆየቱ ተገቢነት የለውም ብለዋል።
እንደ አቶ ተክሌ ማብራሪያ፤ በክልሉ የተነሱ የክልልነት ጥያቄዎችን በአፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት መከናወን ያለባቸው ተግባራት በአፋጣኝ ሊከናወኑ ይገባል። ፓርቲያቸው ወህዴግ የክልሉ መንግሥት ለህዝቡ ጥያቄ ህጋዊ ምላሽ ለመስጠት እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ግፊት እያደረገ ነው።
“በደቡቡ የሀገሪቱ አካባቢዎች ልማትና ዕድገት ወደ ኋላ የቀረው ራሱን በራሱ ማልማትና ማስተዳደር ባለመቻሉ ነው’’ የሚሉት አቶ ተክሌ፤ ህዝቡም የክልልነት ጥያቄዎችን እያነሰ ያለው የመጠየቅ አምሮት ኖሮት ሳይሆን እነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ስለሚፈልግ ነው ብለዋል።
እንደ አቶ ተክሌ ማብራሪያ፤ ወላይታ ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠር እቅድና ስትራቴጂ ነድፎ፤ በጀት በጅቶ ዕድገት ለማፋጠን ስለሚፈልግ ክልል የመሆን ጥያቄ አንስቷል። ህዝቡ ያነሰው ጥያቄ ግን አፋጣኝ መፍትሔ እንዲያገኝ የክልሉ መንግሥትና የምርጫ ቦርድ መከናወን ያለባቸውን ተግባራት በአፋጣኝ ሊያከናውኑ ይገባል።
ሀዲያ ለክልሉ ምክር ቤት ያቀረበው የክልል ልሁን ጥያቄ ምላሽ ሳይሰጠው በመቆየቱ በከቤራ (የሀዲያ ወጣቶች) እና በዞኑ አስተዳደር አስተባባሪነት በሰኔ 21 በሆሳዕና ሊካሄድ የነበረውን ሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ አባልና አክቲቪስት አተረፈ ታምራት፤ በበኩሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት ተቀባይነት ያለው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱትን ሃሳብም እንደሚጋራ አንስቷል።
ክልል ለመሆን ጥያቄ ያቀረቡ ህዝቦች ህግና ስርዓትን በተከተለ መልኩ መብታቸውን ማስፈጸም አለባቸው የሚለው አተረፈ፤ ህግና ስርዓትን ባልተከተለ መልኩ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ለክፍለ ዘመኑም አይመጥኑም፤ ሀገርንና ህዝብንም ዋጋ ያስከፍላል ብሏል።
የሀዲያ ህዝብ ክልል የመሆን ጥያቄ ለክልሉ ምክር ቤት ካቀረበ ዘጠኝ ወራት ቢቆጠሩም፤ጥያቄው ህግን በተከተለ መልኩ ምላሽ እስኪሰጠው በትዕግስት ሲጠባበቅ ቆይቷል፤ የክልሉ ምክር ቤት ግን ተቀምጦ በጉዳዩ ዙሪያ ውሳኔ ሳያስተላልፍ መቆየቱን አንስቷል። ይህም ትክክለኛ አካሄድ አይደለም። የክልሉ ምክር ቤት ተቀምጦ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ጥያቄዎችን አዳፍኖ ማቆየቱ ተገቢ አይደለም። ይሁን እንጂ ሀዲያ የሀገርን ህልውና አደጋ ውስጥ በማይጥል መልኩ ክልል የመሆን ጥያቄውን ይገፋበታል ብሏል።
እንደ አተረፈ ማብራሪያ፤ ህዝቡ እያነሰ ያለው ጥያቄ ህገ መንግሥትን መሰረት ያደረገ ሆነ ሳለ በክልሉ መንግሥት እየተካሄደ ያለው ጥናት ተቀባይነት የለውም። ጥያቄዎች በህገ መንግሥቱ መሰረት ምላሽ ማግኘት አለበት። የጥናት ቡድኑ በክልሉ እየተነሱ ያሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችል አይደለም።
እንደ አቶ አተረፈ ማብራሪያ፤ ህዝቡ የክልልነት ጥያቄ እንዲያነሳ እያደረገ ያለው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበዘዘ የመጠውን የሀዲያን ማንነት ማስመለስ፣ በልማት ወደ ኋላ እንዲቀር የተደረገው አካባቢ የልማቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል፤ የተለያዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ምላሽ እንዲያገኙ ነው።
የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲኣን) ሊቀመንበር አቶ ዱካሌ ላሚሶ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት ሀይለ ቃል የታከለበት ንግግራቸው በፓርቲው አባላትና በሲዳማ ህዝብ ዘንድ ክርክር አስነስቷል፤ ቅሬታም ፈጥሯል።
ከሱማሌ ክልል ጋር አያይዘው ያነሱት ሃሳብ ተገቢ ነው ብለው እንደማያምኑ የተናገሩት አቶ ዱካሌ፤ ሃዋሳ የተለያዩ ሀገራት መሪዎችን ተቀብላ በሰላም ስታስተናግድ ኖራለች። የተደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች ላይም የተፈጠሩ ችግሮች አልነበሩም። ይህ ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አምና ከተከሰተው ችግር ጋር አያይዘው ማንሳታቸው ተገቢ አይደለም ብለዋል።
እንደ አቶ ዱካሌ ማብራሪያ፤ ሲዳማ ጥያቄውን በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 በተቀመጠው መሰረት ህግን ተከትሎ አቅርቧል። በብሄሩ ምክር ቤት አጽድቆ፤ ለክልሉ ምክር ቤት ያቀረበ ሲሆን፤ የክልሉ ምክር ቤትም ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ዙሪያ ህዝበ ውሳኔ እንዲያካሂድ ደብዳቤ ጽፏል።
ህዝበ ውሳኔው በአንድ ዓመት ውስጥ መካሄድ እንዳለበት በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 ላይ የተቀመጠ ቢሆንም ምርጫ ቦርድ የተለያዩ ሰበቦችን በማቅረብ ህዝበ ውሳኔ ሳያካሂድ አንድ ዓመት ሊሞላው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዳዲስ ክልሎች የሚመሰረቱ ከሆነ አንቀጽ 46 መቀየር አለበት የተባለውም ቢሆን ሊሆን የማይችል ነው። ህገ መንግሥቱን ማሻሻል ከሲዳማ ጥያቄ ጋር ሊገናኝ አይችልም ሲሉም ይሞግታሉ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2011
መላኩ ኤሮሴ