በጠረጴዛ ዙሪያ ሰክኖ ለችግሮች ሰላማዊ መፍትሔ ማመንጨት ከዴሞክራሲ ሥርዓት መገለጫዎች ዋናው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ስርዓት የብዙሃንን አስተሳሰብ የሚያራምድ እንደሆነ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ ከዚህ አንጻር በቅርቡ በአገራችን በከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ላይ የተፈጸመው ግድያ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ የጋራ መግባባት እንደሌለ አንዱ ማሳያ እንደሆነ ምሁራኑ ይወቅሳሉ።
አቶ መዓዛ ኃይማኖት በኢፌዴሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ረዳት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ናቸው። እርሳቸው እንደሚገልጹት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በመርህ ደረጃ የብዙሃንን አሠራር መቀበል ማለት ነው፡፡ በብዙሃን ህግ የሚከናወን ማንኛውም አሠራርን ደግሞ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊም፤ ግድም ነው ሲሉ አፅንኦት ይሰጣሉ።
ከዚህ ውጪ ከሆነ ግን ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጠላት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የግለሰብ ፍላጎትና አስተሳሰብን መሰረት ያደረገ አካሄድም ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንቅፋት ነው፡፡ በመሆኑም በአመራሮች ላይ የተፈጸመው የግድያ ወንጀል ከብዙሃን ፍላጎት ይልቅ የግለሰብ ፍላጎት ጎልቶ የታየበት ክስተት ሆኖ ይገለጻል፡፡
በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ሃሳቡ ተሳፋም ሃሳባቸውን በመጋራት ከዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሰረታዊ እሴቶች አንዱ የሃሳብ ልዩነቶችን በመቻቻል ማስተናገድ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የሦስት ሺ የመንግሥት ታሪክ ባላት ኢትዮጵያ እና በ21ኛው ክፍለ ዘመን ለመንግሥት ቁመና የሚመጥን አስተሳሰብ ማዳበር ላይ ክፍተት መኖሩን የግድያ ወንጀሉ ማሳያ እንደሆነ ይገልጻሉ።
‹በዴሞክራሲ የሃሳብ ልዩነት ፀጋ እንጂ መገዳደል አይደለም፤ ሰውን በሃሳብ ልዩነቱ መግደል ሃሳብን መግደል ነው›› በማለት የሃሳብ ልዩነት በዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ላይ መግባባት አለመፈጠሩን ይገልጻሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት የሃሳብ ብዝሃነት አልተራመደም፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተጨባጭ የሚታየው ሀቅ ሃሳብን በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታትና ወደ ከፍታ ማሸጋገር እንዳልተቻለና ፈተናውም በግልጽ እየታየ መሆኑን ግድያው አሳይቷል ሲሉ አቶ ሃሳቡ ይከራከራሉ፡፡
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር መኮንን ፍሰሐ በበኩላቸው የግድያ ወንጀሉን ቀጥታ ከዴሞክራሲ ሥርዓት ጋር ብቻ ማገናኘት ከባድ ነው፡፡ በሀገሪቷ ፀጥታና ሰላምን የማስከበር እንቅስቃሴ እንዲሁም ችግሮችን አስቀድሞ በመተንበይ አስቸኳይ መፍትሔ ለማምጣት ያለው ዝግጁነትና ጥንካሬው መፈተሽ ይኖርበታል ሲሉ ሌላ አመክንዮ አቅርበዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን ድርጊቱ ከዴሞክራሲ መርህ ውጪ ነው፤ በሃሳብ ማሸነፍ እንጂ በኃይል ማሸነፍ የዴሞክራሲ ሥርዓት መገለጫ አይደለም ሲሉም አቶ መኮንን ያስገነዝባሉ፡፡
አቶ መዓዛ ኃይማኖት በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቷ በዴምክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ የጋራ መግባባት አለ ብለው አያምኑም፡፡ እርሳቸው እንዳሉት ሁሉም ሰው የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት እንዲሁም ልማትና ዕድገት ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን አብዛኛው ሰው ሁኔታውን በተለያየ መልኩ እንደተረዳው ይገል ጻሉ፡፡ የጋራ ሃሳብ ከሌለና ሁሉም በየግሉ የሚሮጥ ከሆነ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባት የሚኖረው አበርክቶ ቅንጣት ይሆናል፡፡ የጋራ መግባባት የሌለበት ማንኛውም እንቅስቃሴና ዕርምጃ ደግሞ ውጤቱ የከፋ ነው፤ አሉታዊ ጎኑ ያመዝንና አገሪቱን ሌላ ችግር ውስጥ ይከታታል፡፡
‹ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በኢትዮጵያ በጅምር ደረጃ ነው፤ በአንድ ጀንበር የሚያድግ አይደለም› ተብሎ በተደጋጋሚ የሚገለጽ ሃሳብ ነው፤ ይሄ ሁልጊዜ በምክንያትነት መቅረብ እንደሌለበትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ የጋራ መግባባት እንዳይኖር እንቅፋት እየፈጠረ እንደሆነ አቶ መዓዛ ኃይማኖት ወቀሳ አዘል አስተያየታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
ባለፈው አንድ ዓመት በመንግሥት በኩል የተወሰዱ ዕርምጃዎችን የሚያስታውሱት አቶ መዓዛ የፖለቲካ እስረኞችን ከእስር በመፍታት፣በውጭ ይኖሩ የነበሩትንም ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግና ሌሎች የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ለማጠናከር የተወሰዱ ዕርምጃዎችን በፀጋ ተቀብሎ በጋራ ማስቀጠል እና መንግሥት የሚያመጣቸውን አቅጣጫዎች መከተልና ህግ የማስከበር ጉዳይ ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡
በአገሪቱ ህግና ሥርዓት መመራትና የጋራ መግባባት ይዞ መጓዝ ከተቻለ ተተኪው ትውልድም ሀገርን የማስቀጠል ኃላፊነቱን እንዲወጣ ማድረግ እንደሚቻል የገለጹት አቶ መዓዛ አሁን ስለሚስተዋለው የሀገሪቷ ነባራዊ ሁኔታም በፍርሐት ደረጃ የሚገለጽ እንጂ የፌዴራል መንግሥቱ ሙሉ ለሙሉ ስልጣኑን አጥቷል ለማለት የሚያስችል እንዳልሆነና በሀገሪቷ ቀጣይ ጉዞ ላይ የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ አስገንዝበዋል፡፡
መምህር ሃሳቡ ለዴሚክራሲያዊ ሥርአት ግንባታ የሚተጋና በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመቅረጽ የሥነዜጋና ሥነምግባር ትምህርት በሀገሪቷ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ተቀርጾ ትምህርቱ ቢሰጥም የሚፈለገውን ውጤት አምጥቷል ብለው አያምኑም፡፡ መምህራን በችሎታቸው ሳይሆን በፖለቲካ ታማኝነታቸው እንዲያስተምሩ መደረጋቸው በትምህርት አቀባበሉ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን እንደ አንድ ምክንያት ያነሳሉ፡፡
በዘርፉ ላይ ያለው ሙያተኛም ያሉትን ክፍተቶች በጥናት ለይቶ ተደራሽ በማድረግ ላይ ሚናውን በመወጣት ላይ የቁርጠኝነትና የድፍረት ክፍተት መኖሩ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን እንደጎዳው አመልክተዋል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር መኮንን እንዳመለከቱት በ1987 ዓ.ም የጸደቀውን ህገመንግሥት መሰረት አድርገው በወጡት ህጎች ባለፉት 27 ዓመታት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በጎ ጅምሮች ነበሩ። በብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብት ላይ ያተኮረ ብዝሃነት የሚያስተናግድ፣ ህብረ-ብሄራዊ ፌዴራሊዝምና ፓርላሜንታዊና ለዚህም ውክልና ያለው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
ከለውጡ በኋላም ባለፈው አንድ ዓመት የፖለቲካውን ምህዳር ለማስፋት የሚያስችሉ እርምጃዎች ተወስደዋል። ይሁን እንጂ ያለፉት 27 ዓመታት በጎ ጅምርም ሆነ አሁን ያለው እንቅስቃሴ በተጠናከረ መልኩ እየሄደ ሳይሆን አንዱ የገነባውን ሌላው የሚያፈርሰው፣ የጎበዝ አለቃ እንደፈለገው ዕርምጃ የሚወስድበት ሁኔታ መፈጠሩን መታዘባ ቸውን ተናግረዋል፡፡
አሁን የሚታዩት ክስተቶች በመንግሥትና በህዝብ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አለማደጉን፣ መቻቻል ፣በሃሳብ የበላይነት መስማማት ላይ ያልተደረሰበት ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት ጫፍ የደረሰ ሥርዓት የሚስተዋልበት እንደሆነ ረዳት ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ፡፡
‹‹ሀገሪቷ በዴሞክራሲ ሥርዓት ወዴት እየሄደች ነው? ብለን ስንጠይቅ ግልጽ የሆነ መልስ የለም። ሊብራል ዴሞክራሲ ወይንስ ሶሻል ዴሞክራሲ ነው የምንከተለው? አብዮታዊ ዴሞክራሲስ ከሽፏል ወይንስ ምንድ ነው ያለው? ብዥታ ተፈጥሯል›› በማለት በሀገሪቷ የዴሞክራሲ ሥርዓት ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ምላሽ የሚሹ ጉዳዮች መኖራቸውን አስቀምጠዋል።
አስተያየት ሰጭዎቹ አሁንም ሆነ በቀጣይ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች እና ህዝቡ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ የጋራ መግባባት ላይ ካልተደረሰ ኢትዮጵያን በአንድነት እመራታለሁ ለሚል መንግሥትም ሆነ ለሁሉም እጅግ ፈተና ይሆናል። ከዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውጪ ሌላ ምርጫ ሊኖር እንደማይገባ ሁሉም ወገን ተገንዝቦ ስርዓቱን ወደሚፈለገው ደረጃ ማሻገር ለነገ የሚተው ሥራ አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2011
ለምለም መንግሥቱ