
ዜና ሀተታ
አሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል ሃይማኖታዊ ተምሳሌት ያላቸው ትልልቅ የአደባባይ በዓላት ናቸው። አሸንዳ በትግራይ፣ ሻደይ በዋግኽምራ፣ ሶለል በራያ ቆቦና አሸንድዬ በላሊበላ በልዩ ልዩ ባህላዊ ክዋኔዎች ይከበራሉ። በዓላቱን ወጣቶችና ልጃገረዶች አደባባይ በመውጣት በአንድነት ተሰብስበው ያከብሩታል። በዓላቱ የሴቶች ቢመስሉም ወንዶችም ከፍተኛ ተሳትፎ አላቸው።
በዓላቱ የወርሃ ነሀሴ ድምቀት የአዲስ ዓመት ብስራት ናቸው። ለልጃገረዶች ሁሉ የነጻነት መድረካቸው ነው። ህጻናትና ልጃገረዶች በልዩ አለባበስና አጋጊያጥ ይደምቃሉ። መልካም ምኞታቸውን ይገልጻሉ። የክረምቱ ዝናብ ሲቀንስ፣ ወንዞች ሲጎድሉ፣ ሜዳና ጋራው በአበቦች ሲያሸበርቅ ከቤት ወደ መስክ በመውጣት “አሸንድዬ አሸንዳ ሙሴ ፈሰስ በይ በቀሚሴ” በማለት ያከብራሉ።
የበዓሉ ተሳታፊዎች ለአለባበስ፣ ለጸጉር አሠራርና ለጌጣጌጥ ልዩ ትኩረት ይሰጣሉ። የአካባቢያቸውን ባህል ሊገልጽ በሚችል መልኩ ተውበው በመውጣት በዓሉን ያከብራሉ። በበዓሉ የሚከወኑት ጭፈራዎችም እንደየአካባቢው የተለያዩ ናቸው። በዓላቱ ከነሀሴ 16 ጀምሮ እስከ አዲስ ዓመት መቃረቢያ ድረስ ይከበራሉ።
ኢትዮጵያ የበርካታ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ባለቤት ናት። እነዚህ በዓላት በሕዝቦች መካከል ማህበራዊ ትስስርን ለመፍጠር፣ አንድነትን ለማጠናከር፣ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ያላቸው ፋይዳ ምንድን ነው? የዝግጅት ክፍላችን ላናሳቸው ጥያቄዎች የዘርፉ ምሁራን ምላሽ ሰጥተዋል።
መስፍን ፈቃዴ (ዶ/ር) ይባላሉ። በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የባህል ጥናት መምህርና የአዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ናቸው። ከነሀሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ይከበራሉ። ከእነዚህም በዓላት መካከል አሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ ከሴ አጨዳና እንግጫ ነቀላ ጥቂቶቹ ናቸው ይላሉ።
በዓላቱ ሃይማኖታዊ መነሻ ያላቸው ቢሆኑም ልጃገረዶች ባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጥ በመልበስ እንዲሁም አሸንዳ በወገባቸው በማሰር ያከብሩታል። በዚህም የአካባቢውን ማህበረሰብ ወግ፣ ባህልና እሴት ለሌሎች ሰዎች ያስተዋውቃሉ። የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን እና ማህበራዊ መስተጋብርን ያጠናክራሉ ይላሉ።
የአደባባይ በዓላት የአንድን ማህበረሰብ ምንነት፣ ባህል፣ ታሪክና አመጋገብ ለሌላው አጉልተው ያሳያሉ። እርስ በእርስ ተከባብረውና ተዋደው እንዲኖሩም ያስችላል ሲሉ ይናገራሉ።
የአደባባይ በዓላት ሲከበሩ የሀገር በቀል አልባሳትንና ጌጣጌጦችን ማድረግ ይገባል የሚሉት መስፍን (ዶ/ር)፤ ከሀገሪቱ ባህል ውጪ ያሉ አልባሳትና ጌጣጌጦች ኢትዮጵያን ሊገልጹና ሊያስተዋውቁ ስለማይችሉ ሁሉም እንደ እድሜ ደረጃቸው የአካባቢያቸውን የባህል አልባሳት በመልበስ ማክበር ይገባል ይላሉ።
የአሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓላት ባለቤቶች በበዓሉ የሚከወኑ ጉዳዮችን ጠንቅቀው ማወቅ፣ የባህልና ቱሪዝም ባለሙያዎች በዓላቱ ለምን ይከበራል፣ ማን ያከብረዋል፣ እንዴት ይከበራልና በዓሉ መከበሩ ምን ፋይዳ አለው የሚሉትን ጉዳዮች በመመዝገብና በመተንተን ማሳወቅ እንደሚጠበቅባቸው ያስረዳሉ።
መስፍን (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ በዓላትን እሴታቸውን በማስጠበቅ በትውልድ ቅብብሎሽ ማስቀጠል ይገባል። ወላጆች ልጆቻቸውን በሥነምግባር ኮትኩተው በማሳደግ የራሳቸውን ባህል እንዲያውቁ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
ትምህርት ቤቶች፣ የባህል ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የበዓላትን እሴትና አንድምታ ለትውልዱ ማስተማር ከቻሉ የባህል ሽግግር ድልድዩ ሳይሰበር ማስቀጠል ይቻላል። በዚህም የሀገርን ገጽታ መገንባት፣ የቱሪዝም ሀብቱን ማሳደግ እና ባህልን ማስተዋወቅ ይቻላል ሲሉ ያስረዳሉ።
በራሱ ባህል የሚኮራ ትውልድን ለማፍራት መንግሥት፣ ወላጆችና መምህራን ድርሻቸው ከፍተኛ ነው የሚሉት መስፍን (ዶ/ር)፤ ወላጆች ለልጆቻቸው በሀገሪቱ የሚከበሩ የሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትን አንድምታ በቤታቸው ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል።
መንግሥትም የበዓላቱን ትርጉም በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ በማካተት ልጆች በትምህርት ቤት እንድማሩት በማድረግ ከሀገሪቱ ባህል፣ እምነት፣ ወግና ሥርዓት ጋር የሚጻረሩ መጤ ባህልን መመከት ይቻላል ይላሉ። አንድምታቸው በቃል ብቻ እየተነገረ ያለ ባህልና ታሪኮችን በጹሁፍና በምስል በማደረጀት የውጭው ማህበረሰብ በሚያውቁት ቋንቋ ተርጉሞ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን በማቅረብ ቱሪስቶችን መሳብ ይቻላል ሲሉ ያስረዳሉ።
የቱሪዝም ጋዜጠኛው ሄኖክ ስዩም በበኩሉ፤ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከበሩት አሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለልና ሌሎች የአደባባይ በዓላት የኢትዮጵያውያን ሃይማኖት፣ ባህል እና ትውፊት በስፋት የሚንጸባረቁበት በመሆኑ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች መሳብና ማቆየት የሚችሉ ናቸው ይላል።
ይህም ለቱሪዝም እድገትና ለአካባቢው ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ ሁሉም በዓላቶች በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡና እንዲታወቁ ማድረግ ይገባል ሲል ያስረዳል። እንደ ሄኖክ ገለጻ፣ በኢትዮጵያ የቱሪስት መቀበያ ጊዜ ተደረጎ የሚወሰደው ከመስቀል በኋላ ያለው ጊዜ ነው። በነሀሴ የሚከበሩ በዓላት ቱሪስትን ማቆየትና የባህል ኢንዱስትሪ ምርትን ለማንቀሳቀስ ከፍተኛ ሚና ያላቸው በመሆኑ በሚገባ ማስተዋወቅ ይገባል ይላሉ።
የአደባባይ በዓላቱ በሚከበሩበት አካባቢዎች የበዓሉ ተሳታፊዎች የሚደምቁባቸውን አልባሳት፣ ጌጣጌጥ እና የአካባቢውን ባህላዊ ምግቦች አዘጋጅቶ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆንና ማስተዋወቅ እንደሚገባም ያስረዳል። በኢትዮጵያ የአደባባይ በዓላትን ወቅቱን ጠብቆ ከማክበር ያለፈ፣ ለማጎልበት፣ በቅርስነት ለመጠበቅ፣ ለሌሎች ሀገራት ለማስተዋወቅና ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሠሩ ገባል ይላል።
የአደባባይ በዓላት ከቱሪዝም ዕድገት በተጨማሪም በሕዝብ ውስጥ ማህበራዊ ትስስር በመፍጠር የማህበረሰብን አንድነት ለማጠናከር፣ ኢትዮጵያን ለሌሎች ሀገራት ለማስተዋወቅ፣ ለኪነጥበብ እድገትና ለከያኒዎች መፈጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ሲል ይናገራል።
የኢትዮጵያን በዓላት አከባበር ለመጎብኘት ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ቱሪስቶችን በአግባቡ በመቀበልና በማስተዋወቅ ለሀገሪቱ ትልቅ የገቢ ምንጭ በመፍጠር በቱሪዝም እንቅስቃሴው የተሻለ ሥራ ማከናወን ይገባል ሲል አብራርቷል።
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 16 /2016 ዓ.ም