በሀገራችን አንገት ላይ ጣል የምናደርገው ስካርፍ አልያም ሻርፕ በተለይ በቅዝቃዜ ወቅት በስፋት ጥቅም ሲውል ይስተዋላል። በሌሎች ሀገራት ደግሞ ከዚህም ባለፈ ለማጌጫነት የሚውልበት ሁኔታም አለ። ይህ ልብስ በተለያየ ብራንድ ለገበያ ይቀርባል ።
በዛሬው የፋሽን ገጻችንም ይህን ስካርፍ በተለያዩ ዲዛይኖች በማምረት ለገበያ ከምታቀርበው ዲዛይነር ቤዛዊት ዳንኤል ጋር ቆይታ አርገናል። ዲዛይነሯ የሀገራችንን ባሕል ሊያንጸባርቁ የሚችሉ ዲዛይኖች ያሏቸው ስካርፎችን ለገበያ በማቅረብ ትታወቃለች። ካሎን ዲዛይን የሚባል ድርጅት አላት፤ የድርጅቱም መሥራች እሷው ናት። በዚህ ድርጅቷ በተለያዩ ጨርቆች ላይ ዲዛይኖችን በማድረግ የምታመርታቸው ስካርፎች ተፈላጊት እንዳላቸውም ትናገራለች።
ቤዛዊት ስለድርጅቱ ስያሜ ስታብራራ ‹‹ካሎን›› የሚለው ቃል የግሪክ ቃል መሆኑን ጠቅሳ፣ ትርጓሜውም ውበት የሚል ነው ትላለች። ‹‹መጽሐፍት በማነብበት ወቅት ያገኘሁት ቃል ነው፤ ወደእዚህ ሥራ ስገባ ይህንን ቃል ለመምረጥ የቻልኩትም ለእዚህ ነው›› ትላለ ች ።
‹‹ካሎን ዲዛይን ከስካርፎች ባለፈ የተለያዩ ጌጣጌጦችን በተለያዩ ዲዛይኖች ይዞ ይወጣል። ለእሷ ፋሽን ማለት አለባበስ አልያም መዘነጥ ብቻ አይደለም። ‹‹የአኗኗር ዘዴያችንን ጭምር የምናንፀባርቅበት ነው›› ትላለች።
ቤዛዊት ከልጅነቷ አንስቶ ፍላጎቷ አርክቴክት መሆን ነበር። በዚሁ መሠረትም ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ስትገባ የአርክቴክት ሙያ መማርን ምርጫዋ አድርጋለች። በዚህም ትምህርቷን አጠናቃለች። የምትሠራው ፋሽን ኢንዱስትሪው ላይ ይሁን እንጂ የአርክቴክት ሙያዋን የምታንፀባርቅበት አርጋዋለች።
ቤዛዊት ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ በተማረችበት ሙያ ለመሥራት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን አድርጋለች። ከዚያም የቤተሰቦቿ ቢዝነስ ወደሆነው የጨርቃጨርቅ ሥራ ውስጥ በመግባት የመሥራት ዕድሉም አግኝታለች። በእነዚህ ጊዜያት ግን በአካባቢዋ የምትመለከተውን እንቅስቃሴ በውስጧ የሚሰማትን ሁሉ በስዕል መልክ ታሰፍርም ነበር ።
እነዚህን ስዕሎች በጨርቆች ላይ ማስፈር እና ወደ ስካርፍ መቀየር የሚለው ሀሳብ እንዴት እንደመጣላት ስትገልጽም፤ በአንድ ወቅት አንድ ኤግዚቢሽን ላይ የክቡር ዶክተር ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ስዕሎች በስካርፎች ላይ ተሠርተው መመልከቷን አስታወሰች። ከዚህም እንደዚህም መሠራት ይችላል የሚለውን ሀሳብ ማግኘቷን ቻለች። ቤዛዊት የክቡር ዶክተር ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የስዕል ሥራዎች አድናቂ ናት።
የስዕል ሥራዎቿን ‹‹ሲልክ›› የሚባለውን የጨርቅ አይነት በመጠቀም በኅትመት መልክ እንዲሠሩ አደረገች። ለመጀመሪያ ጊዜ የተሠራው ስካርፍም በሰዎች ዘንድ ጥሩ ተቀባይነት አገኘላት።
ቤዛዊቲ አሁን ላይ ከ25 በላይ የሚሆኑ በስካርፍ ላይ የሠራቻቸው የራሷ ዲዛይኖች እንዳሏት ጠቅሳ፣ ስካርፉን ለመሥራት የምትጠቀመው የጨርቅ ግብዓት ከውጭ እንደሚመጣ ተናግራለች። ይህ ከባድ አይሆንም ወይ የሚል ጥያቄ አቅርበንላት ነበር። ‹‹ይከብዳል፤ ነገር ግን ሁሉም ሥራ የራሱ ፈተና አለው፤ ከችግሩ ይልቅ መፍትሔው ላይ ማተኮር የተሻለ ነው›› በማለት መልሳልናለች።
በሀገር ውስጥ ከሚገኙ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ከሚወጡ ጨርቆች ይልቅ እነዚህን ጨርቆች ለመቀበል የተገደደችው ምርቶቹን በምትፈልገው መጠን እና ቀጣይነት ባለው መልኩ ማግኘት ባለመቻሏ መሆኑን አስታውቃለች። አሁን ካሎን ዲዛይን ከሚሠራቸው ሥራዎች እነዚህን በሀገር ውስጥ የሚሠሩ ስካርፎች ወደ መሥራት ሙሉ ለሙሉ ተሸጋግሯል ስትል ጠቅሳ፣ ዲዛይኖቹም ሙሉ ለሙሉ የዲዛይነር ቤዛዊት መሆናቸውን ተናግራለች።
እነዚህን ዲዛይኖች ከማቅረብ ውጪ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመሆን እንደምትሠራ ተናግራ፣ ከሌሎች ተቋማት ጋር ስትሠራ የተቋማቱን ሎጎ እና ዓላማ በሚገልጽ መልኩ ዲዛይኖች እንደሚሠሩ ቤዛዊት ትገልጻለች ።
እሷ እንዳለችው፤ በካሎን ዲዛይን የሚሠሩ የስካርፍ ዲዛይኖች በኢትዮጵያ ያልተለመዱ ሲሆኑ፣ ምኑ ኢትዮጵያዊ ያስብላቸዋል? ምን መልዕክትስ ያስተላልፋሉ? ብለን ላቀረብንላት ጥያቄ ቤዛዊት ስትመልስ ‹‹በአካባቢዬ የማየውን ነገር ማስተዋል ላይ ጥሩ ነኝ ብዬ አስባለሁ፤ ዲዛይኖቼም የማየውንና የውስጤን ሀሳብ የሚያንጸባርቁ ናቸው ብዬ አምናለሁ። ሀገራችንን የሚገልጹ ለምሳሌ የራሳችንን ፊደላት የግዕዝ ቁጥሮች፣ ቆየት ያሉ የኢትዮጵያውያን የሆኑ ዲዛይኖችን እጠቀማለሁ ›› በማለት ትገልጸለች።
የካሎን ዲዛይን ሥራዎች በሌሎች ሀገር ዜጎች ጭምር ተወዳጅ ናቸው የምትለው ቤዛዊት፣ ከምትሠራቸው ሀገራዊ ገጽታ ካላቸው ዲዛይኖች ባሻገር አብስትራክት የሆኑ እና ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ የሚሆኑ ዲዛይኖችንም ትሠራለች ።
የካሎን ዲዛይን ስካርፎች ባላቸው ቀለም፣ መጠን እና ዲዛይን በይበልጥ ሰዎች አለባበሳቸውን በተለየ መልኩ ለማስዋብ ስታይል ለማድረግ ከአለባበሳቸው በተጨማሪ ውበትን ለማከል ሊጠቀሙባቸው እንደሚችሉም ተናግራ፣ ለየትኛውም ወቅትና ቦታ የሚለበሱ መሆናቸውንም አመልክታለች።
ቤዛዊት እነዚህን ሥራዎቿን በተለያዩ የማኅበራዊ ገጾች ላይ ታስተዋውቃለች። ይህም ሥራዋን ለማስተዋወቅ እንዲሁም ብዙዎች ዘንድ ለመድረስ ጠቅሟታል። የምትሠራቸው ሥራዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ለኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ክብርት ሣሕለወርቅ ዘውዴ እንዲሁም ለኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ባለቤት ቀዳማዊት እመቤት ራቼል ሩቶ ዘንድ መድረሳቸውንም አስታውቃለች።
‹‹የክብርት ፕሬዚዳንቷ የቅርብ ወዳጅ ከእኛ ወስደው በስጦታ መልክ ካበረከቱላቸው በኋላ ወደውት በተለያዩ ጊዜያት የስካርፋችን ተጠቃሚ ሆነዋል›› የምትለው ቤዛዊት፣ ይህ አጋጣሚ ለእሷ ትልቅ ዕድል እንደሆነ ጠቅሳለች ።
የካሎን ዲዛይን የስካርፍ ሥራዎች በሚቀጥሉት ዓመታት ኢትዮጵያ በዓለምአቀፍ ደረጃ ከምትታ ወቅባቸው ምርቶች ውስጥ አንዱ እንዲሆን ቤዛዊት አቅዳ እየሠራች መሆኗንም አስታወቃለች።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም