ነቢይ በሀገሩ

ያውና እዚያ ማዶ

ብርሃን ያድላሉ፤

አሁን እኔ ብሄድ

አለቀ ይላሉ::

  • • • አለ ባለቅኔው ነቢይ:: በቃላት መንገድን መሥራትና ማበጀትም ያውቃልና ደግሞ “ነገም ሌላ ቀን ነው” ሲል ከሠራት መንገድ ፊት ቆሞ ሩቅ እያየ እሩቅ ተመኘ:: በዳግም ተስፋ ልቡ ላይ የተንጠለጠለችው ይህቺ ሌላ ቀንም ሌላ ነገር ነበራት:: ምን ይዛ እንደምትመጣ ግን ነቢይም ሆነ ሌላ ማንም ሊያውቀው የሚችል አልነበረም:: ታዲያ ነቢይ ግን ማነው? … ነቢይ ሲሉ እሱ እንደ ኤሊያስ፤ አሊያም እንደ ኢሳያስ ያለ አልነበረም:: ምናልባት “ነቢይ በሀገሩ አይከበርም” የሚለውን አብረው ይጋሩ ይሆናል እንጂ:: ምናልባትም ይህ ነቢይ በጥበብ ለምድር ከተጠሩ ነቢያት መካከል አንደኛውና ፊተኛው … ልንልም እንችል ይሆናል:: በእርግጥም ደግሞ ነው:: ይኼ ነቢይም ታላቁና ሁለገቡ የጥበብ ሰው ነቢይ መኮንን ነው:: ሀገሩን ወዳድ የጥበብ ሰው ካሉ እርሱ ነው:: የጥበብ ሰው ሀገሩን ሲወድስ እንዴት ነው? ቢሉ ልክ እንደርሱ ነው:: እርሱስ? ካሉ ደግሞ … እርሱ ሁሉም ነገሩ ከሀገሩ ወደ ሀገሩ … ስለሀገሩ ነው:: ኢትዮጵያዊነት መልክ አለው:: የኢትዮጵያን መልክ ይዞ፣ መልኳንም ለብሷል::

ነቢይ መኮንን ሃሳብና የቃላት ውጥር ውጥን የማያልቅበት ገጣሚ ነበር:: ከብዕር ጋር የቆመ ጋዜጠኛም ጭምር ነበር:: በትያትር ዓለም ውስጥ የተንፏለለ ጸሀፊም ነው:: የሙዚቃ ግጥም ደራሲነትም ይነካካዋል:: ሰዓሊ፣ ያውም የረቂቅ ሰዓሊነትም አለበት:: ሳይበቃውም ተርጓሚና አርታኢም ነው:: በርከት ያሉ መጻሕፍትን ጽፎ ለንባብ ወግ ማዕረግ አብቅቷል:: ብቻ ምን አለፋችሁ፣ ነቢይ “አይደለም” የሚባለው ነገር የለውም:: በዚህም ሆነ በዚያ ሲያልፍ፣ ስለዚህም ሆነ ስለዚያ ሲጨነቅ፤ ከእርሱ ጭንቀትና ውጥረት ፊት ሁሌም ስለ አንዲት ሀገሩ ነበር:: በብሶትም ሆነ በደስታ፣ በትዝታም ሆነ በመከፋት፣ በወኔም ቢሉ በቁጭት ውስጥ ሆኖ ለሀገሩ ስንኝ ያልቋጠረላት ገጣሚ ባይኖርም፤ ነቢይ መኮንን ግን የእነዚህ ሁሉ አውራ አድርጎታል:: በዚህ ነገሩም ከብዙ ገጣሚያን ለየት የሚያደርገው አንድ ነገር አለው:: ይኸውም ስለሀገሩ የገጠማቸው ግጥሞች በቁጥር ከ20 ያለፉ መሆናቸው ነው:: ነቢይ በሀገሩ ገጣሚ ነው:: ልቡን አሸፍቶ፣ ቀልቡን ሰውሮ የሚገጥመውም ስለሀገሩ ነው:: ገጣሚነቱ እንኳንስ የግጥም አንባቢያኑን ቀርቶ ለገጣሚያኑም የሚያስቀና ነው:: ብዕራቸውን እያነሱም ሆነ አንደበታቸውን እየከፈቱ ስለ እርሱና ስለ እርሱ ግጥሞች ማውራት ለብዙ ገጣሚያን አስደሳቹ ነገር ይመስለኛል:: በተለየ መንገድ ደግሞ ስለ ሀገራዊ ግጥሞቹ ብዙ ብዙ ይሉለታል::

ነቢይን ቀርቦ ለሚመለከተው ስለ እርሱ ባህሪ በመጀመሪያ የሚያጤነው ነገር፤ ነቢይ ያለ ብዕርና ወረቀት መታየት የማይችል መሆኑን ነው:: አፍታ ብዕሩ ቢለየው ያቁነጠንጠዋል:: ጭንቅ ጭንቅ ይለዋል:: ይኼ ሰው ታዲያ በአንድ ወቅት ብዕርና ወረቀትም ሆነ መጻሕፍት ከሌሉበት ዘብጥያ ወረደ:: ጊዜው በደርግ ዘመነ መንግሥት ሲሆን የታሠረውም የዚያ መከረኛ “የኢህአፓ አባል ነህ” በሚል ጦስ ነበር:: እናም ጸረ አብዮተኛ ነህ ተብሎ ከአንደኛው የእስር ቤቱ ክፍል ተወረወረ:: በዚያም ሆኖ ወዲህ ወዲያ ይንጎራደዳል:: በሃሳቡ ነገር እያወጣ ያወርዳል:: ከሃሳቡ ውስጥ ቱር! ቱር! የሚልበት ነገርም “ለምንስ ታሰርኩ … እንዴትስ ነው ከእስር የምፈታው?” እያለ ሳይሆን፤ “እንዴት አድርጌ፣ በምን መላ መጻፊያ ወረቀት ላግኝ?” እያለ ነበር:: ልማዱን ያጦዘበት ደግሞ ከኪሱ ውስጥ ብዕር መኖሩ ነበር:: ቀንበር ያለ ማረሻ ዋጋ አልነበረውምና የወረቀቱ መገኘት የግድ ነበር:: ግራ ቀኙንም ተመለከተ:: እስር ቤቷም በተአምራዊ ችሮታዋ ወረቀት እንድትሰጠው በዓይኖቹ ተማጸናት::

ድንገት አንድ የሲጋራ ፓኮ ከዓይኑ ሲገባ አንድ ሃሳብ ብልጭ አለለትና ከመሬቱ ላይ አንስቶ ላጠው:: ከብዕሩም ጋር አገናኘው:: ቀና ብሎም በሌላኛው እጁ ላይ የያዘውን መጽሐፍ ተመለከተ:: ርዕሱ “Gone with Wind” ይላል:: መጽሐፉም የእውቋ አሜሪካዊት ደራሲና ጋዜጠኛ፣ የማርጋሬት ሚሼል መጽሐፍ ነበር:: ሃሀሳቡን ከብዕርና ቁርጥራጭ ወረቀት ጋር አድርጎ ይተረጉመው ጀመረ:: በዚሁ የሲጋራ ወረቀት ሲሞነጫጭር ላየ ሥራ የፈታ ቄስ ነበር የሚመስለው:: ነቢይ ግን እንዲችው እንደተፏከተ ተርጎሞ ጨረሰው:: ሰው ከአካላዊ እስር ውስጥ ሲገባ ከመንፈሳዊው አዕምሮው ጋር ይጣበቃልና ነቢይ ከእስር ቤቱ ውስጥ ሆኖ የምናብ ቡረቃ ውስጥ ገብቶ ነበር:: የትርጉም ሥራውንም “ነገም ሌላ ቀን ነው” በሚል ስያሜ ተረጎመው:: የውጭውን ነገረ ዓለም ሁሉ እረስቶ እስር ቤቱን እንደ ግል ቢሮው ተጠቀመበት:: በሥራ ተጠምዶ በምናብ እንደተዘፈቀ ብዙ ማዕልትና ሌቶች አልፈው አሥር ዓመታት ተቆጠሩ:: ከአሥርት ዓመታት በኋላ ሲወጣም ከእስር ተፈቶ ሳይሆን ከአንድ ሌላ የተመስጦ ዓለም ውስጥ ከርሞ የመጣ ነበር የሚመስለው:: ይህን አስገራሚ ታሪኩን የሰማች አንዲት አሜሪካዊት ጋዜጠኛም በ1990ዎቹ መካከል ወደ ኢትዮጵያ መጥታ ቃለመጠይቅ አድርጋው ነበር::

“Gone with Wind” ስለዚህ መጽሐፍ ሳስስ አንድ የገረመኝን ሌላ ነገር አገኘሁ፤ ይኸውም የዚህ መጽሐፍ ደራሲ የሆነችው ማርጋሬት ሚሸል እና ተርጓሚው ነቢይ መኮንን፤ ሁለቱንም የሚያመሳስሉ ብዙ ነገሮች መኖራቸው ነው:: የመጀመሪያው ነገር ማርጋሬት ሚሸልም እንደ ነቢይ ሁሉ ጋዜጠኛ ነበረች:: መጽሐፉን ለመጻፍ ያበቃት አጋጣሚ በአንድ ወቅት እግሯን ታማ ከቤት መዋል በጀመረችበት ሰሞን ላይ ነበር:: ነቢይ ሲተረጉመው ደግሞ ከእስር ቤት በመግባቱ ነበር:: መጽሐፉን ለመጻፍ ስትነሳ መነሻ የሆናት የሀገሯ፤ የአሜሪካ በርስ በርስ ጦርነት ውስጥ መተራመስ ነበር:: በዚያን ሰሞን የነቢይ ሀገርም በአብዮታዊና በሀገራዊ ጦርነቶች የተከበበችበት የነበረ መሆኑ ነው:: ማርጋሬት ሚሸል የፖለቲከኞቹን ሴራ እየነቀሰችና እየነቀፈች በገጸ ባህሪያት አላብሳ ታፍረጠርጠዋለች:: ልክ የኦሮማይን ዓይነት ዳራ የነበረው ነው:: ታዲያ ይህን መጽሐፍ ለመጻፍ የፈጀችው 10 ዓመታትን ነበር:: ነቢይ ደግሞ ከታሰረበት እስር ቤት ለመውጣት አሥር ዓመታትን ጠብቋል:: የተተረጎመው መጽሐፍም በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ ለንባብ ቢበቃም ዳሩ ግን ባጠላበት ግዙፍ የሳንሱር ጥላ ምክንያት ከውስጡ ብዙ ነገሮች እንዲጎማመዱበት ሆነ:: በወቅቱ ለነበረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንደ ዘንዶ አስፈሪ ሆነው የታዩ ነገሮች በሙሉ ከመጽሐፉ ላይ ተነቅለው እንዲወጡ በመደረጉ ሙሉእነት አልነበረውም:: ቢሆንም ግን በጣም ተወዳጅና በብዙ የተዋጣለት የትርጉም ሥራ እንደነበረ አይካድም::

የነቢይ አበርክቶዎች ለመስማት ባይታክቱም ለመቁጠር ግን ሳያዳግቱ አይቀሩም:: የሆነው ሆነና ከ2 ዓመታት በፊት ነቢይ ሦስት መጻሕፍትን በአንድ መድረክ ላይ አስመርቆ ነበር:: እነዚህም “የኛ ሰው በአሜሪካ”፣ “ነገም ሌላ ቀን ነው”፣ እና “የመጨረሻው ንግግር” ናቸው:: “ነገም ሌላ ቀን ነው” ከዚህ ቀደም ታትሞ ለንባብ የበቃ ቢሆንም፤ በሳንሱር የታጨዱትን የመጻሕፍቱን ገሚስ አካላት አክሎ በድጋሚ ለማሳተም ችሏል:: ተርጉሞ ለእይታ ካበቃቸው ተውኔቶች መካከል “ጁሊየስ ቄሳር” አይረሴው ነው:: ደግሞም ነቢይ መኮንን የሙዚቃ ግጥምም ይነካካዋል ብለናል:: ሲነካም ያውም ጫን፣ ጠብሰቅ አድርጎ ነው:: ከሠራቸው የሙዚቃ ግጥሞች መካከል አንዱ የንዋይ ደበበ “እንኖራለን ገና” የተሰኘው ግሩም ሙዚቃ ነው:: አንጋፋው ነቢይ መኮንን እንደ ጋዜጠኝነት በሙያው ካገለገለባቸው ስፍራዎች አንዱ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ነበር:: ከጋዜጣው መሥራቾች መሀከልም አንደኛውና ቁልፉ ሰው እሱ ነበር:: አልፎም የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ በመሆን መርቷል:: መምራት ብቻም አይደለም፤ እጅግ ጠለቅ ያሉ ሃሳቦችን እያነሳ በርካታ ጽሁፎችንም ዘርቶበታል:: በተለይ በልዩ የርእሰ አንቀጽ አጻጻፉ ሁሉም ያነሳዋል። የግጥም ሥራዎቹ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነታቸው ላቅ ያለ ነው:: በተለያዩ ጊዜያትም በመድበሎቹ እየደበለ አሳትሟቸዋል:: ከግጥም መጽሐፍቶቹ ባሻገር በሌሎች ልዩ ልዩ ዘርፎች ላይም ብዕሩን አንስቷል:: በተለይ ደግሞ “ነገም ሌላ ቀን ነው” የተሰኘው የትርጉም ሥራው ዝነኛ ነው:: ከጉዞ ማስታወሻዎቹ በተጨማሪም፣ የተውኔት ሥራዎቹ የሆኑትን በአንድ ደጉሶ በመጽሐፍ መልክ አኑሯቸዋል::

በአንድ ወቅት አንጋፋው አርቲስት አበበ ባልቻ አንድ መድረክ ላይ ተገኝቶ ከነቢይ መኮንን ጋር ስለነበረው አጋጣሚ እንዲህ ሲል ነበር ያወጋው፤ “ነቢይን መጀመሪያ ያየሁት 1970 ዓ.ም ነበር:: በዚያ ዓመት የጀርመን ተማሪዎች ጂምናዚየም ነበርን:: ወደ ኬንያ የሚሄድ የቅርጫት ኳስና የእጅ ኳስ ቡድንም ልምምድ ጀምረናል:: ሶራ ጃርሶ የሚባል እኩያ የሌለው ሰው ነበር የሚያሰለጥነን:: በኋላም ነቢይን አየሁት:: እየሮጠና እንደ እንዝርት እየሾረ … ጎበዝ ነው ብቻ ሳየው:: እሱ ተመረጠ:: እኔ ሳልመረጥ ቀረሁ:: እኔን ጸጋዬ ገ/መድኅንና አባተ መኩሪያ ተባብረው አስረው እዚህ መድረክ ላይ አወጡኝ:: እሱን ደግሞ ደርግ አስተባብሮ አሰረውና ወደ ሦስተኛ ወሰደው:: ከስምንት ዓመት በኋላ እንደገና ተገናኘን:: ተፈቶ ሲመጣ እኔ ስታሪንግ (ኮኮብ) ሆኜ ጠብቄዋለሁ:: እሱም በሲጋራ ወረቀት…” በማለት ትዝታውን አጋራ:: ያ አጋጣሚም ለነቢይ መኮንን እና ለአበበ ባልቻ ግንኙነት የመጀመሪያው እንጂ የመጨረሻው አልነበረም:: በመሀከላቸው አርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያምን አክለው ድንቅ የሆኑ ተውኔቶችንና የትርጉም ሥራዎችን ሠርተዋል:: በአንደኛው ቀንም አበበ ባልቻ ስለተመለከተው ስለ አንድ የውጭ ፊልም ለነቢይ ይተርክለታል:: ነቢይም አድምጦ ሲጨርስ ወዲያውኑ ብዕሩን ከወረቀት አገናኝቶ መጻፍ ጀመረ:: በመጨረሻም “ባለጉዳይ” የተሰኘው የቴሌቪዥን ድራማ ለመወለድ በቃ:: “ደራሲው ነቢይ በየጊዜው እንዲህ እንዲህ ነው እያለ ይጽፋል:: እኔና ፍቃዱም እንተውናለን” ሲልም ጭምር ነበር አበበ ባልቻ በትውስታው::

በሌላኛው ቀን ደግሞ ነቢይ ከአንዲት ጀርመናዊት ሴት የመኖሪያ ቤቷ ግርግዳና በር ላይ አንድ የሚያምር ረቂቅ (አብስትራክት) ሥዕል ይሥላል:: እናም ሰዎች እንደተመለከቱት “ይኼማ በእርግጠኝነት የሰይጣን ማምለኪያ ቤት ነው” በማለት በቁጣ በሯን ይደበድቡታል:: በነገሩ ግራ የተጋባችው ጀርመናዊትም በጣም አዝና ስታወራቸው እንዲህ ሲሉ ጠየቋት፤ “ቆይ ግን፣ እናንተ ሀገር ይህን እንዴት ነው የቻላችሁት? … ናዚዎች አሉ:: አይሁዳዊው አለ …” እሷም ለምላሽዋ የኤፍሬም ኔልሲንግን “ናታን ዘ ዋይዝ” ጠቢቡ ናታን አንስታ ተረከችላቸው:: ከጨዋታው በኋላም አበበ ባልቻ ወደ ሴትየዋ ጠጋ ብሎ ወደ ነቢይ እያመለከታት “ይኼ ሰውዬ እንዴት ቆንጆ አድርጎ ´ናታን ዘ ዋይዝ´ን መተርጎም ይፈልጋል መሰለሽ …” አላት:: ምኞቱም ሰመረና ይኸው ትያትር በነቢይ ተተርጉሞና በአንድ ጀርመናዊ ዳይሬክት ተደርጎ በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ለመታየት በቃ:: ”ጠቢቡ ናታን” የተሠራውም እንዲህ ባለው የአጋጣሚ መንገድ ነበር:: “ዐሥር” የሚሏት ቁጥር መቼም ከዚህ ሰው የሕይወት ጓሮ መሽከርከሯን አንዴ ቀጥላለችና ከአሥር ዓመታት በኋላም “ባለጉዳይ” የተሰኘው ድራማ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በድጋሚ የታየ ሲሆን፤ ከዚያ ሁሉ ጊዜ በኋላም በተመልካቹ ዘንድ አድናቆትን ተችሮታል::

“ነቢይ በሀገሩ ይከበራል” የሚለውን ከፍ በማድረግ ግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም የነቢይ ወዳጅ ዘመድና አድናቂዎቹ ተሰባስበው በአዲስ አበባ ትያትርና የባህል አዳራሽ ውስጥ ተገናኝተው ነበር:: የመገናኘታቸው ምክንያት ደግሞ ነቢይ በዕድሜ ዘመኑ ከልጅነት እስከ ሽበት በኪነ ጥበቡ ውስጥ ስለሀገሩ መሽጎ፤ ለሀገሩ ላበረከተው ሁሉ በስሙ የምስጋና ዝግጅት ተሰናድቶ የነበረ መሆኑ ነው:: በዚህም በዚያም አጋጣሚ ሁሉ ስለ እርሱ ለማውራት የቆሙ ሰዎች ሁሉ ካለው ልዩ የጥበብ ችሎታው ጋር እኩል በእኩል ስለ ሰዋዊውና መልከ መልካም ባህሪው ያወሩለታል:: በብዙ ሙያዊ ጉዳዮች ዕውቀቱ የሰላ፣ ብቃቱ ደግሞ የሞላ ቢሆንም እንደ አጉል አዋቂዎች አንድም ቀን ቀረርቶውን የሚነፋና በሠራው የሚሸልል አልነበረም:: ለትንሹም ሆነ ለትልቁ ከሙያው ቆርሶ ሲያቋድስ ስስትን አያውቅም:: ባለማወቅ ስህተት ውስጥ ቢያገኛቸው እንኳን ያቺን የሚያውቃትን መንገድ ማሳየት እንጂ በንቀት ማብጠልጠልን አይችልበትም:: ለዚህም ነው ጀማሪ የጥበብ ሰዎች በተለየ ሁኔታ የሚቀርቡት::

ጥበብ ነው ሀገርህ፤

ባገር የመሸ ቀን

ሰው ሀገር አይነጋ፤

እስር ቤት ስደት ቤት

ሕይወት ስትላጋ፤

የእንክርትህ ጉዞ

ሀገርክን ፍለጋ፤

ማብቃቱ ታወቀኝ

ሲደርስ አፈሯ ጋ!

እያለ በግጥሙ ይቀጥላል:: ስለ ሀገሩ ባገሩ ቀልድ አያውቅም:: ባገኘበት አጋጣሚ ሁሉ ስለ ሀገሩ ማውራትና እንዲህ እንሁን፣ እንዲያ እያለ በተለይ ለወጣቱ ምክረ መድኃኒቱን ከመስጠትና ከማዘዝ ወደ ኋላ አይልም:: “´ሆድ ከሀገር ይሰፋል´ የሚለው ተረት … እዚያ ጋር ግራጫው ዞን ግን ከዩኒቨርሲም ይሰፋል:: እንደሱ ብለን ካላሰብነው ደግሞ ጽንፈኛ እንሆናለን:: ጽንፈኛ ከሆንን ደግሞ ዕድሜ ልካችንን ከጦርነት አንወጣም:: … ደርግ አንድ ጊዜ እንዲህ የሚል መግለጫ አውጥቶ ነበር፤ ´ዳሩ ሲነካ መካከሉ ዳር ይሆናል´ የሚል መግለጫ ነበረው:: … በተለይ ወጣቶች በሩ እንደሚንኳኳ አውቀን በሩን በሥነ ሥርዓት መዝጋት ይኖርብናል:: … ይህን ካላደረግን የኋላ መወነጃጀል፣ እሱ ነው እሱ ነው የሚል ሰርክል ነው የምንፈጥረው:: … በዚህ ሰርክል ውስጥ ሁላችንም ስለሀገራችን ተጠያቂዎች ነን ማለት ነው” ይላል:: ተበደልኩኝ … ተገፋሁኝ የማይል ሆኖ እንጂ እንደርሱ በፖለቲካ ዳፋ ውስጥ የተዳጠ አልነበረም:: ቢሠራ ሁሌም ሙያ በልብ፣ ቢገፋ በሁሉም እርሱ እንዳለውም “ሆድ ከሀገር ይሰፋል” ብሎ ችሎ ይኖራል እንጂ በምሬት ጮኾ ማጯጯህን አያውቅም:: ባይሆን በእንዲህ ዓይነቶቹ መሳቅ ይቀለዋል:: ነቢይ በሥራው ሁሉ እንደ ወርቅ በእሳት እየተፈተነ፤ የነጠረ የጥበብ ሰው ነበር:: አሳዛኙ ነገር የነቢይን ታላቅነትና ውለታ የሚያውቁ ጥቂቶች ብቻ መሆናቸው ነው:: ምናልባትም ደግሞ ከእርሱ በላይ ሥራዎቹ ታዋቂዎች ናቸው::

ነቢይ መኮንን በጠና ህመም ተይዞ በሕይወት ማቃሰት ከጀመረ ዋል አደር ብሎ ከረመ:: በትዳሩ የሦስት ልጆች አባት ለመሆን ቢበቃም፣ የዚህ ጊዜ ግን ባለቤቱና ልጆቹ በሀገር ውስጥ አልነበሩም:: ይህችን በጣር ሰቀቀን ውስጥ የምታምጠውን አንድ ነብሱን ለማዳን ደርሶ ያልነካው ዶክተር አልነበረም:: ሆኖም፣ የሁሉም ነገር ፍጻሜ ከዛሬ አንድ ወር በፊት ሆነ:: ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ላይ የሕይወቱ ሰኔና ሰኞ ገጠሙ:: አንድ ጊዜ የመጣባትን ምድር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በ69 ዓመቱ ተሰናበታት:: በስተመጨረሻም ነቢይ በሀገሩ ስለሀገሩ ተከበረ::

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You