ሕልምህን ካላከበርከው፤ ትገፈተራለህ!

በዚች ምጥን ጽሑፍ የአንድ ሰው የሕይወት ዘመን ሕልም ወይም ግብ ለመቅረፅም ሆነ መዳረሻው ላይ ለመገኘት ማለፍ ወይም ማድረግ ስላለበት ጉዳይ ምክረ ሀሳብ ለመስጠት የግል ልምድንና አረዳድን ማዕከል በማድረግ ለአንባቢ ለማድረስ በማሰብ እሞክራለሁ። ስለሆነም በወፍ በረር ተጓዳኝ ጉዳዮችን እንመለከታለን። ጤናማ ስኬት ምን መልክ አለው! የሚለውን በተለየ አፅንዖት ሰጥተን እንመለከታለን፡፡

እነሆ፡-

ለውጥን ገና ማህፀን ውስጥ ሆነን ተለማምደነዋል። እናም እድገት ሁሉ ለውጥ ሲሆን ለውጥ ሁሉ ግን እድገት አይደለም። ስለሆነም ብርቱ ሕይወት የመስዋዕትነት ተምሳሌት ልትሆን የምትችልበት አጋጣሚ በርካታ ነው። ለውጥ በራሱ ከአዲስ ነገር ጋር መፋጠጥ ስለሆነ አዕምሮንና ስሜትን ይፈትናል፡፡

አጥብቀን የምንሻው የትኛውም አይነት ውጤት ሂደት ነው። ሂደት ደግሞ መንገዱ ነው። ነገር ግን የመንገዱ መዳረሻ ስኬት የሚመስለው የትየለሌ ነው። ግን እኮ… ስኬት ሁሌም የምንኖረው እንጂ ነገ የምንደርስበት ወይም ያጣነው ነገር አይደለም። ምክንያቱም ስኬት ሁሌም ከውስጣችን ያለ እንጂ ከውጭ የምንፈልገው ወይም የሚሰጠን አይደለም። ጉዞህን ከለየህበት ቅፅበት ጀምሮ የምትኖረው ነው። የምትኖርለትን ውስጣዊ ገፊ ኃይል መለየት ነው፤ ስኬት። የማያቋርጥ ውጤታማነትና የገደብ የለሽ ደስታ ምንጩም ይህ ይመስለኛል፡፡

ለእያንዳንዱ ሰው ከውጭ የሚሰጠው ነገር በረከት ወይም ስጦታ እንጂ ስኬት አይደለም። ስጦታ፤ እያደረገው ላለው ሥራ ከሆነ፣ ምክንያቱ የውስጥ ማንነት ሽልማት ሆኖ በጉዞ ውስጥ እንደ አንድ ፌርማታ ሊታይ የሚችል ነገር ነው። ከዓላማ ወይም ከሕልም ጋር በመዝለቅ የሚገኝ ሽልማት ነው። ይህም ጉልበት ወይም አነሳሽ ምክንያት ሆኖ ብርታት ያጎናፅፋል። ተጓዳኝ እውቅና ይዞ ይመጣል።

ሆኖም ግን ስኬት የማይረግብ እሾት (መሻት) ዘላቂ ሽልማት ነው። ውስጥን ፈንቅሎ የሚወጣ የሚንቀለቀል ጥሬ ጉልበት ነው። ‹‹እመነኝ፣ እሾትህ ከችሎታህ በላይ ከሆነ ተዓምር ትሠራለህ››። ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ሰዋዊ ችሎታዎች በትምህርት ወይም በልምምድ የሚገኙ ናቸው። ለዚህም ነው ፤ ‹‹እሹ ታገኙማላችሁ፤ አንኳኩ ይከፈትላችኋል›› የሚባለው። ስለዚህም መሻትህን ጠብቀው። ጉጉትህን አክመው። አስቸጋሪና አሻሚ ቢሆንም በምናብህ የጠራ ምስል ተመልከት። መንገድህን ተረዳው። የተገደቡና ያልተገደቡ ተፈጥሯዊ ማንነቶችህን አጥናቸው። ስለሆነም የኃይልህ ብርታት የሚወሰነው በነኚህ ማንነቶችህ ላይ ነው። ማስተዋልና ትዕግስት ተላብሰህ በመንገድህ ከፀናህ ሕልምህ ሁሉ እውን ይሆናል። ብቻ መንገድህን በአዕምሮህ ተመልከተው። መንገድህን ካለየህ የትኛውም መንገድ ወደ የትም ይወስድሀል። የአዕምሮህን ጓዳ ጎድጓዳ ፈትሸው፤ መርምረው። የነፃነትህም ሆነ የሕይወት ግብህ ሚዛን መፍለቂያ፤ የደህንነትህ ምሰሶ፤ አንድም ሁለትም የሆነ ኃይልህ ነውና ለየው፡፡

የጠራ ሕልም ሲባል በግልፅ ቋንቋ ሚዛን ጠብቆ ወረቀት ላይ የሰፈረ፣ የእለት ከእለት እንቅስቃሴዎቻችንን የሚገራ ግብ ያለው ተግባር ነው። የሕይወት ፍሬም ልንለው እንችላለን። ስታስበው! የምትሄድበትን ሳትገነዘብ ስኬት መናፈቅ ሰማይን በጣቶችህ ለመዳሰስ እንደመሞከር አይሆንብህም?… ሐቁ ይሄው ነው፡፡

ለዚህ የሚያበቁ በርካታ ጥቃቅን ተግባራት ቀድመው መከናወን አለባቸው። ‹‹ማለትም›› ሰው በክህሎት እየዳበረ፣ በዕውቀት እየጎለመሰ የሚሄድ ፍጡር ነው። ምክንያቱም ማኅበራዊ ሰንሰለቶች ለተለያዩ ሥርዓቶች መፈጠር ምክንያት ናቸው። ፈትሻቸው። እርምጃህ ወቅቱን የዋጀ ይሁን። ስኬት ከወቅት ጋር የተሳለጠ መስተጋብር ውጤት ነው። ጊዜው የፈጠራቸውን ዓውዶች ተረድቶ ተመጣጣኝ ምላሽ መስጠት ያሸልማል። የራስን አቅም መመዘኛም ይሆናል። ለዚህም መሰለኝ ኤርሚያስ አመልጋ፤ ‹‹ካላታገለኝና ካልፈተነኝ፣ ልኬ አይደለም!…›› የሚለው (የማይሰበረው ኤርሚያስ አመልጋ ፣ ገፅ 178፣ ‹‹አንተነህ ይግዛው›› እንደፃፈው)፡፡

ስለሆነም ስኬት ማለት ምኞት ብቻ አይደለም፤ ለሚሻውና ልቦናውን በጌትነት ላጠመቀው፣ ዓውዱን ላወደው፣ የማግኛውን ዘዴ ለቀየሰው እና በመጨረሻም ያቀደውን ለተከታተለውና ላስፈፀመው ነው ‹‹እምነት ክብረት ዓለም›› ሚሊዮኑን የምታስታቅፈው። ይህም የምትሠራውን ለይተህ ከማወቅ ይጀምራል። ‹‹ያለሥራ የለም እንጀራ›› እንዲሉ አበው። አንድ ሰው ሊያሳካ የሚፈልገውን ጉዳይ ለይቶ ሲከውን ስኬት እንለዋለን። ሂደቱም ውስጥህ ላይ የሚንቀለቀለውን ያልተገራ ፍላጎት በተጠና እርምጃ መግራት ነው። ስለሆነም ሕይወት እንደ ምግብ ቤት ነው። መክፈል እስከቻልን ድረስ የፈለግነውን እናገኛለን። ዋናው ጉዳይ ‹‹ግባችንን ከተረዳን በኋላ የምንከፍለው ዋጋ ምን ድረስ መሆን አለበት›› የሚለው ላይ የሚኖረን አቋምና ፅናት የሚወስነው ነው፡፡

ስኬት ውስጣዊ ነው። ከውስጣችን አድጎ ሕይወታችንን ወደ ምንፈልገው አቅጣጫ የሚመራ ሂደታዊ ወይም የማይቋረጥ እሾት ነው። መለወጥ እችላለሁ! ማድረግ እችላለሁ! የሚል እልህ የተላበሰ ከራስ ጋር የሚደረግ ትንቅንቅ ነው። ወደ ምድር ስንመጣ (ከእናታችን ማህፀን ስንወጣ) አልቅሰን። ተወራጭተን። ተፈራግጠን ቀስ በቀስ ወደ ልምምድ ውስጥ እንገባለን። ኖረን በከፈልነው ልክ አንዳንዴም በላይ ወይም በታች ዋጋ ተቀብለን ከምድር እንሰናበታለን። ሆኖም ግን መቋጫው በፀፀትና በቁጭት መሆን የለበትም። ይህ ሁኔታ የሚስተካከለውና መልክ የሚይዘው በሚኖረን ስኬት ልክ ነው። ስለሆነም በምድር ስንኖር የሚገባንን ወስደን፣ በሚገባን ልክ መጥነን ኖረን፣ የተገለገልናትን ምድርና ዓለም በስፋት አገልግለን፤ ከተጠቀምነው በላይ በማትረፍ ትውልድን አገልግለን፣ ሰጥተንና ተቀብለን፣ በመዳፋችንና በላባችን ዋጋ ፀፀትን አስወግደን በሠላም መሰናበት ያስፈልጋል። ለዚህ ሳይሆን ይቀራል ገጣሚው ከበደ ሚካኤል ፤

“ፅድቅና ኩነኔ ቢኖሩም ባይኖሩም፤

ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም፡፡”

በማለት የተቀኙት፡፡

በቀጥተኛ አገላለፅ ስንተረጉመው ‹‹The ma­jor key to your better future is you!›› የሚለው የእንግሊዘኛ አባባል ይበልጥ ገላጭ ነው፡፡

ስለሆነም ስኬት ማለት ሕይወትን በቁም ነገር በመቀበል ትርጉም የሚሰጠንን የልቦናችንን መሻት በዙሪያችን ካለ ሕግና ሥርዓት ጋር አስማምቶ መዝለቅ ነው። የራስን ዕድል በራስ መወሠንም ጭምር ነው። ስኬታማነታችንን በራሳችን መወሰን እንችላለን ስንል ሰዋዊ ፀጋዎችን ተጠቅመን ነው። ከነዚህ ፀጋዎች መካከል ትልቁን ድርሻ የሚጫወቱት የምናብ (imagi­nation) እና የአመክኒዎ (Reason) ስጦታዎች ናቸው። እንግዲህ የነፃነት ምንጩ እነዚህ ፀጋዎች ይመስሉኛል። ነፃነት ምንድን ነው? ከተባለ ደግሞ ‹‹የበለጠ ተወዳዳሪ መሆን›› ማለት ነው።

እያንዳንዱ ሰው ውስጡ ያለውን ጥበብ ለራሱና ለሌሎች ሊተርፍ በሚችል መልኩ ለማድረስ መጣር ማለት ነው። ውድቀትንና ስኬትን በውሳኔዎቻችን ልክ መቀበልም ነው። የኃላፊነት ምንጩ ነፃነታችንን ተጠቅመን በምናደርገው ውሳኔና ተግባር አማካኝነት የሚመጣን ማንኛውም ምላሽ ወይም ውጤት ተጠያቂው ‹‹እኔ ነኝ!›› ብሎ ጠንካራ አቋም መያዝ ነው። ‹‹ታላላቅ ሰዎች እራሳቸውን ይፈጥራሉ›› የሚለው ብሂል የሚሠራው ለእያንዳንዱ እርምጃቸው ውጤት ሙሉ ኃላፊነት በመውሰድ አዲስ በር ለሚከፍቱ ብርቱ እጆች የተሰነዘረ ነው። በተለይ ያለንበት ዘመን ባሕሪ ይህ ነው።

ታዲያ! መሻትህ ለውስጥህ እውነት ነፀብራቅ ነው። የጌትነትህ ምንጩ ማንነትህን በተገቢው ዓውድ መሾምህ ላይ ነው። ይህ ጌትነትህ ደግሞ የቀረፅከው ግብህ ወይም ወረቀት ላይ ያሰፈርኸው ሕልምህ ረዳት ነው። ብልጫ የምታሳይባቸው ነገሮች ምንጭ ይህ ተግባራዊ ኃይል ነው። ስለሆነም ለአንተ ብቻ የሚታይህ የጠራ መንገድ፤ ለኑሮህ መቃናት ቁልፍ ነው። ጨብጠው። ‹‹ሰው ለማይታየው ሕልሙ አሽከር ነው›› የሚባለው ብሂል አዕምሮህ ላይ በግልፅ የተቀረፀን እና የፀናን መዳረሻ እንጂ ብቅ ጥልቅ የሚልን ተርመስማሽ ሃሳብ አይደለም። በሃሳብ ደረጃ ብዙ ሰው የትም፣ ወደ የትም ደርሶ ይመለሳል። ይህንን የሰው ልጅ የአዕምሮ ባሕሪ ተረድቶ በልምምድና በንቃት ገርቶ በተወሰነና በተለየ (በታወቀ) ጉዳይ ላይ በማሰላሰል፣ በመመርመር ጥልቅ አረዳድ በመጎናፀፍ መንገድን ማጥራት ይጠበቃል። ይህ ተግባር ትኩረት የሚጠይቅ በመሆኑ በሂደት የምንፈልገውን እንድንጎናፀፍ ይረዳል፡፡

ስለሆነም በሕይወት ስትኖር አዕምሯዊ ረቂቅ የምስል ረዳት ይኑርህ። ሕሊናህ በጉልህ ይሳለው። የስኬት የመጀመሪያው ነገር የሚታይ አዕምሯዊ ረዳት ማግኘት ነው። የሚታየው ነገር ሁሉ የመጣው ከማይታየው ነገር ነው። ከተገራ ሃሳብ። ስለሆነም ሕልምህን ቅረፅ። እወቀው። እመነው። ተግብረው። ለመሰናክሎች እጅ መስጠት የያዙትን ለመጣል መፍቀድ ነው። ባልተረዳኸውና በማታምንበት ነገር ፅናትና ትጋት ሊኖርህ አይችልም። ስለሆነም በእጅህ ላይ ላለውን ፀጋ በቀላሉ አትልቀቅ። መርምረው። እወቀው። የግብህ ሾፌር አንተ ስለሆንክ በመንገዱ ያለማቅማማት ዝለቅበት። ፌርማታዎችህ ፤ ምርጫዎችህ ናቸውና በጥንቃቄ ምረጣቸው። መዳረሻህ የፃፍከው አንተነትህ ነው። አጥብቀህ ያዘው። መሸነፍን መፍራት ከስኬት ያርቃል። ትግልህ የመውደቅና የመነሳት፣ አቀበትና ቁልቁለት ያለበት ሸካራ ሜዳ ነው። በሂደት የምትጎናፀፋቸው የሰሉ እይታዎችህ እና የተሞረዱ ልምዶችህ ወደ ውጤት ይቀይሩታል። አባጣ ጎርባጣውን የመጫወቻና የድል ሜዳ ያደርጉታል፡፡

አንለይ ጥላሁን ምትኩ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You