የሳምባ ካንሰር በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት ከሚታወቁ የካንሰር አይነቶች አንዱ ነው። በካንሰር ምክንያት ከሚከሰት የሞት ምጣኔ ውስጥም በቀዳሚነት ይቀመጣል። የሳምባ ካንሰር ሕክምና ውጤታማነት ካንሰሩ በታወቀበት ግዜ ካለው የስርጭት ደረጃ ጋር በቅርበት የተቆራኘ መሆኑንም ነው የዘርፉ ሕክምና ባለሙያዎች ያረጋገጡት። ይህም ማለት ሕመሙ በእንጭጭነቱ ወይም ወደተቀረው የሰውነት ክፍል ከመዛመቱ በፊት መለየት ከተቻለ የታካሚውን ሕክምና ውጤት በእጅጉ ማሻሻል እንደሚቻልም ነው ባለሙያዎች የሚጠቁሙት።
በኢትዮጵያ ከ80 በመቶ የሚልቁ የሳምባ ካንሰር ተጠቂዎች በጣም ዘግይተው ወደ ሕክምና ተቋማት እንደሚመጡ ጥናቶች ያመለክታሉ። ይህም የሳምባ ካንሰር ምልክቶች ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑንና የቅድመ ምርመራና ክትትል ትግበራ እንደሀገር ያልዳበረ መሆኑን ይጠቁማል። በኢትዮጵያ የሳምባ ካንሰር ምጣኔ እየጨመረ መምጣቱን አመላካች ጥናቶች መኖሩን ታሳቢ በማድረግ የሳምባ ካንሰር ቅድመ ምርመራና የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ያመለክታል።
ይህንኑ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው የዓለም የሳምባ ካንሰር ቀን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ግዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ13ኛ ግዜ ‹‹ግንዛቤ ከመፍጠር ወደ ተግባር!›› በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ አስተባባሪነት ከጤና ሚኒስቴርና ከማቲዎስ ወንዱ ኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ጋር በመተባበር ባሳለፍነው ሐምሌ ወር መጨረሻ የተከበረው።
የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ራሔል አርጋው እንደሚናገሩት፣ በብሪስቶል ማየርስ ስኩዊብ ፋውንዴሽን /BMSF/ ድጋፍ የሳምባ ካንሰር ተጋላጭነትን በመፈተሽ የቅድመ ልየታና ክትትል ሥራ ከአራት ዓመት በፊት አዲስ አበባን ጨምሮ በኦሮሚያ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች በተመረጡ የጤና ተቋማት ተጀምሯል። በነዚህ ተቋማት ላይ ግንዛቤ የመፍጠር፣ የጤና ባለሙያዎችን አቅም የማሳደግና ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር የተጣጣሙ ሳይንሳዊ ጥናቶችን የማመንጨት ሥራዎች ተከናውነዋል።
በኢትዮጵያ የሳምባ ካንሰር ላይ የምርምርና ጥናት ውጤቶች ውስንነት በመኖሩ የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ በዘርፉ ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መሥራት ይፈልጋል። የዓለም የሳምባ ካንሰር ቀን በኢትዮጵያ ሲከበር በሳምባ ካንሰር ላይ እየተጠኑ ያሉ የጥናት ግኝቶች ቀርበዋል። በጥናቶቹ ላይም ውይይት ተደርጓል። ዓውደ ጥናት ተዘጋጅቷል። በዓውደ ጥናቱም ተመራማሪዎች፣ የጤና ባለሙያዎችና ፖሊሲ አውጪዎች በኢትዮጵያ ባለው አሁናዊ የሳምባ ካንሰር ገፅታ ላይ ምክክር አድርገዋል። የዚሁ መርሐ ግብር ዋነኛ ዓላማም የዓለም የሳምባ ካንሰር ቀንን አስመልክቶ በኢትዮጵያ ስላለው የሳምባ ካንሰር ገፅታ፣ የሕክምና ሁኔታና ተግዳሮቶች ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው።
የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ግንዛቤው ያለው ሁሉም ሰው ለሳምባ ካንሰር የሚያጋልጡ የግል ባሕሪና የአኗኗር ዘይቤ መረጃን በመለዋወጥ ረገድ ንቁ ሚና እንዲጫወቱ ያበረታታል። ሲጋራና ሺሻ ማጨስ፣ ለከባድ ጭስና ጥቀርሻ ያለ ተጋላጭነት፣ በሥራ ቦታ ለመርዛማ ብናኞች/ንጥረ ነገሮች መጋለጥና ስር የሰደደ የመተንፈሻ አካላት በሽታ ታማሚ መሆን በጥናት የተለዩ የሳምባ ካንሰር አጋላጭ መንስኤ በመሆናቸው ቅድመ ምርመራና የሕክምና ክትትል ማድረግ፣ የባሕሪ ለውጥ ማድረግ በሽታውን በመከላከልና በመግታት ሂደት ውስጥ ጉልህ ሚና አለው።
ፕሬዚዳንቷ እንደሚያብራሩት፣ በኢትዮጵያ ከ6 እስከ 10 በመቶ የሚሆነው ሞት የሚከሰተው በካንሰር ምክንያት ነው። የካንሰር ሕክምና ተደራሽነት አናሳ መሆን ደግሞ ለዚህ አንዱና ቁልፍ ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል። በዚህ ምክንያት 15 ከመቶ ወይም 80 ሺ የሚሆኑት ብቻ የካንሰር ሕሙማን የሕክምና አገልግሎት ያገኛሉ። ይህን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት የጤና ሚኒስቴር ስትራቴጂክ እቅድ በመንደፍ እንዲሁም ለሳምባ ካንሰርና ሌሎች ካንሰሮች የሚሆን ሕክምና መመርመሪያ መምሪያዎችን በመቅረፅ በሽታውን ቅድመ ልየታና ሕክምና አገልግሎት ለማዳረስ እየሠራ ይገኛል።
ከነዚህ ውስጥ አንዱ የኬሞቴራፒ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን ቁጥር በመጨመር ወደ 30 በሚሆኑ ሆስፒታሎች ሕክምናውን መሰጠት መቻሉ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ከካንሰር ሕክምና ውስጥ አንዱ የሆነውን የጨረር ሕክምና አገልግሎት ለማስፋት ባለፉት ዓመታት የሬዲዮቴራፒ አገልግሎትን ከ1 ወደ 7 ማሳደግ ተችሏል። ይህም ሚዛናዊ በሆነ ስርጭት በአዲስ አበባ 2 ተቋማት ላይ እንዲሁም በሌሎች ክልል ከተሞች 5 ማዕከላት ላይ ተስፋፍቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
የጤና ሚኒስቴርም በካንሰር ሕክምና ላይ ያለውን የሰው ኃይል እጥረት ለመቅረፍ የኪሊኒካል ኦንኮሎጂስቶችን ቁጥር ከነበሩበት 4 ወደ 50 ማሳደግ ችሏል። ከነዚህ ውስጥ 40 ያህሉ የስፔሺያሊቲ ትምህርታቸው እየተከታተሉ ይገኛሉ። የካንሰር መድኃኒት አቅርቦትንም ከግዜ ወደ ግዜ እያሻሻለ የመጣ ሲሆን አሁን ላይ የመድኃኒቶች ዋጋ ከ 60 በመቶ በላይ የሚሆነውን ወጪ በመሸፈን በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት በኩል ሕክምናውን ለሚሰጡ ሆስፒታሎች ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
ከካንሰር ሕመም ጋር በተያያዘ ያሉ የመረጃ አቅርቦቶችን ለማሳደግ ጥራትና ተደራሽነት ያለው ሕክምና ለመስጠት እንዲረዳ ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ ብቻ የነበረው የካንሰር ሬጅስትሪ አሁን ላይ ወደ አምስት ሌሎች ተቋማት ለማዳረስ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የማቲዎስ ወንዱ ኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወንዱ በቀለ እንደሚሉት ተቋሙ ከጤና ሚኒስቴርና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣውን የሳምባ ካንሰርን ለመቆጣጠር ሦስት ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ እየሠራ ይገኛል። ከሚተገብራቸው የተለያዩ ፕሮጀክቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ የሚያሳድጉ፣ ዘመናዊ ምርመራና ሕክምናን የሚያበረታቱና በኢትዮጵያ የሳምባ ካንሰርን የተመለከቱ ምርምሮችን የሚደግፉ ናቸው።
እነዚህ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎችና ዩኒቨርስቲ ሆስፒታሎች የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች የሳምባ ካንሰር ሕክምናን ውጤታማ በማድረግ በማድረግ በኩል ሚናቸው ከፍ ያለ ነው። ተቋሙ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች አጋላጭ የሆኑ መንስኤዎች ላይ የሚሠራ እንደመሆኑ ትምባሆ በዋናነት ለሳምባ ካንሰር እንዲሁም ለአብዛኛዎቹ ተላላፊ ላልሆኑ ሕመሞች አጋላጭ በመሆኑ ከጤና ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ሕግ እንዲወጣና ቁጥጥር እንዲደረግ በጋራ ሠርቷል።
በሌላ በኩል ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሳምባ ካንሰር ሕክምና ክፍልን በልዩ ልዩ መልኩ እንዲጠናከር አድርጓል። በቱሉ ቦሎ የኬሞቴራፒ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጥበትን ሁኔታ አመቻችቷል። በአፋር ክልልም ለሳምባ ካንሰር ብቻ ሳይሆን በሌሎች ካንሰሮች ላይ ሕክምና እንዲጀመር ጥረት አድርጓል። ከጤና ሚኒስቴርና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ባለሙያዎች ተሰባስበው ሕሙማኖችን አይተው በየደረጃው ሕክምና የሚሰጡበት የመልቲ ዲስፕሊነሪ ቡድን በማቋቋም እየሠራ ይገኛል። ይህም ሕሙማን ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ እንዳይጉላሉና ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ ትልቅ እገዛ አድርጓል። የሚሰጡ ሕክምናዎችና ልየታዎች በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መንገድ የሚሄድበትን ሁኔታ ለመፍጠርም እየሠራ ይገኛል።
በጤና ሚኒስቴር የካንሰር መቆጣጠርና መከላከል አማካሪ ዶክተር ኩኑዝ አብደላ በበኩላቸው እንደሚሉት የሳምባ ካንሰር ችግር ዋነኛ የጤና ችግር ነው። የካንሰር መርሐ ግብር ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ተቀርፆ ወደ ሥራ ሲገባ የተለዩ ዋና ዋና የካንሰር አይነቶች ነበሩ። ነገር ግን ከሰባት ዓመት በኋላ ያለው መረጃ ሲታይ የሳምባ ካንሰር ዋና ዋና ከሚባሉ አስር የካንሰር አይነቶች ውስጥ አንዱ ሆኗል። ይህ ማለት በሚፈለገው ልክ ሥራዎች ካልተሠሩ፣ አስፈላጊ የሆነ እርምጃ ካልተወሰደ በሽታው ደረጃውን እያሻሻለ ወደ ዋና የካንሰር አይነት ሊመጣ እንደሚችል ሁኔታዎች ያሳያሉ።
የመጀመሪያው የዓለም ሳምባ ካንሰር ቀን ከኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲና ከማቲዎስ ወንዱ ኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ጋር በመተባበር ሲከበር በጤና ሚኒስቴር በኩል የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ከነዚህ ውስጥ አንዱ በሳምባ ካንሰር ዙሪያ መረጃዎችን በሚገባ በማጠናቀር በሳይንሳዊ መንገድ የሳምባ ካንሰር መከላከያና ማከሚያ ዘዴዎችን ተጠቅሞ ችግሮችን ፍንትው አድርጎ እንዲያሳይ ማድረግ ነው። ከዚህ የሚገኘው መረጃ ወደፊት ሀገሪቱ በሳምባ ካንሰር ላይ የምትቀርፀውን የመከላከል፣ የማከም፣ የሕሙማን ማስተላለፍ፣ የክብካቤ ሥራ በመረጃ የተደገፈ ግብዓት እንዲገኝ ያግዛል። ይህ ግብዓት በፖሊሲ፣ አካሄድና ስትራቴጂ ላይ ለውጥና ውጤት እንዲመጣ ያስችላል።
በሌላ በኩል ትልቁ በሳምባ ካንሰር ላይ ያለው ችግር ያለው የግንዛቤ ክፍተት ከፍተኛ መሆኑን ነው። ከታች ካለው ማኅበረሰብ ጀምሮ እስከ ጤና ባለሙያዎች ድረስ ብሎም በጤና ሥርዓት ውስጥ የሳምባ ካንሰርን አክሞ ለማዳን ያለው የግንዛቤ ክፍተት ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ከፍ ያለውን ግንዛቤ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መለወጥ ያስፈልጋል። ኅብረተሰቡ ጋር እየደረሱ ያሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተግባራዊና የባሕሪ ለውጥ ማምጣት አለባቸው። በአጋላጭ ሁኔታዎች ላይ፣ አስቀድሞ በሽታውን በመለየት ላይ፣ ኅብረተሰቡ ወደ ሕክምና ተቋማት ቀርቦ የሳምባ ካንሰር ቅድመ ልየታና ሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ሥርዓት የሚበጅበት ከመሆኑ አንፃር በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባ ጉዳይ ነው።
አማካሪው እንደሚገልፁት በሳምባ ካንሰር ዙሪያ ግንዛቤ ማስጨበጥ ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል። በተለይ ስለበሽታው ምንነት፣ ኅብረተሰቡ ራሱን ከዚህ በሽታ ለመከላከል ምን ማድረግ እንዳለበት፣ የእያንዳንዱ ኅብረተሰብና የጤና ባለሙያው ሚና ምን እንደሆነ፣ የፖሊሲ አውጪዎች ሚና ምን እንደሆነ በግልፅ ማስገንዘብ ይገባል። በዚህ ረገድ ደግሞ በተለይ የሚዲያ አካላት ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው። መረጃ ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን ከሳምባ ካንሰር ጋር በተያያዘ ትክክለኛ መረጃ ማስተላለፍም ከሚዲያዎች ይጠበቃል።
የሳምባ ካንሰር ላይ ያለው ሌላኛው ዋና ችግር አብዛኛው የዚህ ካንሰር ተጠቂ የሆነ ሰው ወደ ሕክምና ቦታ በቶሎ አለመምጣቱ ነው። ይህም ታክሞ የማዳን ዕድሉን ያጠባል። በዚህም ምክንያት የሳምባ ካንሰር ሕክምና ውጤታማ አይደለም። ስለዚህ ይህን እንዴት አድርጎ መቀየር ይቻላል ነው ዋናው ጥያቄ። አብዛኛዎቹ በቶሎ እንዲመጡና በጣም ጥቂት የሚባሉት ደግሞ ወደኋላ ሕክምና ቦታ እንዲመጡ ከተቻለ አጠቃላይ የሳምባ ካንሰር የሕክምና ውጤትና ሁኔታ መቀየር ይቻላል።
ለዚህ ደግሞ በጣም ከፍተኛ የሆነ የመረጃ አሰጣጥና የመረጃ ፍሰት በደምብ ማስተካከል ይገባል። የሳምባ ካንሰርን በግዜ በመለየት ማከምና የተሻለ ውጤት ማምጣት ይቻላል። ከዚህ አንፃር ማኅበረሰቡ ካንሰርን እንደመጨረሻ የሞት ፍርድ አድርጎ መቁጠር አይገባም። ስህተቱ ማንም ጋር ይሁን አንድ ሕመምተኛ በግዜ ወደ ጤና ተቋም እስካልመጣ ድረስ ውጤቱ ምትሓታዊ ሊሆን አይችልምና ይህን ማስተካከል ያስፈልጋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የሳምባ ካንሰር የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚፈልግ አውቆ መንቀሳቀስ የግድ ይላል። በዚህ ረገድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ሚና የመጫወት ኃላፊነትም አለባቸው። ይህን ማድረግ ከተቻለ በሳምባ ካንሰር መከላከልና መቆጣጠር ዙሪያ ውጤት ማምጣት ይቻላል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም