አዲስ አበባ፡- ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተመርቀው ሥራ እንዲፈጠርላቸው የሚጠብቁ ዜጎች ቁጥር መብዛት ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ ተግዳሮት እንደፈጠረበት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስታወቀ። የላቀ አፈፃፀም ያስመዘገቡ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችና ግንባር ቀደም የማዕከላቱ ባለሞያዎች እውቅና ተሠጥቷል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የላቀ አፈፃፀም ያስመዘገቡ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችና ግንባር ቀደም የማዕከላቱ ባለሞያዎች የእውቅና አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት ትላንት በአዲስ አበባ በተካሄደበት ወቅት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ እንዳሉት፤ ተማሪዎች በሚመረቁበት ጊዜ ሥራ ለመፍጠር ሳይሆን እንዲፈጠርላቸው ይጠብቃሉ፤ ይህ በሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ሳንካ ፈጥሯል።
“አገራችን ሁሉን አቀፍ ለውጥ ላይ ትገኛለች” ያሉት ኢንጅነር አይሻ፤ ባለፈው አንድ ዓመት ተግባራዊ እየተደረጉ በሚገኙ የለውጥ ሥራዎች ላይም የልማትና ዴሞክራሲ ምህዳሩን በማስፋት በኩል ለዜጎች ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ፤ የሥራ ዕድል ፈጠራው ሚሊዮኖችን ከአዳዲስ የሥራ መስኮች ጋር እንዲተዋወቁና የሥራ ባህልን እንዲያዳብሩ ከማድረግ ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችንንም ለተሻለ ህይወት እንዲበቁ ያስቻለ ቢሆንም ከዘርፉ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮች ግን አልጠፉም።
የአገሪቷን ሠላምና ፀጥታ በማረጋገጥ ረገድም በርካታ ተግዳሮቶች እንዳሉ ያነሱት ሚኒስትሯ፤ በዘርፉ የታቀፉና በስኬትና በውድቀት መካከል የሚንገዳገዱ አንቀሳቃሾችን ህልውና መታደግም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሌላ የሚጠብቀው ፈታኝ ሥራ ነው ብለዋል።
በአካባቢ ልማት ሥራዎች ላይ የተሰማሩ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች በሁሉም ከተሞች እና የሥራ ዘርፎች ተሟልቶ ወደ ሥራ አለመግባታቸው ሌላው ተግዳሮት መሆኑን ያወሱት ደግሞ የፌደራል የከተሞች ሥራ ዕድል ፈጣራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ኩሞ ናቸው።
እንደ አቶ ዘነበ ገለፃ ከከተሞች የምግብ ዋስትና ጋር በተያያዘ በቀን ሊሠሩ በሚገባቸው የሥራ ሰዓትና መጠን ልክ አለመሥራትና ሌሎችም ችግሮች ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በሚደረግባቸው ከተሞች ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው።
አቶ ዘነበ አክለውም መሥሪያ ቤታቸው ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያለውን ጉልበት፣ እውቀትና ጊዜ ከመቼውም በላይ ተጠቅሞ ለውጥ ማስመዝገብ ግድ የሚለው ወቅት ላይ መሆኑን ጠቅሰው በዘርፉ የሚታየውን የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ቀልጣፋና ውጤታማ አሠራርን ለማጎልበት እንሠራለንም ብለዋል።
በእውቅና አሰጣጥ ሥርዓቱ 78 የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች እንዲሁም 275 ባለሙያዎች ተመርጠው እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2011
ዳግማዊት ግርማ