.የተለያዩ አዋጆችንም አጸደቀ
አዲስ አበባ፡- ምክር ቤቱ ዶክተር ዳንኤል በቀለን የሰብአዊ መብት ኮሚሽን አድርጎ በመሾም፣ አምስት አዋጆችን አፅድቆ የጉምሩክ አዋጅን ለማሻሻልና የመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓት ለመወሰን የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ መርቷል።
5ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን በትናንት ውሎው ዶክተር ዳንኤል በቀለን የሰብአዊ መብት ኮሚሽን አድርጎ ሾሟል። አዲሱ ተሿሚ ዶክተር ዳንኤል በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ መብት አያያዝ ችግር ውስጥ እንደነበረና አገሪቱ በሰብአዊ መብት አያያዝ ስትወቀስ መቆየቷንም ተናግረዋል።
ካለፈው ዓመት ጀምሮ በተፈጠረው ለውጥ የሰብአዊ መብትን ጨምሮ በሌሎች ሁኔታዎች በብዙ መሻሻሎች መታየታቸውን የጠቀሱት ዶክተር ዳንኤል፤ አላግባብ የታሠሩ ሰዎች ከእስር መፈታታቸውን፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት፣ የመደራጀት፣ በፖለቲካ ሁኔታ የመሳተፍና በርካታ በኢትዮጵያ ውስጥ ሳይከበሩ የቆዩ መብቶች መከበራቸው ትልቅ እርምጃ መሆኑን ገልፀዋል።
‹‹ አሁን ምንም የሰብአዊ መብት ችግር የለም ማለት አይደለም ፤ ይልቁንም እጅግ በጣም አሳሳቢ፣ ውስብስብና ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት የታያል፤ ይህንን ሃላፊነት ስቀበል በከፍተኛ ሃላፊነትና የአደራ ስሜት ነው። ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማበርከት ፍቃደኛ ነኝ›› በማለት ዶክተር ዳንኤል ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ የጉምሩክ አዋጅን ለማሻሻልና የመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓት ለመወሰን የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል። ለጉምሩክ አዋጁ መሻሻል ዋነኛ ምክንያት የሆነው የኮንትሮባንድ ዕቃ ጭኖ የተገኘ ማጓጓዣ ስለሚወረስበት ሁኔታ የሚደነግገው ክፍል በርካታ ጥያቄ በማስነሳቱ መንግሥት ማሻሻያ እንዲደረግ አቅጣጫ በማስቀመጡ መሆኑ ተጠቁሟል።
ለኢንቨስትመንት በቀረጥ ነፃ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎች ከተፈቀደላቸው ዓላማ ውጭ እየዋሉ በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሱ በመሆናቸው የዕቃዎቹ መወረስ እንደተጠበቀ ሆኖ ተግባሩ በወንጀል የሚያስጠይቅ እንዲሆን፤ በማሻሻያው እንዲደነገግ መደረጉ ተቀምጧል። በነባሩ አዋጅና በማሻሻያው ግዴታ ለሚጥሉ ድንጋጌዎች በሙሉ ውጤታቸው አስተዳደራዊ መቀጫ እንደሚያስከትል እየተገለፀ፤ መቀጫዎቹ በማሻሻያው እንዲካተቱ ተደርጓል።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ የመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓት ለመወሰን የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሯል። በሰነዱ እንደተቀመጠው በክልል መንግሥታት መካከል የጋራ ጉዳዮችን በተመለከተ ተቋማዊ የምክክርና የትብብር ማዕቀፍ እንዲኖር ያደርጋል። በፌዴራል መንግሥትና በክልሎች መካከል እንዲሁም በክልሎች ርዕስ በርዕስ የሚከሰቱ ግጭቶች የሚፈቱበትን የግንኙነት ተቋማዊ ሥርዓት መዘርጋትና ማጠናከር በዓላማ ከያዛቸው መካከል ይጠቀሳሉ። ረቂቅ አዋጁን የመረመረው ምክር ቤቱ ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
እንዲሁም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን እንደገና ለማቋቋም የቀረበለትን አዋጅ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ማቋቋሚያ አዋጅን ለማስፈፀም የቀረበ ረቂቅ ደንብና የከፍተኛ ትምህርት ረቂቅ አዋጅን አጽድቋል። በተጨማሪም በኢትዮጵያና በእሥራኤል መንግሥት መካከል በጉምሩክ ጉዳዮች፣ በቱሪዝምና በግብርና ዘርፍ ለመተባበር የቀረበውን ረቂቅ አዋጅም አጽድቋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2011
ዘላለም ግዛው