የስፖርት ማህበራት በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ላይ አቤቱታ አቀረቡ

በኢትዮጵያ የተመዘገቡ ብሄራዊ የስፖርት ማህበራት በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጸሚ ቦርድ አባላትና እና ፕሬዚዳንት ላይ በይፋ አቤቱታ አቅርበዋል። ቅሬታው የቀረበው ለኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሲሆን፤ ተገቢው አስተዳደራዊና ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድም ይጠይቃል።

በቅርቡ የተጠናቀቀው 33ኛውን የፓሪስ ኦሊምፒክ ተከትሎ አነጋጋሪ ጉዳዮችን ሲያከናውን የቆየው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እንዲታገድም የስፖርት ማህበራቱ በደብዳቤ ጠይቀዋል። ቅሬታው የቀረበው ኮሚቴውን ከሚመሠርቱና በኢትዮጵያ በተመዘገቡ ብሄራዊ የስፖርት ማህበራት ሲሆን፤ በዋናነት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባላትና እና ፕሬዚዳንቱን ይመለከታል። ማህበራቱ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ተሻሽሎ በወጣው መመሪያ ቁጥር 907/2014 መሠረት በዓለም አቀፍ ስፖርት ፌዴሬሽን አባልነት የተመዘገቡ፣ ስፖርቶቻቸው በኦሊምፒክ ተሳታፊ የሆኑ እንዲሁም በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጠቅላላ ጉባዔ ሕጋዊ አባል ናቸው። የስፖርት ማህበራቱ በሕጋዊ ጠበቆቻቸው አማካኝነት በዘጠኝ ገጽ ሰነድ የተደራጀ አቤቱታ፤ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሕዝብ መብትና ጥቅምን የሚጎዱ ተግባራት ላይ መሳተፉን የሚያመላክት ነው።

ስፖርቱን በበላይነት ለሚመራው የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የቀረበው አቤቱታ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኮሚቴው ከሕግና ሥርዓት ውጪ በሆነ መንገድ በተፈጸሙ ተግባራትን በመመርመር ተገቢው አስተዳደራዊና ሕጋዊ ርምጃ እንዲወስድ ይጠይቃል። የቅሬታው ምክንያት በዝርዝር ተመላክቶ የቀረበ ሲሆን፤ በዋናነት ከቀረቡት መካከል ኮሚቴው ያደረገው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ አንዱ ነው። ግንቦት 04/2016 ዓ.ም ተደረገ የተባለው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ሕግና ሥርዓትን ያልተከተለ፣ ጥሪውም ሆነ የተላለፈው ውሳኔ በመመሪያ ቁጥር 907/2014 አንቀጽ 59/7/ ላይ ከተደነገጉ የተከለከሉ ተግባራት የሚለውን በመጣስ የተፈጸመ ሕገወጥ ተግባር በመሆኑ አስተዳደራዊ ርምጃ ይወሰድበት የሚልም ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ሰኔ 04/2016 ዓ.ም የተከናወነው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ምርጫም በሕገወጥነት የተደረገ መሆኑም በሰነዱ ተመላክቷል። ኮሚቴው ምርጫውን በሚመለከት ፌዴሬሽኖች ባልተሳተፉበትና ባላወቁበት ሁኔታ ሲከናወን፤ ገለልተኛ በሆኑ አስመራጮች መደረግ ቢኖርበትም ስፖርቱን የሚመሩ የመንግሥት አካላት በሌሉበትና የጉባዔው አባል ያልሆኑ አካላት እንዲመራ ተደርጓል። ምርጫው የጉባዔ አባል የሆኑ የስፖርት ማህበራትን ጨምሮ ሌሎች በጉባዔው በድምጽ የሚሳተፉ አባላትን ባለማካተቱም ሕገወጥ መሆኑም ተዘርዝሯል።

በምርጫው ድምጽ በማግኘት ለ3ኛ ጊዜ ሥልጣን የያዙት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የሃረሪ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች፣ በአማራ ክልል የሰቆጣ ቃልኪዳን ድርጅት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊም በሥራ አስፈጻሚ ቦርዱ መካተትም የዓለም አቀፉን ኦሊምፒክ ኮሚቴ ቻርተር የሚጥስ መሆኑ ተብራርቷል። በመመሪያው መሠረት የቦርዱ ሥልጣን ዘመን 10 ወር እየቀረው ምርጫው መከናወኑ፣ ከሕዝብ አይንና ጆሮ በራቀ ሁኔታ መደረጉ እንዲሁም ያለምርጫ በቀጥታ የኮሚቴው ምክትል ፕሬዚዳንት ሆና የተመረጠችው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ጉዳይም በዚሁ ርዕስ ስር ተካቷል።

ኮሚቴው ከመንግሥትና ሌሎች ረጂ ተቋማት የሚሰጠውን ገንዘብ ኦዲት ባለማድረግና ሪፖርት ባለማቅረቡ የፋናንስ ጥሰትና ምዝበራ መከናወኑም በአቤቱታው ተጠቅሳል። በዚህም መንግሥት ለቶኪዮ ኦሊምፒክ 156 ሚሊዮን ብር፣ ለአፍሪካ ብሄራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር ውድድር የወጣው 47 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች 100 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቦ ለኮሚቴው ገቢ ተደርጓል። ነገር ግን እስካሁን በሪፖርት ለዓመታት ያልቀረበ በመሆኑ ማህበራቱ ባላቸው መብት መሠረት ግልጽ እንዲደረግላቸውም ጠይቀዋል። ከዚህ በተጨማሪ የስፖርት ትጥቅ አምራች የሆነው አዲዳስ በየዓመቱ፣ ለአፍሪካ ጨዋታዎች እንዲሁም ለኦሊምፒክ ውድድሮች የሚያቀርበውንና በመቶ ሺህ ዶላሮች የሚገመት የስፖርት ትጥቅን ጨምሮ ሌሎች ከዚሁ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችም ቅሬታው ቀርቧል።

ከቀናት በፊት የተጠናቀቀውን የፓሪስ ኦሊምፒክ በተመለከተም የኢትዮጵያን መልካም ስምና ዝና የሚያጎድፍ ተግባራትም ተከናውነዋል ያሉት ማህበራቱ፣ በዚህም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ጀግኖችን የማይመጥን ተግባር፣ አትሌቶች እና አሠልጣኞች ውድድሩ ከመጠናቀቁ በፊት ከፓሪስ መሸኘታቸው እንዲሁም በጉዞው የተካፈሉ የልኡካን ዘመድ አዝማድን ጭምር ያካተተ መሆኑም ተጠቅሷል። ኮሚቴው ከኦሊምፒክ ተሳታፊ ከሆኑ ስፖርቶች ውጪ ላሉት ድጋፍ አለማድረጉ እና በተቋሙ የሚቀጠሩ ሰዎችና ደመወዝ አከፋፈል ላይ የሚፈጸሙ ሕገወጥ ተግባራት እንዲጣራም ሰነዱ አሳስቧል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ዓርብ ነሐሴ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You