* የሐሳብ ብዝሃነትን ለማስተናገድ ያስችላል
* ሠራተኛውን በአንድ ዓላማ በዕኩል ለማሳተፍም ያግዛል
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን እንደገና ለማቋቋም የጸደቀው አዋጅ የሐሳብ ብዝሃነትን ለማስተናገድና ወቅታዊና እውነተኛ መረጃን ለሕብረተሰቡ ለማስተላለፍ እንደሚያስችለው ተገለጸ። ዘመናዊ የህትመት ሚዲያ አደረጃጀት በመፍጠር ተልዕኮውን ለማሳካት ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረውና ሠራተኛውን በዕኩል ለማሳተፍ እንደሚያግዘውም ተጠቆመ።
5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገና ለማቋቋም ያቀረበውን ሪፖርትና የውሣኔ ሐሳብ መርምሮ አዋጁን አጽድቋል።
የሕግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተወካይ ወይዘሮ የሺእመቤት ነጋሽ፤ አዋጁ በአዲስ መልክ ተሻሽሎ መጽደቁ ከተደራሽነት፣ ከመረጃ ወቅታዊነትና ከጥራት ጋር ተያይዞ ያሉበትን ችግሮች በመቅረፍ ረገድ መፍትሄ እንደሚሆን አመልክተዋል። እንደ አገር ብቸኛው የፕሬስ ሚዲያ እንደመሆኑ በኤሌክትሮኒክስና በህትመት ሚዲያ የመረጃ ምንጭ ሆኖ እንደሚያገለግል ያላቸውን ተስፋም ጠቁመዋል።
በሃሰት መረጃ ላይ ተመስርቶ በርካታ ጥፋቶች እየደረሱ መሆናቸውን በማመልከትም ፕሬስ እንደ ህዝብ ሚዲያነቱ፤ የሐሳብ ብዝሃነትን ለማስተናገድና ወቅታዊና እውነተኛ መረጃን ለህብረተሰቡ ለማስተላለፍ ያስችለዋል ብለዋል – ወይዘሮ የሺእመቤት።
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ አዋጁ ድርጅቱ የራሱን ማተሚያ ድርጅት ሊያቋቁም የሚችልበትን ዕድል ፈጥሮለታል። ከህትመት መዘግየትና ከህትመት ጥራት ጋር ተያይዞ ይደርስበት የነበረውንም ችግር ይፈታል ብለዋል።
ደረጃውን የጠበቀ የስርጭት አሠራር በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ በመዘርጋት በአገር ገጽታ ግንባታ፣ ባህልን በማስተዋወቅ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በመንግሥትና በህዝብ መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ በማገልገል ሚናውን እንዲወጣ ያስችለዋል።
‹‹የሕግ ማዕቀፍ ችግሩ ተፈትቷል። ቀጥሎም አዋጁን ማስፈፀሚያ ዝርዝር ደንብ ይወጣል ይህንን የማመቻቸት ሥራ ቋሚ ኮሚቴው ይሠራል። በፊት ተቋሙ እንደማንኛውም አስፈፃሚ አካል በጀቱን ለገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ጠይቆ ያስፈጽም ነበር›› ብለዋል።
በቀጣይ ቋሚ ኮሚቴው የሚከታተላቸው የዴሞክራሲ ተቋማት ከአስፈፃሚው አካል ነፃ መሆናቸው አንዱ ማረጋገጫው የበጀት ነፃነት ነው። በመሆኑም በጀታቸው ቀጥታ ለምክር ቤት ቀርቦ ታይቶ ሊጸድቅ የሚችልበት ሁኔታ እየተሠራ ነው ያሉት ወይዘሮ የሺእመቤት፣ በቀጣይ የሚያቀርባቸውን የበጀትና ሌሎች ጥያቄዎችን እንደ ቋሚ ኮሚቴ በማየትና በማጽደቅ የመረጃ ምንጭ ሆኖ እንዲወጣ ለማድረግ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉም ቃል ገብተዋል።
የቋሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ኪሚያ ጁነዲ፤ ድርጅቱ አንጋፋ እና ለህብረተሰቡ መረጃዎች ሲያደርስ እንደቆየ አስታውሰዋል። በሁለት አመራር እንዲተዳደር መደረጉ ሥራውን በአግባቡ ለመፈፀም አስቸጋሪና በሠራተኞችም ዘንድ የቅሬታ ምንጭ ሆኖ መቆየቱን ጠቁመዋል። ሠራተኞችን እኩል በማሳተፍና ተጠቃሚ በማድረግ የሚፈለገው ደረጃ ለመድረስ የሚያስቸግሩት ማነቆዎች በአዋጁ እንዲፈቱ መደረጋቸውንም አብራርተዋል።
ተቋሙ ለህብረተሰቡ ጥራት ያለውና ተደራሽ የመረጃ ምንጭ ሆኖ እንዲቀጥል እንፈልጋለን ያሉት ወይዘሮ ኪሚያ፤ የቆዩ ነገር ግን የሚገባቸውን ያህል ተደራሽ ያልሆኑ እንደ በሪሳና አልዓለም ያሉ ህትመቶቹን በአግባቡ ለህዝብ ለማዳረስ ጥረት ሊያደርግ ይገባል። የተጣለበትን ሃላፊነትም በአግባቡ ለመወጣት የበኩሉን ድርሻ ማበርከት ይገባዋል ብለዋል። ተቋሙ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የቋሚ ኮሚቴው ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ታደሰ፤ ተቋሙ የአመራር ለውጥ በማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የቀድሞው አዋጅ ተቋሙ የሚፈለገው ደረጃ እንዳይደርስ ተጽዕኖ ፈጥሮ መቆየቱን ጠቁመዋል። ለአንድ አላማ የተሰለፉ ሠራተኞችን እኩል በማሳተፍ በኩል ተግዳሮት እንደነበረውም አመልክተዋል።
ተቋሙ
በሁለት
አደረጃጀት
ሲመራ
ነበር
ያሉት
አቶ
ጌትነት፤
ግማሹ
በሲቪል
ሰርቪስ
ይተዳደር
የነበረና
ጥቅማ
ጥቅሙና
ደመወዙ
በጣም
አነስተኛ
የሆነ
ሌላው
ደግሞ
በአንፃራዊነት የተሻለ እንደነበር ጠቅሰዋል። በዚህ ምክንያት አዋጁ ሲነሱ የነበሩ ተደጋጋሚ ቅሬታዎችን በመሰረታዊነት ይፈታል ነው ያሉት። ሠራተኛውን በአንድ ዓላማ በእኩል በማሳተፍም የተቋቋመለትን ዓላማ ለማሳካት ያግዘዋል ብለዋል።
አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገበት ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የህትመት ሚዲያ አደረጃጀት የያዘ፣ ተቋማዊ አቅሙ የዳበረ፣ የመፈፀም አቅምና ዓላማውን ለማሳካ የሚችል ጠንካራ ተቋም ለመፍጠር መሆኑን አስታውቀዋል።
‹‹ተቋሙ በቀጣይ የራሱ ማተሚያ ቤት ይኖረዋል፣ ሥርጭቱን የሚያስፋፋባቸው አሠራሮችን ይዘረጋል፣ የገቢ አቅሙ በጠንካራ መሰረት እንዲቆም ያደርጋል፣ የተሻሉ ጋዜጠኞችንና ባለሙያዎችን ወደ ተቋሙ ለመሳብ አቅም ይፈጥራል። በዚህም አጠቃላይ የይዘት ሥራው ጠንካራ ይሆናል። ተቋሙም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆኖ ይወጣል። ተቋሙ የሚያመነጨውን ሀብት መልሶ በመጠቀም የይዘት ሥራዎቹን ተደራሽ ለማድረግ ዕድል ይፈጠርለታል›› ብለዋል።
ድርጅቱ እስካሁን በአራት ቋንቋዎች ህትመቶች እንዳሉት በመጠቆምም፤ በቀጣይነት በአገር ውስጥ ቋንቋ ካሉት የአፋን ኦሮሞና አማርኛ ህትመቶቹ በተጨማሪ ወደፊትም በሌሎች ቋንቋዎች ህትመቶችን እንደሚጀምር ተናግረዋል። ለውጡ የይዘት ሠራተኛው ላይ የፈጠረው መነቃቃት አለ። ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችም በቅሬታ ውስጥ ሆነውም የተጀመሩትን የለውጥ ሥራዎችን በመደገፍ ድርሻቸውን አበርክተዋል ብለዋል።
በድርጅቱ የፋይናንስ ገቢ ክፍል ሃላፊ አቶ ስሜነው በርሄና ወይዘሪት ገዳም ዋሴ፤ የአዋጁ መጽደቅ በሁለት አመራር የነበረውን ወደ አንድ አሰባስቦ ለመምራት ያግዛል ብለዋል። በእኩል ለማሳተፍና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚያግዝም ጠቁመዋል።
በተነሳሽነት ሥራዎችን ለመሥራት እንደሚያግዝና የቡድን ሥራ እንዲጠናከር እንደሚያደርግም ተናግረዋል። የድርጅቱን ተልዕኮ ለማስፈፀም እንደሚረዳም ያላቸውን ተስፋ ጠቁመዋል። የገቢ ምንጭን ለመጨመር፣ የደንበኞች እርካታን ለማሳደግና የሠራተኞች ፍልሰትን ለማቆም እንደሚያግዝም ነው ያብራሩት።
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2011
ዘላለም ግዛው