አዲስ አበባ፡– የፌዴራል መንግስት ህንፃዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ለፌዴራል ዳኞች መኖሪያ ቤት ለማስገንባት ያዘው እቅድ ከአንድ ዓመት መዘግየት በኋላ በመጪው ነሐሴ እንደሚጠናቀቅ አስታወቀ።
የፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተክለፃዲቅ ተክለአረጋይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት የቤቶቹን ግንባታ በ19 ወራት ጊዜ ማለትም እ.አ.አ. በሰኔ 2018 ለማጠናቀቅ ከተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ድርጅት ጋር ውል ቢገባም በኮንትራክተሩ የአቅም ውስንነት፣ የማጠናቀቂያ ግንባታ ግብአት እጥረትና የውጭ ምንዛሬ ችግር ምክንያቶች አፈፃፀሙ ከአንድ ዓመት በላይ ሊጓተት ችሏል።
የመኖሪያ ህንፃዎቹ አራት ባለ 21 ወለል ሲሆኑ፤ አሳንሰርና ጄኔሬተር እንደሚገጠምላቸው ታሳቢ ቢደረግም በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ግብአቶቹን በቅርቡ ማሟላት እንደማይቻል፤ ቀሪዎቹን የግንባታ ስራዎች ግን እስከሚቀጥለው ነሐሴ ወር ድረስ ለማጠናቀቅ የሚያስችሉ ግብዓቶች በመገኘታቸው ሊጠናቀቁ እንደሚችሉ ስራ አስኪያጁ አመልክተዋል።
ለ278 አባወራዎች መኖሪያ እንደሚያገለግሉ የታሰቡት ህንፃዎች 750 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው ሲሆን፤ የህንፃዎቹ ዘመናዊነት ለዳኞች መኖሪያ የሚመጥኑ መሆናቸውንም ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
ፕሮጀክት ጽፈት ቤቱ ቀደም ሲል ለፌዴራል መንግስት ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ 33 የህንፃ ግንባታዎችን በማካሄድ ያስረከበ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም የ17 ህንፃዎች ግንባታ እያካሄደ መሆኑ ተጠቁሟል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2011
አጎናፍር ገዛኸኝ