‹‹ሸሙኔ››የቋንቋናወግ ጨዋታ

የመጽሐፉ ስም፡- ሸሙኔ

ደራሲ፡- መስፍን ወንድወሰን

የህትመት ዘመን፡- 2016 ዓ.ም

የገጽ ብዛት፡- 217

የመሸጫ ዋጋ፡- 496 ብር

መጀመሪያ መጽሐፉ በማህበራዊ ገጾች ላይ በአንዳንድ ሰዎች ሲዘዋወር ተመለከትኩ። መጽሐፍ ፌስቡክ ላይ ማስተዋወቅ የተለመደ ስለሆነ ብዙም ትኩረት አልሰጠሁትም ነበር። እየቆየ ሲሄድ ግን ተደጋገመብኝ። ሰዎች የራሳቸውን አተያይ ጽፈው አየሁ። አብዛኞቹ ቋንቋው ላይ አተኩረዋል። በኋላ ግን የማህበረሰብ ቱባ ቋንቋና ወግ እንደምወድ የሚያውቅ አንድ ጓደኛዬ ይህን መጽሐፍ ማንብ አለብህ አለኝ። አነበብኩት።

ብዙዎች መጽሐፉን ሳላስቀምጥ ነው የጨረስኩት፣ በአንድ ቀን ነው የጨረስኩት፣ በአንድ ምሽት ነው የጨረስኩት… እያሉ ገልጸውታል። እኔ ግን በተቃራኒው ነው የሆነብኝ። ያቺ 215 ገጽ መጽሐፍ ሙሉ ቅዳሜና እሁድ፣ እንዲሁም አንድ ምሽት ወስዳብኛለች።

እያነበብኩ ሳለ በአንዲት ዓረፍተ ነገር ወይም አንቀጽ ወደ ሀገር ቤት እሄዳለሁ። ሌባ ጣቴን ያለሁበት ገጽ መሃል ላይ አድርጌ መጽሐፉን አጥፌ በቁዘማ ሄጃለሁ። አንድ ዓረፍተ ነገር ባነበብኩ ቁጥር በአካባቢያዬ የማስታውሰው አንድ ሰውዬ ይመጣል። የረሳሁትን አካባቢ ያስታውሰኛል። አንድ ወግ ሌላ እኔ የማውቀው የአካባቢ ወግ ያመጣብኛል። መጽሐፉን ሳነብ፣ ካነበብኩት ይልቅ የጻፍኩት ሳይበልጥ አይቀርም። እየቆሰቆሰ የሚያስታውሰኝን የስነ ቃል ግጥሞች ጻፍ ጻፍ ይለኛል። መሳጭ ብቻ ሳይሆን ቆስቋሽ መጽሐፍ ነው።

የስነ ጽሑፍ ባለሙያ ስላልሆንኩ ከስነ ጽሑፋዊ ቅርጽና ዘውግ አንፃር ምንም ማለት አልችልም። አንድ ነገር ግን ያጓጓኛል። የስነ ጽሑፍ ባለሙያዎች በዚህ መጽሐፍ ላይ ሒስ ሰርተውበት ማየት! ‹‹ምን ይሉ ይሆን?›› እላለሁ። ምክንያቱም በየመድረኩ ሲናገሩ እንደሰማኋቸው፣ በመጽሔት ሲከራከሩ እንዳነበብኩት፤ ኪነ ጥበብ ተፈጥሯዊ ስሜትን በነፃነት መግለጽን ይጠይቃል። ስነ ጽሑፍ ያዩትን፣ የሰሙትን እና በውስጥ የተፈጠረን ስሜት መግለጽ ነው። እዚህ ላይ እንግዲህ ‹‹ስታንዳርዳይዜሽን›› እና ‹‹ፖፕላራይዜሽን›› የሚሉት አላቸው።

‹‹ስታንዳርዳይዜሽን›› ማለት አንባቢን ታሳቢ አድርጎ መጻፍ ማለት ነው። የጽሑፉን መልዕክት ታሳቢ በማድረግ ለሆነ ዓላማ የሚጻፍ ማለት ነው። በአጭሩ ለማስተማር ማለት ነው። ይህ ብዙ ጊዜ ለጋዜጣና መጽሔት ሲሆን በዚህ አይነት መንገድ የሚጻፉ መጻሕፍትም አሉ።

‹‹ፖፕላራይዜሽን›› ማለት ግን በቀጥታ የተፈጠረውን ስሜት መጻፍ ማለት ነው። ያዩትንና የሰሙትን መጻፍ ማለት ነው። ዋና ዓላማው ስሜትን መግለጽ ነው። ስነ ጽሑፍ በዚህኛው መንገድ ሲጻፍ ነው ጥሩ ተብሎ ይታመናል፤ ወዲህ ደግሞ ማህበረሰብን ማስተማር አለበት የሚል ክርክር አለ። ሰፊ ማብራሪያውን ለስነ ጽሑፍ ባለሙያዎች እንተወውና ሸሙኔ መጽሐፍን እንመልከት።

የመጽሐፉ መቼት አማራ ሳይንት ውስጥ ነው። በይዘት በኩል፤ ዋና ገጸ ባህሪው አዝማሪ ሲሆን ከቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት እስከ ኢህአዴግ ድረስ ያሉትን ዘመናት ይመላለስባቸዋል። በተለይም በ1977 ዓ.ም የተከሰተውን ረሃብ የሚገልጽበት መንገድ ያስለቅሳል። ወዲህ ደግሞ ወግና ጨዋታው እንደገና ያስቃል። እያሳቀ እያስለቀሰ ያልኖርንበትን ዘመን ጭምር ያሳየናል።

በስነ ጽሑፍ ደረጃ ደግሞ በቋንቋ ይጫወታል። የስነ ጽሑፍ ውበቱ ቋንቋ ነው ይላሉ ባለቤቶቹ። ቋንቋ ሲባል ታዲያ አንድ ወጥ የሆነ የጋራ አገላለጽ አይደለም፤ የየራሱ ቀለም ያለው የፀሐፊዎች አገላለጽ ማለት ነው።

እዚህ ላይ ደራሲው አንድ ልዩ ነገር አሳይቶናል። ብዙዎቻችን ኖርንበት፣ አደግንበት፣ ስንናገራቸው የነበርናቸውን ቃላት ረስተናቸዋል። የምናነባቸው መጻሕፍት፣ ጋዜጦችና መጽሔቶች፣ የምንከታተላቸው መድረኮችና መገናኛ ብዙኃን፣ አዋዋላችንና በዙሪያችን ባሉ ሰዎች ተፅዕኖ ሌላ የቋንቋ ባህል አዳብረናል። ደራሲው በዚህ ሁሉ የትምህርትና የሥራ ሂደት ውስጥ ሲያልፍ (የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መምህር እንደነበር ሰምቻለሁ) ያንን ቱባ ባህልና ቋንቋ አልዘነጋውም።

ሰው እንዴት በዚያ ልክ በጥንቃቄ ራሳቸው የተናገሩት እስከሚመስል ድረስ በገጠር ሰዎች ዘዬ ይጽፋል? ወይስ ራሱም ሲናገር በእነዚያ ቃላት ይሆን? (ሲናገር ስላልሰማሁት)፤ ወይስ በቦታው ላይ በቆየባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ የሚናገሩትን እየቀረጸ ነበር? ግራ ቢገባኝ ምናልባት ድምጻቸውን እያዳመጠ ይሆን የጻፈው? የሚል ስሜት ፈጥሮብኛል።

እኔ እልም ያለ ገጠር ውስጥ ነው ያደግኩት። ምንም እንኳን ዘዬ ከአካባቢ አካባቢ የሚለያይ ቢሆንም መጽሐፉ እኔ ባደኩበት አካባቢ የሚነገሩ ብዙ ዘዬዎች አሉበት። ዳሩ ግን እነዚያን ቃላት ከመርሳቴ የተነሳ ሰምቼው የማላውቀው ቃል እየመሰለኝ ‹‹ምን ማለት ይሆን?›› እያልኩ በጽሑፉ ዓውድ ለመረዳት እታገላለሁ። ደግነቱ ጭራሹንም የማላውቃቸውን ቃላት ሳይቀር በዓውዱ መረዳት በጣም ቀላል ነው። እንደ መዝገበ ቃላትም ጭምር ያገለግላል ማለት ነው፡ መስማት ብቻ ሳይሆን ስናገራቸው የነበሩትን ቃላት ግን እኔ ረስቻቸዋለሁ። በኋላ ትዝ ሲለኝ ለካ ያ ቃል እኔ በጽሑፍ ቋንቋ ተላምጄው እንጂ የሚታወቅ ነበር። እንዲህ እያደረገ በቋንቋ ይጫወታል፤ ያጫውታል።

መጽሐፉ የማህበረሰብ ጥናት (ሶሾሎጂ) ለሚያጠኑ ሰዎች ብዙ ነገር ይነግራል። በነገራችን ላይ የማህበረሰብን ምንነት ለማወቅ ቃለ መጠይቅ ከማድረግ ወይም መጠይቅ ሰጥቶ ከማስሞላት ይልቅ እንደ ሸሙኔ አይነት መጽሐፍ ማንበብ ይበልጣል። ቃለ መጠይቅ በምናደርግበት ጊዜ የሚነግሩን በዚያ ቅጽበት የሚኖራቸውን ስሜት ነው። በሌላ በኩል ውስጣቸው ነፃ አይሆንም። የሆነን ነገር ታሳቢ አድርገው የሚፈሩት ነገር ይኖራል፤ የሆነ ነገር ያሳጣናል ወይም ያስገኝልናል ከሚል የውስጥ ትግል ጋር ነው የሚናገሩት። ምን ብናገር ይፈለጋል? ጠያቂው ምን ፈልጎ ይሆን? ምን ለማድረግ ይሆን? የሚል ነገር በውስጣቸው ይመሳሰላል። ስለዚህ በነፃ ልቦና አናገኛቸውም።

ስነ ቃል እና ሌሎች ወጎቻቸው ግን ሰው አዝዟቸው ሳይሆን የውስጥ ስሜት አዝዟቸው፣ ነፍሳቸው የሚመራቸውን የሚናገሩት ነው። ስለዚህ ትክክለኛ የማህበረሰብ ምንነት የሚገኘው ከእንዲህ አይነት ቱባ ባህልና ወግ ነው።

ሸሙኔ የሚነግረን ይህን የማህበረሰብ ፍልስፍና እና ወግና ልማድ ነው። ድንገት ስቅስቅ ብዬ አለቅሳለሁ። የማለቅሰው በገጸ ባህሪው በተገለጸው ታሪክ ውስጥ በአካባቢያችን ወይም በቤተሰብ የማውቀው እውነተኛ ታሪክ ስላለ ነው። ለምሳሌ፤ ምኸኛት (የአዝማሪው ሚስት) ከሞተች በኋላ ልጆቿ ልብሷን እያወጡ ያሸቱታል። በአካባቢያችን እናት ወይም አባት እህት ወይም ወንድም፣ ልጅ ወይም ሌላ የቅርብ ቤተሰብ ሲሞት ልብስ ይዞ ማልቀስ የተለመደ ነው። ለሚመለከቱ ሰዎች በጣም የሚረብሸው ግን ሟች ከሞተ ከብዙ ጊዜ በኋላ ልብሱን እያወጡ ማሽተት ነው። ይህ የማውቀው ልማድ ስለሆነ እንዲህ አይነት ልማዶችን እየጠቀሰና እያስታወሰ ያስለቅሰኛል።

በገጠር ውስጥ ያለው ማህበረሰብ ፍልስፍና አልተነገረለትም። የኪነ ጥበብ፣ የሳይንስ፣ የእምነት፣ የፍልስፍና ምንጩ ከዚያ ሆኖ፣ ዳሩ ግን አልተነገረለትም። ዘመናዊ በሚባለው ተውጧል። ፍልስፍናቸው ግን ጥልቅ ነው። እንዲያውም መጽሐፉ አንዳንድ ጊዜ ከስነ ጽሑፍ ይልቅ ሪፖርት ይሆንብኛል። እዚህ ላይ ግን አንድ ነገር ታሳቢ ይደረግ። የጋዜጠኝነት ሙያ በባህሪው ከቋንቋ ውበት ይልቅ ገለጻ (ይዘት) ላይ ስለሚያተኩር የዚያ ተፅዕኖ ስለሚኖርብኝ ይሆናል።

የገጠር ሰዎች በጣም ሲበዛ አማኝ ናቸው አይደል? ይህንን ማንም ያውቃል። የሚገርመው ግን በፈጣሪ ላይ ሳይቀር ያምጻሉ፤ ፈጣሪን ይቆጣሉ። በነፃነት ይፈላሰፋሉ። ሸሙኔ ይህን ሁሉ ነው የሚነግረን። ለምሳሌ፤ በመጽሐፉ ገጽ 14 ላይ የሚከተለውን እናገኛለን።

‹‹እግዜርን አኩርፈህ ነበር የሚባለው እውነት ነው?››

‹‹እንዴታ!››

‹‹ከቶ ምን ቢያደርግህ ከኸለቀህ ተጣላህ?››

‹‹የኸለቀ አካላቴን በሞላ በእሳት ጎረብ ቢመታኝ››

‹‹አዲያ አሁን ጠብ ነህ እርቅ?››

‹‹እርቅ። ተርቅም ሽርክ!››

………… እያለ ይቀጥላል። የገጠር ሰዎች ወግና ጨዋታ ሲያደምቁ በፈጣሪ ላይ ሳይቀር በመቀለድ ነው። ለምሳሌ፤ በክረምት ዝናብ ሳይዘንብ ዋል እደር ካለ ‹‹አንተዬ ይሄ እግዜሃር ክረምት መሆኑን ረሳው እንዴ?›› ብሎ ይጠይቃል አንዱ ገበሬ። ‹‹ምን አንተ ዴሞ እንዴት አይረሳው! አረጄ እኮ!›› እያለ ይመልሳል ሌላኛው። በዚህ ልክ ቀለል ብሏቸው መቃለዳቸው ያስፈራኝ ነበር።

ሸሙኔ መጽሐፍ እንዲህ የረሳናቸውን ወጎች ያስታውሳል። የማህበረሰብን ቱባ ምንነት ይነግረናል።

መጽሐፉ ምናልባት ለከተማ አደግ ሰዎች ግን የሚያስቸግር ይመስለኛል። ቀደም ሲል እንዳልኩት የቃላቱን ትርጉም ለማወቅ ዓውዱ ስለሚነግረን አያስቸግርም። አንዳንድ ቦታ ግን ሙሉ ዓረፍተ ነገሩ አዲስ ሊሆንባቸው ይችላል ብዬ የምፈራው አለ። በእርግጥ የስነ ጽሑፍ ውበቱም ይሄው ነው። የሆነ ነገር ፍለጋ አዕምሮን ማሰራት።

ሸሙኔ የንግግር ቃላትን ስለሚጠቀም አንዳንድ ሰዎች ያስቸግራቸው ይሆን? እያልኩ እፈራለሁ። ወይም ደግሞ ‹‹ይሄን ካላወቁት ቀረባቸው!›› እያልኩ እቆጫለሁ። እኔ ሳነበው ዜማውን ጭምር እያስታወስኩ ነው። በዚያ ቃል የተናገረ የሆነ የአካባቢያችን ሰውዬ ይመጣብኛል። ዓረፍተ ነገሩን የማነበው በዚያ ሰውዬ ዜማ ነው። ለምሳሌ፤ አንድ ቦታ ላይ ‹‹ከዚያ ምን ትመጣለች? እብድ። ›› የሚል አገላለጽ አግኝቼ ‹‹በዚህ እኔ በማውቀው ዜማ ያነቡት ይሆን?›› ብዬ አስቤያለሁ። ዜማ እኮ አይደለም! ምን ልበለው? ብቻ የሆነ የራሱ ቃና ያለው አነጋገር አለ። መልሱን የሚመልሰው ራሱ ጠያቂው ነው። እንዲህ አይነት ወጎችን አምቆ የያዘ ነው።

በከተማ ቦታ ቀልድ አዋቂ ሰው ካለ መተዳደሪያው ነው። ነገር አዋቂ፣ መልስ የሚዋጣላቸው ሰዎች፣ አገላለጻቸው አስቂኝ የሆነ… ሰዎች ብርቅ ስለሚሆኑ ነው መሰለኝ ይደነቅላቸዋል። በሀገር መሪ ደረጃ ሳይቀር (ለምሳሌ አቶ መለስ ዜናዊ) የሚናገሩት መልስ አስቂኝ ስለሚሆን በማህበራዊ ገጾች ለቀልድ ተብሎ ይዘዋወራል። ገጠር ውስጥ ግን ብዙ እንዲህ አይነት ሰዎች አሉ። ወግና ጨዋታ ወዲህ ደግሞ አሽሙር ይችሉበታል። በነገር ወጋ ያደርጋሉ። ሸሙኔ የእነዚህን ሰዎች አሽሙር ሁሉ ሳይቀር ነው የነገረን። ለምሳሌ፤ ስብሰባ ውስጥ ካድሬው በድምጽ ማጉያ (ማይክራፎን) ሲናገር አንዷ ተሰብሳቢ ከጎኗ ላሉ ሰዎች ‹‹አፉ አንሶን ደግሞ ድምጽ ማጉያ ጨመረበት!›› ትላለች። ይህን አሽሙር የተናገረችው ምናልባትም የካድሬው ድምጽ ከሌሎች የበለጠ ትልቅ ሆኖ ሳይሆን፤ ንግግሩ ውሸት እና አሰልቺ ስለሚሆን እንደ ጩኸት ስለሚያዩት ነው። መስማት ስለማይፈልጉ ነው። እንዲህ አይነት አሽሙረኞችም ናቸው።

ስብሰባ ላይ ማጨብጨብ የተለመደ ነው። የሸሙኔ ወገኞች ግን ይህ አዲስ ሆኖባቸዋል። እነርሱ ጭብጨባን የሚያውቁት ለዘፈን ወይም ለመዝሙር ነው። ለዚህም ነው ‹‹አጨብጭቡ›› ሲባሉ ‹‹እኛ ያለዘፈን ጭብጨባን የምናውቀው ለእርግማን ነው›› ያሉት። ስብሰባ እርግማን ነው እያሉ ይሆን? የሸሙኔ ሰዎች አሽሙረኛ ስለሆኑ ማን ያውቃል!

ሸሙኔ ታሪክም ነው። የቋንቋ ታሪክ። ዘመን የየራሱ ባህሪ አለው። የየራሱ ቀለም አለው። ይህን ግን በጽሑፍ ውስጥ አናገኘውም። ምክንያቱም በብዛት የሚጻፈው የተማረ የሚባለው የህብረተሰብ ክፍል በሚኖርበት ከተማ ውስጥ ያለው ሁነት ነው። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ገላጭ ቃላት ባክነው ቀርተዋል። ‹‹ቀንኛ›› የሚለውን ቃል ሸሙኔ ውስጥ ሳገኘው፤ ‹‹ይሄ ነገር ግን ለምን በሀገር አቀፉ አማርኛ ውስጥ አልታወቀም?›› አልኩ። ቀንኛ ማለት ቀን የሚበላ (ምሳ) ማለት ነው። በእኛ አካባቢ ቁርስ የሚባል ቃል አይታወቅም። ቁርስን ተክቶ የሚያገለግለው ቃል ምሳ ነው። በአጭሩ፤ በጠዋት የሚበላው ምሳ፣ ቀን የሚበላው ቀንኛ የሚባል ሲሆን ማታ የሚበላው ግን በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚታወቅበት ስም እራት ይባላል። ቀንኛን እንዳይታወቅ እና አካባቢያዊ ዘዬ ብቻ ሆኖ እንዲቀር ያደረገው የተጻፈላቸውና የተነገረላቸው ሌሎች ስለሆኑ ነው። ቋንቋ ደግሞ ማህበረሰባዊ ስምምነት ስለሆነ በብዛት በሚነገረው ነው። ሸሙኔ ግን በራሳቸው በገጸ ባህሪያቱ አካባቢያዊ ቃላት ስለሚነግረን የቋንቋ ጥናት ታሪክም ይሆናል።

አንድ ግራ የገባኝ አገላለጽ ግን አለ። የአክብሮት ስም (አንቱታ) ሲጠቀም ‹‹እርሳቸው›› መሆን የሚገባውን ‹‹እርስዎ›› በሚል ይገልጸዋል። ለምሳሌ፤ ‹‹ገበያ የዋሉም አይመስሉ አያ ጉልላት›› አልኩዎ እንደደረስኩብዎ (ገጽ 112)። ›› ይላል። ከዓውዱ መረዳት እንደሚቻለው ለማለት የተፈለገው ‹‹አልኳቸው እንደደረስኩባቸው›› ነው። ‹‹አልኩዎ፣ እንደደረስኩብዎ›› ሲል ለራሱ ለባለቤቱ የሚናገር ይመስላል። እየነገረን ያለው ግን ለእኛ ለተደራሲያን ነው።

ትረካው በአንደኛ መደብ ስለሆነና ራሱ ሸሙኔ ስለሚተርከው የሸሙኔ ዘዬ ይሆን? ምናልባት በዚያ አካባቢ ያሉ ሰዎች የአክብሮት ስም የሚጠቀሙት በዚሁ አገላለጽ ሆኖ ይሆን? እንዲያ ሊሆን ይችላል ብዬ አሰብኩ።

ምንም እንኳን በዓውድ መረዳት ቢቻልም ለአንዳንድ ቃላት ግን የግርጌ ማስታወሻ ቢኖራቸው ጥሩ ነበር። ለስነ ጽሑፋዊ ውበት ጥሩ ላይሆን ይችላል። ስነ ጽሑፍ ማብራሪያና ገለጻ ሲበዛበት ጥሩ አይደለም ይባላል፤ ዳሩ ግን አንዳንድ ነገሮችን ግልጽ ለማድረግ በቅንፍ ውስጥ ይጠቀማል። ስለዚህ የመፍቻ ቃላት ቢኖሩ ጥሩ ነበር።

መጽሐፉ ከስነ ጽሑፍነት ባሻገር የባህልና የቋንቋ ጥናት የሚያደርጉ ሰዎች ሊያነቡት የሚገባ ነውና አንብቡት!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 9 /2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

 

 

 

Recommended For You