አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል በ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ባለ 38 ወለል ህንፃ ግንባታ መጀመሩን አስታወቀ።
የተቋሙ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን፤ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት ግንባታው መካሄድ የጀመረው ሜክሲኮ በሚገኘው የድሮው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ቦታ ላይ ሲሆን፤ ባለ 38 ወለልና 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሚወስድ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ተቋሙ የቢሮ ህንፃ ለመገንባት ረጅም የዝግጅት ጊዜ አድርጓል። ህንፃውን ለመገንባት የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ ነበር። ኤም ኤች ኢንጅነሪንግ ከተባለ ድርጅት ጋር ውል በመግባት የዲዛይን ሥራዎች አዘጋጅቷል።
ዲዛይኑ ከተዘጋጀ በኋላም ተቋሙ ካሉት የሚክሲኮና የኮተቤ ቦታዎች በየትኛው ቦታ ይገንባ የሚለው መረጣ ተካሂዷል። ከማዕከላዊነቱና የቦታው ምቹነት ተጠንቶ በሜክሲኮ እንዲካሄድ ተመርጧል።
ዲዛይኑ ከተሠራና ግንባታው የሚካሄድበት ቦታ ከተለየ በኋላ በተካሄደው ጨረታ ከ20 በላይ ተቋራጮች ተሳትፈው ሲ.ጂ.ሲ.ኦ. የተባለ የቻይና ተቋራጭ በ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ያሸነፈ ሲሆን፤ ከተቋራጩ ጋር በተደረገው ስምምነት ግንባታው በሦስት ዓመት የሚጠናቀቅ፣ ከመሬት በታች 4 ከመሬት በላይ 34 ፎቅ ያለው ፣ በአጠቃላይ 38 ወለሎች ያሉት ህንፃ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ግንባታው ሲጠናቀቅ በኪራይና በእራሱ ቢሮ በተለያየ ቦታ ተበትነው ያሉ የማዕከሉ ሠራተኞችን በመሰባሰብ ሁሉንም አገልግሎቶቹን በአንድ ቦታ ለመስጠት ያስችላል። ለደንበኞቹ የሚሰጠውን አገልግሎት በማቀላጠፍ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
የተቋሙ ዋና መሥሪያ ቤት በወር 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር እየከፈለ በኪራይ የሚኖር ሲሆን፤ ተቋሙ በአሁኑ ወቅት በሃያ ማመንጫዎች፣ ከ190 በላይ ማከፋፈያና በማዕከል ከ5ሺ በላይ ሠራተኞች አሉት።
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2011
አጎናፍር ገዛኸኝ