አዲስ አበባ፡- በአሜሪካ አገር የሚኖሩና በማህበራዊ ሚዲያ ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት የጥላቻ ንግግር የሚያሰራጩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት አስታወቀ።
የምክር ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ተጠሪ አቶ አምሳሉ ፀጋዬ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት መረጃ፣ ምክር ቤቱ በአሜሪካና በመላው ዓለም የኢትዮጵያ የዜጎች መብትና ጥቅም መከበር የሚንቀሳቀስና ህጋዊ ዕውቅና ያለው ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም HR-128 የተሰኘውን የውሣኔ ሐሳብ በአሜሪካ ኮንግረስ እንዲፀድቅ መሥራታቸውን አስታውሰው፣ አሁን በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ በመደገፍና ቀጣይነቱ እንዲረጋገጥ እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ለረጅም ዓመታት ሲታገሉለት የቆዩት ለውጥ በአገሪቱ በመምጣቱ ሁሉም የምክር ቤቱ አባላት ደስተኛ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ አምሳሉ፣ ህዝቡ ነገሮችን በጥሞና በማየት ለሰላምና መረጋጋት በጋራ ሊሠራ ይገባል ያሉ ሲሆን፣ አሁን በውጭ አገር ተቀምጠው በማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻና የመከፋፈል መልዕክቶችን የሚያሰራጩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ በአሜሪካ መጀመሩን ገልፀዋል።
በውጭ አገራት የተደላደለ ኑሮ እየኖሩ አገር ውስጥ ያለውን ድሀ ህዝብ ርዕስ በርዕስ ለማጋጨት የሚሠሩ ግለሰቦችን ሙሉ መረጃ በመሰብሰብ በአሜሪካ ሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ምክር ቤቱ ከአሜሪካ ኮንግረስ አባላት እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይቶ ይሁንታ ማግኘቱን የጠቀሱት አቶ አምሳሉ፣ ለዚህም ጠበቃ በማዘጋጀት መረጃዎችን የመሰብሰብ ሥራ መጀመሩን ጠቅሰዋል።
በአሜሪካ በነፃነት የመናገር መብት ቢኖርም ጥላቻ፣ ጥቃትና መከፋፈል በሌላ አገር እንዲፈፀም የሚያደርጉ ነዋሪዎችን በሕግ ተጠያቂ ማድረግ የሚቻልበት አሠራር መኖሩን የጠቆሙት የህዝብ ግንኙነት ተጠሪው፣ ብሔር ተኮር ግጭት እንዲቀሰቀስና በጥላቻ ንግግር የተጠመዱ ግለሰቦችን የኢትዮጵያ መንግሥት በሕግ ለመጠየቅ ስለማይችል ምክር ቤቱ ከዚህ እኩይ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ፣ የአሜሪካ ሕግ በሚፈቅደው መሰረት ተጠያቂ በማድረግ ተገቢውን ቅጣት እንዲቀበሉ ብሎም ሌሎች እንዲማሩበት ሥራውን መጀመሩን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር ባህልን የሚሸረሽር ተግባር በማህበራዊ ሚዲያ የሚያሰራጩት እነዚህ ግለሰቦች በሚኖሩበት አገርም ተጠያቂ ማድረግ እንደሚቻል ማሳየት ተገቢ ነው ያሉት አቶ አምሳሉ፣ አሁን የተጀመረው እንቅስቃሴ በአሜሪካ ሕገ መንግሥት በቀጥታ የተቀመጠ ሕግ ባይኖረውም መሰል ድርጊቶችን ለመቆጣጠር በየጊዜው የሚወጡ ደጋፊ ሕጎች ውስጥ የተካተተ በመሆኑ ግለሰቦችን ሕግ ፊት ማቅረብ እንደሚቻል አረጋግጠዋል።
በአሜሪካ ዜግነት ወይም የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ግለሰቦች በሌላ አገር ጉዳይ በመግባት ብሔርን ከብሔር የማጋጨት፣ የጥላቻ መልዕክቶችን የማስተላለፍና መሰል ተግባራትን እንዲፈፅሙ የአገሪቱ ሕግ አይፈቅድም ያሉት ተጠሪው፣ የምክር ቤቱ አባላት የአገራችን ጉዳይ ስለሚያሳስበንና ለውጡ ህዝቦችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው ብለን ስለምናምን እኩይ ተግባሩን ለማስቆምና ቅጣት ማግኘት ያለባቸውን ቅጣታቸውን እንዲቀበሉ ለማድረግ እየሠራን ነው ብለዋል።
በለውጥ ጎዳና ላይ ላለችው አገራችን እና ህዝቦቿ ሞትና ጥይትን የሚሰብኩ እነዚህ ግለሰቦች በሚኖሩበት የሰለጠነ አገር ልክ እያሰቡ ነው ብለን አናምንም ያሉት አቶ አምሳሉ፣ ግድያና ሞትን በሚያውጁ ግለሰቦች እንደ ወንጀሉ ክብደትና ቅለት በአሜሪካ አገር ተጠያቂ ከማድረግ ጀምሮ ከአገሪቱ ለቀው እንዲወጡ እስከማድረግ የሚያደርስ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው አረጋግጠዋል።
ምክር ቤቱ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው የገለፁት አቶ አምሳሉ፣ ትክክለኛና የሀሰት አድራሻዎችን በመለየት ግለሰቦቹን ተጠያቂ ለማድረግ መሰል እኩይ ተግባራት ላይ የተሰማሩና በአሜሪካ የሚኖሩ ግለሰቦችን የማህበራዊ ሚዲያ አድራሻ በteamusalegal@gmail.com በመላክ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ከትናንት በስቲያ የመንግሥታቸውን የ2011 ዓ.ም ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት በሌሎች አለማት የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በማህበራዊ ሚዲያ እየተሰራጨ ያለው የጥላቻና የጥፋት ዘመቻን ኮንነው ለመቆጣጠር መቸገራቸውን በመግለፅ “ የእውነት አምላክ ይፍረድባችሁ” ማለታቸው የሚታወስ ነው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2011
በድልነሳ ምንውየለት