ኢትዮጵያ ከ1956ቱ የሜልቦርን ኦሊምፒክ ጀምሮ እስካሁኑ ፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ ድረስ 15 ጊዜ በታላቁ መድረክ ተሳትፋለች፡፡ ከመጀመሪያ ተሳትፎዋ ሜልቦርን ኦሊምፒክ በስተቀር በ14ቱም የኦሊምፒክ ተሳትፎዋ ካለ ሜዳሊያ ተመልሳ አታውቅም፡፡ በዚህም 24 ወርቅ፣ 14 ብር እና 24 የነሐስ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ በዓለም መድረክ ደማቅ ታሪክ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ተሰልፋ እናገኛታለን፡፡
በዚህ ዘመናትን በዘለቀው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ተሳትፎ ከታሪካዊው አትሌት አበበ ቢቂላ የሮም ኦሊምፒክ የማራቶን የባዶ እግር ገድል አንስቶ እስካሁኑ ጀግና አትሌት ታምራት ቶላ የፓሪስ ኦሊምፒክ የማራቶን ድል ድረስ እልፍ ጀግኖች በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያን ስም በወርቅ ቀለም ፅፈዋል፡፡
ከእንቁ አትሌቶቻችን ውጤት ይልቅ ከስፖርቱ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር የሚነሱ ውዝግቦች ገንነው በታዩበት በዘንድሮው የፓሪስ 2024 ኦሊምፒክም አንድ ወርቅ በወንዶች ማራቶን እና ሦስት ብር በሴቶች ማራቶንና 800 ሜትር እንዲሁም በወንዶች 10 ሺህ ሜትር ሜዳሊያ ተመዝግቧል፡፡ አትሌቶቻችን በተሳተፉበት ውድድር ሁሉ ለሀገር የሚገባውን ተጋድሎ ፈጽመዋል፤ ለዚህም ሀገራዊ ምስጋናና ክብር ይገባቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን የፓሪስ ኦሊምፒክ ውጤት የኢትዮጵያ አትሌቲክስና ኦሊምፒክ መታመሙ የታየበት ሆናል፡፡
ከሳይንስ የተፋታና ተለምዷዊ የሆነ የአትሌቶች ምልመላ፣ መረጣና ሥልጠና ብዙ ርቀት እንደማይወስደን ከፓሪስ የኦሊምፒክ ውጤት በላይ ሊያስተምረን የሚችል አጋጣሚ የለም፡፡ በፍጹም ከሳይንስ ጋር የማይተዋወቅና ዘመኑን የማይመጥን የአሠለጣጠን ዘዴን መከተላችን ለውጤት መጥፋት ሌላኛው ምክንያት መሆኑን በርካታ ዘርፉ ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው።
ለዚህ ማሳያው ደግሞ አትሌቶቻችን በታላቁ የኦሊምፒክ መድረክ ያሳዩት የአሯሯጥ ቴክኒክና ታክቲክ እንዲሁም የብቃት ደረጃ ነው። ተፈጥሯዊ አቅም ያላቸውን አትሌቶች ተቀብለን በምንከተለው ኋላ ቀር የምልመላ፣ መረጣና አሠለጣጠን ዘዴም ልንፈትሸው የሚገባ ጉዳይ ነው። ወቅቱን የሚመጥንና ወደ ሳይንሱ የሚያስጠጋን ስር ነቀል ለውጥ ያስፈልገናል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ የውጤትም ሆነ የአስተዳደር ድክመት አደባባይ ላይ ተሰጥቷል:: የኦሊምፒክ ውጤታችን ማሽቆልቆል የጀመረው ግን አሁን አይደለም፡፡ ከሦስት ኦሊምፒኮች አስቀድሞ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮች ተንከባለው አሁን ላይ ለታየው ቀውስ ዳርገውናል፡፡ ይህም የቀጣዩን ኦሊምፒክ ጉዟችንን ስጋት ውስጥ የከተተ አፋጣኝ መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡
ብርቅዬ አትሌቶቻችን አቅሙና ብቃቱ እያላቸው ውዝግብና ጭቅጭቅ በማያጣው አስተዳደራዊ እንቅፋት ተሸብበው የእኛ የሆኑ በርካታ ወርቆች ከእጃችን ወጥተዋል፡፡ እነዚህ ችግሮች በቀጣይ ኦሊምፒኮች እንዳይደገሙና ወደ ላቀ ውጤታማነታችን ለመመለስ አፋጣኝ መፍትሔ ማበጀት ለነገ የምንተወው የቤት ሥራ አይደለም፡፡ ለዚህም በዋናነት ከስፖርቱ አስተዳደራዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ብዙ ጉዳዮችን ፈትሾ ፈር ማስያዝ ያለብን አሁን ላይ ነው፡፡
በግለሰቦች ላይ ጣት ከመጠቆም ወጥተን ኢትዮጵያ በቀጣይ ወደ ተለመደው ውጤታማነት መመለስ የምትችልባቸው መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ተገቢ ነው፡፡ ስፖርቱን በሚመሩ ግለሰቦች መለዋወጥ ሳይሆን በሥርዓት የሚመራ አስተሳሰብ መገንባት ያስፈልጋል፡፡
መንግሥት፣ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ክለቦች፣ ማናጀሮች፣ አሠልጣኞች፣ አትሌቶች፣ ምሑራን፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጋራ ለለውጥ መሥራት አለባቸው፡፡ የዚህ ችግር ዋነኛ ተዋንያንም ተጠያቂ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡
በተለይም በኦሊምፒክ ኮሚቴና በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስር ነቀል ለውጥ የግድ ነው፡፡ እየታዩ የሚገኙ አስተዳደራዊ ችግሮች ጥቂት ጀግኖች አትሌቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች በሚያስመዘግቧቸው ድሎች ተሸፋፍነው ማለፍ የለባቸውም፡፡ የነበሩንንና ያሉንን አትሌቶች አቅምና ክብር የሚመጥን ግልጽና ዘመኑን የዋጀ አሠራር መኖር አለበት፡፡
ተጠያቂነት በመጥፋቱ ኢትዮጵያ የምትታወቅባቸውን የአትሌቲክስ ውጤቶች እየተቀማች መቀጠል የለባትም፡፡ ኦሊምፒክ በመጣ ቁጥር ትርምስ የሚፈጥሩም ሆነ በሀገር ውጤት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዲፈጠር የሚተጉ ግለሰቦችም ይሁኑ ቡድኖች እየቆመሩ ያሉት በሀገር ጥቅም እና ገጽታ ላይ መሆኑን ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል፡፡
በስፖርቱ ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ አመራሮችም ሆኑ ባለሙያዎች ከሴረኝነት እና ከጥቅማ ጥቅም አነፍናፊነት እንዲሁም ከሀሜትና አሉባልታ ወጥተው የመርሕ ሰው መሆን አለባቸው፡፡ ካለፈው ስህተት ተምረን ስፖርቱ እውቀት፣ ክሒሎት፣ ሥነ-ምግባርና ኃላፊነት ባላቸው ሰዎች እንዲመራ ማድረግም ግድ ነው!
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም