አዲስ አበባ፡-
የጀነራል አብርሃ ወልደማ ርያም (ኳርተር) የቀብር ስነ ሰርዓት ትናንት ከሰዓት በኋላ በመቐለ ከተማ እንዳ ገብርኤል ቤተክርስትያን ቤተሰቦቻቸው፣ የክልል እና የፌዴራል መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ተፈጽሟል።
ጀኔራል አብርሃ በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን በእንዳባፃህማ ወረዳ እንዲጪዋ ቀበሌ ነሐሴ 21 ቀን 1953 ዓ.ም የተወለዱ ሲሆን፣ በትጥቅ ትግሉ ወቅት ከተራ ተዋጊነት እስከ ክፍለጦር አዛዥነት ድረስ በተለያዩ ውጊያዎች ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡
ጄኔራሉ በ1983 ዓ.ም በመደበኛ የሠራዊት ግንባታ ከተጣለባቸው ኃላፊነት ጊዜ ጀምሮ በጡረታ እስከ ተሰናበቱበት ሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል፡፡
ጄኔራል አብርሃ ከሀገር ውስጥ ግዳጅና ተልዕኮ በተጨማሪ በሩዋንዳ ዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተልዕኮም የመጀመሪያውን የጉና ሻለቃ በምክትል አዛዥነት በመምራት የተሰጣቸውን ተልዕኮ በፍፁም ህዝባዊ መንፈስ ተወጥተዋል፡፡
ጀኔራል አብርሃ ወልደማርያም በጠና ታመው በታይላንድ ባንኮክ በሚገኝ ዓለም አቀፍ ሆስፒታል ህክምና ሲከታተሉ ቢቆዩም ሰኔ 21 ቀን 2011 ዓ.ም ህይወታቸው አልፏል።
የጄነራል አብርሃ አስከሬን ሰኔ 23/2011 ዓ.ም አዲስ አበባ ሲገባ ቤተሰቦቻቸው፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና ወታደራዊ ባለስልጣናት በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው አቀባበል አድርገዋል። ወደ መቐለም ሸኝተዋል፡፡
በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ የክልሉን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤልን ጨምሮ የክልሉ እና የፌዴራል መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ወዳጅ ዘመዶቻቸው የተገኙ ሲሆን ለክብራቸውም 15 ጊዜ መድፍ ተተኩሷል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ ዶክተር ደብረጽዮን “ጀነራል አብርሃ ለህዝብ ክብር ያበረከተና የማይደበዝዝ ታሪክ የሰራ የጦር መሪ ነበር” በማለት ምስክርነት ሰጥተዋል። “ከመስዋእት መሸሽ ሳይሆን መስእዋት እስኪመጣ ድረስ ለህዝብ አገልግለህ መሞት ክብር ነው” ያሉት ዶክተር ደብረፅዮን “ጄኔራል አብርሃ ለዚሁ ተምሳሌት ተጠቃሽ ነው” ብለዋል።
የትጥቅ ትግሉ ካፈራቸው ኢትዮጵያዊ ምርጥ ጄኔራሎች አንዱ ስለመሆናቸው ምስክርነታቸውን ሰጥተው በተሳተፉባቸው አውደ ውጊያዎች ሁሉ ታሪክ ከመስራት ባለፈ ሃገሪቱ ሰላሟን አስጠብቃ ሕዳሴዋን እንድታስቀጥል ከፍተኛ ድርሻ ያበረከቱ ታጋይ እንደነበሩም ተናግረዋል።
በተወለዱ በ58 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ጀነራል አብርሃ ባለትዳርና የሁለት ወንድና የሁለት ሴት ልጆች አባት ነበሩ፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/2011
በድልነሳ ምንውየለት