”የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ላይ ስር ነቀል ለውጥ እንደሚያመጣ ይጠበቃል‘ ኢንጂነር ግርማ ሀብተማሪያም የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ፕሬዚዳንት

አዲስ አበባ፦ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ላይ ስር ነቀል ለወጥ እንደሚያመጣ የሚጠበቅ መሆኑን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ግርማ ሀብተማሪያም ገለጹ። የሀገር ውስጥ ተቋራጮች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አቅም በሚያሳድግ መልኩም በጥናት የተደገፈ ድጋፍ እንደሚያሻውም አመላክተዋል።

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ግርማ ሀብተማሪያም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በዘርፉ ቀደም ሲል ያጋጥሙ የነበረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር የሚቀርፍ ነው። ይህም የኮንስትራክሽን ዘርፉ በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የግንባታ እቃዎችን በቀላሉ እንዲያገኝ ያስችለዋል።

ማሻሻያው የኮንስትራክሽን ግብዓት አስመጪ ድርጅቶች ከባንኮች በቀላሉ የውጭ ምንዛሪ የሚያገኙበትን ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸው። ይህም በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት እስካሁን ይታይ የነበረውን የኮንስትራክሽን ግብዓት ችግርን ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

“የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ባለድርሻ እንደመሆናችን ማሻሻያው በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ እንዲሆን ከፍ ያለ ፍላጎት አለን ያሉት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት፣ ማሻሻያው በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት የቆሙ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁ ለማድረግም ትልቅ አስተዋፅዖ ይኖረዋል ብለዋል።

የግንባታውን ዘርፍ ከባሕላዊ እና ከልማዳዊ አሠራር ወደ ቴክኖሎጂ ማሳደግ እንደሚያስፈልግም ጠቅሰው፣ በዚህ በኩል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አስታውቀዋል።

የሀገር ውስጥ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪ ሆኖ ከሀገር አልፎ ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም የመሄድ ፍላጎት እንዳለው ጠቅሰው፣ ማሻሻያው በዚህ ረገድም ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ገልጸዋል። ማሻሻያው ተከትሎ በገበያው ላይ ቀደም ብለው የገቡ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችና መሣሪያዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ ከፍተኛ ቁጥጥር እና ክትትል መደረግ እንዳለበት አመላክተዋል።

ማሻሻያው በአተገባበር ብዙ ፈተናዎች ሊያጋጥሙት ይችላሉ ሲሉም ስጋታቸውን ጠቁመው፣ በዚህ ዓይነት አሠራር ለጉዳት የተዳረጉ ሀገሮች ዓይነት ችግር እንዳያጋጥመን በትግበራው ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች ሥራ በጥራት አይጨርሱም፤ የውጭዎቹ በጥራት ይጨርሳሉ” ሲባል እንደሚሰማም ጠቅሰው፣ በቂ ድጋፍ ከተደረገላቸው የኢትዮጵያ ተቋራጮችም የውጭዎቹ የሚሠሩትን ለመሥራት የሚያስችል አቅም እንዳላቸው ገልጸዋል። በቅርቡም አንዳንድ ሥራ ተቋራጮች የውጭ ሥራ ተቋራጮች ከሚሠራቸው ጥራት በላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሠርተው ያስረከቡበት ሁኔታ መኖሩንም ጠቅሰዋል።

ፕሬዚዳንቱ እንዳብራሩት የሀገር ውስጥ ሥራ ተቋራጭ ተወዳዳሪ ሆኖ ወደ ውጭ ለመውጣት በመጀመሪያ ደረጃ ሀገር ውስጥ ያለውን ገበያ ማሸነፍ እና ራሱን ማብቃት ያስፈልጋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 7/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You