አዲስ አበባ፡- በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዋናው ግድብ ኮንክሪት ሙሊት ሥራ ከቀጣዩ መስከረም ወር በኋላ እንደሚጀመርና ከሜቴክ ሥራውን የተቀበሉ አምስቱ ኩባያዎች ወደሥራ መግባታቸውን የግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ገለፁ፡፡
ሥራ አስኪያጁ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት ከዋናው ግድብ የኮንክሪት ሙሌት ሥራ በስተቀር በኃይል ማመንጫ ጣቢያ ውስጥ ያልተቋረጠ ከፍተኛ የሥራ እንቅስቃሴ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ከዋናው ግድብ ጋር ተያይዞ ግን መተከል ያለባቸው ብረታ ብረቶች ስላሉ እነሱ ከተተከሉ ከመስከረም ወር በኋላ የግድብ ሙሌቱ ሥራ የሚካሄድ ይሆናል፡፡
እንደ ኢንጂነር ክፍሌ ገለፃ፤በአሁኑ ውቅት አምስት ኩባንያዎች ሥራውን ከብኢኮ ወስደው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ኩባንያዎቹ በግድቡ ላይ የየራሳቸውን ሥራ እየሰሩ ሲሆን፣የመጀመሪያው ከቦቶም አውትሌት (የውሃ ማስለቀቂያ) እና ከመጀመሪያዎቹ ሁለት ዩኒቶች ጋር እንዲሁም ከካለበርት ጋር የተገናኘ የብረታ ብረት ሥራ የሚሰራ ኩባንያ ነው፡፡ ይህ ኩባንያ በአሁኑ ወቅት እዛው በመስክ ላይ አንደኛ ለውሃ ማስተላለፊያ አሸንዳ በሜቴክ የተሰራውን ጥገና እያደረገ የጥራት ችግር ያለበትን ቦታ እንደገና እየሰራ ተከላ ጀምሯል፡፡
ከቦቶም አውትሌት ጋር በተገናኘ ያለውን የጥራት ጉድለት ለማስተካከልም የቀድሞው እንዳለ ተነስቶ አሁን እሱን ሊተካ የሚችል ብረት ተገዝቶ ወደ ዎርክሾፕ የደረሰ ሲሆን፣መስከረም አካባቢ ወደአገር ቤት ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢንጂነሩ ገልፀዋል፡፡ የትራንስፖርቱ ሂደት በራሱ አንድ ሁለት ወር ያህል ጊዜ እንደሚፈጅም አስረድተዋል፡፡
‹‹እነዚህ ብረታብረቶች እንዲሁ ከገበያ የሚገዙ አይደሉም፡፡››ሲሉ ጠቅሰው፤ ‹‹በተባለው አይነት ተመርተው በሰኔ ወር ውስጥ ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ መጓጓዝ እንደሚጀምሩ አብራርተዋል፡፡ ስለዚህ የቦተም አውትሌቱ ተከላ ከመጪው መስከረም አጋማሽ አንስቶ ይጀመራል፡፡
በውሃ ማቀባበያ አሸንዳዎች ላይ የቀድሞው ተቋራጭ ብኢኮ የሰራው ጉድለት ያለበት ሆኖ መገኘቱን ጠቅሰው፣ አሸንዳዎቹ እየተስተካከሉ መተከል መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
ኢንጂነሩ ሁለተኛው ኩባንያ ደግሞ የጄነሬተሮችን ሥራ የሚሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣የተርባይንና ጀነሬተሮችን አቅርቦትና ተከላ የሚሰራው ለቅድመ ኃይል ማመንጨት መሆኑን ገልጸዋል፡፡የሁለቱ ዩኒቶች ውሃ ወደተርባይኑ አቅጣጫ የሚወስድ ትልቅ የብረት መዋቅር የሆነው ሥራ ተጀምሯል ብለዋል፡፡
ሶስተኛው ኩባንያም ግድቡ ውስጥ መተከል ያለባቸው የብረት ሥራዎች ለመስራት ያስችል ዘንድ መስክ (ሳይት) ላይ ወርክሾፕ እና ካምፕ እየገነባ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ተቋራጩ በአገሩ ቻይና የ11ዩኒቶች የብረታብረት ሥራዎችን እያመረተ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ እሱም መስከረም አጋማሽ ላይ ከቻይና መጥቶ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እንደሚደርስ ጠቁመዋል፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጁ ማብራሪያ፤አራተኛው ኩባንያ ሁለት ኮንትራት የወሰደው ነው፡፡ አንደኛው ባላንስ ኦፍ ፕላንት የሚባለው ሲሆን፤ይህ ማለት ተርባይነሮቹ፣ጀነሬተሮቹና የሚተከሉ ነገሮች ሁሉ የተቀናጁ ሆነው ኃይል ማመንጨት እንዲችሉ እንዲሁም ቁጥጥር የሚያደርግ ነው፡፡በአሁኑ ወቅት የዲዛይን ሥራውን እያጠናቀቀ ነው፡፡ ይህን ሥራ ኢብኮም አልጀመረውም ነበር፡፡
ሁለተኛው ሥራ የተርባይን ጀነሬተር ኮንትራት ሥራ ነው ያሉት ኢንጂነር ክፍሌ፣ በግራ በኩል ያለውን የኃይል ማመንጫ የሚትክሉ እነሱ ናቸው፤በቀኝ በኩል ያለውን ደግሞ የሚተክለው ደግሞ ሌላው ኩባንያ ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ በግድቡ ኃይል ማመንጫ ውስጥ መቀበር ያለባቸውን ሥራዎች ኮንትራክተር አስማርተው እየሰሩ ነው፡፡
ኢንጂነር ክፍሌ እንዳሉት፣ሌላው ሥራ የኃይል ማከፋፈያና ማሰራጫው ጣቢያና የትራንስፎርመር አቅርቦቱ ሲሆን፣ እሱ ደግሞ በአምስተኛው ኩባንያ የሚሰራ ይሆናል፡፡ ይህም በዲዛይን ደረጃ ሲታይ እያጠናቀቀ ነው፡፡ቅድመ ኃይል ማመንጫ ጋር የሚገናኙ ሥራዎችን በአሁኑ ወቅት እየሰራ ነው፡፡
እርሳቸው እንዳሉት፤ከአምስቱ ሁለቱ ኩባንያዎች በቅድሚያ እየሰሩ ያለው በሁለቱ የኃይል ማመንጫ ዩኒቶች ላይ ነው፡፡እነዚህም ሁለቱ ዩኒቶች ኃይል ለማመንጨት የሚወስዱት ጊዜ ቢያንስ ሁለት ዓመት ያህል ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ቀደም ሲል ታሳቢ ተደርጎ የነበረው በሜቴክ ተተክለው የነበሩት የቦቶም አውትሌት ብረቶች በጥገና ተስተካክለው ይሰራሉ ተብሎ ነበር፡፡
አሁን ግን ተጠግኖ መግባት የሚቻልበት ደረጃ ላይ አይደለም ያሉት ሥራ አስኪያጅ ፤ ባለበት ቢተው በግድቡ የወደፊት ቆይታ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል ተብሎ ስለታሰበ ቀደም ሲል በእነሱ የተሰሩት ተነስተው እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ይህ እንደ አንድ ተግዳሮት ሊወሰድ ይችላል፡፡
በእስካሁኑ ሂደት ከግድቡ ሥራ ጋር ተያይዞ የጎል ችግር የሌለ ሲሆን፣ ግድቡ ያለበት ደረጃም 66ነጥብ24 በመቶ ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/2011
አስቴር ኤልያስ