ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ‹‹እውነት ከእኛ ጋር ስለሆነ ማንም አያቆመንም፤የኢትዮጵያ አምላክ የማይተኛና የማያንቀላፋ በመሆኑም አንወድቅም፡፡ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንሥራ፡፡›› ሲሉ ነበር ባለፈው አንድ ዓመት የተከሰቱ ፈተናዎችን በዘረዘሩበት ወቅት የተናገሩት፡፡
ዶክተር ዐብይ፣ ባለፈው አንድ ውስጥ ከተከሰቱ ድርጊቶች መካከል የሰኔ 16ቱ የግድያ ሙከራ፣ ወደ ቤተመንግሥቱ የተደራጁ ወታደሮች መምጣት፣ በምዕራብ ኢትዮጵያ የተፈጠረው ችግር፣ መፈናቀሉ፣ በተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ ማስነሳት እናሌሎችም ፖለቲካዊ ፍላጎት የሆኑና በተቀናጁ የበሬ ወለደ መረጃ አቀባዮች የተፈጠረ ዘመቻ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡
በቅርቡም እንኳን ሊገድሉት ሊቆጡት ያልተገባው ዶክተር አምባቸውን ጨምሮ የማይተኩ አመራርን ማሳጣታቸውንም ይናገራሉ፡፡ ‹‹ይቅርታችንና ደግነታችን ለኢትዮጵያ አንድነት ስለሆነ ነገም ግንባራችንን እንሰጣለን፡፡›› ሲሉ ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ ህልውና የሚመጣ ካለ እስክሪቢቶ ሳይሆን ክላሽ አንግበን እንሠራለን፡፡›› በማለት ነው የተናገሩት፡፡ በግርድፉ ውሸትን እንደማይቀበሉና በውጭ ያሉትና በውሸት አገርን የሚያባሉትን እግዚአብሄር እንደሚፈርድ አመልክተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ የ2011 በጀት ዓመት የመንግሥት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርትና ከምክር ቤቱ ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች መመለሳቸውን በምክር ቤቱ የተከታተሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ባነጋገርንበት ወቅት እንደገለጹት፤ የዕለቱ ንግግር በጣም ጥልቅ ስሜት የታየበትና ትክክለኛ ሆኖ አግኝተውታል፡፡ በተለይም የኢትዮጵያን አንድነትን አስመልክተው ያሰሙት ሁሉም የሚደግፉት ነው፡፡
የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንደሚሉት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የለውጡ አጀንዳ አሁንም መስመሩን ይዞ እንደሚሄድና የአገሪቱ አንድነት አሁንም ቢሆን በምንም ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ የማይገባ እንደሆነ መናገራቸው አስደስቷቸዋል፡፡ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መፍጠሩ ምንም ወደኋላ ሊቀለበስ የማይቻልና የማይገባ እንደሆነ መናገራቸውንም ተቀብለውታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዴሞክራሲን መፍጠር የሚቻለው በተረጋጋ ሁኔታ ማሰብ የሚችል ሰላማዊ ህብረተሰብ ሲኖር እንደሆነና ያንን ማድረግ ደግሞ የመንግሥት ኃላፊነት የሆነውን ያህል ህብረተሰቡም ማገዝ እንዳለበት መናገራቸው አግባብነት ያለው ንግግር መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
‹‹በእርግጥ በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲን ለመፍጠር ብዙ ፈተናዎች እንዳሉ ይታወቃሉ፡፡ እነዚህ ፈተናዎች በተፈጠሩ ቁጥር መደናገጡ ሊኖር ይችላል፡፡ ይሁንና ይህ ረጅም ጉዞ እንደመሆኑ ፈተናዎችን ለመቀነስ መሞከር ክፍያ ማስከተሉ አይቀርም፡፡›› በማለትም ይናገራሉ፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገለጻ፤ ለውጡ ሁሉ ሰው ይዋጥለታል ማለት አይደለም፡፡ በለውጡ ሂደት ደግሞ ችግር አለኝ የሚል ሰው በህጉ መሰረት እንጂ በጉልበት መጠቀም የለበትም፡፡ በጉልበት ሐሳብን መጫን ከተጀመረ የዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ትርጉም የሌለው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸው አግባብነት ያለው ንግግር ነው፡፡ በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ የሐሰት መረጃዎች መሰራጨታቸው ማህበረሰቡም ምን ያህል ሊጎዳ እንደሚችል አፅንዖት መስጠታቸውም ልክ ነው፡፡
‹‹የተጀመረውን ለውጥ ከዳር ማድረስ የሁላችንም ኃላፊነት ነው፡፡ የመንግሥት አሊያም የእነ ዶክተር ዓብይ ኃላፊነት ብቻ አይደለም፡፡ አገሪቱ ለመኖር ዴሞክራሰያዊ ስርዓት ያስፈልጋታል፡፡ በሂደቱም መስማማት አለብን፡፡›› ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፣‹‹ሁላችንም ኃላፊነት ሊኖረን ይገባል፡፡›› ብለዋል፡፡
ህገ መንግሥቱን በሚመለከት የተሰጠው መልስ አግባብነት ያለው መሆኑንም ጠቅሰው፤ በሐሳቡ እርሳቸውም እንደሚስማሙበት ተናግረዋል፡፡ ህገ መንግሥትን ማክበርና ማስከበር የሁሉም ኃላፊነት የመሆኑን ያህል ህገ መንግሥቱ ከጊዜውና ከሁኔታዎች ጋር እየታየ የሚለወጥና የሚሻሻል ቢሆንም፤ ይህ የሚደረገው ግን በጉልበት አለመሆኑንም አመልክተዋል፡፡
መሻሻል ካለበት ደግሞ ሐሳብን ከነምክንያቱ ለህዝብ ማቅረብና በማወያየት እንጂ አንድ አካል ስለሚጠላው ብቻ መሆን እንደሌለበትም አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡ ህገ መንግሥቱ ካልተቀየረ ምንም ዋጋ የለውም ብሎ በደፈናው መናገርም አግባብነት እንደሌለውና ህገ መንግሥቱ ጥሩም ትክክል ያልሆኑ አንቀፆችም እንዳሉትና ማሰብን የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር አምባሳደር መስፍን ቸርነት በበኩላቸው፤ጠቅላይ ሚኒስትሩ በርካታ ጉዳዮችን ማንሳታቸውንና ከእነዚህም መካከል የአገሪቱን ሰላም የተመለከተ ሲሆን በዚህም በትኩረት እየሠሩ ስለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በላይ ግን ሁሉም ዜጋ ለአገሪቱ አንድነት ትኩረት መስጠት እንዳለበትና እርሳቸውም ሥራዎችን ሲሠሩ እንደቆዩ መናገራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያን አንድነት የሚገዳደሩ ብሄርተኝነት፣ ክልላዊነትና አክራሪነት እንዳሉና ይህን በተመለከተ ህዝቡም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች በማስተዋል እንዲንቀሳቀሱ ማስፈለጉንም አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ምንም የማያወላዳ አቋም እንደሌላቸው አበክረው መናገራቸውና የኢትዮጵያን አንድነት ለአደጋ የሚጥል ነገር እስከመጣ ድረስ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን መግለጸቸው የዕለቱ ንግግር ከፍ ያለ መሆኑን እንደተረዱ አብራርተዋል፡፡
በዚህም ሐሳብ ምክር ቤቱ ትልቅ እምነት እንደጣለባቸውና ከጎናቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በተለያየ መልክ የኢትዮጵያን አንድነት የሚፈትኑ ሁኔታዎችን በተመለከተ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የሚያደርጉ ወገኖች ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤የክልል አደረጃት ጥያቄም ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት አቅጣጫ ህገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድና በህዝብ ፍላጎት የክልሉ መንግሥትና ክልል የሚመሩ ፓርቲዎች እንዲሁም ህዝቡንም ባሳተፈ መልኩ የሚሆን እንጂ በችኮላና በጥድፊያ፣ የአገሪቱን አንድነት በሚያናጋ፣ ህዝቦችን ወደ እልቂት በሚያመራ መልኩ መሆን የለብትም ማለታቸው ልክ ከመሆኑም በተጨማሪ ያቀረቡት ንግግር ጠንካራ መሆኑ ነው የሚያምኑት፡፡
በጥቁር አንበሳ የአጥንት እስፔሻሊስት ሐኪም ዶክተር ብሩክ ላምቢሶ እንደሚሉት ደግሞ፤እንደ ሀኪምም ሆነ እንደ ዜጋ የማንም ሰው ህይወት ሲያልፍ ያሳዝናል፡፡ በአጋጣሚ በቅርቡ ከተሰውት መካከል አቶ ምግባሩ ከበደ በሆስፒታሉ ነበሩና ክስተቱ አስደንጋጭ ነበር፡፡ ይህንን ማድረግ ግን ከአንድ ጤናማ ከሆነ አዕምሮ የሚጠበቅ አይደለም፡፡
‹‹ከዓመት በፊት በነበረው የግድያ ሙከራ ላይ ህይወታቸውን ያጡና የቆሰሉ ሰዎችን ስናክም ነበር፡፡ ይህን በተመለከተም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በመገኘት ከጤና ሚኒስሩና ሌሎች ከሚመለከቷቸው አካላት ጋር ልንዘክርም ነበር›› ያሉት ዶክተር ብሩክ፣ይህ ሁሉ ግን በዓመቱ በተፈጠረው ክስተት መጨናገፉንና ይህ በኢትዮጵያውያን ላይ የተቃጣው ጥቃት መቆም እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ በቀጣይ ግን ይህ እንዳይሆን በፅናት መሥራት እንደሚያስፈልግም ያመለክታሉ፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/2011
አስቴር ኤልያስ