ከጋዜጠኛው ጎጆ

ስለ ጻፈው እንጻፍለት…ስላነበበውም እናንብብለት። ህይወት እንደ ጎጆ ናትና ጋዜጠኛውም አንዲት ጎጆ ሠርቶ አቁሞ ነበር:: ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ የህይወት ጎጆ ቢያቆምም፤ የመጣበትን ዓላማ ሳይረዳ ለቀረ “ተወለደ… ኖረናም ሞተ!” ከሚል የግርግዳ ላይ ጥቅስ በስተቀር ምንም አይኖረውም:: በሞተበት ቅጽበትም ደሳሳዋ ጎጆ ትፈርሳለች:: እንደ ሙሉጌታ ሉሌ ያሉትን ግን በዚህ ጎጆ ውስጥ ትተውልን የሚሄዱት ቅርስና ውርስ አላቸው::

ሙሉጌታ ሉሌ ጋዜጠኛም ደራሲም ነበር:: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ እስከ ኢሳት ቴሌቪዥን ድረስ በነበረው ህይወቱ የሠራት ጎጆ አቤት ማማሯ! ግዝፈት ውበቷ! የምታሰኝ ነበረች:: ውስጥና ውጯን ሁሉ በብዕሩ ቀለም አሸብርቋታል:: የብዕሩ ተአምር ብዙ ነው:: ታዲያ ግን ጋዜጠኛው የብዕር መድፍ ተኳሽና አስተኳሽ ነውና እንደ አንድ ሰው ስሙም አንድ አልነበረም:: ከአንዱ ብዕሩ ላይ “ተርቡ”፣ ከሌላኛው ደግሞ “ስንሻው”፣ ወዲህ ይልናም “ስልቁ”፣ ብሎ ብሎም “ጸጋዬ ገብረመድኅን አርአያ” ብሎ አረፈው:: ጉድ ነው እንደገናም ይቀጥላል…

በሙሉጌታ ሉሌ ጎጆ…በዚህች ጎጆ ውስጥ የምናገኘው የመጀመሪያው ነገር ጋዜጠኝነት ነው:: የሀገራችን የጋዜጠኝነት ዕድሜ ሲለካ የሜትር ገመዱም ሆነ ውሀልኩ ጋዜጣ ነው። ምክንያቱም ከጋዜጠኝነት ሁሉ በፊት የነበረው የመጀመሪያ ነገር ጋዜጣ ነውና:: ሙሉጌታም በመጀመሪያ ሥራው በጋዜጣ፣ ስሙም ከጋዜጣ ላይ ነበር:: ከአይረሴዎቹ ባለውለታዎች ከዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ አዲስ ዘመንና ከኢትዮጵያን ሄራልድ እንዲሁም ከመነን መጽሔት ውስጥ ብቅ ብለው ከጎመሩ ፍሬዎች አንዱም ሙሉጌታ ሉሌ ነው። ድምጹ አይሰማም ነበር። ብዕሩ ግን ሞገደኛና መግነጢሳዊ ኃይል ነበረው።

ቱሁትና ታዛዥ ነው፤ ግን ደግሞ እውነትን ከጋረዱበት በብዕሩ የነብርን ቁጣ ያሳያል። በቃላቱ የአንበሳን ብራቅ ጩኸት ያሰማል። በጋዜጠኝነት ላይ የሚጫነውን ቀንበር ለመሸከም አንገቱን አይሰጥም። ልቡን በአሜኬላ እየወጉት እንደምንም ክንዱን አፈርጥሞ በጨበጠው ብዕር ነጻ ፕሬስን፣ የነጻነት ዓለምን ለመሥራት ከመፍጨርጨር አይገታም።

ፊትና ኋላ፣ ግራና ቀኝ ነገሮችን አብጠርጥሮ በማወቅም የሚስተካከለው አነበረም። እርሱም የእውነትን ብርሃን አስፈንጥቆ የጋዜጠኝነት ጮራ ሆኗል። በእርሱ ፈለግ የቆሙ ብዙዎችንም አስከትሏል። በጋዜጠኝነቱ እንደ ጋዜጠኛ፣ በጸሐፊነቱ ብዕር አንጣቢ፣ በታሪክ የታሪክ ሊህቅ፣ በፖለቲካ ዕውቀቱም ወደር አልባ ተንታኝ ነበር። ታዲያ ይኼ ሰው ከወዴትስ ተገኘ?

የባለጎጆው የታሪኩ መነሻና መጀመሪያ፤ ከጀግና አብቃይዋ ከጎጃም ክፍለ ሀገር፣ ከዝነኞች እናት ከቢቸና መንደር ውስጥ ነው። መስከረም 24 ቀን 1933ዓ.ም፤ ከእናቱ ወ/ሮ ወርቅነሽ ጎሹ እና ከአባቱ ሉሌ ደስታ ከዚሁ ተወልዶ ለታላቅ የህይወት ዘመቻ ታጨ። አስኳላን ግን ከዚያ ስፍራ አላገኛትም ነበር። ከልጅነቱ ጋር አብሮ ወደ አምቦ ከተማ አቀና። በአምቦ ከተማ በቀዳማዊ ኃ/ ሥላሴ ትምህርት ቤትም የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ ወጣ። ወጣትነቱን ይዞም ከአምቦ ወደ ደብረ ብርሀን፣ ከቀዳማዊ ኃ/ ሥላሴም ወደ ኃይለማርያም ማሞ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተሸጋገረ።

በዚያም ሁለተኛ ደረጃን ፈጸመው። በ1950ዓ.ም ሙሉጌታ ሉሌ ወደተሠራበት ወደ ሌላኛው ቅጥር ገባ። ወደ ናዝሬት የመጽሐፍ ቅዱስ አዳሪ ትምህርት ቤት ነበር። ህይወትን ሲያነባት፣ ዕውቀትን ሲገነባትና አዋቂነትን ሲላመዳት እዚህ ደርሷል። ቀደም ሲል ተልዕኮውን ፈጽሞ እንደተሰናበታቸው ሦስቶቹ ሁሉ ትምህርቱን ቢጨርስም የናዝሬትን ቅጥር ለቆ አልሄደም።

የተማረውን በተማረበት የማወራረድ ዕድሉን አግኝቶ በመምህርነት በዚያው ቀጠለ። ተማሪው አስተማሪ፣ ተቀባዩም ሰጪ ሆነ። ከብዙ ህይወት ብዙ ዕውቀት በአንዲቷ ጎጆው ውስጥ ሁሉንም በእውን ገልጦ የተመለከታቸው በናዝሬት አካዳሚ ውስጥ በነበረው ቆይታው ስለመሆኑ የራሱም ምስክርነት ነው።

ጋዜጠኛውና ጋዜጠኛነት…አስቀድሞ በ1955ዓ.ም በምስራች ድምጽ ሬዲዮ ጣቢያ ውስጥ በጋዜጠኝነት ቢሠራም የብዕሩን ፍሬ ግን ለጋዜጣና መጽሔቶች ይልክ ነበር:: በጊዜው በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ እየሠሩ የነበሩት እነ ብርሀኑ ዘሪሁንና ጳውሎስ ኞኞም በጽሁፎቹ ተማርከው ያደንቁት ነበርና ተቀላቅሎ ቋሚ ባልደረባቸው እንዲሆን ግብዣ አቀረቡለት:: ሙሉጌታ ሉሌም በ1960ዓ.ም በይፋ አዲስ ዘመንን ተቀላቀለ:: በአማርኛ እየጻፈ ለአዲስ ዘመንና ለሌሎች ጋዜጣና መጽሔቶች፣ በእንግሊዝኛ እየጻፈም ለሄራልድ ያቀብል ነበር:: ወርቃማ ብዕሮቹም እየፈነጠቁ መውጣት መታየት ጀመሩ::

በዚህቹ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ብዕሩን እያነሳ ጓዳ ጎድጓዳዋን አስሶባታል:: በጸሐፊነት ብቻም ሳይሆን በአዘጋጅነትም ሠርቶባታል:: ከታች በአምዶቹ ከላይ በኃላፊነቱ በኩርታ ታይቶባታል:: በጊዜው ጋዜጣ አግኝቶ በእጅ መያዝ ብርቅ ነበር። የሙሉጌታ ሉሌን ጽሑፎች አግኝቶ ማንበቡም ለአንባቢው አስደሳች ነው። “ሙሉጌታ ሉሌ አቀርቅሮ ሲያነብ አሊያም ብዕር ይዞ ሲጽፍ እንጂ ሌላ ነገር ሲያደርግ አይታይም” ይሉታል፤ ቀርበው የተመለከቱት ሁሉ። ስለብዙ ጉዳዮች ያለው አጥልቆ የሚያስቀዝፍ ዕውቀቱ ተንቀሳቃሽ የዓለም መዝገብ አድርጎታል። እንደሚናገሩለትም አንዲት መጽሐፍ ብቻ አንብቦ ስለ አንድ ነገር አወቅኩ አይልም:: ከዚህም ከዚያም ያነባል:: ያውቃል:: በዚህም በዚያም ይጽፋል።

ያስነብባል። በጊዜው ለመረጃም ሆነ ለመዝናናት ሰው ሁሉ የሚጎርፈው ወደ ጋዜጣና መጽሔቶች ነበር። ከእነዚያ ሁሉ ውስጥም የሙሉጌታ ሉሌ ስምና ብዕር ዕለት ዕለት ቢያንስ ከአንዱ ጋር ይወጣል። ዛሬስ ስለምን ጉዳይ ምንስ ብሎ ይሆን ማለቱም ያለ ነው። በመነን መጽሔት ውስጥም አዘጋጅ ሆኖ የግዙፍ ብዕሩን አሻራ ሲያኖር ቆይቷል። እንደገናም በ1968ዓ.ም በግዳጅ ወደ ኤርትራ ተጉዞ “ኢትዮጵያ” በተሰኘችው ሳምንታዊ ጋዜጣ በዋና አዘጋጅነት መምራት ጀመረ:: በዚያው በኤርትራ በተጀመረው የቀይ ኮከብ ዘመቻ ወቅትም በበዓሉ ግርማ ሲመራ የነበረውን የጋዜጠኞችን ቡድን በምክትልነት ሲያቀናጅ ነበር:: ከዚህ በኋላም ትልቁን የሥልጣን ዙፋን ለመረከብ በቃ:: በ1975ዓ.ም ሙሉጌታ ሉሌ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ሆነ::

እያነጻ የሚታነጽበት የጋዜጠኝነት ጎጆው በጋዜጠና መጽሔቶች ላይ ብቻ የታጠረ አልነበረም:: ከዓለም አቀፍና ብሔራዊ የሬዲዮ ጣቢያ የሚነሱ ሞገዶች የእርሱን ድምጽ ተሸክመው ከሕዝቡ ጆሮ አድርሰዋል:: ከምስራች ድምጽ ሬዲዮ ጣቢያ ሆኖ ስለ በርካታ ጉዳዮች በርካታ ዝግጅቶችን አሰናድቷል:: በኢትዮጵያ የቴሌቪዥን መስኮት ውስጥም ላላነሱ ጊዜያት ታይቷል:: በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ኔትዎርክ(ኢትኤን) እንዲሁም በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ(ኢሳት) በመሥራት ሁለገብ ጋዜጠኛ መሆኑን አሳይቷል::

በእያንዳንዱ ቦታና ጊዜም ከእሳት ፍም አመድ ላይ የተቀመጠውን የሀገራችንን ጋዜጠኝነት ነጻ ለማውጣት መድከም አይታክትም ነበር:: ስለ ሁሉም ነገሮች ያለው ዕውቀት ደንደስ ያለ በመሆኑ ከብዙ የሀገራችን ጉምቱ ጋዜጠኞች በዚህ የተለየ ስለመሆኑ ብዙኋኑ ይስማማበታል:: አዕምሮው በሳል፣ እጁ የጠነከረ፣ ብዕሩም ረዥም ነበር:: ከጋዜጣ እስከ መጽሔቶች የማይደርስበት አልነበረም:: ከዚህም ተሻግሮ በ1970ዎቹ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ስር በነበረው በፕሬስ መምሪያ በኃላፊነት የሥልጣን ወንበር ላይ ተቀመጠ::

ሙሉጌታና ሉሌና አብዮቱ…በደርግ መንግሥት የውድቀት ማግስት ሀገር ምድሩ ሁሉ አብዮት ነበር:: የጀበናና ሲኒውም ጨዋታ ሁሉ ስለ አብዮትና አብዮታዊነት ነው:: ጭምምታው ከሹክሹክታው ጋር ይተራመሳል:: እዚያ የሥልጣን ወንበሩ ላይ ቁጭ ብሎ የሚሆነውን ለሚመለከተውና የፖለቲካውን የዝንብ እርጉዝ አበጥሮ ለሚያውቀው ሙሉጌታ ሉሌ ሁሉም ነገር ግልጽ ነበር:: ከ16 ዓመታት በፊት የፈነዳው አብዮት መጥፊያው ደርሶ ነበር:: ነገሩም አልቀረለት የ1966ዓ.ም አብዮት ከስሞ የ1983ዓ.ም ሌላኛው አብዮት ፈነዳ:: ከአብዮት ወደ አብዮት… የተወረወረች ኮከብ እንደ መብረቅ ወርዳ ማጭድ ሰበረች::

የደርግ መንግሥት ገንቦ ወጥቶ የኢህአዴግ ማሰሮ ተተከለ:: ሙሉጌታም ለእርሱ የመጀመሪያው የነበረውን ሸኝቶ ሁለተኛውን አገዛዝ ተቀበለ:: የአንደኛውን ዕጣፈንታ ይዞም ከዙፋኑ አብሮ ወረደ:: በሰዓቱ ብዙ ነገሮች ያልተዋጡለት ሙሉጌታ በ1984ዓ.ም እንዲህ ሆነ…ሙሉጌታ ሉሌ “አጥፍቶ መጥፋት” የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ ጻፈ:: መጽሐፉ የወጣውም በራሱ ስም ሳይሆን ዮሐንስ ሙሉጌታ በተሰኘ በልጁ ስም ነበር:: “ጦቢያ” ከተሰኘው መጽሔት ጋር የተገናኘውም በደርግ ውድቀት ሰልስት ላይ ነበር:: መጽሔቱም ቀደም ሲል ከሙያ አጋሮቹ ጋር ባቋቋመው በአጥቢያ ኮከብ አሳታሚ ድርጅት እየታተመች ትወጣ ነበር::

እርሱም ከዮሐንስ ሙሉጌታ ወደ ጸጋዬ ገብረመድኅን አርአያነት ተለውጦ “ጸጋዬ ገብረመድኅን አርአያ” በሚለው የብዕር ስሙ ሰረገላውን እየጫነ በዳገት ቁልቁለቱ ይገፋው ነበር:: ከምንጊዜውም በላይ ለፕሬስ ነጻነት የታገለውም በዚህ የብዕር ስምና በዚሁ መጽሔት ላይ ነበር:: ሲታገል ታዲያ በደረቅ ፖለቲካና በደረቅ መጅ ሳይሆን ቅኔያዊና ጥበባዊ ዘይት በፈሰሰባቸው በመጣጥፍና ወጎቹ ነበር:: ከዚህም የተነሳ በመጽሔቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በብዙ አንባቢያን ልብ ውስጥም ነገሠ:: በእንዲህ እየቀጠለ በ1980ዎቹ ማገባደጃም ሀገሩን ለቆ ወደ ምድረ አሜሪካን ተሰደደ::

በዚያን ዘመን በሀገራችን ውስጥ በጣት ከሚቆጠሩ ዋቢ ጋዜጠኞች አንዱ ወይንም ግንባር ቀደሙ ሙሉጌታ ሉሌ አይደለም ብሎ የሚሞግት ማን ነው? ጋዜጠኝነት እንደዛሬው ሰፊ በሮች አልነበሩትም። ያሻውን እውነታ ጽፎ ከአሳዳጆች የማምለጫ ምንም ማምለጫም የለውም ነበር። ለምን? እና እንዴት? ብሎ መጠየቅም አይቻልም። የጋዜጠኝነት ሙያውን የሚወድ ግን ግራውን ሲመታ ቀኙን ይሰጣል። እየተመታ ለእውነት ይኖራል። እየተመታም ለእውነት ይሞታል።

ለጋዜጠኛ ዕጣፈንታው ይኼው ብቻ ነው። ይኼ ግን የስንቶቹ ዕጣፈንታና የውዴታ ግዴታ ነበር? ሙሉጌታ ሉሌስ በዚህ ውስጥ ካለፉት የጣት ቁጥሮች መሀከል አይደለም የሚል ያለ አይመስለኝም:: እውነትን በብዕር ማውጣት እንጂ መቅበር ማዳፈንን አይወድም ነበር:: “ሰው ስንፈልግ ባጀን” ባላት ጽሑፉ ውስጥ በቅን ልቦና ለሀገሩ ያለውን ቀናኢነት በሚገባ ያንጸባረቀበትና የብዕሩን ጉልበት ያሳየበት ስለመሆኑ ይወሳለታል::

ከጋዜጠኝነት ጀርባ…የሙሉጌታ ሉሌ የኑሮ ጎጆ “ኑሮ ካሉት መቃብርም ይሞቃል” በሚለው የተረት እሳት በመሞቅ እንጂ እየሠራ ከነበረው አንጻር ቅንጣት ምቾት አልነበረውም:: ጭንቅላትና ልቡ እንጂ ኪሱ እንኳን የተራቆተች ነበረች:: ስለራሱ ሳይጨነቅ ባለችው ነገር ሌላውን መርዳት፣ ማብላትና ማጠጣት የሚወድ ነበር:: በብዕሩ እጅግ ይፈጥናል፤ሲናገር ግን በዝግታ ነው:: ከአንደበቱ ይልቅ በብዕሩ ቦምብ አምካኝ ነበር:: ምን ቢያውቅ እኔ አውቃላችኋለሁ ባይ አይደለም::

በሙያው ሥነ ምግባር የማያወላዳ በመሆኑ እውነትን በብዕሩ ሊያቆማት ሲል በቆሪጥ ተመልክተው እንደ ጠላታቸው የፈረጁት ብዙዎች ይሆናሉ:: በሌላ ህይወቱ ያለው መስመር ግን በቄንጥና በወጉ፣ ለቀረበው ሁሉ እንዲመች አድርጎ ያሰመረው በመሆኑ ደርሰው ክፉ የሚያስወሩበት አልነበሩም:: አንዳንዶቹ ጋር “አቶ ሙሉጌታ”፣ ገሚሱ ጋር ደግሞ “ጋሼ” እንዲሁም በቤተሰቡ ውስጥ ደግሞ “ላሉዬ” የሚሉ መጠሪያዎች አሉት:: በሁለተኛው የሚጠሩት አብዛኛዎቹም የልብ ወዳጅና የህይወት ተማሪዎቹ፣ የመንፈስ ልጆቹ ናቸው::

በዕድሜ የሚያንሱትና የሚበልጡትም ሆኑ አቻዎቹ ቀርበው ከእርሱ መማርን ይወዳሉ:: እሱ ጎበዙ መምህራቸው፣ እነርሱም ወደው የሚከተሉት ደቀመዝሙሮቹ ናቸው:: ተማሪና አስተማሪን ካነሱስ አይቀር፤ ሙሉጌታ ሉሌ አስተምሮ ለሀገር ካበቃቸው መሀከል ዶ/ር ላጲሶ ጋዴቦ፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና አቶ ሌንጮ ለታ ተጠቃሽ ናቸው::

የቀረቡትና ቀርበው የተመለከቱት በሙሉ የሚያወሩት አንድ ዓይነት ነገር አለ:: ይኼውም “የሙሉጌታ ሉሌ የአዕምሮ ጥልቀትና ልህቀት የተለየ ነው” የሚል ነው:: እንዲያውም አንዷ ወዳጁ ስለዚሁ ነገር ስታወራ እንዲህ ነበር ያለችው፤ “ጋሽ ሙሉጌታ ከ1 ሺህ 500 በላይ የሚደርሱትን አብዛኛዎቹን የመ/ ቤቱን ሠራተኞች ስልክ ቁጥር በቃሉ መያዙን ስመለከት አንድን ነገር የመያዝ ችሎታው ከኛ ጋር የማይመጣጠን ልዩ ፍጡር ያስመስለዋል” በማለት መደነቋን ትናገርለታለች::

ሌላው ደግሞ ነገሮችን በፍጥነት የመከወን ችሎታው ነው:: ለነገ ምሳ ቢሉት ቀድሞ ለቁርስ ያደርስላቸዋል:: እርሱ በኅልቁ መሳፍርት ገጾች የተጠገጠገ መዝገብ፣ የፈለጉትን ፈልገው የማያጡበት ቤተ መጻሕፍት ነው:: ስለ አንድ ርዕሰ ጉዳይ ለመጻፍ ከጀመረ አፍታም አይፈጅበትም:: አስቀድሞ አዕምሮው ውስጥ ሰፍሮ ያስቀመጠው ያህል ያለማቋረጥ በብዕሩ ያርከፈክፈዋል::

ሙሉጌታ ሉሌ በሀገሩ ውስጥ ባቆማት ጎጆ ውስጥ ዘልቆ ወደ ውስጥ ገብቷል:: ተስፋ እየቆረጠ እንደገናም ወጥቷል:: በህይወት መንገድ ሽቅብ እየወጣ ቁልቁልም ወርዷል:: ግራና ቀኝ እያለም በብዕሩ ከጋዜጦችና ጋዜጠኝነት ጋር ተጨባብጦም ተናንቆም ኖሯል:: የሚወዱትም የሚጠሉትም ፊቱ ቆመው አንድ ነገር ብለውታል:: ፖለቲካም ፖለቲከኛም ደቁሰውታል:: በብዕሮቹ ምክንያት ለ16 ጊዜ ያህል ተከሶ ማስጠንቀቂያ ደርሶታል:: በአንድ ወቅትም የደኅንነት አባላት ናቸው ተብለው በሚጠረጠሩ ሰዎች በመኪና አደጋ የመግደል ሙከራ ተደርጎበት በተአምሩ ተርፏል:: ሕክምናውንም ከመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ለማድረግ ተገደደ:: ወዳጅ ዘመዱ ሁሉ ይቅርብህ እያሉ ሲመክሩት “እንኳን እጄን አልቆረጡኝ፤ ብዕር የምይዝበት እጄ እስካለስ ተርፌያለሁ” ነበር የሚላቸው:: እናም በዚህ ሁሉ እየጻፈና እያስነበበ ቀጠለ::

ከሀገር ወጥቶ በስደት ኑሮ ጎጆ ከቀለሰ 19 ዓመታት ተቆጠሩ:: ከሰማይ ምድር የተዘረጋው የዘመን መቁጠሪያ ቀስት እየተሽከረከረ ሄዶ 2008 ዓ.ም አናት ላይ አረፈ:: አይጠሩ ጠሪው፣ ድንገቴው ሞትም ከግራ ወደ ቀኝ ከሚሽከረከረው፣ የመቁጠሪያው ጫፍ ላይ እንደ ጦር ቀስት ተሰክቶ የዕድሜውን ገመድ በጠሰው:: መስከረም 23 ቀን 2008ዓ.ም በዚያው አሜሪካ፣ በዚያው ቨርጂኒያ ውስጥ አንቀላፋ:: በዚያን ጊዜም የ75 ዓመት አዛውንት ሆኖ ነበር:: ከቢቸና እስከ አምቦ፣ ከአምቦ እስከ ናዝሬት ትምህርት ቤት፣ ከትምህርት ቤቱም ወደ ሥራ ዓለም በዚያው የህይወት ጎጆ…ሞገደኛ ብዕሮች ከዛሬይቱ ኢትዮጵያ እስከ አዲስ ዘመንና መነን መጽሔት አሁንም በጎጆው ውስጥ…ከጋዜጠኝነትና ደራሲነት እስከ ሥልጣን ወንበር…ከአዲስ አበባ ኢትዮጵያ እስከ አሜሪካ ቨርጂኒያ የነበሩትን የህይወት ዘመን አሻራዎች በሙሉ ሲሄድ ከአንዲት ጎጆ ታዛ ስር አኑሯቸው እብስ አለ::

የጻፈበት ብዕር ቀለሙ አይደርቅም:: የጻፋቸው ገጾችም አይቀደዱም:: ታሪኮቹም አይደበዝዙም:: ከጎጆዋ ሳሎን ውስጥ ያኖራቸው ሁሉም አይበሰብሱም:: ሠርቶ ከማጀቷ ያስቀመጣቸውም አይሻግቱም:: ወትሮም ጋዜጠኛ የሞተ ዕለት እንጂ በኖረ ዕለት አይወራለትም። በህይወት ሳለ የዘራው የሚበቅለው ከመቃብር በላይ ነው:: ከሳጥን አፈር ገብቶ ታሪክ ይገለጣል:: ህይወት እንደ ኑዛዜ ቃል ከሞት ኋላ ይነበባል። ሲሞት መኖር ይጀምራል:: በታች ሆኖ በላይ ያፈራል።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 5/2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You