እንደመልካችን ሁሉ የየራሳቸን ፀጋ የተለያየ ነው፡፡ አንዳንዶቻችን በመስጠት፣ ሌሎች ደግሞ በማስተባበር እና መንገድ በማሳየት ይዋጣልናል፡፡ የሚያስተባብሩ ሰዎች እንደሚሰጡ ሰዎች ገንዘብና ንብረታቸውን ባይሰጡም ጊዜያቸውን እና ሀሳባቸውን መስዋት ማድረጋቸው አይቀርም፡፡ አጠቃቀማችን ይለያይ ይሆናል እንጂ በምድር ላይ ላለን ለእያንዳንዳችን እኩል የተሰጠን ነገር ቢኖር ጊዜና ሀሳብ ነው፡፡
የራሳችንን ጊዜ በመሰዋት፣ በራስ ተነሳሽነት ቀን የጣላቸውን፣ ሕይወት ፊቷን ያዞረችባቸውን ሰዎች እንዲረዱ ማድረግ እና መንገድ መጥረግ በእውነትም መሰጠት ነው፡፡ የበጎ አድራጎት ስራን በማስተባበር፣ ሀሳብ በማመንጨት በርካቶች በእነሱ ምክንያት የሕይወት ፀሐይን ገልጠው እንዲመለከቱ ያስቻሉ እንደ ወይዘሮ አልማዝ ለገስ ያሉ ግለሰቦች በከተማችን፣ በሰፈራችን አይጠፉም፡፡
ወይዘሮ አልማዝ ሰፈራቸው ላይ ባጋጠማቸው አንድ ክስተት ምክንያት ወደ ማስተባበር ስራ ሊቀላቀሉ ቢችሉም፤ የኑሮ መንገድ ሆኖባቸው ለበርካቶች በተለያየ ዘርፍ በማስተባበር ያለምንም ክፍያ ሠርተዋል፡፡ በሰሩት የማስተባበር ሥራም በ2009 ዓ.ም በከተማ ደረጃ ተሸላሚ ሊሆኑ ችለዋል፡፡
ትውልድና እድገት
ወይዘሮ አልማዝ ለገሰ የተወለዱት በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ፤ ልዩ ስሙ ሶጃጄ በሚባል አካባቢ 1958 ዓ.ም ነው፡፡ ለወላጆቻቸው ሁለተኛ ልጅ መሆናቸውን የሚገልጹት ወይዘሮ አልማዝ፤ በተወለዱበት አካባቢ የቆዩት ለሶስት ዓመታት ብቻ ነው፡፡ ‹‹በሶስት ዓመቴ ከተወለድኩበት አካባቢ ወደ ሐረር ከተማ ስለተወሰድኩ እድገቴ ሐረር ከተማ ነው፤ ስለዚህ የሐረር ሰው ነኝ ማለት እችላለሁ፡፡›› ይላሉ፡፡
ወይዘሮ አልማዝ በእናታቸው እቅፍ ተቀማጥለው አላደጉም፤ እንደውም እርሳቸው እንደገለፁልን እናታቸው ጥላቸው የሄደቸው በልጅነታቸው ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ያደጉት አክስታቸው ቤት ነበር፡፡ አሁን የሚጠሩበት የአባት ስም ማለትም አቶ ለገሰ የስጋ አባታቸው መጠሪያ ስም አይደለም፤ የምጠሩትም ባሳዳጊያቸው ስም መሆኑን ነግረውናል፡፡
የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ሐረር ከተማ አሰበ ተፊሪ ትምህርት ቤት ነው፡፡ በትምህርታቸው በጣም ጎበዝ እንደነበሩ የሚናገሩት ወይዘሮ አልማዝ፤ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ባሉት ደረጃዎች ካልወጡ ያለቅሱ እንደነበር ገልፀውልናል፡፡ በትምህርታቸው ጎዝና ጠንካራ ተፎካካሪ የነበሩ ቢሆም፤ ትምህርታቸውን መቀጠል የቻሉት እስከ ዘጠነኛ ክፍል ብቻ ነበር፡፡ በወይዘሮ አልማዝ እምነት ከወላጆቻቸው ጋር ማደግ አለመቻላቸው በትምህርታቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮባቸዋል፡፡
ባለታሪኳ እንደሚሉት፤ አክስታቸው ጋር በሚያድጉበት ወቅት ታናናሾቻቸውን የአክስታቸውን ልጆች የሚያሳድጉት እርሳቸው ነበሩ፡፡ ባደጉበት የዘመድ ቤት በርካታ ልጆችን ለማሳደግ መገደዳቸው የስነልቦና ጫና ውስጥ ከቷቸው ነበር፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳን በትምህርታቸው ጎበዝ የነበሩ ቢሆንም፤ ዘጠነኛ ክፍል ላይ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ፡፡ አሁን ያሳደጓቸው የአክስታቸው ልጆች እህትና ወንድሞቻቸው እነርሱ ሆነዋል፡፡
ልጅ ከማሳደግ ቀጥለው ከነበሩበት ሐረር ከተማ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ወደ አዲስ አበባ ከተማ ቢመጡም፤ እንዳሰቡት አልሆነላቸውም፡፡ በዚህም የተነሳ የኑሮ አቅጣጫቸውን ለመቀየር ተገደዱ፡፡ ‹‹ትምህርቴን ለመቀጠል ከሐረር አዲስ አበባ ወዳለችው ሌላኛዋ አክስቴ መጣው፡፡ ከመጣሁ በኋላ አዲስ ከተማ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ትምህርቴን ጀመርኩ፡፡ ነገር ግን የከተማዋ ሁኔታ አልተመቸኝም ይላሉ፡፡
ትምህርት ቤት ያለው ሁኔታ ከእርሳቸው አስተዳደግ እና ሁኔታ ጋር የሚሄድ አልነበረም፡፡ ወይዘሮ አልማዝ እንደተናገሩት፤ ‹‹ የአዲስ አበባ ልጆች የኑሮ ዘይቤ ከእኔ ጋር የሚሄድ አልነበረም፡፡ ይህም ትምህርቴን እንዳቋርጥ አስገደደኝ፡፡ ከዛ ትምህርቴን አቋርጬ ስራ መስራት ጀመርኩ፡፡›› ይላሉ፡፡
ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ስራ መግባታቸውን ቢገልጹም፤ የጀመሩትም ስራ እንዳሰቡት ውጤታማ ሊሆን ባለመቻሉ ትዳር መሰረቱ፡፡ በትዳራቸውም ሶስት ልጆችን አፍርተዋል፡፡
በጎ አድራጎት
ወይዘሮ አልማዝ የበጎ አድራጎት ሥራን መሥራት የጀመሩት በ1984 ዓ.ም ነበር፡፡ጊዜው በኢትዮጵያ የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ተስፋፍቶ የነበረበት ወቅት ነው፡፡ በዛ ዘመን በርካታ የቫይረሱ ተጠቂዎችን ወይዘሮ አልማዝ ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ቤት ለቤት በመሄድ ገላቸውን በማጠብ፣ በመንከባከብ እንዲረዱ እንዲፈቀድላቸው ለወረዳው ጥያቄ አቀረቡ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አሳዳጊ የሌላቸውን እና ወላጆቻቸው ለማሳደግ አቅም ያነሳቸውን ልጆችን ከየወረዳው በመመልመል ለሴቶችና ህጻናት ቢሮ እርዳታ እንዲያገኙ ማቅረብ ጀመሩ፡፡
ወይዘሮ አልማዝ የበጎ አድራጎት ሥራ የጀመሩበትን አጋጣሚ ሲያስታውሱ፤ ‹‹እኔ የበጎ አድራጎት ሥራን የጀመርኩበት አጋጣሚ በ1984 ዓ.ም በአንዲት ሴት ምክንያት ነው፡፡ ከባሏ ጋር ከጅግጅጋ ተፈናቅለው መጥተው ነበር፡፡ ባልና ሚስቱ የሚኖሩት እኔ በምኖርበት ሰፈር የግለሰብ ቤት ተከራይተው ነበር፡፡ እናም ሁለቱም የኤች. አይ. ቪ ቫይረስ ተጠቂ ናቸው፡፡ ነገር ግን ባልየው በሽታው እንዳለበት አውቆ እንክብካቤ የጀመረ ቢሆንም ለሚስቱ አልነገራት፡፡
ሚስትየዋ በሽታው በጣም ስለጸናባት ታማ እቤት ተኛች፡፡ ተፈናቀይ ስለነበሩ የሚረዳቸው ዘመድ እንኳን አልነበራቸውም፡፡ ልጅም የላቸውም ነበር፡፡ ተከራይተው የሚኖሩበት ቤት መውጫ እና መግቢያ ስለነበር፤ በዛ የሚያልፉ ሰዎች ሚስትየዋ መታመሟን ያስተውላሉ፤ እዚህ ቤት እኮ ብርቄ ታማለች ተብሎ ሲወራ ሰማሁ፡፡ እኔ ከልጂነቴ ጀምሮ የማስተባበር ነገር ይሳካልኛል፡፡ የሰፈሩን ሰው ማስተባበር ጀመሩኩ፡፡›› በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ፡፡
“ያኔ ሁለት ብር ዋጋ ነበራት፡፡” የሚሉት ባለታሪኳ፤ ጎረቤቶቻቸውን አስተባብረው በሰበሰቡት ገንዘብ ታማሚዋን እንድትታከም ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታ ወሰዷት፡፡ ወይዘሮ አልማዝ እንደሚናገሩት፤ ሲያስተባብሩላት የነበረችው ሴት የኤች. አይ.ቪ ተጠቂ እንደነበረች ሴትየዋም ሆነች እነርሱ አያቁም ነበር፡፡ ‹‹ዘመድ የላትም የመጣቸው ከክፍለ ሀገር ነው፤ ብለው ብቻ ነበር፡፡ ከወረዳ አንድ ሰው ተጨምሮ እርሳቸውና አንዲት ጓደኛቸው ሆነው፤ ዘውዲቱ ሆስፒታል ከወሰዷት በኋላ ሶስታቸውም፤ እንደቤተሰብ ሆነው እየተመላለሱ ሲያስታምሟት ቆዩ፡፡ በመጨረሻም ሴትየዋ በደሟ ውስጥ ኤች .አይ. ቪ ቫይረስ እንዳለ እንደተነገራቸው ይገልጻሉ፡፡
እንደወይዘሮ አልማዝ ገለፃ፤ በዛ ጊዜ ፈርተው እንዳይሸሷት ምን መደረግ እንዳለበት ወይይት አደረጉ፡፡ እርሳቸውን ጨምሮ ለሰባት ሴቶች ስልጠና ተሰጣቸው፡፡ ለሶስት ቀን ስልጠናውን ከወሰዱ በኋላ፤ ለታማሚዎቹ ማስታመሚያ የሚሆን ሶፍት፣ በረኪና እና ሳሙና እንዲሁም ቦርሳ እንደተሰጣቸው ይናገራሉ፡፡ የተሰጣቸውን ይዘው በበሽታው ለተጎዱ ቤት ለቤት እየሄዱ እንክብካቤ መስጠት መጀመራቸውን ይናገራሉ፡፡
በዛ ሰዓት ስለበሽታው ለማህበረሰቡ የነበረው ግንዛቤ ዝቅተኛ ከመሆኑ የተነሳ ታማሚዎቹ፤ ገመናቸው እንዳይወጣ በጣም ይደበቁ ነበር፡፡ ሲሉ በወቅቱ በግንዛቤ እጥረት ምክንያት የበሽታው ተጠቂዎች ምን ያህል እንደሚጎዱ ያስረዳሉ፡፡ በኤች. አይ.ቪ ቫይረስ የተጎዱትን በመንከባከብ 12 ዓመት መስራታቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ አልማዝ፤ ምንም አይነት ክፍያ እንዳልነበራቸው ገልፀውልናል፡፡ ሳሙና እንኳን እንዳልነበራቸውም ይገልፃሉ፡፡
ወይዘሮ አልማዝ በኤች. አይ. ቪ ቫይረስ የተጎዱትን በመንከባከብ ለ12 ዓመታት ከሰሩ በኋላ፤‹‹ ዘ-ቡር›› በሚባል በአንድ በጎ አድራጎት የምግብ ድርጅት ሁለት መቶ ብር እየተከፈላቸው መስራት ጀመሩ፡፡ ድርጅቱ አቅመ ደካማ ለሆኑ ቤተሰቦች ዘይት፣ ቅንጬ፣ ዱቄት፣ ቦቆሎ እና ሌሎች የምግብ አይነቶችን ይሰጣል፡፡ የእርሳቸው ተራ በወር በሚደርስበት ወቅት እህሉ የሚሰጣቸው ሰዎች በትክክል እህሉ ለሁሉም ቤተሰቦች ለእያንዳንዳቸው በስረዓት መድረሱን ይከታተላሉ፡፡
እርሱ ብቻ ሳይሆን እንክብካቤ ለማድረግ የ31 ቤተሰቦችን ታሪክ ማወቅ እንዳለባቸው የሚናገሩት ወይዘሮ አልማዝ፤ የእርዳታ እህሉ በሚሰጥበት ወቅት እያንዳንዳቸው መውሰዳቸውን ለማረጋገጥ ሁሉም ወስደው እስኪያልቁ ይጠብቁ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ ያልመጡ ካሉም እቤት ለቤት እንደሚያደርሱ በመጠቆም፤ በእዚህ ሥራ አራት ዓመት እየሰሩ መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡
ወይዘሮ አልማዝ ለበጎ ተግባር ሲያስተባብሩ ዘርፍም ሆነ ድንበር የማይገድባቸው ደፋርና ቁርጠኛ ሴት ናቸው፡፡ አሁን ከሀገር ውጭ ያሉ ሰዎችን በማስተባበር በሰፈራቸው ለሰባት አቅም ደካማ ቤተሰቦች ድጋፍ እንዲደረግ እያገዙ ናቸው፡፡ ይህንን ሲያደርጉ አቅም ደካማ ቤተሰቦችን የሚረዱ ግለሰቦች ከሚኖሩበት ባህር ማዶ በሁለት ዓመት ሆነ በአንድ ዓመት ሲመጡ ተረጂዎቹን እንዲጎበኟቸው ያደርጋሉ፡፡ የተላከውን ገንዘብ በአግባብ መጠቀም አለመጠቀማቸውንም ይከታተላሉ፡፡ ከተረጂዎች የሞተም ካለ ሪፖርት እንደሚያደርጉ ያስረዳሉ፡፡ ባለታሪኳ አርቆ አስተዋይ፤ ከዛሬ አልፎ ለነገ መቆጠብ የስልጣኔ እና የጥንካሬ አንዱ መለያ መሆኑ ስለገባቸው፤ እነዚህ ድጋፍ የሚደረግላቸው ሰዎቸ ቁጠባ እንዲጀምሩ አስደርገዋል፡፡
‹‹አብዛኞቻችን ለጤና ብለን ገንዘብ የመቆጠብ ባህላችን ብዙም የዳበረ አይደለም፡፡ ጤና መድህን ክፍያው በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው፤ ስለዚህ ለአቅመ ደካሞች ከሰው ፊት ወጥተው ከሚለምኑ እንዲቆጥቡ እና ጤና መድህን እንዲገቡ እመክራቸዋለው›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ወይዘሮ አልማዝ በእርሳቸው በኩል ድጋፍ የሚደረግላቸው ሰዎችም የጤና መድህን እንዲያወጡ አድርገዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች የቁጠባ ልምድ እንዲኖራቸው ነገ ክፉ ቀን ሊመጣ ይችላል በማለት መቶም ይሁን ሁለት መቶ ብር እንዲቆጥቡ እያደረጉ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡
አንዳንድ ሰዎች ሌሎችን የመርዳት አቅም እና ፍላጎት ቢኖራቸውም ማንን መርዳት እንዳለባቸው ፤ በምን መልኩ መርዳት እንዳለባቸው ባለማወቅ ይቸገራሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ አቅም ባይኖራቸውም የመርዳት ክህሎት ኖሯቸው መንገድ በማሳየት የተካኑ እንደ ወይዘሮ አልማዝ አይነት ሰዎችም አሉ፡፡ እነዚህን ተመሳሳይ ዓላማ ኖሯቸው ነገር ግን በተቃራኒ አቅጣጫ የቆሙ ሰዎች ተገናኝተው በጋራ ሲሰለፉ ነገሮች መስመር ይይዛሉ፤ ውጤቱም ምርጥ እንደሚሆን አያጠያይቅም፡፡
ባለታሪካችን እነዚህ ሰባት ቤተሰቦች እርዳታ ከሚያደርጉላቸው ከባህር ማዶ ካሉ አካላት ጋር ሊያገናኙዋቸው የቻሉት በታላቅ ልጃቸው በኩል እንደሆነ ያሰረዳሉ፡፡ ልጃቸው በቤተክርስትያን የምትተዋወቀው ጓደኛ ነበራት የሚሉት ወይዘሮ አልማዝ፤ የእርሱ ዘመዶች በኢትዮጵያ ለተወሰኑ ሰዎች ድጋፍ ማድረግ እንፈልጋለን እና እስኪ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ካሉ ጠቁመን ይሏታል፡፡ በወቅቱ እሱም ስላላወቀ ታላቋን ልጃቸውን ጠየቃት እና እርሷ ደግሞ በበኩሏ እርሳቸው እንዲያስተባብሩ እንደጠየቀቻቸው ይገልፃሉ፡፡
‹‹ልጄ አንቺ ብዙ ሰው ስለምታዉቂ ምናልባት ሊረዳ የሚችል አንድ አምስት ሰው አዘጋጂ አለችኝ ፡፡ ስማቸውን ስነግራት የስማቸውን ዝርዝር በቴሌ ግራም ላከችለት››፤ ሲሉ አሁን መርዳት የቻሉበት መንገድ በምን መልኩ እንደተጀመረ ይገልጻሉ፡፡ ወቅቱ አዲስ ዓመት እየተቃረበበ እንደነበር አስታውሰው፤ የልጃቸው ጓደኛ የሰዎቹን ቤት ለማየት ጥያቄ አቀረበ፡፡ የሁሉንም ቤት ወስዳው አሳዩት፡፡ ተረጂዎቹ ኦቲዝም የሆኑ እና የተለያየ ችግር ያለባቸው ነበሩ፡፡ ሁሉንም ካየ በኋላ ፎቶ አንስቶ አሁን ድጋፍ እያደረገችላቸውጉ ላሉት ሰዎች ወደ አሜሪካ ላከ ፡፡
ወይዘሮ አልማዝ እንደሚናገሩት፤ አሜሪካ ያሉት ሰዎች ድጋፍ የሚደረግላቸውን ሰዎች ፎቶ ከተመለከቱ በኋላ፤ በእርሳቸው የባንክ ቁጥር ለተረጂዎች ብር አስገቡላቸው፡፡ ከዛን ያ በእርሳቸው የባንክ ቁጥር የገባላቸው የነበረውን ብር አውጥተው ለእያንዳንዳቸው ሁለት ሺህ ብር ሰጥዋቸው፡፡ ተረጂዎቹም በጣም ደስ ብሏቸው አመሰገኑ፡፡ አንዲት አሜሪካን ሀገር ሆና ድጋፍ የምታደርግላቸው ግለሰብ ለአዲስ ዓመት ወደ ኢትዮጵያ በመጣችበት ወቅት ለእያንዳንዱ ቤተሰብ የበዓል ስጦታ ብላ፤ በርበሬ፣ ዘይት ጨምሮ የተለያዩ ነገሮችን ከሰጠች በኋላ፤ ለእንጀራ እና ለዳቦ ብላ አንድ አንድ ሺህ ብር ሰጠቻቸው፡፡ ከዛ ጊዜ በኋላ በቋሚነት በየወሩ ገንዘቡ እንዲገባላቸው ተደረገ፡፡
‹‹በሕይወት እስካለን ድረስ መታመም ሆነ የተለያየ ችግር ሊያጋጥም ይችላል፡፡ እኔም ይሄን በማሰብ ድጋፍ የሚደረግላቸውን ሰዎች የባንክ ቁጥር በመላክ የሚላከው ገንዘብ ለእያንዳንዳቸው በግል እንዲደርስ አደረኩኝ›› ሲሉም የነበረውን ሁኔታ ያብራራሉ፡፡ እርሱ ብቻ ሳይሆን አለመተማመንም ሊኖር ስለሚችል ወደ መስመር እየገቡ ሲመጡ ኃላፊነቱን ከእራሴ አወረድኩ ይላሉ፡፡ አሁን እነዚህ ሰዎች ድጋፍ ማግኘት ከጀመሩ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ እስከ አሁን ምንም ሳይቋረጥ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ይላሉ፡፡
ወይዘሮ አልማዝ በወረዳው ለነዋሪው ተብሎ የሚመጡ ጉዳዮችን በኃላፊነት ተቀብለው ሰዎችን በመመልመል እና በመለየት የማስተባበር ስራ ይሰራሉ፡፡ አሁን በሀገር ደረጃ የሌማት ትሩፋት፣ የከተማ ግብርና የሚባሉ ተዘርግተው በግብርናው ዘርፍ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ በእነዚህ ተግባራትም ትልቅ ለውጦች መመዝገባቸው ይነገራል፡፡ ይህ ሰራ በማስተባበርም የወይዘሮ አልማዝ ሚና የጎላ ነው፡፡
‹‹በሌማት ትሩፋት ላይ የማስተባበር ስራ እሰራለሁ፡፡ በዚህም በአካባቢው ዶሮ የሌለው ማነው? የሚለውን በመለየት ለብሎክ አስተባባሪዎች የስም ዝርዝራቸውን አቀርባለሁ ሲሉ ይናገራሉ፡፡
ግብርና
በወይዘሮ አልማዝ መኖሪያ ግቢ በተገኘንበት ወቅት፤ ከሙዝ ተክል ጀምሮ የተለያዩ የፍራፍሬ፣ የአትክልት እና የቅመማ ቅመም ተክሎችን በግቢው ተክለዋል፡፡ ይህም ወይዘሮዋ በጎ ስራ መስራት ማስበባበር ብቻ ሳይሆን፤ በአረንጓዴ ልማት ጊቢያቸውን ማስዋብ እንደያዙ መገንዘብ ችለናል፡፡ ለራሳቸው፣ ለሰፈሩ እና ለወረዳው ሞዴል መሆናቸው የሚነገርላቸው ባለታሪኳ፤ ‹‹ስሠራ “አልማዝ ገበሬዋ ነኝ” ስለብስ ደግሞ በአማረ መልኩ ነው፡፡›› በማለት እራሳቸውን ይገልጻሉ፡፡
የከተማ ግብርናን ለማስፋፋት በመንግስት ደረጃ እየተሰራ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ወይዘሮ አልማዝ የከተማ ግብርና ስራንም በአካባቢያቸው በማስተባበር አይተኬ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በአካባቢው ቦታ ያላቸውን እናቶች መኮትኮት ስለማይፈልግ ሁለት ፓፓያ እንኳን ወስዳቹ ግቢያቹ ውስጥ ትከሉ እያሉ ሰዎች እንዲተክሉ እንደሚያበረታቱ ይገልፃሉ ፡፡
የልጅነት ዝንባሌ
‹‹እኔ ያደጉት ማህበራዊ መስተጋብሮች በሚበዙበት አካባቢ ነው፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ የማስተባበር ተግባር የሚጠይቁ ስራዎች የመወጣት አቅሜ ከፍተኛ ነው፡፡›› ሲሉ ከልጅነታቸው ጀምሮ የማስተባበር ስራ እንደሚወጣላቸው ያስረዳሉ፡፡ በተፈጥሯቸው እንደማይፈሩ የሚናገሩት ባለታሪኳ፤ በእንደዚህ አይነት ስራዎች ደፍረው ሲሳተፉ ፈጣሪ ደግሞ እንደሚረዳቸው ይገልፃሉ፡፡ ሁሉም ነገር እንደሚሳካላቸው ይገልፃሉ፡፡ ‹‹ለምሳሌ ምግብ ዋስትና ወይም ሴፍቲኔት ሲመጣ አልማዝ አስተባብሪልን፣ እስኪ ማንን መርዳት እንዳለብን ቤት አሳይኝ እያሉ ከወረዳ ይመጣሉ፡፡ እኔ በብዛት ምሰራውደመወዝ የሌለው ስራ ነው ፡፡ እግዚያብሔር ግን በእጅ አዙር ገቢ ይሰጠኛል፡፡›› ሲሉም ይናገራሉ፡፡
ወይዘሮ አልማዝ በአንድ ወቅት እግራቸውን ታመው እቤት ውስጥ መቆየት ግዴታ ሆኖባቸው ነበር፡፡ ለአንድ ዓመት ያህል እግራቸው (ፓራላይዝድ) ሆኖ መንቀሳቀስ አቅቷቸው ከቤት አይወጡም ነበር፡፡ እናም በወቅቱ ሰፈራቸው የኮብልስቶን ንጣፍ መንገድ ለመስራት ልየታ ከተደረገ በኋላ ሰዎቹ ትተው ሄዱ፡፡ እርሳቸው ግን የልማት ቡድን አቋቁመው፤ በተደጋጋሚ ሄደው በመሞገት ሊሰራላቸው እንደቻለ ይገልፃሉ፡፡
ወይዘሮ አልማዝ ሶስት ልጆች ያሏቸው ሲሆን፣ ለማስተባበር በሚወጡበት ወቅት ድሮ ልጆችን ጎረቤት ማስቀመጠ ስለሚቻል ብዙ አይቸገሩም ነበር፡፡ የምትንከባከባቸው ሰራተኛቸው ናት፡፡ ‹‹ድሮ እንደ አሁኑ ለቤት ሰራተኛ የሚከፈል ደመዎዝ ውድ ስላልነበር ሰራተኛም ነበረኝ፡፡ አሁን ደግሞ ወጥቼ የማስተባበር ሥራ ስሠራ ባለቤቴ በቤት ውስጥ ስራ ይረዳኛል፡፡ ›› ይላሉ፡፡
ወይዘሮ አልማዝ፤ በቤታቸው ምንም ሳይኖራቸው እንኳ በዙ ሰው ይኖር እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ በሌላ በኩል ቡና ለመጠጣት ሰው ቤት በመሄድ በወሬ ጊዜያቸውን እንደማያጠፋም ይናገራሉ፡፡ አንድ ቦታ እንኳን ቢሄዱ የሄዱበትን ዓላማ ፈጽመው በጊዜ የሚመለሱ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ሌሎች ሙያዎች
ወይዘሮ አልማዝ በእጅ ስራም የተመሰከረላቸው ባለሙያ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ተቀጥረው የሚከፈላቸው ደመውዝ ባይኖርም፣ ወጥተው ባይነግዱም፤ ቤታቸውን ለማስተዳደር ባለቤታቸው ከሚያገኙት ገቢ በተጨማሪ እርሳቸውም በቤት ውስጥ ሲሆኑ ዳንቴል እና ሌሎች ነገሮች ሰርተው በመሸጥ ገቢ ያገኛሉ፡፡
‹‹እኔ አንድ ስራ ብቻ መስራት አልችልም፤ ምናልባት ልብስ እያጠብኩ ካልሆን፤ ማንኛውንም ስራ ስሠራ በጎን ዳንቴል እሰራለሁ ፣ ጥጥ እፈትላለው፣ በተጨማሪም የቤት ውስጥ ጌጦችን እሰራለሁ፡፡ በዳንቴል ስራ የሚፎካከረኝ የለም፡፡›› ሲሉ በእጅ ሥራውም ተወዳዳሪ እንደሌላቸው ይገልጻሉ፡፡ የመሶብ ልብስ ይሰራሉ፤ እቤት ውስጥ እንጀራ ይሸጣሉ፤ ዶሮም አርብተው ይሸጣሉ፡፡ የማሳድጓቸው የባለቤታቸው እህት ልጆች ስላሉ እነሱም እንደሚረዷቸው ይገልፃሉ፡፡
ቀጣይ ፍላጎት
ቀጣይ እቅዳቸውን የሚናገሩት ባለታሪኳ፤ በከተማው በውሃ ማፋሰሻ ቦዮች የሚጣለውን ፕላስቲኮች እና ሌሎች ቆሻሻዎች መጣል ሊቀር ይገባል የሚል እምነት አላቸው፡፡ በተጨማሪም በየመንገዱ የሚጸዳዱ ሰዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የራሳቸውን ድርሻ መውጣት ይፈልጋሉ፡፡ ከከንቲባዋ ጎን ሆነው ህብረተሰቡን የማስተባበር ሰራ መስራት እንደሚፈልጉ ገልፀውልናል፡፡
‹‹ይህን ተግባር ደግሞ የምጀምረው ከሰፈሬ ነው፡፡ ኳስ የሚጫወቱ ህጻናት በማስተማር እንደሚጀምሩ በመግለጽ፤ ሶፍት ሲጥሉ እንዲያነሱ በማድረግ ፤ ሌላው ደግሞ በሰፈሩ የፕላስቲክ ብልቃጥ እና የተለያየ ደረቅ ቆሻሻ መጣያ ማዳበሪያ የማስቀመጥ እቅድ አለኝ፡፡›› ብለውናል፡፡
በቅንነት የሚሰሩ ሥራዎች ገንዘብ ባይገኝባቸውም እንኳን ለአዕምሮ እርካታ በመስጠት፣ በአካባቢው ሰዎች ተወዳጅነት በማስገኝት፣ እውቅና በማሰጠት ያሸልማሉ ብለዋል፡፡ ወይዘሮ አልማዝም በሰሩት ሥራ የሚያገኙት ክፍያ ባይኖርም በእንቅስቃሴያቸው ብዙ የሕይወት ትምህርትና ልምድ እንዳስገኘላቸው ከንግግራቸው መረዳት አያዳግትም፡፡
በሰሩት በጎ ተግባር ጡረታ ባይኖራቸውም እንኳን እውቅና ያገኙበት በመሆኑ እጅግ እንደሚደሰቱ የሚናገሩት ባለታሪኳ፤ በዚህም በሰሩት ሥራ በከተማ ደረጃ በማስተባበር ስራ በ2009 ዓ.ም ከቀድሞው ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ የሜዳሊያ እና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ የበጎ ፈቃድ ስራዎች ሲያስተባብሩ በሌሎች ደካማ እህቶች እና ወንደሞች ለመጠቀም ፍላጎት እንደሌላቸው በመግለፅ፤ ለእርሳቸው ፈጣሪ ያዘጋጀላቸውን ነገር ብቻ እንደሚጠቀሙ ይገልፃሉ፡፡
‹‹አንዳንድ ችግሮች አይጠፋም የተደረገለት ሲያመሰግነኝ፤ ያልተደረገለት ደግሞ ልደብደብሽ፡፡›› ይላል ሲሉ በስራቸው የሚያጋጥማቸው ተግዳሮት ይገልጻሉ፡፡ ‹‹እኔ ያኔ መልስ የለኝም፤ ልብሴን እንኳን ቢይዙት በዝምታ አልፋቸዋለው፡፡ መጯጯህ አልወድም፤ ምን አይነት ሴትዮ ናት ይሉኛል፡፡ ›› የሚሉት ወይዘሮ አልማዝ፤ ቆይቶ ሲጸጽታቸው ይቅርታ የሚጠይቋቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ሌላው ከህብረተሰቡ ጋር የሚያጋጫቸውን ስራ በፍጹም እንደማይሠሩ በመጠቆም፤ ሁሌም ፍላጎታቸው ህበረተሰቡን እና ወረዳውን ማገልገል ብቻ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ሴትነት
አዕምሮ የተሰጠው ለወንድ ብቻ አይደለም፤ ሴቶችም አዕምሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሰነፍ ሴቶች ብዙን ጊዜ ስራ የላትም፣ እሷ ቤት ብዙ ሰው ስላለ ነው ይሉኛል፡፡ ሁሉም ሰው ማድረግ የሚፈልገው የራሱ የሆነ ፍላጎት አለው፡፡ እንደኔ ደግሞ ሰዎችን አምጥቶ ማሰራትም መፍትሄ ነው ይላሉ፡፡ ከእዚ በተቃራኒው ደግሞ ብዙ አስተባብረው ከቤት ያወጧቸው እናቶች መኖራቸውን በመናገር፤ ከተለያዩ ሃይማኖት ተቋማት ጋር በመሆን ማህበር እንዲመሰርቱ ማድረጋቸውን ይናገራሉ፡፡
ከሃይማኖት አባቶች ጋር በሚወያዩበት ወቅት፤ ሁልጊዜ ከመስጠት፤ ሴቶች ከሚሰጣቸው ነገር ላይ፣ ከሚያገኙት ገንዘብ ቁጠባ መጀመር አለባቸው፡፡ ለምሳሌ ቁጠባ ቢመሰረት፣ 20 ሴት አባላት ቢሆኑ 19ኙ የቆጠቡትን አንዷ ተበድራ ትሰራበታለች ሲሉ ምክር መስጠታቸውን ይናገራሉ፡፡
ቁጠባ ቢጀምሩ አሁን መበደር የሚቻልበት ሁኔታ አለ፡፡ በማለት የራሳቸውንም ልምድ አካፈልዋል፡፡ ድሮ ዳንቴል ሲሠሩ ‹‹እራስሄድ›› ከሚባል ድርጅት ብር ተበድረው ክር ይገዙና በሳምንት እየመለሱ፤ ክፉ ጊዚያቶችን መሻገር እንደቻሉ ይናገራሉ፡፡ በእርሳቸው ምክረሃሳብ ላይ በመመርኮዝ፤ የቁጠባ ማህበር ለመመስረት ተወሰነ፡፡ እናም ከ15 እስከ 20 ሴቶች ተመዘገቡ፤ ገንዘብ አያያዝ እና ወጪ አወጣጥ ላይ የሶስት ቀን ስልጠና ተሰጣቸው፡፡ አንድ ሺህ 500 ብር ለሁሉም አባላት ተሰጠ፡፡ በዛ ገንዘብ ቁጠባ ጀመሩ፡፡ አሁን የአባላቶቹ ቁጥር 80 ደርሷል፡፡
አሁን እርሳቸውም የማህበሩ አባል ናቸው፡፡ አስተባባሪ እና ገንዘብ ያዥም ናቸው፡፡ የማህበሩ አባል በመሆናቸው 23 ሺህ ብር ተበድረው 40 ዶሮ ገዝተው እያረቡ ነው፡፡ የተበደሩትንም ገንዘብ በየወሩ ያስገባሉ፡፡ እንደባለታሪኳ ሁሉ፤ የማህበሩ አባላትም እንደዚህ አይነት ስራ መስራት በመቻላቸው ለወይዘሮ አልማዝ ምስጋናቸው ከፍ ያለ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
“በፊት ከነበረው ትውልድ የአሁን ሴቶች ነቅተዋል፡፡ በፊት እኮ የራሳቸውን መታወቂያ ቀበሌ ሄደው ለማውጣት ቀበሌውን የማታውቅ ሴት ወይም እናት ነበረች፡፡” የሚሉት ወይዘሮዋ አሁን ትልቅ ለውጥ አለ በማለት ያስረዳሉ፡፡
ወይዘሮ አልማዝ በርካታ ቦታዎች ላይ የማስተባበር ስራ የሚሰሩ ቢሆንም፤ የፕሮግራም መደራረብ እያጋጥማቸውም፡፡ ምናልባታ በሌላ ሰው ምክንያት መደራረብ ቢያጋጥማቸውም በቀጥታ እንደማይመቻቸው ይናገራሉ እንጂ ፤ በእርሳቸው ምክንያት ነገሮች እንዲደናቀፉ በፍፁም እንደማይፈቅዱ ያስረዳሉ፡፡ በበርካታ ቦታዎች ላይ ዘላቂ በሆነ መልኩ ማስተባበራቸውም አንደኛው የአንደኛውን ጊዜ እንደማይሻማ ያስረዳሉ፡፡
በዓላት በሚደርሱበት ወቅት ማእድ የማጋራት ስራ ላይ ስለማስተባበር ከቤት ስራ ጋር ተያይዞ መጨናነቅ ሊኖር የሚችልበት ሁኔታ አለ፡፡ አሁንም ከታሰበበት ጠዋት 11 ሰዓት በመነሰት እስከ ሁለት ሰዓት ከቤት እስከሚወጣ ድረስ መስራት ይቻላል፡፡ ማእድ ማጋራትን በተመለከተ የተለያዩ የምግብ አይነቶችን በማስተባበር እንደሚሰበስቡ ይገልጻሉ፡፡
ባለሀብቶችን በማስተባበር ገንዘብ ይሰበሰባል፣ ባለሱቆች ጋር በመሄድ የፈለጉትን የእቃ አይነት እንዲሰጡ የማግባባት እና የተሰጠውን እቃ በመሰብሰብ፤ ከሰፈር ደግሞ አቅመ ደካሞችን የመለየት ስራ እንደሚሰሩ ያብራራሉ፡፡ወይዘሮ አልማዝ ከማስተባበር ጎን ለጎን፣ በንፋስልክ ክፍለከተማ የወረዳ አምስት ምክርቤት አባል ናቸው፡፡ በተጨማሪም ቋሚ ኮሚቴ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
ለበርካታ ዓመታት በበጎ ፈቃድ ሲያስተባብሩ እንደመቆየታቸው የእርሳቸውን አርአያ የሚከተልላቸው ሰውም አላጡም፡፡ የመጨረሻ ልጃቸው በእርሳቸው እንደወጣች የሚናገሩት ወይዘሮዋ፤ የማስተባበር ስራ ላይ ፈጣን ናት ይላሉ፡፡‹‹ከሰፈርም ብዙ ሴቶችን በዚህ ስራ እየወጡ ነው፡፡ እድሜዬም እየገፋ፣ የጤና ጉዳይም አሳሳቢ እየሆነብኝ እንደውም አሁን እንደጡረታ ብዙ ነገሮች ላይ ከመስራት ገብ እያልኩ ነው፡፡›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
አመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 5 / 2016 ዓ.ም