– ሀገሪቱ ከግርግር ወጥታ ወደ ተሻለ የመስከን ሂደት ተሸጋግራለች
– ህገ መንግሥቱ በብዙ ደምና መከራ የመጣ ብዙ ነፃነትንም ያጎናፀፈ ነው
– ምርጫ ቦርዱ ሳይጠናከር ክልል ለመፍጠር መመኘት ፍላጎት ብቻ ይሆናል
– በአሁኑ ወቅት መፈንቅለ መንግሥት ማሰብ እብደት ነው
አዲስ አበባ፡- ‹‹መሻገር ያለብን በርካታ መሰናክሎች ቢኖሩም፣ በለውጡ ማግስት ከነበርንበት ግርግር ወጥተን ወደ ተሻለ የመስከን ሂደት እየተሻገርን እንገኛለን፡፡›› እንገኛለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስታወቁ፡፡
በብዙ ደምና መከራ የተገኘውን የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ለማሻሻል በቅድሚያ አሳማኝ ሐሳብ በማቅረብ ከህዝብ ጋር መወያየትን እንደሚጠይቅ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ2011 በጀት ዓመት የመንግሥት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርትን በኢፌዴሪ 5ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 8ኛው ልዩ ስብሰባ ላይ ትናንት ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የበጀት ዓመቱ እቅድ ዴሞክራሲን የማስፋት፣ ሰላምና መረጋጋትን የማስፈን፣ኢኮኖሚውን የማነቃቃትና ለውጡን የሚሸከሙ ተቋማትን መገንባት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩንም ለማስፋት ትኩረት ተሰጥቷል፡፡የፖለቲካ ሥራዎቹም ዋና ግብ የህዝብን የለውጥ ፍላጎትና ሀገርን ከትርምስና ከመፍረስ ለመታደግም ጭምር የተከናወኑ ናቸው፡፡
‹‹አሁንም መሻገር ያለብን በርካታ መሰናክሎች ቢኖሩም በለውጡ ማግስት ከነበርንበት ግርግር
ወጥተን ወደ ተሻለ የመስከን ሂደት እየተሻገርን እንገኛለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ በህዝብና ሀገር ላይ የተጋረጡትን አደጋዎች በመጀመሪያ ለመቀነስ ቀጥሎም ለማስቆም አያሌ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ለህዝብ ተቃውሞ ምክንያት የሆኑ አመራሮችን የመቀየር፣ አሰራሮችን የማስተካከል፣ ተቋማዊ መዋቅሮች በፍጥነት እና በስፋት የመገንባት እና የማደስ ርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
ተቋማዊ ሪፎርም ማከናወንና ለግጭት መንስኤ የሚሆኑ ጉዳዮችን በዘላቂነት መፍታት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣በዚህ ረገድ ባለፈው አንድ ዓመት በሁሉም የደህንነትና የጸጥታ ተቋማት የሕግ የአሰራር ሥርዓትና የአመራር ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡ ብለዋል፡፡ ሪፎርሞቹ የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት ባሻገር ዘላቂ የሰላም መደላድል ለመፍጠር የሚያስችሉ መሰረታዊ መፍትሄዎች መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ሰላምን ለማረጋገጥ የተሰራው ሁለተኛው ሥራ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡በዚህም አጥፊዎች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ የማድረግ ሥራዎች መከናወናቸውን ፣ በዚህም በተደራጁ ቡድኖች ውስጥ በመንቀሳቀስ በሰብአዊ መብት ጥሰትና በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የሥራ ኃላፊዎችና ግብረ አብሮቻቸው በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ልዩነትን የመፍቻ ነባር መንገዶችን በመጠቀም ዘላቂ የሰላም ግንባታ ሥራዎች መከናወናቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፤ ህገ መንግሥት ላይ ያልተመቹ ጉዳዮች ካሉ ማሻሻል እንደሚቻል በህገ መንግሥቱ ላይ ሰፍሯል፡፡ ከዚህም በላይ ለህገ መንግሥቱ ጠበቃ የሆነ የለም፡፡ ህገ መንግሥቱ
የሚሰጠውን መብት ላይ በማድረግ ህገ መንግሥቱ አይሰራም ማለት ግን አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ህገ መንግሥቱ በብዙ ደምና መከራ የመጣ ብዙ ነፃነትንም ያጎናፀፈ ነው፡፡ ስለዚህም የአንድ ቀበሌ ወረቀት ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ሰነድ ነው፡፡የለወጥ ባዮች የተሻለ ሐሳብ እስካቀረቡና በህዝብ እስካወያዩ ድረስ ለማሻሻል ችግር አይኖረውም፡፡
የክልል እንሁን ጥያቄ በተመለከተ በሰጡት ምለሽ አንድ ክልል ራሱን በራሱ ለማስተዳደር ሲፈልግ ጥያቄው የሚፈጸመው በምርጫ ቦርድ በኩል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ቦርዱ ባለፉት ስድስት ወራት በርካታ ሥራዎችን መስራቱን ተናግረው፣ተቋሙ በሁለት እግሩ ሳይቆም ክልል ለመፍጠር መሞከር ፍላጎት ብቻ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡ የአንድ ክልል ጥያቄ ሲመለስ ተጨማሪ በሽታ የማይፈጥር ስለመሆኑ ማረጋገጥ የሚችልበት ጊዜ ሊሰጥ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በደቡብ ክልል የቀረበውን የክልል ልሁን ጥያቄ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄም (ደኢህዴን) እንደተቀበለው ጠቅሰው፣ውሳኔ እስኪያገኝ በትዕግስት መጠበቅ ይገባል ብለዋል፡፡ ከህግ ውጭ ምንም አይነት ሙከራ ማድረግ እንደማያስፈልግ ፣በደቦና በጩኸት የሚፈጠር ነገር እንደማይኖርም አስገንዝበዋል፡፡ ለዚህ አይነቱ ተግባር የመንግስት ትዕግስት ማለቁን ገልጸዋል፡፡
ሰሞኑን በአማራ ክልል የተፈጸመው ድርጊት መፈንቅለ መንግሥት ነው አይደለም ለሚለው በሰጡት ምላሽ እንዳብራሩት፤ መንግሥት ሲባል የፌዴራልና በተዋረድ ደግሞ የክልል ነው፡፡ አንዱ ክልል ከጎደለ የኢፌዴሪ መንግሥት ማለት አያስችልም፡፡
በየትኛውም ክልል ጥቃት ከተፈፀመ የፌዴራል መንግሥትም ላይ እንደተፈጸመ ይቆጠራል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ጥቃቱን ያደረሰው አካል ከገደለ በኋላ ለመገናኛ ብዙሃን ሲያሳወቅ ከመፍንቅለ መንግሥት ውጪ ሌላ ምን ሊባል ይችላል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/2011
አስቴር ኤልያስ