
-160 ሚሊዮን ብር የሚገመት የዓይነት ድጋፍ ተደርጓል
-108 ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብ ተሰብስቧል
አዲስ አበባ፡– በጎፋ ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተትና ናዳ አደጋ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ዜጎች ከተለያዩ ተቋማት ቃል የተገባውን ሳይጨምር 160 ሚሊዮን የሚገመት የአይነት ድጋፍ መደረጉን የጎፋ ዞን አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የዞኑ አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በዞኑ ለተከሰተው አደጋ እስከ ነሐሴ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ባለው ጊዜ የሕክምና ቁሳቁሶችንና ከተለያዩ ተቋማት ቃል የተገባውን ሳይጨምር 160 ሚሊዮን ብር የሚገመት የዓይነትና 108 ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ተሰብስቧል፡፡
አደጋው ከተከሰተ ጀምሮ በገንዘብና በዓይነት ከፍተኛ ድጋፍ እየተደረገ ነው ያሉት አስተዳዳሪው፣ የገንዘብ ድጋፉ በክልሉና በዞኑ በተከፈቱ የሂሳብ ቁጥር የተሰበሰበ ነው ብለዋል፡፡ የተሰበሰበው የድጋፍ ገንዘብ በአደጋው ለተጎዱ ዜጎችን በቋሚነት ለማቋቋም እንደሚውል ጠቅሰው፣ በዓይነት የተደረገው ድጋፍ በቀጥታ ለተጎጂዎች የሚደርስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የተለያዩ አካላት በተደረገ ጥናት አደጋው በተከሰተበት በገዜ ጎፋ ወረዳ የሚገኙ 15 ቀበሌዎች ስጋት እንዳለባቸው መገለጹን ጠቅሰው፤ በተለዩት ቀበሌዎች የሚኖሩ ሁለት ሺህ 18 አባወራዎች ወደ ተሻለ ቦታ ለማስፈር የቦታ ልየታ ሥራ መሠራቱን አስረድተዋል፡፡
በተከሰተው የመሬት መንሸራተትና ናዳ አደጋ 249 ሰዎች ሕይወት መቀጠፉን አውስተው፤ ከዚህ ውስጥ የ243 ሰዎች አስከሬን ተገኝቶ ሥርዓተ ቀበራቸው መፈጸሙን አውስተዋል፡፡ ኢንጂነር ዳግማዊ፤ የስድስቱ ሰዎች አስከሬን ባለመገኘቱ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመነጋገር አካባቢውን በማጠር መታሰቢያ እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል፡፡
በሕይወት ከወጡ አስር ሰዎች ውስጥ አራቱ በተደረገላቸው ሕክምና የዳኑ ሲሆን ቀሪዎች ስድስት ሰዎች ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በአካባቢው ተጨማሪ ጉዳት እንዳይከሰት ጥንቃቄ እንዲደረግም ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
የተለያዩ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ ዞኖች ወረዳዎችና ከተሞች የተለያዩ ድጋፍ ማድረጋቸውን በመግለጽ፣ በቀጣይ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ላይ ሁሉም እንዲሳተፉ ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ በአደጋው ለተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎች ፈጣን ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ የተጎዱ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም እንቅስቃሴ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አማን ረሺድ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 4 /2016 ዓ.ም