ከእናቴ ጋር ነው የምተኛው..የምነቃውም አብሬያት ነው። እሷ ጓዳ ጎድጓዳውን ስትንጎዳጎድ ቀሚሷን ይዤ በሄደችበት ሁሉ እከተላታለሁ። በልጅነቴ የእናቴ ጭራ ነበርኩ። ከጎኗ፣ ከስሯ፣ ከጉያዋ፣ ከቀሚሷ ስር ማንም ፈልጎ የማያጣኝ። ስንተኛ እጇን አናቴ ላይ ጥላ ሳትዳብሰኝና ሳታሻሸኝ ቀርታ አታውቅም። ጭንቅላቴን ሙሉ በእጇ እየዞረች በጎረበጣት ቦታ ላይ ቅማል ያገኘች እየመሰላት በሌባ ጣቷ አናቴን እየቆፈረች በአውራ ጣቷ እገዛ የጎረበጣትን ነገር ከአናቴ ውስጥ መዛ ታወጣለች። አንዳንዴ ቅማል ይቀናታል አንዳንዴ ደግሞ ፎረፎር ዕጣ ፈንታዋ ይሆናል። እናቴ በጎረበጣት ቁጥር ቅማል ያገኘች እየመሰላት ብዙ ቀን የደረቀ የአናቴን ፎረፎርና እንዴት እንደገባ ያላስተዋልኩትን ብናኝ እድፍ ተጋፍጣ ታውቃለች።
ዳብሳኝ ዳብሳኝ ሁለት ነገሮች ከአፏ አይቀሩም..አንድ..‹እንዳው ከየት አመጣኸው ይሄን ከርዳዳ ፀጉር? ድሮ እንዴት ያለ ሉጫ መሰለህ? ስትል ትጠይቀኛለች። ይሄን ወሬዋን ለዘመናት ሰምቼዋለሁ። እናቴ ፀጉሬን በዳበሰችኝ ቁጥር፣ አናቴ ላይ ቅማል ፈልጋ ባጣች ማግስት ከንፈሯ ላይ የሚጸነስ ወሬ ነው። አልመልስላትም..እሷም አታብራራልኝም። ‹እንዳው ከየት አመጣኸው ይሄን ከርዳዳ ፀጉር? ድሮ እንዴት ያለ ሉጫ መሰለህ› ብላኝ ዝም። ለምን እንደምትጠይቀኝ አላውቅም..ግን ትጠይቀኛለች..እጇ አናቴ ላይ ሲያርፍ፣ እንደ ሽቦ የጠነከረ ፀጉሬ መዳፏን ሲፈትነው አፏ ነፍስ ይዘራል።
ሁለተኛው ከእናቴ አፍ ላይ የማይጠፋው ቃል ‹ፀጉርህ አድጓል..ያከሳህ እሱ ነው› የሚለው ቃል ነው። ፀጉሬን እየዳበሰችኝ ሰንብታ፣ ቅማል ፍለጋ ባዝና ባዝና አልሆን ባላት ሰሞን ‹ፀጉርህ አድጓል..ያከሳህ እሱ ነው›
ትለኛለች። እንዲህ ሳትለኝ ቀርታ አታውቅም። መክሳቴን የማውቀው ያኔ ነው። አንድም ቀን ክሳቴን በመስተዋት አይቼው ወይም ደግሞ ከሌላ ሰው ሰምቼው አላውቅም። እንዲህ ባለችኝ በነጋታው ራሴን እናቴ ጉያ ስር አጎንብሼ አገኘዋለሁ። በግራ መዳፏ ወደ መሬት ደፍቃኝ ምላጭ በያዘ ቀኝ እጇ አናቴን እየላጨች። ለግማሽ ሰዓት ያክል በእናቴ መዳፎች ተፅዕኖ ደርሶብኝ እግሯ ስር ተደፍጥጬ ራሴን አገኘዋለሁ። ጫናዋ ሲበረታብኝ ራሴን ለማዝናናት በተደፈቁበት ላመል እላወሳለሁ።
‹ምን ያቁነጠንጥሀል? ይልቅ እንዳልቆርጥህ አርፈህ ተቀመጥ› ትለኛለች። በሚያስፈራራና በሚያስጠነቅቅ ድምፅ። አርፌ መቀመጥ ሳልችል አርፌ ለመቀመጥ እሞክራለሁ። ግን አይሆንልኝም የእናቴ ድፍጠጣ ሲበረታብኝ ወዲያው ራሴን ካዘነበለበት ቀና ለማድረግ እሞክራለሁ።
‹አትሰማም እንዴ! እንዳታስቆርጠኝ አትንቀሳቀስ አልኩህ እኮ!› ስትል ትቆጣኛለች። በልጅነቱ መላጨት ስቃይ የሆነበት የመጀመሪያው ሰው እኔ ሳልሆን አልቀርም እላለሁ። መላጣነቴ ምኑ እንደሚያስደስታት አላውቅም ገና ፀጉሬ ባቆጠቆጠ በሠልስቱ ነበር እናቴ ፀጉሬን መላጨት እንዳለብኝ የምታረዳኝ። ደሞ ውጣ ውረዱ..ዝም ብላ ጉያዋ አድርጋ የምትላጨኝ መሰላችሁ? አይደለም።
መጀመሪያ አረፋ ባለው ሳሙና ፀጉሬን ታጥበኛለች። አጥባ አትተወኝም..ድጋሚ ሳሙና ትመታኝና ሳሙናውን ፀጉሬ ላይ እንዳለ ወደ ጉያዋ ታስጠጋኛለች። የሳሙናው መኖር ለምን እንዳስፈለገ ቆይቼ ነው የገባኝ። አንድ ቀን ሳሙናው እያለ አልላጭም ብዬ ሳምጽባት ሳሙናው እኮ ጥሩ ነው..እንዳትቆረጥ፣ ጥሩ ሆኖ እንድትላጭ ያደርግሀል አለችኝ። የኔ ነበር ብልሀቷ የተገለጠልኝ። ተላጭቶ ለሚወድቅ ፀጉር ያ ሁሉ እንክብካቤና ሽር ጉድ ይገርመኝ ነበር።
አረፋው ዓይኔ ውስጥ እየተማገደ ስቃይ ፈጠረብኝ። ለነገሩ ለምጄዋለው..ስላጭ ከነአረፋዬ ስለሆነ ዓይኖቼ በሳሙናው መለብለባቸው ግድ ነበር። የሳሙናውን ቁጥቋጤ ሰበብ አድርጌ እናቴ ላይ እንደፈለኩ አርጎመጉማለሁ.. እቁነጠነጣለሁ..ለማልቀስ ይቃጣኛል።
በዚህ መሐል ‹ጨርሻለሁ..ትንሽ ብቻ ነው የቀረኝ› የሚል የእናቴን ድምፅ እሰማዋለሁ። በቃሏ ላይ ተስፋን ጥዬ እረጋጋለሁ። ወዲያው በሳሙናው፣ በድፈቃው ባጎነበስኩበት እንደ ስንኩል ወዲያ ወዲህ እንፏቀቃለሁ..
‹አይዞህ..ጨርሻለሁ በቃ! ስትል ልታባብለኝ ትሞክራለች።
ለለቅሶ የቀረበ ሲቃ የሚመስል ድምፅ እያወጣሁ ባጎነበስኩበት ዝም እላለሁ..
‹ቁንጮ ላድርግልህ ወይስ ጋሜ? ስትል ትጠይቀኛለች።
አኩርፌ ዝም እላለሁ..
‹አትናገርም እንዴ?
ማኩረፌን የሚነግራት ዝምታዬ ነው። ዝምታዬ የእናቴን ልብ የሚያራራልኝ ሞገሴ ነው። እናቴ ስትላጨኝ ሳላኮርፍ ቀርቼ አላውቅም። እያኮረፍኩም ቢሆን ላጭታ ትጨርሰኛለች። ቁንጮም ጋሜም ሳታደርገኝ ራሴን ርቃኑን ታስቀረዋለች። አንዳንዴ በእኔ ይሁንታ ቁንጮ አድርጋልኝ ታውቃለች። ጋሜ ምን እንደሆነ አላውቅም። ግን በላጨችኝ ቁጥር ‹ቁንጮ ላድርግልህ ጋሜ? ብላ ትጠይቀኛለች። የቱን መምረጥ እንዳለብኝ ለአፍታ ዝም እላለሁ። የማላውቀውን ጋሜ መርጬ እዝራ እንዳያበሽቀኝ ስል ብቻ ቁንጮ አድርጊልኝ እላታለሁ።
ከተላጨሁ በኋላ የእናቴ ተቀዳሚ ሥራ ፀጉሮቼን ከሜዳ ላይ መሰብሰብ ነው። ‹ፀጉርና ጥፍር የትም አይጣልም› ብላ ፀጉሮቼን ሰብስባ አንድ ጥግ ላይ ትወሽቃቸዋለች። ቀጥላ ወደ ጓዳ ነው የምትገባው..እሳት በገል ጭራ ትመጣና ከለቃቀመችው ፀጉሬ ጥቂት ታስቀርና እሳቱ ላይ ትጨምራቸዋለች። ከዛም ‹ምች እንዳይመታህ ታጠን› ስትል አንገቴን ይዛ ወደ ጭሱ ትደፍቀኛለች።
ከተላጨሁ በኋላም ከመከራ አላርፍም። እናቴ እጇን አናቴ መሐል እያርመሰመሰች ‹ፀጉርህ አድጓል..ያከሳህ እሱ ነው ካለችኝ ሰዓት ጀምሮ ባለመከራ ነኝ። በመዳፏ ተደፍቄ፣ በአረፋ እየተለበለብኩ ተላጭቼ እንደጨረስኩ ከሁሉም የሚከፋ መከራ ይጠብቀኛል። ወደ ቤት ታስገባኝና ከቅባት እቃው ውስጥ መጠነኛ ቅባት በሌባ ጣቷ ዝቃ መዳፏ ላይ እያሳረፈች በሁለት እጆቿ ታርመጠምጠዋለች። ከዛ መላጣ ራሴን ትቀባዋለች። አቤት ያኔ የምሆነው መሆን..ገና ቅባት ልትቀባኝ እንደሆነ ሳስብ ነበር ልቤ የሚርደው። እናቴ ሳትቆርጠኝ ላጭታኝ አታውቅም። ቅባቱን መላጣዬ ላይ ስትለቀልቀው በጣም ያቃጥለኛል። ያኔ ነፍሴ ከልቤ ውስጥ መሹለክ ይቃጣታል። ያኔ ምን ያክል እንደገበጠችኝ አውቃለሁ።
ከመላጣነቴ በኋላ እናቴ ፀጉር ያለኝ እየመሰላት እጇን ወደ አናቴ ስትሰድ ከመላጣ አናቴ ጋር ትገናኛለች። በእናቴ መሳሳት በውስጤ እስቃለሁ። እሷም ጣቶቿን ለመላጣ ራሴ ሳትነፍግ ወዲያ ወዲህ ታርመሰምሳቸዋለች።
ከእናቴ ጋር ያለኝ ቁርኝት ሞቼም የሚከተለኝ ይመስለኛል። በወዲያኛውም ዓለም ከእናቴ ነፍስ ጋር ዳግም የምጫወት ይመስለኛል። የትም ይሁን መቼም እናቴ አጠገቤ ካለች እጇ ጭንቅላቴ ላይ ነው። ሲዳብሰኝ..ሲያሻሸኝ የማገኘው ደስታ ዛሬም ውስጤ ይላወሳል። ነፍሴ በዚህ ሁሉ የዘመን እንደናቴ መዳፍ ደስታ ጎብኟት አያውቅም። ከነፍሷ ያጋራችኝ ዛሬም ድረስ የሚከተለኝ ስውር ዳና አለ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ነሐሴ 3/2016 ዓ.ም