የብሄራዊ ስታዲየም ምዕራፍ ሁለት ሎት አንድ የግንባታ ስምምነት በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና በቻይና ኮንስትራክሽን ኮሚዩኒኬሽን ካምፓኒ (CCCC) መካከል ከትናንት በስቲያ ተደርጓል፡፡ ይህ የግንባታ ምዕራፍ በአንድ ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቅ መሆኑም ታውቋል፡፡
ግንባታው በ2008ዓ.ም የተጀመረው ብሄራዊ ስታዲየም የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው የተጠናቀቀ ቢሆንም፤ ስራውን ለማስቀጠል ከተቋራጩ ጋር በተፈጠረ ልዩነት ምክንያት ተቋርጦ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ከሰሞኑም የምዕራፍ ሁለት ግንባታውን ለመቀጠል የሚያስችል ስምምነት በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና በቻይና ኮሚዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ (CCCC) መካከል ተደርጓል፡፡ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ እና የተቋራጩ ማናጀር ሚስተር ታኡ ፊርማም ስምምነቱ ተፈጽሟል፡፡ ይህ የግንባታ ምዕራፍ የሚካሄደው በሁለት ተከፍሎ ሲሆን፤ ስምምነቱም የመጀመሪያውን ሎት ለማከናወን የሚያስችል መሆኑ በፊርማ ሥነሥርዓቱ ላይ ተጠቁሟል፡፡
ምዕራፍ አንድ ስራው ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀው የግንባታው ቀሪዎቹን ስራዎች በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ በማጠናቀቅ ወደ ሎት ሁለት የሚሸጋገርም ይሆናል፡፡ በስምምነቱ መሰረትም በስታዲየሙ ውስጥ እንዲሁም ውጪ የሚቀሩ ግንባታዎች ይከናወናሉ፡፡ ይኸውም ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የእግር ኳስ ሜዳ፣ ማሟሟቂያ፣ የመሮጫ መም፣ የ60ሺ ወንበር ገጠማና ሌሎችንም የሚያጠቃልል ይሆናል፡፡ የቴክኖሎጂ ስራዎች እንዲሁም በስታዲየሙ ውስጥ ያሉ ዘርፈብዙ ክፍሎች የማጠቃለያ፣ የኤሌክትሪክና ፍሳሽ ማስተላለፊያ መስመሮች ዝርጋታ እንዲሁም ከስታዲየሙ ውጪ 3ሺ500 ሰዎችን የመያዝ አቅም ያለው ሜዳ፣ ቅጥር ግቢ ማስዋብ፣ የመኪና ማቆሚያ፣ የእግረኛ መንገዶችና ሌሎች ግንባታዎችም ይከናወናሉ፡፡
ስራው በውጪ ምንዛሬ የሚከናወን ሲሆን፤ የሁለተኛ ምዕራፍ ሎት አንድ ስራዎችን ለማጠናቀቅ የሚያስችለው 50 ሚሊዮን ዶላርም ከዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ መንግሥት ተገኝቷል፡፡ ይህም ገንዘብ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ጥረት የተገኘ መሆኑም ነው በስምምነት ሥነሥርዓቱ ላይ የተጠቀሰው። የጣሪያ፣ ለንግድ ሥራ የሚውሉ ክፍሎች እና የሌሎች ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታን የሚመለከተው ሥራ ደግሞ በሎት ሁለት የሚቀጥል ሲሆን፤ ይኸውም በኢትዮጵያ ገንዘብ የሚከናወን ይሆናል፡፡
የብሄራዊ ስታዲየም ስትራክቸራል ዲዛይን አዘጋጅና አማካሪ ድርጅት የሆነው ኤችኤም ኢንጂነሪንግ ማኔጂንግ ዳይሬክተር መሰለ ኃይሌ፤ ከዚህ ቀደም የምዕራፍ ሁለት ግንባታ ጨረታ ቢወጣም በውጪ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት መቋረጡን ያስታውሳሉ፡፡
ችግሩን ለመቅረፍም ሁለተኛውን የግንባታ ምዕራፍ ለሁለት በመክፈል በውጪ ምንዛሬ እና በሀገር ውስጥ ገንዘብ የሚካሄድ ይሆናል። የሎት አንድ ግንባታ ውስጥ የተካተቱ ስራዎች ዓለም አቀፍ የስፖርት ተቋማትን መስፈርት አሟልቶ የሚካሄድ ሲሆን፤ የአንድ ዓመት የጊዜ ገደብም ተቀምጦለታል፡፡ የሎት ሁለት ስራዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ የስታዲየሙ ግንባታ ተጠናቆም እአአ በ2029 የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ያስችላል በሚልም ይጠበቃል፡፡
በርካታ ግንባታዎች በሚከናወኑባት ኢትዮጵያ ሜዳዎቿ ከደረጃ በታች በሚል ዓለም አቀፍ ውድድሮችን እንዳያካሂዱ መታገዳቸው ይታወቃል፡፡ ይህንን ተከትሎም የብሄራዊ ስታዲየም ግንባታ ይኸው እጣ ፋንታ እንዳደርሰው ያሰጋል፡፡ በኢትዮጵያ 13 ስታዲየሞች (ብሄራዊ ስታዲየምን ጨምሮ፣ ባህርዳር፣ ሃዋሳ፣ አሶሳ፣ ሰመራ፣ አምቦ፣ ነቀምት፣…) ግንባታ ውስጥ የተሳተፈው የኤችኤም ኢንጂነሪንግ አማካሪ ድርጅት በበኩሉ ሁሉም ደረጃቸውን ጠብቀው መካሄዳቸውን ያረጋግጣል።
በዓለም አቀፎቹ ተቋማት በልኬት የሚቀመጡትን እያንዳንዱን መስፈርት በመጠበቅ ግንባታዎች ስለሚከናወኑ በዚህ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች የሉም። ነገር ግን በበጀት እጥረት ምክንያት አንዳንድ ስራዎች የሚከናወኑት በግማሽ ነው፤ ይህም ማለት አህጉር እና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማከናወን የሚያስችሉ እንዳልሆነም ዳይሬክተሩ ይጠቁማሉ፡፡
በተጨማሪም እንደ አፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ያሉ ተቋማት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የተቀመጠ መስፈርት ሳይኖራቸው ነበር ‹‹ያሟላል፣ አያሟላም›› የሚሉት፡፡ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ መስፈርት አያሟሉም ከተባሉት ስታዲየሞች ባነሱ ሜዳዎች ውድድር መደረጉም ለዚህ ማሳያ ይሆናል፡፡ በየጊዜው የሚጨመሩ ማሻሻያዎችም ከዚህ ይካተታል፡፡ ነገር ግን ካፍ እአአ ከ2023 አንስቶ የራሱን መስፈርት በማዘጋጀቱ የብሄራዊ ስታዲየም ግንባታም ይህንኑ ያማከለና አዳዲስ ማሻሻዎችን ጭምር ያካተተ እንደሚሆንም ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 2 / 2016 ዓ.ም