ሙስና በፀረ-ሙስና ይስቃል

ኢሕአዴግ በትረ መንግሥቱን ከጨበጠ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የፌዴራል ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ተቋቋመ። ዓላማው ስሙም እንደሚናገረው ሙስናን ማጥፋት ነው፤ ግን ኮሚሽኑ ሲቋቋም ሙስናን ከማጥፋት ይልቅ ለማስፋፋት የተቋቋመ ይመስል ሙስናን በሀገሪቱ ሰፍቶ ተንሠራፍቶ አገኘነው።

በወቅቱ ፀረ-ሙስና ስሙን ታቅፎ ጽሞናን ተደግፎ እያየ እንዳላየ እየሰማ እንዳልሰማ ሆኖ ተገኘ። በሙስና የደለቡ ባለሥልጣናትን እያዩ እንዳላዩ በማለፍ የተወሰኑ በሙስና ተዘፍቀው ተገኙ የተባሉ መናኛ ካድሬዎች በየጊዜው እንዲከሰሱ ይደረግ ነበር። ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ በፖለቲካ ተቃርኖ በመታከክ የተከሰሱና የታሠሩ ነበሩበት። እነታምራት ላይኔ እነ ስዬ አብርሃ በስኳር ሙስና ስም ተከሰው ነበር። ዋና ዋና ሙስና ላይ ሲዋኙበት የነበሩ የሚከሰሱ ስላልነበሩ የልብ ልብ ተሰምቷቸው እስከመጨረሻው በድርጊታቸው ቀጥለውበታል። እነሱ የገዥው መደብ አካል ናቸዋ! ተብሎ ታለፉ። ‹‹ሰማይ አይታረስ ንጉሥ አይከሰስ›› የሚለውን ብሂል በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ንጉሦች ዘመን ተተግብሮ ዓየነው። ለነገሩ የላይኞቹን ቢነካ ኖሮ ፀረ ሙስና ራሱ ውሃ ውስጥ እንደገባ ሳሙና ይሟሟ ነበር።

ሙስና ቃሉ የግዕዝ ነው፤ አማሰነ ሲባል አባከነ አጠፋ ከሚለው ቃል ተመሳሳይ ነው። ሙስና በአማርኛ ጉቦ የሚለው ቃል ነው። ቦጋለ አሰፋ የሕዝባዊ ወያኔ አርነት ትግራይ እና የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ የንግድ ኢምፓየር በሚል ርዕስ በ1996 ዓ.ም ባወጡት መጽሐፍ፤ የሕወሓት 56 ሁለገብ ድርጅቶች በሥሩ ያሉ ንዑስ ድርጅቶች ሳይጨመሩ ከ3ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ነበራቸው። ማን እንደዘረፈኝ … ልቤ እያስተዋለ የለመደው አፌ … የመንግሥት ያለህ አለ! የሚለው ሥነ ቃላዊ ግጥምም ዘራፊዎቹ መንግሥት ነን ባዮቹ እንደነበሩ ያሳየናል።

የቀድሞው ፌዴራል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞች በአንድ ወቅት እንደነገሩኝ፤ ለሚሠሩት የስኳር ፕሮጀክት መረጃ የሚሰጥ ቢጢሌ መጽሔት (ቡክሌት) እንዲያዘጋጁ በመመሪያ ትዕዛዝ ይወርድላቸዋል። መጽሔቱን ለመዘጋጀት ተጉ። በዚህ መሐል የተወሰኑ የፋብሪካዎቹ ፕሮጀክት ግንባታዎች በሚካሄድባቸው ቦታዎች አንድ ሁለቱን ለመጎብኘት ጓጉ። ቢጎበኙ ለሥራው እንደሚረዳቸው ለሚመለከታቸው ጠየቁ፤ መጀመሪያ በተሰጣችሁ ትዕዛዝ መሠረት ጽሑፉን ጨርሱና ትሄዳላችሁ ተባሉ። ጽሑፉን እንደጨረሱ ተጨማሪ የመስክ ሥራ ሲጠይቁ የጻፋችሁት በቂ ስለሆነ አያስፈልግም ተባሉና ቢጢሌ መጽሔቱም ታትሞ ተሠራጨ።

መናገር የፈለኩት ስለ መስክ መሄድና መቅረት፣ ስለ መጽሔት መታተምና መሠራጨት አለመሆኑ ይሰመርበት። በአካል የሌሉት መዘዘኞቹ አስር የስኳር ፋብሪካ ግንባታዎች ለሚዲያ ፍጆታ ተብለው ብቻ እንዲዘገቡ ተፈልገው ነው። ቢጢሌ መጽሔቷን ታትማ ወጥታ በወቅቱ ሳነባት የሚያጓጉ ነገሮች ነበሩዋት። ኢትዮጵያ በስኳር ፋብሪካዎቹ ግንባታ ምርታማ ውጤታማ እንደምትሆን ይጠቅሳል። ከንጉሡ ጊዜ ጀምሮ በቡና ላኪነት ትልቁን የውጪ ምንዛሪ የምታገኘው ሀገራችን በስኳር የውጪ ንግድ ገቢ፤ የቡናን ቀዳሚ የውጪ ገቢ ቦታ ትረከባለች የሚል ሀሳብ ነበረው።

እነ ኩባን በስኳር ኤክስፖርት ትፎካከራለች ትቀድማች፤ ብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል ያገኛሉ፤ ብዙ ከተሞች ይስፋፋሉ ይመሠረታሉ የሚሉ ሕልሞችን (ዕቅዶችን ለማለት ስለ ከበደኝም እንደሆነ እወቁልኝ) ይዛ ነበር። ሕልሞቹ ሕልም ሆነው እልም ብለው ቀሩ። የስኳር ፕሮጀክቶቹ እንደ ስኳር ሟሙ። የወቅቱ ባለሥልጣኖች በስኳር ሙስና ተዘፈቁ። ተደብቆ እየዳኸ የነበረው ሙስና ፤ ቀና ብሎ ከመሄድ አልፎ በአደባባይ መሮጥ ጀመረ።

አሥር ስኳር ፋብሪካዎች ይከፈታሉ ተብሎ፤ ለግንባታዎቹም ከውጪ ገንዘብ በብድር መጣ። በተመረጡት ቦታዎች ገበሬዎች እንዲለቁ፤ እንዲፈናቀሉ ተደረገ፤ ሕዝቡ ቅር እያለው ማለት ነው። የአባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ገዳምም ፋብሪካው ከሚመሠረትበት አንዱ ነበር። ገዳሙና መንግሥት መስማማት አልቻሉም። ገዢዎቹ እንገነባለን ሲሉ ከሕዝቡ ጋር ሳይመካከሩ ስለነበር፤ ገንዘቡም ባከኖ ቀረ። ሌሎቹን የሙስና ጉዳዮች ብናነሳ ቦታ አይበቃንም። ሜቴክ ብቻ የዘረፈው ብር በራሱ ምትክ የለሽ ነው። ይህ ሁሉ ሲሆን ሲነገረን የነበረው፤ ባለ ሁለት አኅዝ ዕድገት አስመዘገብን ተብሎ ነበር። የተመዘገበው ዕድገት ግን አልታይ ያለን ጥቁር ሰሌዳ ላይ ተጽፎ ምቀኞች አጥፍተውት ይሆን እንዴ? ብለን ለረጅም ዓመታት ስንጨነቅ ኖረናል።

አንዳንዶች ለሙስና እንደ ኢሕአዴግ ሥርወ መንግሥት ምቹ ዘመን አልነበረም ይላሉ። ከደርግ ዘመን ጋር ሲያነፃፅሩት ማለት ነው። በደርግ ጊዜ የሠርቶ አደሩ የቁጥጥር ኮሚቴ የሚል ነገር ነበር። ዓላማው ጉቦን መከላከል ነበር፤ አልፎ አልፎ ጉቦ ነገሮች ቢኖሩም ተስፋፍቶና ተንሠራፍቶ የተገኘው በኢሕአዴግ ዘመን ነው ብለው ይናገራሉ።

ተቋማትን ነፃና ገለልተኛ አድርጎ ከማደራጀት፣ ብቁ አመራሮችንና ባለሙያዎችን ከመመደብ፣ ሕግና ሥርዓት በማስፈን ግልጽነትና ተጠያቂነትን ከማስፈን አኳያ ትልልቅ ሥራዎችን ማቀድ ተገቢ ነው። የዘፈቀደ አመራር ለብልሹ አሠራሮች ምክንያት በመሆኑ በርካታ ችግሮች አጋጥመዋል። ኢትዮጵያ ከማንም ጫና መላቀቅ የምትችለው በሥርዓት ስትመራ ብቻ ነው። በመንግሥት መሥሪያ ቤት ብቻ እየዞሩ ገቢህ ስንት ነው? ምን አለህ? ብቻ ብሎ መዝግቦ ፀረ-ሙስና እየሠራሁ ነው ብሎ ካሰበ ውጤት እንደማይመጣ ያለፈው ልምዳችን ምስክር ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር) ሙስናን አስመልክቶ ሲናገሩ ‹‹ሌብነት ነቀርሳ ነው፣ ሌባ ሰው ምንም ቢሆን ዋጋ የለውም። ለራሱም ለልጆቹም ዋጋ የለውም፣ ልንዋጋውና ልናቆመው ይገባል፤›› ማለታቸው ለማቆም መረባረብ እንዳለብን ማሳያ ነው።

በርግጥ ያለንበት ወቅት ስለሙስናም ስለ ሕልውና የምናስብበት ነው። እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የሚሉ ቡድኖች እኛ ሀገር ካልመራን ዐሻራ እንነቅላለን፣ አቧራ እናቦናለን፣ እናሸብራለን፣ እንበታትናለን ብለው ተነስተዋል። ለሀገር የማያስቡ የራሳቸውን ጥቅም የሚያሳድዱ መሆናቸውን ማሳያ ይሆናል። በየቦታው ሁከትና እግት እየፈጠሩ ብር እየጠየቁ ነው። እነዚህ ሌቦች ናቸው እንዴ ሀገር የሚመሩት? የተነገደበት ሀገር ወዳዱ የትግራይ ሕዝብንም እያየው ነው። ከድህነት ማጥ እናወጣለን ብለው፤ ልጁን ለጦርነት እየማገዱት አባትና እናትን ኀዘንና ጭንቀት ድህነትና አዘቅት፣ ድርቅ ውስጥ ከተቱት።

ከለውጡ ዓመታት ወዲህ አመርቂ ሥራዎችን ተሠርተዋል። ሙስና ግን እንዳለ ነው። በሙስና ምክንያት ቆሞ የነበረው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሥራ እንኳ ተነቃቃ፤ ውጤታማ ሆነ። የግድቡ ወደ ፍፃሜው መድረሱ በራሱ ኩራት ነው። ኤሌክትሪክ በማመንጨት የበለጠ የውጪ ገቢ እየሰበሰብን ነው። ክረምቱን ጠብቆ ሲከናወን የነበረው የአረንጓዴ ዐሻራ ዘመቻ የሃገራችንን ስም በዓለም አቀፍ ደረጃ እያስጠራ ነው። ሌሎች ብዙ አመርቂ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። ሆኖም ከቀበሌ እስከ ላይኛው እርከን ሙስና አሁንም እየተከተለን ነው። እያንዳንዷን ጉዳይ ለማስፈጸመም እጅን ኪስ ውስጥ መክተት ግድ ሆኗል።

ሙሰኞች በዚህ ብቻ አያበቁም። የእነሱ ሆድ እስኪጠረቃ በረባ ባልረባው ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ በማድረግ በጨለማ ሕዝቡን ሲዘርፉት ይታያሉ። ለውጡን ሊያናውጡ የሚፈልጉ በየቦታው ሁከት ሊፈጥሩ እየተፍጨረጨሩ ነው። ዜጋውና መንግሥት ለሀገር ሕልውና ሲታገል፤ በጎን ተሸሽገው ሙስናቸውን የሚያሳድዱ የውስጥ አርበኞችና ጥቅም አሳዳጆች አሉ። ይህም አጋጣሚው ተጠቅመው ሀገር እየቦረቦሩና እየመዘበሩ ያሉት ሙሰኞች ናቸው።

እነኚህን ከጎናችን ያሉት ሙሰኞችን ከወዲሁ እርምጃ ለመውሰድ ጥረት ማድረግ ይገባል። ተገልጋዩን ከኪሱ እያጎደሉ ራሳቸውን እያደለቡ ነው። እነኚህ ፋኖና ሸኔ ማለት ናቸው። ዜጋው መንግሥትን ላይ ቅሬታ እንዲሰማው የሚታገሉ። በሩቅ ጫካ የሚታገሉትን ብቻ ሳይሆን ከጎናችን ሆነው በሙስና የሚወጉን መውጋት አለብን።

ባለፈው ሐምሌ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባቀረበው ሪፖርት ሙስናን መከላከል በዓመቱ 2.1 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም 46.4 ሚሊዮን ካሬ ሜትር የከተማና ገጠር መሬት ከሙስናና ምዝበራ ወንጀል መታደጉን ይፋ አድርጓል። የ175 ሺሕ አመራሮችንና የሥራ ኃላፊዎችን ሀብት ምዝገባ ማከናወኑን ያመለከተው ኮሚሽኑ በግዥ፣ በንብረት ማስወገድ፣ ገቢ አሰባሰብ በመሳሰሉ የመንግሥት ተቋማት የሥራ ክዋኔዎች ሒደት ሊፈጸሙ ይችሉ የነበሩ በርካታ የሙስና ነክ ወንጀሎችን መታደግ ስለመቻሉ ይዘረዝራል። በዚህም ሙስና መከላከል ላይ ጥሩ መሥራቱን ያትታል።

እኛ ግን መች ተነካና ይቀራል ገና እንለዋለን። ከወንጀል መታደጉን እናደንቃለን። ግን ሙስና ኮሚሽን በሙስና የወደቁትን ሰዎች እያነሳ እስከ መቼ ይቀጥላል? በሙስና የወደቁትን አንሱ የሚል መ.ያ.ድ. ያለ ይመስላል። መች ነው የሚከሳቸው? ሕዝብ እየከሰሰ ነው። ስለዚህም ሙሰኞች ፍርድ አደባባይ ቆመው የእጃቸውን እንዲያገኙ ሕዝብ ይፈልጋል።

የወረዳ አመራሮችም መሬት አስተዳደር ወሳኝ ኩነቶች፣ ገቢዎች ቢሮዎችና መብራት ኃይል እየተባለ የሚታመው መብራት ኃይል፣ የኢሚግሬሽን፣ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች በሙስና አንጋፋ መሆኑን ያስመሰከረው ዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ሳይዘነጋ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች ሌሎችም ተገልጋይ በማጉላላት የሚታሙ ራሳቸውን ሊፈትሹ ይገባል። ገቢዎች ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ ባለፉት ወራት ሐሰተኛ ደረሰኝ ብቻ እየሸጡ የሃገር ሀብት ወደ ኪሳቸው ሲያስገቡ የነበሩ 63 ድርጅቶችን አጋልጦ ነበር።

በገቢዎች ሚኒስቴር አዳማ ቅ/ጽ/ቤት 1ነጥብ5 ሚሊዮን ብር ጉቦ ለመቀበል ተስማምተው የቅድሚያ ክፍያ 500 ሺህ ብር ሲቀበል እጅ ከፍንጅ መያዙን ሰምተናል። በተመሳሳይ በሚኒስቴሩ ምስራቅ አዲስ አበባ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅ/ጽ/ቤት 5 ሚሊዮን ብር ለመቀበል ተስማምተው የመጀመሪያ ክፍያ 200ሺህ ብር ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውንም አድምጠናል።

በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ሞጆ ቅ/ጽ/ቤት 200 ሺህ ብር ሲቀበል እጅ ከፍንጅ መያዙን በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት መረጃው ደርሶናል። እንዲሁም በገቢዎች በሚኒስቴሩ በመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቅ/ጽቤት ሁለት ኦዲተሮች 12 ሚሊዮን ብር ጉቦ ለመቀበል ተስማምተው የመጀመሪያ ክፍያ 100 ሺ ብር ለመቀበል በሂደት ላይ እያሉ እጅ ከፍንጅ ለመያዝ መቻሉን አድምጠናል።

ከላይ በተወሰዱት እርምጃዎች ያልተማሩ የውስጥና የውጭ ሌቦች ዛሬም በተቀናጀ መንገድ የሀገርና የሕዝብ ሀብት የሆነውን ከፍተኛ የታክስ ገንዘብ ለድርጅቱ እንዲቀር በማድረግ ይህን ለሚሠሩበት ውለታ 3ነጥብ7 ሚሊዮን ብር ወደ ግላቸው ሊያስገቡ ሲሉ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

እንዲሁም ሰሞኑን በወጣ ዜና በወላይታ ዞን ዳሞት ወይዴ ወረዳ ከኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ጋር በመተባበር ወንጀል ሲፈጽም በመገኘት የተጠረጠረ የወረዳው ፖሊስ አዛዥ በቁጥጥር ስር ሆኖ ምርመራ መቀጠሉን የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ም/ኮ/ር ንጋቱ ጌታቸው አስታውቀዋል።

ከመንግሥትና ከሕዝብ የተሰጠውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ከሕገ ወጥ ነጋዴዎችና ኮንትሮባንዲስቶች ጋር በመተባበር ከወላይታ ሶዶ እስከ ሞያሌ ድረስ የሌብነት መስመር በመዘርጋት የዞኑንና የወረዳውን ሕጋዊ ነጋዴዎች እንዲዳከሙ ከማድረጉም በላይ መንግሥት የጀመረውን የብልፅግና ጉዞ የሚያደናቅፍ ተግባር መፈጸሙን የወረዳው አጠቃላይ የፖሊስ አመራርና አባላት በተገኙበት በተደረገ የግምገማ መድረክ በመረጋገጡና በሙስናና ብልሹ አሠራር የተዘፈቀ መሆኑ ገልጸዋል።

ከዚሁ ጎን የትራንስፖርቱም ዘርፍ መንቀራፈፍ ይታይ። የተሳፋሪውን ጋጋታ እንደ ሠርግና ምላሽ የሚቆጥሩ አሽከርካሪዎች ከታሪፍ ውጪ በእጥፍ እያስከፈሉ ነው። «መኪና የለም ከፈለክ ተሳፈር፤ ካልፈለክ ሌላው ይሳፈራል» እያሉ ተሳፋሪውን የሚያመናጭቁ በዝተዋል። አዲስ አበባ ያለው የትራንስፖርት ችግር እንዳለ ሆኖ ወደ ተለያዩ ገጠራማ አካባቢዎች መሳፈር የሚፈልጉ በእጥፍ እንዲከፍሉ እንደሚጠየቁ በመናኸሪያዎች የሚታይ ነው። እንዳይጠየቁም 50 ብር የሚያስከፍለውን መንገድ እጥፍ ክፍያ አስከፍለው የ50 ብር ደረሰኝ ይሰጣሉ። ሁነቱ የሙስና ጎዳና ስለሆነ የሚመለከታቸው ይመልከቱት።

ሙስናው በየቦታው የበዛው የሚመለከተው አካል ስለማይመለከተው ይመስለኛል። የፌዴራል ኦዲተር መሥሪያ ቤት በሚያቀርበው ሪፖርት የባከኑ ገንዘቦች ተሰምተዋል። ፀረ ሙስና በዚህ ረገድ ድምፁ ምንም አይሰማም። በየመሥሪያ ቤቱ ገንዘብ አላግባብ ሲወድም የየቢሮው ኦዲተሮችና የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ‹ሠራተኞች› ተጠያቂ መሆንም አለባቸው። ተጠያቂ ካልሆኑና ኃላፊዎች ብቻ ቢያዙ አሠራሩ ‹‹ከመረቁ አውጡልኝ ከሥጋው ፆመኛ ነኝ›› እንደሚሉት ብሂል ይሆናል።

በሕግ ብያኔ ሰው በሁለት ይከፈላል፤ የተፈጥሮ ሰውና በሕግ ሕጋዊ ሰውነት የተሰጠው ተቋም። ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሕጋዊ ሰውነት አለው። ኮሚሽኑ ካሸለበበት ይንቃ፤ ሳስበው ሙስና በፀረ ሙስና እየሳቀ ይመስለኛል። አንድ ወዳጄ ሙስናን ለምን ቦልድ አደረከው (አደለብከው) ብሎ ጠየቀኝ ያው ሙስና እየደለበ ፀረ ሙስና እየሳሳ ስለሆነ ነው አልኩት። ኮሚሽኑ ከፌዴራልና ከክልል ኦዲተር መሥሪያ ቤቶች ጋር ያለውን ግንኙነት ያጠናክር። ለተለያዩ ሕዝባዊ አገልግሎቶች ከሕዝብ ገንዘብ ሲሰበሰብ ነበር፤ የሕዝቡን ተሳትፎ የአስፈፃሚዎችን ትጋት ማበረታታት ይገባል። ነገር ግን ገንዘቡ ለሚፈለገው ዓላማ መዋሉን አለመመዝበሩን የሚፈትሹ ደግሞ ይንቁ።

በአጠቃላይ ጸረ ሙስና ይጧጧፍ!

ይቤ ከደጃች .ውቤ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 2 / 2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

 

 

Recommended For You