‹‹ክረምቱ እስከሚጠናቀቅ እስከ አምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሜካናይዜሽን ለማረስ እየሠራን ነው›› -አቶ ኢሳያስ ለማ በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሚባለውንና አብዛኛው የሃገሪቱ ሕዝብ የሚተዳደርበትን የግብርና ዘርፉን ለማሳደግ መንግሥት የተለያዩ የልማት መርሐ-ግብሮችን ቀርፆ በመሥራት ላይ ይገኛል። በተለይም የተበጣጠሰ መሬትን መሠረት ያደረገውን ኋላቀር የአስተራረስ ሂደትን በኩታ ገጠም (ክላስተር) እርሻ ሥርዓት በመለወጥ፤ በተቀናጀ መልኩ የቴክኖሎጂና ሜካናይዜሽን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት አበረታች ውጤት እያስገኘ ነው።

በተለይም ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ላይ የተጀመረው ሥራ እንደሃገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ሁነኛ አቅም እየፈጠረ ከመሆኑም ባሻገር ለሌሎች የአፍሪካ ሃገራት አብነት መሆን እየቻለም ጭምር ነው። በዘንድሮ ክረምት ያለውን የዝናብ ወቅት በመጠቀም አርሶአደሩን በክላስተር የማደራጀትና የሚታረሱ መሬቶችን የማስፋት ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ማስገንዘባቸው ይታወሳል። ከዚህ አንፃር ምን እየተሠራ ነው? ስንል በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኢሳያስ ለማን ጠይቀናል። እንደሚከተለው ይቀርባል።

 አዲስ ዘመን፡- እንደሃገር የኩታ ገጠም (የክላስተር) እርሻ መስፋፋት ያለውን ፋይዳ ያብራሩልንና ውይይታችን እንጀምር?

አቶ ኢሳያስ፡- ኩታ ገጠም እንደአጠቃላይ ስንመለከተው ከቃሉ ስንጀምር (Agricultural Mechanization Cluster ) የሚለውን የእንግሊዘኛ ቃል ለመተካት የመጣ ነው። የዚህ አደረጃጀት ዋና ዓላማ ሲባል ማሳቸው በድንበር የሚዋሰኑ አርሶአደሮች በጋራ አቅደው በጋራ እንዲሠሩ ማድረግ ነው። ይህ አርሶአደሩን በጋራ እንዲሠራ የማድረግ ስትራቴጂ በተለያየ ጊዜ ተሞክሮ ነበር፤ ሆኖም በሚፈለገው ደረጃ ውጤት አላመጣም። ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ግን ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን ፓይለት በማድረግ የተጀመረው ሥራ አበረታች የሚባል ለውጥ እያመጣ ነው። የክላስተር አደረጃጀት ዋና ዓላማው አርሶአደር የመወሰንና የመደራደር አቅምን ለማጎልበት፤ እንዲሁም ደግሞ በጋራ ሠርቶ በጋራ የማደግ እሴቶችን ከፍ ማድረግ ነው።

ይህም ሲባል ለምሳሌ በተናጠል በሚካሄደው የእርሻ አሠራር አንድ አርሶአደር ዘር ቢፈልግና ቢጠይቅ ለማግኘት አዳጋች ይሆንበታል። ድር ቢያብር አንበሳ ያስር እንደሚባለው ሁሉ በጋራ ሆነው ቢጠይቁ ግን ይበልጥ ተደማጭ ይሆናሉ፤ ድጋፍ ለሚያደርገው መንግሥትም ሆነ አቅራቢ ድርጅቶች ቀላል ስለሚሆን አርሶአደሩ ማንኛውንም ግብዓት ለማግኘት አይቸገርም። ከዚህ ባሻገር ግን በጋራ መሥራቱ አንዱ ያለው መልካም ተሞክሮ ለሌላው መነሳሳት ምክንያት እንዲሆን ያደርጋል። ቡድን ስለሆኑ በጋራ የሚያቅዱበት፣ የሚያርሱበት፣ ያመረቱትን ደግሞ የሚሰበስቡበት ሁኔታ መፍጠር ያስችላል። እንደአጠቃላይ ከእቅድ ጀምሮ እስከሽያጭ ድረስ ያሉትን ሥራዎች በጋራ የሚሠራበትና የአርሶኦደሩን አቅም ማጎልበት የሚያስችል ሥርዓት ነው።

ይህ ሲባል ግን መሬት ማዋሓድ ማለት አይደለም፤ ወይም የቀድሞውን ድንበር አጥፍቶ አንድ ላይ መቀላቀል ማለት አይደለም፤ ይልቁንም ሁሉም የየራሱን መሬት ይዞ በጋራ ያርሳል፤ ተመሳሳይ ሰብል ይዘራል፤ አንድ ላይ ሆኖ ያጭዳል። ገበያም በጋራ ሆነው ነው የሚደራደሩት። የሚደራጁትም ሆነ የሚዘሩትን ሰብል የሚመርጡት ራሳቸው ናቸው። በግዳጅ አናደራጅም፤ የማይፈልጉትንም ዘር እንዲዘሩ አናደርግም። ግን ደግሞ ሃገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ሰብሎች እንዲመርጡ እናደርጋለን፤ ይህ ሲሆን ደግሞ መንግሥት የሚደግፋቸው ሰብሎች ላይ ቢያተኩሩ ምክረ ሃሳብ እንሰጣቸዋለን።

በነገራችን ላይ በክላስተር አሠራር የመጀመሪያ የምንመርጠው ወረዳዎችን ነው፤ ከወረዳው ደግሞ የተወሰኑ ቀበሌዎች ውስጥ ያሉ የአርሶ አደር ቡድኖችን ይለያሉ። በእነዚህ አደረጃጀቶች ከ15 እስከ 30 የሚሆኑና የጋራ መሬታቸው ከ15 ሄክታር ያላነሰ አርሶአደሮችን በጋራ የሚሠሩበትን ሂደት ነው። በአንድ ወረዳ ላይ ኩታ ገጠሞች አስርም 20 ሊሆኑ ይችላሉ። በኩታ ገጠም ውስጥ ጠንካራም ሆነ ደካማ ገበሬ ይኖራል፤ ሆኖም አንዱ ሌላውን እያነቃና እየደገፈ በጋራ የሚሠራበትና የሚያድግበት ሥርዓት ነው።

እንደአጠቃላይ በኩታ ገጠም የምንሠራው እርሻ የሰብል ምርጫቸውን ወስደን ድጋፍ እናደርግላቸዋለን። በተቻለ መጠን የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውን ማሳደግ ትልቁ ሥራ ነው። ይህንን ስናድርግ ከፍተኛ አምራች ለሆኑ አካባቢዎች ቅድሚያ እንሰጣለን። ምክንያቱም ክላስተር የማይሆኑ ቦታዎች ደግሞ አሉ። ለምሳሌ ለዓመት የሚሆን ቀለብ ማምረት የማይችሉና በሴፍትኔት የሚረዱ አካባቢዎች አሉ። እነዚህ አካባቢዎች ላይ ከክላስተር ይልቅ ሌሎች አማራጮችን መጠቀም ነው የሚያሻው። ክላስተር መሆን የሚችሉት አምራች አካባቢዎችና ቢደገፉ ምርት መስጠት የሚችሉ ናቸው። በዚህ ሂደት አርሶአደሩ ዘርም ራሱ ነው የሚገዛው፤ ምርቱንም የሚሸጠው በራሱ ነው። ግን አንድ ላይ ሆነው ምርት ካመረቱ በኋላ የመደራደር አቅማቸውን ያሳድጋል።

አዲስ ዘመን፡- እስካሁን ባለው ሂደት አብዛኛው አርሶአደር የተበጣጠሰ መሬት ላይ በሚሠራበት ሁኔታ እንደሃገር ምን አሳጥቶናል? ግብርናው ለኢኮኖሚው እድገት የበኩሉን ሚና እንዳይጫወት የነበረው አሉታዊ አስተዋፅዖ እንዴት ይገለፃል?

አቶ ኢሳያስ፡– አንደኛ ነገር በኢትዮጵያ የመሬት ስሪት መሠረት አብዛኛው መሬት የተያዘው በአርሶአደር ነው። 80 በመቶ የሚሆነው ኅብረተሰባችን የሚኖረው በገጠር ነው። ይህ ሕዝብ ደግሞ ዋነኛ መተዳደሪያው እርሻ ነው። የተለያዩ ሃገሮች የተለያየ ተሞክሮ አላቸው። ለምሳሌ መሬት ለአርሶአደር በመሸጥ የተወሰኑ ሰፋፊ ባለሃብቶችን በመፍጠር ሃገራዊ ምርት ፍላጎትን ለማሳካት ጥረት የሚያደርጉ አሉ። ብዙ ሃገሮች ላይ ይህ አይነቱ አሠራር የተለመደ ነው።

እኛ ሃገር አርሶአደሩ ከመሬት ጋር በተያያዘ ካለው አመለካከት አኳያና ዘርፉ የሚይዘው ሰፊ የሰው ኃይል አንፃር አዋጭነቱ እምብዛም ነው። በነገራችን ላይ ‹‹ጥቂት ሰዎች ናቸው ገበሬ መሆን ያለባቸው›› የሚለው አስተሳሰብ የኢንዱስትሪ አብዮቱን ተከትሎ የመጣ ሲሆን፤ አርሶአደሩ መሬቱን ለቆ ወደ ከተማ የገባበት፤ ብዙዎች ሰዎች በኢንዱስትሪ የሚቀጠሩበት፤ ጥቂት ደግሞ ሰፊ እርሻ ይዘው የሃገሪቱን የምግብ ፍላጎት፤ ኤክስፖርት፣ የተለያዩ አቅም ሊሆኑ የሚችሉበት ብዙ ያደጉ ሃገሮች አሉ።

እንዳልኩሽ ግን እኛ ሃገር ደግሞ አርሶአደሩ መሬት የራሱ በማድረግ ማልማት ነው የሚፈልገው። በመሆኑም መንግሥትም አርሶአደሩ ባለበት በባለሀብት የሚሠራውን ሥራ መሥራት ይቻላል የሚል እምነት አለው። በክላስተር አርሶአደሩን በማደራጀት እስከ ትልቅ አክሲዮን ወይም ድርጅት ድረስ ማሳደግ ይቻላል። ለዚያ ደግሞ ስድስት ደረጃዎችን ማለፍ ይጠይቃል። የመጀመሪያው ነገር ተስማምቶ መሥራት፣ በመቀጠል በጋራ ማቀድና በጋራ መሥራት ነው። ቀጥሎ መሬታቸውን ማዋሓድና ኢንተርፕራይዝ ማድረግ ይችላሉ። በዚህ ሂደት 100 ሄክታር ሊሆን ይችላል፤ እነዚያ ሰዎች ድርጅት አቋቁመው፤ ድርጅታቸው ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ ለሌላ ሰው ሳይሸጡ የሚፈለገውን ግብ ማሳካት ይችላሉ።

ለዚህም ነው እኛም ከዚህ መነሻ ነው በክላስተር የሚፈለገውን ግብ ማሳካት ይቻላል ብለን የጀመርነው። በመሠረቱ የክላስተር አደረጃጀት ለድጋፍም ይመቻል። አስቀድሜ እንደገለፅኩልሽ መንግሥት እያንዳንዱን አርሶአደር ከሚረዳ ክላስተሩን ቢረዳ ይቀለዋል። ነጋዴውም የተመረተውን ምርት በአንድ ጊዜና ቦታ ቢገዛ የተሻለ ይመርጠዋል። በዚህ በክላስተር አሠራር ብዙ ሃገሮች አድገዋል። ጎረቤታችን ኬኒያ ብዙ ሥራዎችን የሠራችው በክላስተር አደረጃጀት ነው። እነብራዚልና ሌሎችም ሃገራት የልማት ኮሪደር እና የተለያየ ስም ሰጥተውት በተመሳሳይ መንገድ ሠርተው ምርታማነታቸውን ማሳደግ ችለዋል።

እንደሚታወቀው የክላስተር አሠራር ምርትን መሠረት ያደረገ አሠራር ነው፤ መንግሥትም ይህን ሥራ ሲጀምር መጀመሪያ በስድስት ሰብሎች፣ በ300 ፓይለት ወረዳዎች ላይ ነበር። አሁን ግን በአብዛኛው የሃገሪቱ ክፍል ላይ እየሄድንበት ነው። በወቅቱ 1ነጥብ 5ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የተጀመረ ሲሆን አሁን 12 ሚሊዮን ሄክታር ደርሰናል። እንዳነሳሽው ከዚህ ቀደም እንደነበረው በተበጣጠሰ መሬት ላይ የሚሠራው የግብርና ሥራ ምርታማነትን ለማሳደግም ሆነ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት ያዳግታል። መንግሥትም ቢሆን 18 ሚሊዮን አርሶ አደርን በተናጠል ከመደገፍ ይልቅ በክላስተር ቢደግፍ የበለጠ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ይችላል። እንዳጠቃላይ በተናጠል ወይም በ0 ነጥብ 5 ሄክታር ላይ የሚታረሰው እርሻ ሃገር እንደማይቀይር ታምኖበትነው ወደዚህ ሥራ የተገባው። በመሠረቱ አርሶአደሩም ቢሆን በጋራ መሥራቱ በተናጠል ከሚያደርገው ጥረት የበለጠ ተጠቃሚ ያደርገዋል፤ የመደራደር አቅሙም ይጎለብታል።

አዲስ ዘመን፡- መደራደር ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?

አቶ ኢሳያስ፡– መደራደር ሲባል ግብይትን ብቻ አይደለም። አስቀድሜ እንደገለፅኩልሽ ግብዓትንም ለመጠየቅ ከግል ይልቅ በጋራ ሲሆን የበለጠ ተቀባይነት አለው። ይህ ደግሞ በተመጣጣኝ ዋጋ ማሽኖችንና ቴክኖሎጂዎችንም ማግኘት ይችላል።አቅማቸውን ካሳደጉ ደግሞ እነዚህን አገልግሎቶች በጋራ መግዛትም ይችላሉ። ወደ ኢንተርፕራይዝ ሲያድጉ የዘር አምራች ድርጅት ይፈጥራሉ። ሃገሪቱም ቢሆን ተመሳሳይ ምርት ከአንድ ቦታ ታገኛለች። ጥራቱን የጠበቀ በተለይ ለፋብሪካ ግብዓት የሚሆን ግብዓት ከማግኘት አንፃር ክላስተር ትልቅ ጠቀሜታ አለው። በተበጣጣሰ መሬት ላይ ግን ሲሆን የተለያዩ ዝርያ ያላቸው የተለያዩ ሰብሎች የሚመረቱ በመሆኑ ውጤታማ መሆን አይቻልም። ለግብይት አይመችም፤ ለኢንዱስትሪውም በቂና ተመሳሳይ ምርት ለማቅረብ አይቻልም። የእኛ ሃገር ተሞክሮ የሚያሳየውም ለፋብሪካ የሚቀርበው የምርት መጠን ለዓመት የሚበቃ አይደለም። እናም ምርታማነት ማደግ አለበት። ምርታማነትን ለማሳደግ ደግሞ ድጋፎቻችን በቡድን ብንደግፍ ውጤት እናመጣለን ብለን በተመረጡ ሰብሎች ላይ ሥራውን የጀመርነው።

አዲስ ዘመን፡- በክላስተር የአስተራረስ ዘዴ የተመረጡ ሰብሎች ላይ ማተኮር ለምን አስፈለገ?

አቶ ኢሳያስ፡- የክላስተር እርሻ ሥራ ስንጀምር ለሃገሪቱ የምግብ ዋስትና ወይም የምግብ አቅርቦት ወሳኝ የሚባሉ ሰብሎችን መርጠን ነው። በተጨማሪም ለፋብሪካ ግብዓትነት፣ ለኤክስፖርት የሚፈለጉ ሰብሎች ላይ ነው ትኩረት ያደረግነው። ሁሉንም ሰብል አንደግፍም፤ በሁሉም ሰብል ግን የአርሶአደሩ የመደራጀት መብቱ የተጠበቀ ነው። ምክንያቱም ደግሞ እንደመንግሥት ሃገሪቱ ባላት ውስን ሃብት መደገፍ የምትችለው በተመረጡት ላይ ብቻ በመሆኑ ነው።

ከዚህ አኳያ በክላስተር አሠራር ላይ ሰፊ ሥልጠና ይሰጣል፤ የግብዓት አጠቃቀም ከመነሻ ጀምሮ ምን እድገት አሳየ የሚሉትን ነገሮች ይታያሉ። ከምርት አንፃር ምንአይነት የምርታማነት እድገት መጣ? የሚለውን ለማወቅ ጥናት ያስፈልጋል። እነዚህ ጉዳዮች ሀብት ይጠይቃሉ። በመሆኑም ጊዜም ገንዘብም የሚፈልግ በመሆኑ መጀመሪያ በውስን ቦታዎች ላይ በተመረጡ ሰብሎች ላይ ነው የጀመርነው። አሁን ደግሞ ክልሎችም በራሳቸው አስፋፍተው እየሠሩ ነው። ለምሳሌ ማሽላ በፌዴራል ደረጃ ለክላስተር የተመረጠ ሰብል አይደለም፤ አማራ ክልል ግን አለ። ደቡብ ላይ ደግሞ ቦሎቄ በስፋት የሚመረት ሰብል እንደመሆኑ በክልሎች ክላስተር አደረጃጀት የማካተት ሥራ ተሠርቷል።

እንደየክልሉ ነበራዊ ሁኔታ ሰብሎች እየተመረጡ ክልሎች በራሳቸው ተነሳሽነት እየሠሩ ይገኛሉ። በመሆኑም ለምግብ ዋስትና፣ ለኢንዱስትሪና ለኤክስፖርት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸውን ሰብሎች ተመርጠው ነው እየተሠራ ያለው። ደግሞም የክላስተር ሥራ በአንድ ጊዜ መሥርተን የምናቆመው ሳይሆን እያንዳንዱ የምርት ክላስተር ኢንተርፕራይዝ እስኪሆን ድረስ ከስድስት እስከ ስምንት ደረጃዎችን ማለፍ የሚጠበቅበት በመሆኑ እዚያ እስኪደርሱ ድረስ የመንግሥት ድጋፍ ይሻሉ። ይህም በተለይ ዘላቂ የምግብ አቅርቦት ከማቅረብ አንፃር ትልቅ ፋይዳ አለው። ከተበጣጠሰ ማሳ የሚሰበሰበው ምርት የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት አያስችልም፤ በሌላ በኩል የማምረቻ ወጪው ከፍተኛ ነው። ይህም አንዳንዴ ከውጭ ከሚገባው በላይ ወጪው የሚበልጥበት ሁኔታ አለ።

አዲስ ዘመን፡- የኩታ ገጠም እርሻ በመንግሥት ደረጃ ከተጀመረ ወዲህ ምን አይነት ተጨባጭ ውጤት መጥቷል? በቀጣይስ ለማስፋት ምን እየተሠራ ነው?

አቶ ኢሳያስ፡- በነገራችን ላይ የክላስተር እርሻ ሲባል ከመደራጀት ባለፈ የዘር ማባዣ ተቋማትን በየአካባቢው ማቋቋም ፣ ያደጉትን ክላስተሮች ወደ ተቋም ከፍ እንዲሉ የመደገፍ ሥራ መሥራት ይጠይቃል። ከዚያ አኳያ የተወሰኑ ክላስተሮች በተሻለ ሁኔታ ላይ አሉ። ለምሳሌ ሄጦሳ ላይ አንድ ክላስተር ወደ ስንዴ የዘር ብዜት ማኅበር አድጓል። ምክንያቱም ያ ክላስተር ጥሩ ሥራ የሠራ እና ጥሩ ቅንጅት ስላለው ሌሎች የዘር አባዥ ተቋማት ከእነሱ ጋር ለመሥራት ይመርጧቸዋል። የተሻለ ግብዓት አጠቃቀም በማምጣት ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ነው ዋናው ዓላማው። ከዚህ አንፃር ጎን ለጎን ከተሠሩ ሥራዎች አንደኛው የሜካናይዜሽን ሥራ ነው።

ለዚህ ደግሞ እንደመንግሥት ከተሠሩ ሥራዎች ውስጥ ከውጭ የሚገቡ እርሻ ማሽኖችን ከታክስ ነፃ ማድረግ ሲሆን፤ በቡድን በማሠራትና በግለሰብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አማካኝነት አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ላይ ድጋፍ ይደረግላቸዋል። የሜካናይዜሽን እርሻን ባለፉት ዓመታት ስንመለከት ሁለት ሚሊዮን ሄክታር ነበር፤ ዘንድሮ በክረምቱ እርሻ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመካናይዝድ መልኩ ታርሷል። ክረምቱ እስከሚጠናቀቅ እስከ አምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሜካናይዜሽን ለማረስ እየሠራን ነው። በክልሎች ድጋፍና ኮላተራል በማስያዝ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሺ በላይ ትራክተሮች ሃገር ውስጥ ገብተዋል። እነዚህ አይነት አገልግሎቶች ክላስተርን ይደግፋሉ። የዘር አቅርቦታችንም ያድጋል ተብሎ ይታመናል።

በክላስተር ተደራጅተው ለሚሠሩ ማዳበሪያና ግብዓቶችንም ቅድሚያ እንዲሰጣቸው የማድረግ ሥራ ተሠርቷል። ይህንን ጠቀሜታ አርሶአደሩ እየተገነዘበ በመሆኑ የመደራጀት ፍላጎቱ ጨምሯል። አንደኛ ነገር ከ30 አርሶአደሮች ውስጥ ብዙ ደካማ አለ፤ ግን ጥቂት ጠንካሮች በመኖራቸው እነዚያን ተከትለው ያርሳሉ። ስለዚህ በዚያ መሠረት ሞዴሎቹ ሌላ ሞዴል እየፈጠሩ ነው ያሉት። ይህ የክላስተር አደረጃጀት ያመጣውን ለውጥ ሲመለከቱ ደግሞ ሌሎችም አርሶአደሮች አደራጁን ወደሚል ሁኔታ መጥተዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ ትልቅ ለውጥ የፈጠርነው ክልሎች የራሳቸው አድርገውታል፤ እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅራቸው የራሳቸውን እቅድ በማዘጋጀት የራሳቸውን ሰብሎች መርጠው ማምረት ጀምረዋል። በዚህም የአትክልትና ፍራፍሬ ሰብሎች ተካተዋል። እንዲሁም በእንስሳት ተዋፅዖ የተደራጀ አለ። በአጠቃላይ በሰብል ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የግብርና ዘርፎች ላይ የመስፋት ሁኔታ ነው ያለው።

አዲስ ዘመን፡- ክላስተር በተለይ ስንዴ ላይ ያመጣው እምርታ እና በሃገር ኢኮኖሚ እድገት ላይ እያበረከተ ያለውን አስተዋፅዖ ቢያብራሩልን?

አቶ ኢሳያስ፡- እንደአጠቃላይ ግብርናው የሃገሪቱ ኢኮኖሚ መሠረት ከሆኑ ዘርፎች ዋነኛው እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ ረገድ ከግብርናው ከሚጠበቁት ነገሮች መካከል የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ነው። እንዲሁም ፋብሪካዎች የሚፈልጉትን የጥሬ እቃ አቅርቦት በበቂ መጠንና በዘላቂነት ማቅረብ፤ ከውጭ በጥሬና እሴት ተጨምሮባቸው የሚመጡ ምርቶችን መቀነስ፤ የኤክስፖርት አቅምን ማሳደግ ነው። ይህም ሲባል ወደ ውጭ የምንልከውን ምርት በብዛትም ሆነ በጥራት በማሳደግ የውጭ ምንዛሪን ግኝትን ከፍ ማድረግ ነው። የመጨረሻው የሥራ ዕድል መፍጠር ነው።

ከዚህ አንፃር ባለፉት ስድስት ዓመታት ከሠራናቸው ሥራዎች ውስጥ ከውጭ የምናስገባው ምርቶችን መቀነስ ችለናል። እንደሚታወቀው ደግሞ ከዚህ ውስጥ ዋነኛ ከፍተኛ ወጪ የሚወጣባቸው ስንዴና ዘይት ነበሩ። እነዚህን ምርቶች በሃገር ውስጥ ለመተካት ለአስር ዓመት አቅደን ሰፊ ሥራ እየሠራን ነው። ለዚህም የቅባትና የአትክልት ሰብሎች እንዲሁም የእንስሳት ተዋፅዖ ምርቶችን የማስፋት እየተሠራ ነው።

ከስንዴ አኳያ በተለይ ባለው ላይ ምርታማነትን ማሳደግ አንደኛው አቅጣጫ ሲሆን ለዚህም የተሻለ የግብዓት አጠቃቀም ማሳደግ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ሲሠራ ነበር። በሁለተኛ ደረጃ የክላስተር እርሻን ማስፋፋት ሲሆን ለዚህም የማይታረስ መሬትን መጨመር ነው። ይህ ሲባልም በዝናብም ሆነ በመስኖ የሚመረተውን መሬት ማስፋት ላይ ሰፊ ርብርብ ተደርጓል። በዚህ ረገድ ስንጀምር በመስኖ የሚታረሰው መሬት 20 ሚሊዮን ሄክታር ብቻ ነበር። አሁን 12 ነጥብ 97 ሚሊዮን ደርሰናል። መሬትን በመጨመር ሂደት ደግሞ የመስኖ አማራጭን መጠቀም የሚለው ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ነው። ግን ምርታማነትን በማሳደግ ሰፊ ሥራ የተሠራበት የክላስተር አሠራር ነው። በተለይ በመኮሮኒ ስንዴና በዳቦ ስንዴ ላይ ሰፊ ሥራዎች ተሠርቷል። በእነዚህም ላይ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው እርሻ በክላስተር እየታረሰ ነው ያለው።

ምርታማነቱን ስንመለከት በክላስተር የሚያርሱ ወደ በአማካኝ 40 ኩንታል ማግኘት ችለዋል። ገና ስንጀምርም እንኳን በመደበኛው 27 ኩንታል ሲመረት በክላስተር እስከ 35 ኩንታል የደረሰበት ሁኔታ አለ። አሁን ደግሞ ወደ ክላስተር እርሻ ማደጉና ለስንዴ ትኩረት በመሰጠቱ ምርታማነታችን ወደ 40 ኩንታል ከፍ ብሏል። እናም በክላስተር ሲሠራ ሁሉም የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ለማሳደግ ጥረት ይደረጋል። እንደአጠቃላይ ስንዴ አሁን ወደ 70 በመቶ አካባቢ በክላስተር የሚታረስበት ሁኔታ አለ። እንደሃገር በአስር ዓመት ሃገር በቀል የልማት መርሐግብር ላይ ያስቀመጥነው መርሕ መሠረት የመጀመሪያ ሥራ ወደ ሃገር ውስጥ የሚገባውን ምርት ቀንሰናል። በተወሰነ ደረጃ ኤክስፖርት ተጀምሯል።

በቀጣይ ደግሞ በሃገር ውስጥ አቅርቦትን ማሳደግ፣ የግብይት ሥርዓቱን ማሻሻል፤ በተለይ እያመረትን ዓለምአቀፍም ሆነ በሃገር ውስጥ ያለውን የዋጋ ንረትና የኢኮኖሚ ጫና ለመቀነስ ግብይት ላይ መሥራት ይገባል ብለን እየተረባረብን ነው። ሌላው ደግሞ በተለይ አሁን የሠራነው ትልቁ ሥራ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ በክልል ፕሬዚዳንቶች መሪነት የተሠራ ሥራ ነው። በቀጣይ ደግሞ ይህ ሥራ መደበኛ ሥራ የማድረግና ሁሉም እንዲሠራውና የግብይት ሥርዓቱ ላይ ያሉ ችግሮችን መፍታት ይገባል፤ ከዚያ ባሻገር ግን ወደ ውጭ የሚላከውን የስንዴ ምርት በማሳደግ የውጭ ምንዛሪ ግኝታችንን ከፍ ማድረግ ይጠበቃል።

አዲስ ዘመን፡- በዚህ የክላስተር ሥራ የምርምር ተቋማት ሚና እንዴት ይገለፃል?፤ አንዳንድ ቦታዎች ላይ በተለይ በቆሎ ላይ የተሻሻሉ ምርጥ ዝርያዎችና የቴክኖሎጂ እጥረት መኖሩን ሲገለፅ እንሰማለን፤ በተመሳሳይ መጤ ተምችና ግሪሳ ወፍን በመከላከል ረገድ ከምርምር ጋር ያላችሁ ጥምረት ምን ይመስላል?

አቶ ኢሳያስ፡– ዘር ላይ ሁለት አይነት ችግር ነው የሚስተዋለው። አንደኛው እንደተባለው የዘር እጥረት አለ፤ ይህም ሲባል ፍላጎቱ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ነው። ሁለተኛ ግን ሰፊ የገበያ ሥራ በመሠራቱ በጣም ተፈላጊ የሆኑ የዲቃላ ዝርያዎችን ብቻ የመምረጥ ዝንባሌ አለ። በመሆኑም ከምርምር ተቋማት ጋር በመተባበር የአርሶአደሩን ፍላጎት ለማሟላት እየሠራን ነው። ያም ቢሆን እጥረቱ አለ። ዩኒየኖችና በዚህ ሥራ ላይ የተሠማሩ የውጭ ኩባንያዎች የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ በመሆኑ የተሻለ አቅርቦት ይኖራል ብለን እናስባለን። ከምርምር ተቋማት ጋር ግን በተለይ ዝርያዎችን በመለየት የምሠራቸው ሥራዎች አሉ። ለአብነት መጥቀስ ካስፈለገ አዋሽ ተፋሰስን ተከትሎ የተሠሩ ሥራዎች ከእነዚህ ተቋማት ጋር በመተባበር ነው። ከዚህ አኳያ የወረር ግብርና ምርምር ስምንት የሚሆኑ አዳዲስ ዝርያዎችን አውጥቷል። ከሌሎች ጋር በመሆንም በተለይ ከስንዴ ጋር ተያይዞ ወደ አስር ዝርያዎችን መርጠን ነው ወደ ሥራ የገባነው። በዚህ ሂደት ውስጥ በጋራ ሆነን ነው ስንሠራ የቆየነው። በመሠረቱ እንዲህ አይነት ሃገራዊ ፕሮግራሞች የሚቀረፁት ከምርምር ተቋማት መነሻ በመውሰድና የተሠሩ ሙከራዎችን በማየት ነው። የምንሠራው ተቀናጅተን ነው፤ እያንዳንዱን ሥራ ስንገመግምም በጋራ ነው።

መጤ ተምችና አንበጣን በተመለከተ የተነሳው ጥያቄ በቀጥታ የእኛ ዘርፍ ጋር የሚገናኝ አይደለም፤ የፌዴራል ሥልጣን ነው፤ ይሁንና እነዚህን ለመከላከል እንደሃገር ትልቅ አቅም ፈጥረናል። ከምሥራቅ አፍሪካ አንበጣ መከላከል ድርጅት ጋር አብረን እንሠራለን፤ ዋና መሥሪያ ቤቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ከክልሎች ጋር በመሆንም መድኃኒት ለሚረጩ አውሮፕላኖች ማረፊያ በሌላቸው አካባቢዎች ላይ ቦታ እያዘጋጀን ነው። እኛ የገዛናቸው አውሮፕላኖች ደግሞ በቅርቡ በተደረገው ስምምነት የሚመራ ድርጅት ተፈጥሮ በማሠልጠን የማብቃት ሥራ ይሠራል። በዚህም የግሪሳ ወፍን መከላከል የምንችልበትን አቅም እየፈጠርን ነው።

ከክልሎች ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ አቅም ገንብተን የሚያርፍባቸውን ቦታዎች የመለየት፣ ሥራ ይሠራል። እንዲሁም ዓለምአቀፉ የእርሻ ድርጅት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት ያለው በመሆኑ ያንን ተጠቅመን በየጊዜው ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ በመስጠት በራሳችን በአውሮፕላን ጭምር አሰሳ የማካሄድ ሥራ ይሠራል። ይህም የመከሰት ዕድሉን የሚቀንስ ሲሆን ከተሰከተ ደግሞ የመከላከል ሥራ ይሠራል። እንደአጠቃላይ በመከላከል ሃገራዊ አቅም የገነባንበት ሥራ ነው።

በዚህ ዓመት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በአፋርና በሌሎች አካባቢዎች ላይ የአውሮፕላን ሜዳ እየተሠራ ነው። በሚቀጥለው ዓመት እንዲህ አይነት የአንበጣም ሆነ የግሪሳ ወፍ ወረርሽኝ ቢከሰት ለመከላከል የሚያስችል አቅም እየገነባን ነው። በተጨማሪም መሠረታዊ የሚባሉ አቅርቦቶችን የማሟላት ሥራ እየተሠራ ነው።

በጎረቤት ሃገራትም ሲከሰት ኢትዮጵያ ሳይደርስ እዛው እያለ የመከላከል ሥራዎችን ከኢጋድ ጋር እንሠራለን። እኛ ጋር ያሉት ዘመናዊና የመከላከል አቅማቸው ከፍተኛ የሆነ አውሮፕላኖች ነው ያስገነባነው፤ ድሮኖችንም አስገብተናል። የመኪና መርጫዎችን አዘጋጅተናል። እነዚህን መሣሪያዎች በእርዳታ ከዓለም የምግብ እርሻ ድርጅትና ከሌሎችም አካላት አግኝተናል። እንዲሁም መንግሥት የራሱን በጀት በመመደብ ያሟላንበት ሁኔታ አለ።

አዲስ ዘመን፡- እንደአጠቃላይ በዘርፉ ሊፈቱ የሚገባቸው ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?

አቶ ኢሳያስ፡- በተለይ ቴክኖሎጂ ማስረፅ ላይ ጉድለቶች አሉብን። ሁሉንም አርሶኦደር ተደራሽ ማድረግ ላይ ክፍተት ያለብን በመሆኑ ከምርምር ተቋማት ጋር ተቀናጅተን እየሠራን ነው። ሀገሪቱ ሰፊ እንደመሆንዋ የተለያየ ሥነ-ምሕዳር ያላት እንደመሆኑ ችግሮቹም በዚያው ልክ ይለያያሉ። ይህንን ማዕከል ያደረገ ሥራ ነው እየሠራን ያለነው። በተመሳሳይ አብዛኞቹ ቴክኖሎጂዎች ከውጭ የሚመጡ መሆናቸው፤ በተለይ ከትራክተር ጀምሮ እስከ ኮምባይነር ድረስ አብዛኞቹ ከውጭ የሚመጡ በመሆኑ የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችን ላይ ውስንነት ይታያል። በእርግጥ መንግሥት ከታክስ ነፃ እንዲገቡ አድርጓል። ሆኖም መሣሪያዎችን በቡድን በማደራጀትና ጥቅም ላይ ማዋል ላይ አሁንም ክፍተት አለብን።

በመሆኑም የቴክኖሎጂና የሜካናይዜሽን አጠቃቀም ዝቅተኛ መሆኑ የሚፈለገውን ውጤት እንዳናመጣ አድርጎናል። ወጣቱንም ወደ ግብርናው ዘርፍ እንዳይሳብ አድርጎታል የሚል እምነት አለኝ። ሌላው ግብይት ነው ትልቁ ችግር፤ ምርታማነት የቱንም ያህል ቢጨምርም አሁንም ግብይት ላይ ዋጋው ውድ የሚሆንበት ሁኔታ አለ። ይህ ደግሞ በተለይ አስገዳጅ ሕግ በማውጣት በሰፊው መሥራት ያስፈልጋል። ይህ ሲባልም ልክ ምርታማነትን ለማሳደግ በተሠራው ልክ ግብይት ላይ ያለው ክፍተት ሊታይ ይገባል። አሁን ባለው ሁኔታ ብዙ ቢመረትም ግብይቱ ላይ ካልተሠራ ትልቅ ማነቆ ነው የሚሆነው።

የግብርና ምርቶች ላይ አሁንም ጥቂት አካላት የሚወስኑበት ሁኔታ ነው ያለው። አብዛኛው የአርሶአደሩ ምርት መርካቶ ተወስኖ ነው የሚሸጠው። ይህ ግብይቱ በሕግ ማዕቀፍ የሚመራ ባለመሆኑ አርሶአደሩ ሰርቶ አመድ አፋሽ አድርጎታል። ስንዴም ሆነ ሌሎች ሰብሎች በስፋት እየተመረተ ነው፤ አኩሪአተርና ሌሎችም ሰብሎች ላይ ተዓምራዊ የሚባል እድገት ያስመዘገቡ ምርቶች ናቸው፤ ሆኖም ገበያ ላይ ውድነቱ እንዳለ ነው። እዚያ ላይ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እስከታች ባለው ትስስር የምንሠራው ሥራ አለ፤ ሆኖም ችግሩን በዘላቂነት መፍታት አልተቻለም። በመሆኑም ግብርናችንም ሆነ ግብይቱን እኩል ማዘመን ይጠበቅብናል። እንደመንግሥትም ተለይቶ እየተሠራባቸው ናቸው።

እነዚህን ችግሮች መፍታት ከቻልን በዋናነት የምግብ ዋስትናችንን እናረጋግጣለን፤ ሃገሪቱ የተሻለ ምርት በመላክ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ታገኛለች፤ አቅርቦትና ፍላጎት የሚቀራረብበት ሁኔታ ይፈጠራል፤ ያ ደግሞ ለኅብረተሰቡ የሚፈልገውን ምርት በአቅሙ መግዛት ያስችለዋል። እንደአጠቃላይ ሁለንተናዊ እድገት እናመጣለን። ምክንያቱም ደግሞ አብዛኛው ኅብረተሰባችን አርሶአደር እንደመሆኑ አርሶአደር ሲለወጥ ሃገርም ታድጋለች የሚል እምነት አለኝ።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።

አቶ ኢሳያስ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ማሕሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ነሐሴ 2 / 2016 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You