በኦሮሚያ ክልል በ2011 ዓ.ም በዘጠኝ ወራት ውስጥ 3ሺህ 566 የትራፊክ አደጋ መድረሱን የክልሉ የትራንስፖርት ባለስልጣን ገለፀ፡፡
በትላንትናው ዕለት በአዳማ ከተማ የኦሮሚያ ትራንስፖርት ባለስልጣንና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በመተባበር የትራፊክ አደጋን ለመከላከል በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የትራፊክ አደጋ መከላከያና መቆጣጠሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ተመስገን ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን የአለም የጤና ድርጅት ያወጣውን መረጃ በመጥቀሰ በክልሉም በ2011 ዓ.ም የደረሰውን የትራፊክ አደጋን በፅሁፋቸው አቅርበዋል፡፡
በዚህመ መሰረት በ2011 በዘጠኝ ወራት 1 ሺህ 339 የሞት እንዲሁም 418 ሚሊዮን 16 ሺህ 291 የሚሆን በንብረት ላይ የደረሰ አደጋ መመዝገቡን በቀረበው ፅሁፍ ላይ ተገልጿል፡፡
ይህንን በሰው ልጆች ህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳትን እያደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ሁሉም ጉዳዩ የሚመለከተው አካል በሀላፊነት ሰሜት በመስራት አደጋውን መቆጣጠር እንደሚገባም አቶ አዲሱ ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ሲሳተፉ ያገኘናቸው ከኦሮሚያ ልዩ ዞን የመጡት ኢንስፔክተር አዲሱ አበራ በበኩላቸው ይህ በየአመቱ የሚካሄደው የትራፊክ አደጋ የመከላከል ንቅናቅ ከተጀመረ ጥቂት አመታት ቢሆኑትም በርካታ ስራዎች እንደተሰሩ ይናገራሉ፡፡
ከዚህን ቀደም የትራንስፖርት ባለስልጣንና ፖሊስ ኮሚሽን በጥምረት መስራት ላይ ብዙም አይታዩም ነበር፤ ዘንድሮ ግን በጥምረት በመስራታቸው በትራፊክ አደጋ መከላከል ላይ ጥሩ ውጤት መታየቱን የተናገሩት ኢንስፔክተር አዲሱ ይህ በጥምረት መስራት በሌሎቹም ክልሎች ሊሰራበት ይገባልም ብለዋል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው በ2018 እ.ኤ.አ 1.32 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን ከ20-50 ሚሊዮን የሚሆኑት ከባድ ና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ 93 በመቶ የሚሆነው የሞት አደጋ የሚከሰተው በታዳጊ ሀገራት መሆኑንም የድርጅቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
በሀይማኖት ከበደ