ለሰው ልጅ የህይወት መጥፋት ዋነኛ ምክንያት የሆነውን የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የሚመለከታቸው አካላት በጥምረት መስራት እንደሚገባቸው የኦሮሚያ ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
ባለስልጣኑ ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባባር በተለያዩ አካባቢዎች ሲካሄድ የነበረው የትራፊክ አደጋን የመከላከል የንቅናቄ መርሃ ግብር በትላንትናው ዕለት በአዳማ ከተማ በተካሄደው የምክክር መድረክ ተጠናቋል፡፡
መድረኩን በእንኳን ደህን መጣችሁ ንግግር የከፈቱት የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ አሰግድ ጌታቸው የትራፊክ አደጋ ከዕለት ዕለት የሰው ልጆችን ህይወት የሚነጥቅ አስከፊ አደጋ መሆኑን በመጥቀስ ይህንን አደጋ ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
የኦሮሚያ ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ሀላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ በበኩላቸው የትራፊክ አደጋ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ የሀገሪቱን አምራች ዜጋ እያሳጣን ነው ብለው ይህን አስከፊ አደጋ ለመከላከል ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት በመስጠት ሊሰሩ ይገባልም ብለዋል፡፡
እንደ ሀላፊው ገለፃ ባለስልጣኑ የትራፊክ አደጋን ለመቆጣጠር በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቅሰው አሁንም ከከልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ሌሎች ስራዎችን ለመስራት ማቀዳቸውን ተናግረዋል፡፡
ባገባደድነው አመት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጠጥቶ የማሽከርከር መቆጣጠሪ መሳሪያን ማሰራጨት፣በመንገዶች ላይ የማስጠንቀቂያ መብራቶችን(warning light) መግጠም፣የትራፊክ ምልክቶችን መትከልና የተሰበሩትን መጠገን፣የመንደገኛ ማቋረጫ መንገዶችን መስራት፣ የትራንስፖርት መንገዶችን የማዘመን ሰራዎችና የትራፊክ አደጋን ለማስተማር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ እንዲካተት መደረጉ፣ የሚዲያ ፎረመን ተዘጋጅቶ በተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች መካሄዳቸውና ሌሎችም በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ አስታውቀዋል፡፡
ባለስልጣኑ በ2012 ዓ.ም የትራፊክ አደጋን ለመቆጣጠርና ለመከላከል በርካታ ስራዎችን ለመስራት ማቀዱንም ሀላፊው አያይዘው ገልፀዋል፡፡
በክልሉ ሀሰተኛ የሰሌዳ ቁጥር ለጥፈው የሚንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎች መኖራቸው ህጋዊ የሆኑ አሽከርካሪዎች ላይ ችግር እየፈጠረባቸው እንደሆነም ከመድረኩ ተሳታፊዎች የተነሳ ሲሆን ባለስልጣኑ ይህንን ሃላፊነት ወስዶ እንደሚሰራ ሀላፊው አስታውቀዋል፡፡
በሀይማት ከበደ