“የምትተክል ሀገር የሚያጸድቅ ትውልድ”

ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እየተሰሩ ካሉ አበይት ሀገራዊ ሥራዎች መካከል የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ይገኝበታል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁሉንም ማህበረሰብ ባሳተፈ መልኩ በየአመቱ የክረምት ወቅትን ታሳቢ በማድረግ የሚተከሉ ችግኞች ቀላል የሚባሉ አይደሉም። ዘንድሮም በተመሳሳይ መልኩ ‹የምትተክል ሀገር የሚያጸድቅ ትውልድ› በሚል መሪ ሃሳብ በአረንጓዴ ዐሻራ ፕሮግራም ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ ተጀምሮ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡

በዚህ ሀገራዊ ንቅናቄ ላይ እንዳለፈው ጊዜ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል በበረታ ተነሳሽነት የራሱን ዐሻራ በማሳረፍ ይሁንታ እያሳየ ነው። በአዲስ አበባ ጨምሮ በሁሉም የክልክ ከተሞች እስከ ወረዳ ድረስ በሚደርስ የተቀናጀ ሥራ በመተግበር ላይ ይገኛል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር ፊታውራሪነት ኢትዮጵያን በአረንጓዴ የመሸፈን ተግባር በሁሉም የሀገራችን ክፍል ተጀምሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የዘንድሮውን ጨምሮ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብርን በተመለከተ በተለያዩ ጊዜ የተለያዩ ንግግሮችን አድርገዋል። ካለፈው ጊዜ ተነስተን ወደ ዘንድሮው መሪ ቃል ስንመጣ የሚከተለውን እናገኛለን። ባሳለፍነው 2013 ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት የተናገሩት ንግግር የመርሀ ግብሩን ዓላማ በግልጽ ያሳየ እንደነበረ ይታወሳል፡፡

‹የችግኝ ተከላ መርሀ ግብሩ የአካባቢ ብክለትንና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን ሀገራዊና ማህበራዊ ችግሮች ለመቅረፍና ለመመከት የወጣው የአራት ዓመት እቅድ አካል እንደሆነ በመጥቀስ በሚቀጥሉት ጊዜአትም ቀጣይነት እንደሚኖረው መናገራቸውን ማስታወስ እንችላለን።

ቀጥሎ ባለው 2014 ዓ.ም ተመሳሳይ ንግግሮችን አድርገዋል። የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር እንደ ዓለም የተደቀነብንን የህልውና አደጋ የምንወጣበት ብቸኛ መንገድ እንደሆነ ከንግግራቸው ይዘት መረዳት ችለናል። እንዲሁም ባለፈው ዓመት ‹ነገን ዛሬ እንትከል› በሚል የንቅናቄ ትግበራ ላይ የካቻምናውን መሰል ንግግሮችን አድምጠናል። ዘንድሮም በምትተክል ሀገርና በሚያጸድቅ ትውልድ እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡

የአረንጓዴ ዐሻራ ዓላማ በየትኛውም ሀገርና ማህበረሰብ አንድ አይነት ዓላማ ያለው ነው። ሞትና ጉስቁልና ስጋቱ ለሆነው የአየር ለውጥ ለየትኛውም የሰው ልጅ እውቀትና መረዳት ተመሳሳይ ግንዛቤ ነው ያለው። ዓላማው ሁልጊዜም የሰው ልጅን ከአየርን ብረት ለውጥና ተያይዞ ከሚመጣው የህልውና አደጋ መታደግ ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ አስተማማኙና ሁነኛው መፍትሄ በአረንጓዴ ዐሻራ አረንጓዴ ምድር መፍጠር ነው። የአረንጓዴ ዐሻራን ጥቅም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ብቻ አያይዘን የምንጨርሰው ጉዳይ አይደለም። በየትኛውም የሰው ልጅ ጉዳይ ውስጥ ከፊት ተሰለፎ የምናገኘው ነው፡፡

የአረንጓዴ ዐሻራ እሳቤ የለውጥና የተሀድሶ ከዚህ ከፍ ካለው የጤናና የደስተኝነት ሰንደቅ እንደሆነ መረዳት ያሻል። አእምሮ ህልውናውን የሚያገኘው ከአካባቢው እውነታ ተነስቶ ነው። አካባቢ ስንል ደግሞ ከፍተኛውን ድርሻ የምንሰጠው በዙሪያችን ላለው ተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስተጋብር ነው፡፡

ይሄ መስተጋብር ለአእምሮ ምቹና ተስማሚ ካልሆነ አደጋው አስከፊ ነው። እናም ይሄን አይነቱን ችግር ለመቅረፍ በአረንጓዴ ልማት እሳቤ ውስጥ መቆም አማራጭ የሌለው ግዴታ ይሆናል። ከዚህ እውነት በመነሳት መንግሥት ለአየር ንብረት ለውጥ የሰጠው ቦታ ምን ያክል እንደሆነ ከትግበራው መረዳት ይቻላል፡፡

ከጉዳዩ አሳሳቢነት አንጻር መንግሥት ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀሱን ያለፉትን አራት ዓመታት ጨምሮ የዘንድሮውን ትግበራ ከነውጤታቸው ማየት ይቻላል። ከዚህ ቀደም መንግሥት የጎረቤት ሀገራት ጉዳይ የኢትዮጵያ ጉዳይ እንደሆነ በመቀበል የችግኝ ተከላው መርሀ ግብር ከሀገር አልፎ ጎረቤት ሀገራት የደረሰ እንደነበር አይዘነጋም።

ችግኝ ተከላን በተመለከተ አብዛኛውን ጊዜ የምንታማበት አንድ ነገር አለ እርሱም ምንድነው ለመትከል የተነሳሳንውን ያክል ለእንክብካቤ አለመነሳታችን ነው። ይሄን ችግራችንን ቀርፈን ተክለን ለማጽደቅ ብርቱ ሥራ ላይ እንገኛለን። ሁሉም ሰው የተከለውን ችግኝ እስኪጸድቅ ድረስ እንዲንከባከብና ሃላፊነቱን ወስዶ እንዲከታተል በሚያስችል ልክ የተገነባ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በመሆኑ ብዙም ስጋት አለው ተብሎ አይታሰብም።

እርግጥ ነው የተከልነውን ያክል ጸድቆልን አያውቅም። ያለፉት አራት ዓመታት የትግበራ አቅጣጫ ግን መትከልን ከመጽደቅ ጋር ያቆራኘ ሂደት ነበር። ከዚህ ባለፈ መንግሥት ከእቅዶቹ አንዱ በማድረግ ብዙ ሃይልና ገንዘብ መድቦ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ሲሆን በዘንድሮው አመት ደግሞ ለአረንጓዴ ዐሻራ በሚል ራሱን የቻለ በጀት ተመድቦለት ወደሥራ የሚገባበት አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

በሃላፊነት የሚያንቀሳቅሰው ስለሆነ በብዙ ሃላፊነት የታጀበ እንደሆነ ማረጋገጡ ተአማኒነት ይሰጣል። ያለፉትን ዓመታት ብናይ እንኳን በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተተከሉ ችግኞች ውስጥ አብዛኞቹ የጸደቁ ሲሆን ይሄም ማለት በመቶኛ ሲሰላ 87 ከመቶ የሚሆኑት ችግኞች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳሉ በመንግሥት ደረጃ የተገለጸበት ሁኔታ እንደነበር ማስታወስ ተገቢ ነው። ከዚህ አኳያ የምንለፋው እና የምንደክመው ለለውጥ እና ለተሻለ እምርታ እንደሆነ በመረዳት ወደ ፊት መቀጠሉ አዋጭነት አለው፡፡

የአረንጓዴ ዐሻራ እሳቤ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው እሳቤ ነው። ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ የመጣውንና ወደፊትም የሚመጣውን የህልውና ጥያቄ ለመቆጣጠር እንደዋና አማራጭ የያዘችው የችግኝ ተከላ ንቅናቄን ነው። በየአመቱ የክረምት ወርን ጠብቆ መንግሥት ችግኝ መትከልን እንደ ትልቅ ሀገራዊ አጀንዳ ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ ያለው ከዚህ እውነታ በመነሳት ነው።

ከፍ ብዬ እንዳልኳችሁ የአረንጓዴ ዐሻራ እውነታ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ብቻ የሚያበቃ አይደለም ብዙ ትሩፋቶች ያሉት እሳቤ ጭምር ነው። እንዲህ አይነቱ ለጋራ ጥቅም የጋራ ተሳትፎን የሚሻ ልማት ደግሞ በመንግሥት ትከሻ ላይ የሚጣል ብቻ ሳይሆን የዜጎችም ይሁንታ ያለበት ነው፡፡

አረንጓዴ ዐሻራ የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ጎን ለጎን ያለውን ሀገራዊ በረከት ብነግራችሁ እንዲህ ይሆናል። ኢትዮጵያ ሀገራችን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ተስፋና ትንሳኤን በአንድነት ይዛ ለሌሎች ግድቦችም በመሰናዳት ላይ ያለች ተስፈኛ ሀገር ናት። እየገነባነው ላለነውና ወደ ፊትም ሊገነቡ እቅድ ለተያዘላቸው ትልልቅ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦች ዛሬ ላይ ችግኝ መትከላችን የውሃ እጥረትን ከመከላከል ባለፈ ጤናማና የተስተካከለ አካባቢ እንድናገኝ ስለሚረዳን ጥቅሙ ከፍ ያለ ነው።

ጥቅሙ በዚህ የሚያበቃ አይደለም ድርቅና በርሃማነትን በመከላከል፣ ወቅቱን የጠበቀ ዝናብ በመስጠት ህልውናችንን የሚያረጋግጥልን ነው። ሌላም በረከት መጥቀስ ይቻላል በጸሀይ ጨረር የሚመጡ እንደ ካንሰርና የቆዳ በሽታዎችን ከመከላከል አኳያ አረንጓዴ ዐሻራ የጎላ ድርሻ አለው። ወደችግሩ ስንመጣ ደግሞ በአሁኑ ሰአት የዓለም ትልቁ ስጋት የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት እንደሆነ እንደርስበታለን።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ደግሞ በአብዛኛው የዚህ ገፈት ቀማሽ ከሆኑ ሀገራት መካከል ድሃ ሀገራት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ። ይህ ማለት ሀገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ መሰል ታዳጊ ሀገራት የገፈቱ ግንባር ቀደም ተጠቂዎች ናቸው ማለት ነው። ችግሩ ይሄ ብቻ አይደለም ከአየር ንብረቱ ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚመጡ በርካታ ሀገራዊ ችግሮችም አሉ፡፡

እንደ በረከቱ ሁሉ የዝናብ እጥረትን በማስከተል ድርቅና መሰል ኢኮኖሚያዊ እንቅፋቶችን በመፍጠር በሀገርና ሕዝብ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ የት የሌሌ ነው። ይሄ ብቻ አይደለም ተለምዶአዊ የአካባቢ ምህዳርን በመዛባት በሰው ልጅ ላይ እና ሕይወት ባላቸው ማናቸውም ፍጡራን ላይ መጥፎ ዐሻራውን በማሳረፍ ህልውና አደጋ ላይ ይከታል። እንደነዚህ አይነት ተጨማሪ እንከኖች ታክለውብን ይቅርና ወትሮም ኑሯችን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው።

ሃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ ግን ከመንግሥት ጎን በመቆም በአረንጓዴ ዐሻራው ላይ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ብናደርግ አንድም ለራሳችን አንድም ለሀገራችን መትረፍ እንችላለን። ክረምቱ ሳያልፈን፣ ወቅቱም ሳይሄድብን መንግሥት በጀመረው በዚህ የአረንጓዴ መርሀ ግብር ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ነጋችንን ብሩህ ማድረግ ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል። የኢትዮጵያ አረንጓዴ መልበስ እንደመሪ ቃሉ እንደሀገር ልንተክል እንደትውልድ ደግሞ ልናጸድቅ እንጂ የታይታ ሊሆን አይደለም። ነገን ዛሬ መትከል የሚለው ጽንሰ ሃሳብ በአንድ ሀረግ ቢገለጽ እንዲህ ባለው ዘላቂ እውነት በኩል መቆም ይችል ነበር።

ችግሮቻችንን ከወዲሁ መርታት ነው። ዛሬ ላይ የምንተክላት እና የምንከባከባት አንድ ችግኝ ነገ ላይ ለኔና ለእናተ ብሎም ለልጆቻችን የሕይወት ዋስትና ሆና መምጣቷ የማይቀር ነው። ስለሆነም በተባበረ ክንድ ኢትዮጵያን እናልብሳት። ከዚህ ጋር አያይዤ አንድ ያስገረመኝን ነገር ላውጋችሁ። ከሰሞኑ አምስት ኪሎ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም ጎራ ብዬ ነበር። ግድግዳው ላይ ሌላ ዓለም፣ ሌላ ሰማይና ምድር የሚመስል ፍጹም የሚደንቅ አረንጓዴ የለበሰ አንድ ፎቶ ግራፍ ግድግዳው ላይ ተሰቅሎ ተመለከትኩ።

ቀርቤ አየሁት.. ከስሩ ያለውን ጽሁፍ ሳነበው ለካ ከሚሊዮን ዓመት በፊት የነበረችው የኛ ምድር ፎቶ ግራፍ ነበር። ከጎኑ በበርሀ የተዋጠችው አሁናዊ የምድራችን ገጽታ አለ። የሁለቱን ልዩነት በአግራሞት ነበር ያየሁት። በነገራችን ላይ ከስጋት ባለፈ ዓለም ትጠፋለች ተብሎ በሳይንሱ ከሚተነበይባቸው እውነታዎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የአየር ንብረት ለውጥ ነው፡፡

ይህ ማለት የዓለም ፍጻሜ የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ የሚመጣ ነው ማለት ነው። ለመጪው ትውልድ የተራቆተችን ሀገር ማስረከብ የለብንም። ተባብረን ኢትዮጵያን ማልበስ አለብን። አረንጓዴ መሬት፣ አረንጓዴ ምድር ታስፈልገናለች። በዚህ የተቀናጀ ልማት ውስጥ አረንጓዴ ምድር ብቻ ሳይሆን አረንጓዴ እሳቤም አብሮ ይፈጠራል። የአየር ንብረት ለውጥ ሁሉንም ማህበረሰብ የሚያጠቃ የዓለም በሽታ ነው።

ዋናውና ብቸኛው መከላከያ መንገድ ዛፍ መትከል፣ ችግኞችን መንከባከብ ብቻ ነው። መንግሥት በያዘው የአረንጓዴ ልማት መርሀ ግብር ላይ በመሳተፍ ኢትዮጵያንና ምድሯን ከበርሃማነት መታደግ ለነገ የማንለው፣ ለማንም ሳይሆን ለራሳችን የምንውለው ቀዳሚ ውለታ ነው፡፡

በአየር ንብረት ለውጥ አማካኝነት የሚመጡ ጉዳቶችን ለመከላከል ከድሃ ሀገራት ይልቅ የበለጸጉ ሀገራት የተሻለ አቅም ቢኖራቸውም ሙሉ በሙሉ ከችግሮ መላቀቅ ግን አይችሉም። በኢኮኖሚያቸው ልክ እንደዚህ አይነት ችግሮችን ለመመከት የሚያስችል አቅም ያዳበሩ ቢሆንም የጉዳቱ ሰለባ ከመሆን የሚያድናቸው አንዳች ሃይል ግን የለም። ምክንያቱም የአየር ንብረት ለውጥ በጋራ የምንከላከለው የዓለም ሁሉ የጋራ ችግር ስለሆነ ነው፡፡

አብዛኛውን ጊዜ ችግሩ ድህነትና ኋላ ቀርነትን ታኮ የሚመጣ ነው። ለዚህም ነው ባለጸጋ ሀገራት በለኮሱት ድሃ ሀገራት የሚጨሱት። በሀብታም ሀገራት የሥልጣኔ ገፈት ድሀ ሀገራት አሳራቸውን የሚያዩት። የአየር ንብረት ለውጥ የሁሉም ሀገራት የጋራ ችግር ቢሆንም ቀደም ብዬ እንዳልኳችሁ በድሃ ሀገራት ላይ በይበልጥ ያይላል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ከትላናት እስከዛሬ የዓለም የቤት ሥራ ሆኖ ያለ ትልቅ ጉዳይ ነው። እልባትና መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ግን አብዛኛው ሀገር ለችግሩ መባባስ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ናቸው። በተለይ በኢኮኖሚያቸው አደጉ የሚባሉ ሀገራት ለችግሩ መፈጠር የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ ከፊት የሚሰለፉ ሆነው ይታማሉ፡፡

አፍሪካና ሕዝቦቿ ምንም በማያውቁት ባለጸጎቹ በፈጠሩት ችግር ስቃይ ላይ ይገኛሉ። በዓለም ዙሪያ በተለያየ ጊዜ የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ የበለጸጉ ሀገራት ለድሃ ሀገራት ድጎማ ማድረግ አለባቸው የሚሉ በርካታ መከራከሪያ ሃሳቦች ሲነሱ ቆይተዋል። አሁንም ድረስ እኚህ ሃሳቦች መቋጫ አላገኙም።

ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ መንግሥታችንም ይሄን ተገንዝቦ እያደረገ ያለው የቅድመ መከላከል ተግባር እጅጉን የሚደነቅ እንደሆነ መናገር ይቻላል። ልክ እንደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሁሉም የዓለም ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የበኩሉን ማድረግ ቢችል ምድራችን በዚህ ልክ ሲኦል አትሆንብንም ነበር፡፡

ችግኝ በመትከል የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ጎን ለጎን መንግሥት ማህበረሰቡ ለምግብ የሚሆኑ ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችንም እንዲተክልና ራሱን በምግብ እንዲችል እያደረገ ያለውም ጥረት የሚደነቅ ነው። አሁን ላይ ከችግኝ ተከላው እኩል ሁሉም በየደጁና በየጓሮው በከተማ ግብርና ራሱን ከወጪ ተከላክሎ ከጓሮው ቀጥፎ የሚበላበት ሁኔታ እየተፈጠረ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው።

አዲስ አበባን ጨምሮ በርካቶች በዚህ የመንግሥት መርሀ ግብር ውስጥ በመሳተፍ በጓሮአችውና በግቢያቸው ውስጥ ለምግብ የሚሆኑ አትክልቶችን በመትከል ራሳቸውን በመደጎም ላይ እንደሆኑ በተለያየ ሚዲያ ላይ ምስክርነታቸውን ሲሰጡ አድምጫለው። በቀላል መንገድ፣ በትንሽ ቦታ ላይ ራስን ከወጪ መታደግ ዘመናዊነት ነው ባይ ነኝ፡፡

ይሄ ተግባር በስፋት ተሠርቶበት ማህበረሰቡ ከጓሮው ቀጥፎ መብላትን ልምድ እንዲያደርግና ድህነትን አሸንፎ እንዲወጣ መንግሥት በያዘው በጎ መንገድ መቀጠል አለበት። በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ማለት ይላሉ ይሄ ነው። የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ችግኝ እየተከሉ በዛውም ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ፍራፍሬና አትክልቶችን በመትከል ራስን በምግብ መቻል።

ይህ ተግባር መንግሥትን እንደ መንግሥት ሲያስመሰግነው ማህበረሰቡን ደግሞ ከመጠበቅና ከልመና ወጥቶ በሕይወት ለመኖር የተለያዩ አማራጮችን እንዲፈልግ መንገድ ሲጠቁም ትውልዱን ደግሞ በጎ ልማድን በማዳበር ዛፍ ከመቁረጥ ዛፍ ወደመትከል እንዲሸጋገር ያደርገዋል፡፡

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ሐምሌ 30 /2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You