• ሜሪትና ሹመትን በልካቸው እንዲጓዙ እየሠራ መሆኑንም አስታውቋል::
አዲስ አበባ፡– በቀጣይ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ምን መሆን እንዳለበት የሚያሳይና በሲቪል ሰርቪሱ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችል የሲቪል ሰርቪስ ፍኖተ ካርታ እያዘጋጀ መሆኑን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ገለጸ፡፡ ሹመትና ሜሪት በልካቸው እንዲጓዙ ለማድረግ ጥናት እያከናወነ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በዛብህ ገብረየስ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ መጻኢ እድል ፈንታው ምን መምሰል አለበት፤ ምን አይነት ነገሮችንስ መቀየር ይገባል፤ የሚሉ አንኳር ጉዳዮችን መሰረት በማድረግ የፍኖተ ካርታ ቀረጻ ተጀምሯል፡፡ ፍኖተ ካርታውም እንደ ቀደመው በለውጥ መሳሪያዎች ስም ተበጣጥሶ የሚቀርብ ሳይሆን አጠቃላይ የኢትዮጵያ የሲቪል ሰርቪስ ዘርፍ የመንግሥት ቢሮክራሲ ምን መምሰል እንዳለበት የሚያሳይ ነው፡፡
ፍኖተ ካርታው የሲቪል ሰርቪሱን አገልግሎት ማዘመንን ማዕከል በማድረግ፤ የሲቪል ሰርቫንቱን አቅም፣ ክህሎት፣ የፈጠራና ችግር ፈቺ ሀሳብ አመንጪነት፣ የሙያና የሥራ ስነ ምግባርን የሚመለከቱ ጉዳዮችን እንደሚዳስስም ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል፡፡ ከሠራተኞች ምዘናና ምደባ፣ የጥቅማጥቅምና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘም የሚነሱ ጥያቄዎችን ኮሚሽኑ በትኩረት በመዳሰስ የመፍትሄ አቅጣጫ ያስቀምጣል ብለዋል፡፡
የፍኖተ ካርታው የመንግሥትና ሲቪል ሰርቪሱ ትስስር የዜጎች ጥቅምና ለዜጎች ጥቅም የተቀመጡ ሕገ መንግስታዊ ነገሮችን ከማሳካት አኳያ እንደሚሆንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ፤ ኮሚሽኑ በፍኖተ ካርታ ዝግጅቱ ሜሪትና ሹመት በልካቸው የሚጓዙበትን እድል ለመፍጠር እየሠራ ነው። ምክንያቱም ሜሪትና ሹመት በየትም ዓለም አይቀሩም፡፡ በመሆኑም በፍኖተ ካርታው የሜሪትና ሹመት ምጣኔው ምን ይሁን? በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ የሹመት ስራዎች የትኞቹ ይሁኑ? በመካከላቸውስ ምን አይነት ጥምረትና ቅንጅት ይኑር? የሚለውን ከተለያዩ አካላት በወጡ ባለሙያዎች እያስጠና እንደሆነና ይሄውም በፍኖተ ካርታው እንዲካተት ይደረጋል ብለዋል።
ኮሚሽነሩ አያይዘው እንደገለጹት፤ በሲቪል ሰርቪስ ተቋማት የሠራተኛ ቅጥር እንዲቆም የተደረገው አዲሱ ካቢኔ ከተቋቋመ በኋላ ተቋማት በመፍረሳቸው፣ አንዳንዶቹም በመቀላቀላቸውና አንዳንዶቹም ለሁለት በመከፈላቸው ምክንያት በእነዚህ ተቋማት የነበሩ ሠራተኞችን ቦታ ለማስያዝ ሲባል ነው፡፡ በዚህም መዋቅሩ ሲሰራ ቦታዎች ቀድመው ከመያዛቸው በፊት እነዚህን ሠራተኞች ክፍት ወደሆነበት ቦታ ሄደው ክፍተቱ እንዲሞላ፤ ሠራተኞችም ሳይመደቡ እንዳይቀሩ ማድረግ ተችሏል፡፡
ያም ሆኖ ግን በኢትዮጵያ ከ1ነጥብ7 ሚሊዬን ያላነሰ ሠራተኛን በመያዝ መንግሥት ከፍተኛ ቀጣሪ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የድሃ አገር መንግሥት በዚህ መልኩ ሁል ጊዜ ቀጣሪ ሆኖ እስከመቼ ይቀጥላል ያሉት ኮሚሽነሩ በሚቀጥሉት 15 ዓመታትም የመንግሥት የቀጣሪነት ሂደት እየቀነሰ፤ ዜጎችን በብዛት ቀጥረው የሚያሰሩ ተወዳዳሪ የግል ድርጅቶች እየተበራከቱ ይሄዳሉ የሚል ታሳቢ አለ ብለዋል።
በተቋማት ያለን የቦርድና የሲቪል ሰርቪስ አደረጃጀት አስመልክቶ ኮሚሽነሩ እንደገለፁት፤ በተቋ ማት የሚኖር የቦርድና ሲቪል ሰርቪስ አደረጃጀት በአዋጅ የሚቋቋም ነው፡፡ በዚህ ሂደት በተቋማቱ ውስጥ የሚታይ የአሠራርና ተያያዥ ችግሮች ካሉም ከአደረጃጀት ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ሳይሆኑ ከመሪዎች አቅም ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2011
ወንድወሰን ሽመልስ