ቀርከሀን በፋሽን ኢንዱስትሪው የምታስተዋውቀው ዲዛይነር

ቀርከሀን በመጠቀም በፋሽን ኢንዱስትሪው ላይ ተፈላጊ የሚባሉ ምርቶችን በማቅረብ ደንበኞችን አፍርታለች። ምርቱን በማስተዋወቅና በመጠቀም ለእናቶች እና ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር የሚችል ‹‹ጤና አዳም›› የተሰኘ ተቋምም መስርታለች፡፡ የእደጥበብ ውጤቶች ዲዛይነርም ናት፡፡ ወይዘሮ ትዕግስት አበበ የጤናአዳም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት መስራችና ባለቤት ፡፡

ትዕግስት ከልጅነቷ ጀምሮ ለእደጥበብ ውጤቶች እና ለተፈጥሮ ቅርበት የነበራት ሲሆን፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ ገብታ ከተመረቀች በኋላም ከተፈጥሮ ጋር የተቆራኘ የራሷን ስራ መስራት ትፈልግ ነበር፡፡ ትዕግስት ከዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ በኋላ በአየር መንገድ ውስጥ በበረራ አስተናጋጅነት ለዓመታት ሰርታለች፡፡ በዚህ አጋጣሚም ሌሎች ሀገራትን የማየት እድሉን አግኝታ ነበር፡፡

‹‹ወደ ተለያዩ ሀገራት ስበር ዜጎቻቸው ለተፈጥሮ ሀብቶቻቸው ያላቸው ቦታ እና አጠቃቀማቸው ያስቀናኝ ነበር›› የምትለው ወይዘሮ ትእግስት፤ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የምትጠራበት ያለቀላቸው ምርቶች አናሳ መሆን ቁጭት ይፈጥርባትና ያንንም ለመቀየር ትፈልግ እንደነበር ትገልጻለች፡፡

ሶስተኛ ልጇን ወልዳ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለም ላይ ተስፋፍቶ ስጋት መሆኑ በታወጀበት ወቅት በቤት ውስጥ መቀመጥ የግድ ሲሆን ትዕግስት ከተፈጥሮ ጋር የተገናኘ ምርት ማሰብ ጀመረች፡፡ ‹‹ምን ላይ ብሰራ ይሻላል? የሚለውን ጥናት ሳደርግ ጥሩ ሆኖ ያገኘሁት የቀርከሀ ምርትን ነበር›› የምትለው ወይዘሮ ትእግስት፤ አሁን አሁን የተጠቃሚው ፍላጎት ከተፈጥሮ ይልቅ በፕላስቲክ ከተሰሩ ምርቶች ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ትገልጻለች።

ይህ ልምድ ደግሞ ምርቶችን ተገልግሎ ለማስወገድ በሚሞከርበት ወቅት አካባቢን የሚበክል ስለሆነ የራሱ አደገኛ ጉዳት እንደሚያስከትል ትናገራለች። በዚህ ምክንያት በቀላሉ ማስወገድ በምንችላቸው አካባቢን የማይበክሉ ምርቶች ላይ ለማተኮር ወሰንኩ ስትል ታስረዳለች።

ከዚህ ውሳኔዋ በኋላ ነው ትእግስት ቀርከሀን በፋሽን ኢንዱስትሪው ለመጠቀም ጥናት በማድረግ ስልጠናውን በመውሰድ ስራውን የጀመረችው። ሆኖም ግን ወደ ተግባር ስትገባ ቀርከሀውን ወደ ምርት የምትቀይርበት መሳሪያ ከፍተኛ ድምፅ ስላለው ያንን ማስወገድ የሚያስችል ምቹ ቦታ ለማግኘት ተቸገረች። ስራውን ማቋረጥ መፍትሄ ስለማይሆን ቀጠለችበት።

‹‹በቅድሚያ የጀመርኩት በማበጠርያ ነበር፤ ከዚያ በምሰራበት ወቅት ሌሎች ዲዛይኖች እየመጡልኝ ቦርሳ የእጅ ብራስሌት፣ ቀለበት የአንገትና የጆሮ ጌጥ መስራት ቀጠልኩ›› የምትለው ወይዘሮ ትእግስት፤ በአሁኑ ሰዓትም ቀርከሀን እንደ ዋና ግብዓት በመጠቀም እና ከሌሎች የሀገራችን ሀብቶች ጋር በማጣመር የእደጥበብ ውጤቶችን ጌጣጌጦችን እና ቦርሳዎችን በመስራት ለገበያ እንደምታቀርብ ታስረዳለች። ከተለያዩ ሆቴሎች ጋር በጋራ በመሆን የድርጅታቸውን ብራንድ እና ሌሎች መገልገያዎችን ትሰራለች፡፡

እንደ ወይዘሮ ትእግስት ማብራሪያ፤ ቀርቀሀ በሀገራችን በስፋት የሚገኝ ሲሆን፤ በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ለምግብነትም ጭምር ይውላል፡፡ በመሆኑም በጤናአዳም የሚሰሩ እነዚህ የቀርቀሀ ውጤቶች በተቻለ መጠን የሚጠቀሟቸው ግብዓቶች ሙለሙሉ በሀገር ውስጥ የሚገኙ ብቻ እንዲሆኑ ይፈለጋል፡፡ በዚህም ጌጣጌጦችን ለመስራት የሚጠቀሟቸው ሌሎች ብረት ነሀስና መዳብ ሲሆን፤ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ናቸው። ምንም አይነት የጎንዮሽ ጉዳት የላቸውም። በጆሮም ሆነ አንገት ላይ የሚደረጉ ጌጦችም ክብደት የሌላቸው በመሆናቸው ምቹ ያደርጋቸዋል፡፡ ከቀርከሀ የሚሰሩ ቦርሳዎችም ከቆዳ፣ ፈትል እና ከባህል አልባሳት ጋር በማጣመር ይሰራሉ፡፡

ወይዘሮ ትእግስት እንደምትለው፤ ጌጣጌጦችንም ሆነ ቦርሳዎችን ዲዛይኖች ከሀሳብ በመነሳት የምትፈጥራቸው ሲሆን፤ የራሳቸው የሆነ መልዕክትን እንዲያስተላልፉም ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ በተለያየ መጠንና ዲዛይን የሚሰሩ ሲሆን ለገበያ ከመቅረባቸው በፊት የየራሳቸው ስያሜ ይሰጣቸዋል።

‹‹አንድ አዲስ ዲዛይን ሰርተን እንዳወጣን ስም ስላላወጣንለት ምርቱን የገዛችንን የደንበኛችን ስም በመጠቀም ‹ንባቤ› ብለን ሰየምነው›› በማለት የምትገልጸው ወይዘሮ ትዕግስት፤ ሌሎች ምርቶቻቸውም ምጥን ፣ ዘወትር (ሁል ጊዜ ሊያዝ የሚችል ቦርሳ ሲሆን) ኩሩ፣ እንዲሁም በእንስቶች ስም ውቢት፣ የውብዳር፣ ዝናሽ የሚሉ ስያሜዎችን እንደሰጧቸው ትናገራለች። በተለይ ለየት ያሉ የቦርሳ ስያሜዎች መኖራቸውን ገልጻ፤ በተለምዶው ዋሌት ተብሎ የሚጠራውን ገንዘባቸውን በመቀነታቸው ይይዙ የነበሩ እናቶችን ለማስታወስ በማሰብ መቀነት የሚል ስያሜ እንደሰጡት ትገልጻለች፡፡

እንደ ወይዘሮ ትእግስት ገለጻ በተለይ ከቀርከሀ ምርት የተሰሩትን ቦርሳዎች ተጠቃሚዎች ወደ ስራ ሲሄዱ፤ ጉዞ በሚኖራቸው ጊዜ፣ ስፖርት ቤት መሄድ ሲፈልጉ፣ ኮምፒውተር መያዝ ሲፈልጉ በቀላሉ ሊጠቀሟቸው ይችላሉ። ቦርሳዎቹ ከቀርከሀ ባሻገር ቆዳን እንዲሁም በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚገኙ የባህል አልባሳትን በማጣመር የሚሰሩ ናቸው፡፡ እነዚህ የቀርከሀ ውጤቶች በሰዎች ዘንድ ባህላዊ እይታ መጨመር ብቻ ሳይሆን ዘመናዊ የሆነ ይዘት የተላበሱና ለፋሽን ተጠቃሚዎች ምቹ ናቸው፡፡

‹‹ቀርከሀ በባህሪው እንደሌሎች እንጨቶች አይሰበርም ፤ተጣጣፊ ነው ፤ስንሰራውም ደግሞ በጣም ተልጎ በከፍተኛ ጥራት ነው›› የምትለው ዲዛይነሯ፤ ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች ቦርሳዎቹ ባላቸው ውበት አድናቆት ቢኖራቸውም ከቀርከሀ የተሰሩ መሆናቸውን ሲያውቁ ጥንካሬው ላይ ጥርጣሬ እንደሚያሳድርባቸው ትናገራለች፡፡

የጥንካሬና ጥራት ጉዳይም ሊያሳስባቸው እንደማይገባ ትመክራለች። እነዚህን ስራዎች የሚሰሩ እናቶችን ጊዜ ወስደው እንደሚያሰለጥኑም ታነሳለች፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜም 20 የሚሆኑ እናቶችን በዚህ ዘርፍ በማሰልጠን ራሳቸው ቀርከሀውን ተረክበው በሚፈለገው መንገድ ሰርተው እንዳስረከቡ ታነሳለች፡፡

ዲዛይነር ትዕግስት ሰዎች አሁን ላይ ያላቸው አቀባበል መልካም የሚባል መሆኑን አንስታ፤ እንደ ሀገር ባለን ሀብት ልክ ዘርፉ ይበልጥ መተዋወቅ አለበት ትላለች። አምራቾች፣ ባለሙያዎች፣ ወጣቶች ዲዛይነሮችም በዚህ ስራ ላይ እንዲገቡ ትጋብዛለች፡፡

‹‹ጤናአዳም›› አሁን ከሚሰራቸው ስራዎች ባለፈ ቀርከሀን በመጠቀም የሚሰሩ የውበት መጠበቂያ ምርቶችን የማምረት እቅድ አለው። ዲዛይነሯ ወደፊት ቀርከሀ ከሚያድግበት መንገድ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ውጤት ድረስ ሰዎች ጎብኝተው ራሳቸው የሚፈልጉትን አይነት ጌጣጌጥ አዝዘው የሚሄዱበትን መንደር የመገንባት ፍላጎት አላት፡፡

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You