ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ሊሬቦበሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ዲዛይንና ፕላን መምህር (ፎቶ ዶከመንት)
ካለ ከተሞች እድገት ያደገ ሀገር እንደሌለ መረጃዎች ያመላክታሉ። ከተሞች ለሀገር እድገት ሰፊ ሚና ያላቸው በመሆኑ የከተሞች መሰረተ ልማት ዕድገት ወሳኝ ነው። በኢትዮጵያ በየዓመቱ በብዙ ሚሊዮን ወደ ከተሜነት እየተቀየረ ነው። የሀገራችን ፈጣን የከተሜነት መስፋፋት በተገቢ መሰረት ልማት ሊመራ የሚገባ መሆኑን የከተማ ልማት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
በፍጥነት እያደገ ያለውን ከተሜነት በአግባቡ ማስተዳደር ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው። ከተሞች የአንድን ሀገር እድገት ወይም ልማት ሊወስኑ የሚችሉ የልማት ሞተሮች ናቸው። ስለዚህም ዜጎች ከከተሞች ትሩፋት መጠቀም እንዲችሉ ከተሞች በፕላን ሊመሩ ይገባል። የከተማ ነዋሪው የተሟላ ኑሮ እንዲመራ፣ ምርታማ ዜጋ እንዲሆን ደረጃውን የጠበቀ መኖሪያ ቤት ውስጥ መኖር ይኖርበታል። አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች የተሟሉለት መሆን አለበ። አይቀሬ ከሆነው ከተሜነት አኳያ በተለይ አዳዲስ የከተማ ማዕከላትም ከምስረታቸው ጀምሮ በእቅድ ሊመሩ ዝግጁ መሆን አለባቸው።
በአጠቃላይ በከተማና ከተሜነት እንዲሁም የዚሁ አንድ አካል የሆነው በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች እየተተገበረ ስለሚገነው በኮሪደር ልማት ዙርያ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ዲዛይንና ፕላን ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር)፣ ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ።
ፎቶ:- ከዶክመንት
አዲስ ዘመን ፦የኢትዮጵያን የከተሞች አመሰራረት ምን ይመስላል? ከተሞች የልማት ማዕከልነታቸውስ እንዴት ይገለጻል?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል፦ የሀገራችን የከተሞች አመሰራረት የሌሎች ሀገራት ከተሞች ከተመሰረቱት የተለየ ነው። በሌላው ዓለም ላይ ያሉ ከተሞች በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ የተመሰረቱ ናቸው። የሀገራችን ከተሞች ካለ ኢንዱስትሪ፣ አለ ማኑፋክቸሪንግ የተመሰረቱ ናቸው ተብሎ ይወሰዳል። እንደ ቁልቢ ገብርኤል ያሉ ከተሞች በሃይማኖት ምክንያት የተመሰረቱ ሲሆን፤ የሀዋሳ ከተማ የመሳሰሉት ደግሞ በአስተዳደራዊ ማዕከልነት የተመሰረቱ ናቸው። ሌላው ደግሞ ንግድ ወይ ደግሞ የትራንስፖርት መንገድ ተከትሎ የተመሰረቱ ናቸው። ቢሾፍቱ፣ አዳማ ከተሞች የባቡር መንገድን ተከትለው ተመስርተዋል። በመሆኑም አሁን የአሀገራችን መንግሥት እያደረገ ባለው ጥረት የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተመሰረቱ ናቸው። ለስራ እድል ፈጠራ ፋብሪካዎችን የማቋቋም፣ ትላልቅ የስራ እድል ፈጣራ ስራዎች እየተፈጠሩ ናቸው።
ማኑፋክቸሪንግ እና ኢንዱስትሪ ሌሎች የዓለም ከተሞች የደረሱበትን ደረጃ ለመድረስ አንዱ ምክንያት ነው። አሁን ላይ ከዚህ ተሞክሮ በመውሰድ ሌሎች የዓለም ከተሞች እንዴት እዚህ ደረሱ የሚለውን በማየት ሀገራችንም ወደ እድገት ጎዳና በመግባት ላይ ነች። የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተቋቋሙ ነው። በከተሞች የቱሪዝም፣ የማኑፋክቸሪንግ፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እንቅስቃሴ ላይ እየተሰራ ይገኛል። በመሆኑም በፍጥነት እያደገ የመጣውን የከተሜነት ጉዳይ ትኩረት በመስጠት በሥርዓት እና በእቅድ መምራት ይገባል።
ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ግብርና መር አሁን ደግሞ የማኑፋክቸሪንግ ወይም ከተማ መር የልማት አቅጣጫ በመያዝ እየለማች ነው። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከተሞች የሀገሪቱን የልማት አቅጣጫ የሚያመላክቱ ናቸው። በመሆኑም በሀገር ልማትና ዕድገት ላይ የከተሞች ሚና ሰፊ ድርሻ አለው። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የኢትዮጵያ የከተሞች ምጣኔ 25 በመቶ አካባቢ ደርሷል ተብሎ ይገመታል። የከተሜነት መስፋፋት ፍጥነቱም አምስት ነጥብ አራት በመቶ ነው። ይህም ሀገሪቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን የከተሞች እድገት ካለባቸው ሀገሮች ተርታ ያሰልፋታል። ይህ ፈጣን የከተሜነት እድገት በአግባቡ ከተመራ የሥራ ፈጠራ እና የኢኮኖሚ ብልጽግና ማዕከላት ይሆናሉ።
ከተሞች በፕላን ከተመሩ፣ የመኖሪያ፣ የመነገጃ፣ የማኑፋክቸሪንግና የሥራ ፈጠራ ማዕከላት የመሆን አቅም አላቸው። የኢትዮጵያን ብልፅግና እና ልማት ወደ ፊት ሊወስኑ የሚችሉ ስለሆኑ በአግባቡ ሊመሩ ይገባል። አሁን እየተካሄዱ ያሉት የኮሪደር ልማት እንቅስቃሴዎች ከተሞቹን በአግባቡ የመምራት መገለጫዎች ናቸው።
እንዲሁም ከተሞች የፈጠራ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የተለያዩ ፈጠራዎች ማዕከላት ተብለው ይወሰዳሉ። ንፁህ አካባቢ መሆን አለባቸው፤ እግረኛ በነፃነት የሚንቀሳቀስባቸው፣ ወንጀለኛ የሌለባቸው፣ ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆኑ ይጠበቃል። ደረጃቸውን ጠብቀው ማደግም አለባቸው። ደረጃውን የጠበቀ መንገድ፣ የመብራት ዝርጋታ፣ የልጆች መጫወቻ ስፍራ፣ የአረንጓዴ ስፍራ፣ የቱሪስት መስህቦች፣ የመናፈሻ ስፍራዎች ለከተሞች ያስፈልጋሉ። ከዚህ አኳያ የሚሠሩ ሥራዎች ለመጪው ትውልድ ጭምር የሚሆን ከተማን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ደረጃቸውና ሥነውበታቸው ተጠብቆ መገንባት ይኖርባቸዋል።
የመሬት አጠቃቀምም በአግባቡ እና በሥርዓት መመራት አለበት። መንገዱን፣ መናፈሻ ስፍራውን፣ የንግድ ቦታውን ቅይጥ ቦታዎችን በአጠቃላይ የታሰበውን የትምህርት፣ የመዝናኛ፣ የሃይማኖት ስፍራዎችን በሙሉ ማኅበራዊ፣ አካባቢያዊ፣ ሕጋዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ እንዲሁም ባህላዊ ጉዳዮችን ግምት ውስጥ በማስገባት በፕላን መምራት ያሻል። ከዚህ አኳያ ሲታይ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማትም ከዚህ አኳያ እንደ ሞዴል የሚታይ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ከተሞች ከተማ ለመባል በመሰረታዊነት ምን ያስፈልጋቸዋል? የኢትዮጵያ ከተሞች ከዚህ አንጻር እንዴት ይታያሉ?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል፦ አንድ ከተማ ከተማ ለመባል ጥራት ያለው መሰረተ ልማት የተዘረጋለት መሆን አለበት። ሰዎች ደግሞ ከግብርና ውጪ በሆኑ በማኑፋክቸሪንግ ውስጥ የሚሰሩ በአገልግሎት ዘርፎች ውስጥ የሚሰሩ መሆን አለባቸው። ስለሆነም ከተማ የሚባለው አንዱ የንፁህ ውሃ መኖር፣ የመንገድ ድርና ማጉ የተሳለጠ መሆን፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በሰለጠነ የሰው ኃይል በቂ መሰረተ ልማት በአግባቡ የተሟላ እና የተደራጀ ከሆነ ነው። ይህ በመሆኑም ነው በገጠር የሚኖረው ሕዝብ ኑሮውን ወደ ከተማ እያደረገው የሚገኘው። በጥግጊት ደረጃ በአንድ ሄክታር ቢያንስ በትንሹ 100 ሰው የሚኖር ከሆነ ከተማ ይባላል። ሁለት ሺህ ሰው ሲባልም 20 ሄክታር ላይ ላይ ይኖራል እንደማለት ነው። በመቀጠልም ጥራት ያለው መሰረተ ልማት መኖር ነው። ሶስተኛው ደግሞ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ነው። ከተሞች የኢኮኖሚ፣ የገቢ ወጪ፣ የኢንዱስትሪ፣ የትምህርት፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከላት ናቸው። በመሆኑም ከተማ ሲባል ይሄ ሁሉ አብሮ ተደራጅቶ ያለበት ነው።
አዲስ ዘመን፦ የሀገራችን ከተሞች ከአረንጓዴ ሽፋን፣ ከተለያዩ የመንገድ መሰረተ ልማቶች አኳያ ምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ፦ የትኛውም ሀገር የልማቱ ምንጭ እና መሰረቱ ከተሞች ናቸው። ስለዚህ ከተሞቻችን በፕላን ይመሩ ተብሎ ሲታሰብ በመሰረተ ልማት፣ ውሃ፣ መብራት፣ ቴሌ፣ መናፈሻ ስፍራዎች፣ የልጆች መጫወቻ ስፍራዎች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ትምህርት ቤቶች በሙሉ የተሟላ መሆን ይኖርበታል። ከተሞች ንፁህ አካባቢ መሆን አለባቸው። እግረኛ በነፃነት የሚንቀሳቀስበት፣ ወንጀለኛ የሌለበት፣ ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢ ከማድረግ ከዚህ አኳያ መስራት ይጠበቃል። በመሆኑም ደረጃውን የጠበቀ መንገድ፣ የመብራት ዝርጋታ፣ የልጆች መጫወቻ ስፍራ፣ የአረንጓዴ ስፍራ፣ የቱሪስት መስህቦች፣ የመናፈሻ ስፍራዎች ያስፈልጋሉ።
ከዚህ አኳያ የሚሰሩ ስራዎች ለትውልድ የሚሆነውን ከተማ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ደረጃቸውንና ስነውበታቸውን ጠብቀው መከናወን አለባቸው። በመሆኑም በፍጥነት እያደገ የመጣውን የከተሜነት ጉዳይ ትኩረት በመስጠት በሥርዓት እና በእቅድ መምራት ይጠይቃል። የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ከክልል፣ ከዞን እና ከወረዳ መንግሥታት እና አስተዳደሮች ጋር በመሆን መስራት ይኖርበታል።
ፕላን ሲሰራም በሀገራችን ባለው በከተማ መሰረተ ልማት የተቀመጠው ስታንዳርድ 30/30/40 ነው። 30 በመቶ የአረንጓዴ ለምለም እና መናፈሻ ስፍራዎች፣ 30 በመቶ የመንገድ ድርና ማግ እና የመኪና ማቆሚያ፣ 40 በመቶ ደግሞ ህንጻ የሚያርፍበት በሚል ክፍፍል ተቀምጧል። አረንጓዴ ለምለም ማለትም አሁን ዓለም ላይ እየመጣ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ጭምር የሚቋቋም ነው። ሰው የሚኖርበት፣ የሚነግድበት፣ የሚዝናናበት፣ የአየር ንብረቱ የተስተካከለ ከተሞችን መፍጠር ይሆናል። ከዚህ አንፃር የወንዝ ዳር ልማት፣ የመናፈሻ ስፍራዎች እና የአረንጓዴ ለምለም ስፍራዎች በመንደር ውስጥ፣ በመሬት ላይ ብቻ ሳይሆን በህንፃዎች ሽቅብ ጭምር ያሉ የከተማ እርሻዎች፣ የምግብ ዋስትናን የሚያግዙ ናቸው።
የከተማ እርሻንም በማስፋፋት አረንጓዴ እርሻ ፣ የከተማ እርሻ፣ የከተማ ጫካ፣ የመንደር ውስጥ የመናፈሻ ስፍራዎች የወንዝ ዳር ልማትንም ጭምር በማሳለጥ ከተሞቻችንን በአረንጓዴ ለምለም ውስጥ እንዲገኙ መስራት ይኖርብናል። አረንጓዴ ለምለም በከተማ ውስጥ ሳይሆን (City in The Park) በሚለው ፅንሰ ሃሳብ በከተሞች ህንፃዎች ላይ ሁሉ አረንጋዴ ሆነው የምግብ ዋስትናንም በማረጋገጥ ከተሞቻችን የምንኖርበት እና ድህነት የሌለበት ከተሞችን ከመፍጠር አንፃር መስራት አለብን። አሁን የአረንጓዴ አሻራ የምንለው እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው በዩኒቨርሲቲዎች፣ በመንግሥት አስተዳደር ፅህፈት ቤቶች ወስጥ፣ በተቋማት፣ በመንደር ውስጥ የአረንጓዴ ለምለም ዛፍ ብቻ ሳይሆን የሚመግብ ከተማ መፍጠር ይገባል።
አዲስ ዘመን ፦ ከተሞቻችን እንዴት ይገለጻሉ? አሁናዊ ገጽታቸው ምን ይመስላል?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል፦ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከተሞቻችን ሲታዩ በትክክል ልናስብ የሚገባው ጊዜ አሁን ነው። ጉድለት አለ፤ ከተሞች በፕላን እየተመሩ አይደለም። ዘላቂ የሆነ የመሬት አጠቃቀም በፕላን በማዘጋጀት የታሰበውን የመሬት አጠቃቀም ለታሰበው ዓላማ በማድረግ የዜጎችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ በአግባቡ ሊሰራ ይገባል። አሁን ባለው ሁኔታ የፕላን ጉድለት አለ። አሁን አዲስ አበባ ላይ ሲታይም የፕላኑ አካል እንዲሆን ማስተካከያ እየተሰራ ነው ያለው።
የኮሪደር ልማት ቀደም ሲል በነበረው ክፍተቶች ነበሩበት። አሁን ሕግና ደንብ አድርጎ በማምጣት የከተማው ካቢኔም የፕላኑ አካል እንዲሆን በማድረግ የአዲስ አበባ የአስረኛ ፕላን ትግበራ አንዱ አካል ሆኖ እንዲመጣ ተደርጓል። በሌሎች ከተሞቻችንም አሁን የሚታየው ገፅታ ደካማ በመሆኑ ከዚህ ትምህርት በመውሰድ እና በመንቃት በትክክል ሊታሰብበት የሚገባ ነው። ማህበረሰቡ እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከተሞችን ለማስዋብ፣ ከተሞች የስራ ማዕከላት እንዲሆኑ፣ የውበት፣ የቱሪዝም ማዕከላት እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ አሁን መንቃት ይገባል። አሁን በየከተሞቻችን የሚታየው ደካማ አካሄድም እንዳለ ይቀጥል ወይስ ከዛ በመውጣት ራዕይ እና ፕላን ተግባራዊ በማድረግ እናልማቸው የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት። ስለሆነም ስንጓዝበት ከነበረው አካሄድ በመውጣት ስማርት ከተሞችን መፍጠር ተገቢ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ከተሞችን ስማርት ሲቲ የማድረግ ስራዎች ይታያሉ፤ ስማርት ሲቲ ማለት ምን ማለት ነው፤ ለከተሞች ያለውን ፋይዳ ቢያብራሩልኝ? የእኛ ከተሞች በተለይ አዲስ አበባና አንዳንድ ሰፋፊ ከተሞች ከዚህ አኳያ ምን ደረጃ ላይ ናቸው?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ፦ ስማርት ሲባልም ቅይጥ ነው። ስማርት ከተማ ሲባል በትንሽ ቦታ ላይ ብዙ ሰዎች እንዲኖሩ የማድረግ፣ ሰው ረጅም ርቀት እንዳይጓዝ በማድረግ፣ በአንድ ህንፃ ውስጥ ቢሮና የንግድ ስራ፣ መኖሪያ ያለበት የሚለውን ጭምር ያካተተ ነው። ከተማው ከወንጀል ነጻ የሆነ፣ ወንጀለኛ የሚጠፋበት፣ ከተማው ገላጣ የሆነ ለሁሉም ሲታይ በሲስተም የተቀናጀ፣ ዲጂታል የሆነ፣ በቴክኖሎጂ የሚመሩ ከተሞችን ከመፍጠር አኳያ እየተሰራ ያለበት ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
ከተሞች ስማርት ናቸው ሲባልም ሰው ቀለል ያለ ኑሮ የሚኖርባቸው፣ መሬት አስተዳደር በመሄድ የመልካም አስተዳደር ችግር የተቀረፈበትና በቀላሉ በሲስተም የሚስተናገድበት፣ ወረቀት አልባ መስተንግዶ ያለበት ነው። ሰው በቀላሉ በአጭር ጊዜ የሚስተናገድበትን ሥርዓት በማምጣት በካዳስተር ሥርዓት በመሬት አስተዳደር እየተሰራበት ነው። ይህ ሲሆን ካርታ ለማሳተም መመላለስ ይቀራል። በትራንስፖርት ሲስተሙ ሰው ገጭቶ አይጠፋም፤ በሲሲቲቪ ካሜራ ከተማው በራሱ መቆጣጠር ይችላል። ለመብራት እና ውሃ መጨነቅ ይቀራል። ከዚህ አኳያ በተቋማት መሰረተ ልማቶችም ስማርት እንዲሆኑ ወይም ስልጡን እና ብልህ የሆኑ ከተሞችን ከመፍጠር አንፃር ተግባራዊ በማድረግ ከተሞቻችን አሁን ካሉበት ደካማ ሁኔታ ነቅተው ወደ ፍፁም እድገት መቀላቀል እንደሚገባ ማሰብ የሚገባበት ወቅት ላይ ነን።
በሀገራችን ስልጡን ከተሞችን ከመፍጠር አኳያ ጅማሮዎች አሉ። በ2025 ኢትዮጵያ ዲጂታል ሀገር እንድትሆን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቀመጠው አቅጣጫ የሚታወስ ነው። በቴሌኮም፣ በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ እና በመሳሰሉት የተቀመጠውን ስትራቴጂ በመከተል ከተሞቻችንን ዲጂታላዝ የማድረግ፣ በኢንዱስትሪ፣ ኢትዮጵያ ታምርት፣ በኮንስትራክሽን ኢትዮጵያ ትገንባ ንቅናቄዎች ሚናቸው የዚህ አካል ነው። በመሆኑም በ2025 አንዱ አንዱን የማይጎዳበት ግልፅ አሰራር ያለበትን ቅልጥፍና ለማምጣት ተግባራዊ የሚሆንበት እና ማዘጋጃ ቤቶቻችን የስማርት ከተማ አስተሳሰቡን ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
በገቢ አሰባሰብ፣ በውሃ እና በመብራት፣ በባንኮች፣ በተመሳሳይ ተጀምሯል፤ ኢትዮ ቴሌኮም ጎን ለጎን እየሰራ ነው። በስማርት ከተማነት በኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀሰው አዳማ ናት። አዳማ ላይ የኢንተርኔት ሲስተምን በመዘርጋት በማናጅመንት ላይ፣ በገቢ አሰባሰብ ላይ፣ በመሬት አስተዳደር ላይ ተጀምሯል። አዳማ ላይ መሬት በካዳስተር አሰራር በተቀናጀ መልኩ ወደ መተግበር ተገብቷል። በአዲስ አበባም ላይ ተጀምሯል፣ ባህርዳር፣ ሀዋሳ ከተሞችም ጅማሮዎች አሉ። ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ከማድረግ አኳያም የአመራር ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ነው።
ሰው ተኮር የሆኑ ከተሞችን ለመፍጠር ቀን እና ለሊት መስራቱ ተገቢ ነው። በሙያቸው የተካኑትን በማሰማራት ከተሞቻችን ለዘላቂ ልማት እንዲበቁ በተባበሩት መንግሥታት የተቀመጠውን የሚሊኒየሙ የዘላቂ ልማት ግብ 11 መሰረት በመንግሥታትም በሀገራችን ተግባራዊ እየተደረገ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ አዲስ አበባ ከተማ እንደ ሀገሪቱ ርእሰ መዲናነቷ፣ እንደ አፍሪካ ህብረትና ሌሎች ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት መቀመጫነቷ በእዚህ ደረጃ ካሉ ከተሞች አኳያ በምን ደረጃ ላይ ትገኛለች ይላሉ? የሚጎድላት ብዙ ነው ካሉ እንዴት አርጋ መሙላት ትችላለች?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል፦ አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ዋና ከተማ፣ የተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ከተማ መሆኗ ከሌሎች ከተሞች ልዩ ባህሪ እንዲኖራት አድርሎጓል። በዓለም ካሉት አራት ከተሞች አንዷ የዲፕሎማቲክ ከተማም ናት። ይሄ ሁሉ ትሩፋት እያላት ከዚህ ሁሉ መጠቀም የሚያስችላትን ደረጃ ሳታሟላ ቆይታለች። ይሄንን ግምት ውስጥ በማስገባት አዲስ አበባ ዳግም እየለማች ነው። አሁን ለሌሎችም ጥሩ ምሳሌ በምትሆንበት ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ከተማዋ የፕላን ጉድለት አለባት። ፕላኑን የማስተግበር ጉድለትም አለ። ወደ ሀገሪቱ ሌሎች ከተሞች በሚኬድበት ጊዜም ፕላን ይዘጋጃል፤ ነገር ግን መሬት ወርዶ ተፈፃሚ አይሆንም። አንዳንዱ ፕላን ደግሞ ያለጊዜ ይመጣል። ከተሜነትን መምራት እንጂ ማቆም አይቻልም። ከተማን በእቅድ እና በፕላን በመምራት የ10፣ የ20፣ የ30 ዓመታት በቂ የኃይል እና የውሃ አቅርቦት፣ በቂ ትምህርት ቤት፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ጤና ተቋማት፣ የመናፈሻ እንዲሁም የልጆች መጫወቻ ስፍራዎች መገንባት ያስፈልጋል።
ከተሞችን ዳግም ማልማት የሚለው ሃሳብ የተጀመረው በእንግሊዝ ሀገር በተካሄደው የኢንዱስትሪ አብዮት ወቅት በተለይም በ1850 ዓ.ም ነው። በወቅቱ የኮሪደር ልማት ካስፈለገባቸው ምክንያቶች መካከል የፋብሪካ ምርትን በአግባቡ ማጓጓዝ፣ የአካባቢን ፅዳት ማስጠበቅ፣ የከተማ ውበት ማስጠበቅ የሚሉት ይገኙበታል።
በ1900 ዓ.ም አካባቢ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሲመሠረት ሚናስ የሚባል የመጀመሪያው አርመናዊ ማስተር አርክቴክት ከተማዋን በፕላን ለመሥራት ጥረቶች አድርጓል። በወቅቱ ሰፈሮችን የማፍረስ እንቅስቃሴዎችም ነበሩ። በጣሊያን ዳግም ወረራ ወቅትም እንዲሁ አዲስ አበባ የፈረንሳይ እና የጣሊያን አርክቴክቶች ሲፈራረቁባት ነበር።
እስከአሁን ባለው አካሄድ አዲስ አበባ በቂ ውሃ የላትም፤ የኃይል አቅርቦት እጥረትም ነበረባት። የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የመናፈሻ ስፍራዎች፣ የልጆች መናፈሻ ስፍራዎች እጥረት አለ። ይህንን ከግምት በማስገባትም አሁን በኮሪደር ልማቱ የእግረኛ መሄጃ ክፍት ስፍራዎች፣ የብስክሌት መሄጃዎች፣ በየቦታው ባሉ ኪስ ቦታዎች ዛፎችን በመትከል እና አረንጓዴ ስፍራዎችን የመፍጠር ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።
መዲናዋን ዳግም የማልማት ጥያቄ የከተማ አስተዳደሩንና የፌዴራል መንግሥቱን አመራር ውሳኔና ቁርጠኝነትን የጠየቀ ነው። ከምሥረታዋ ችግር የነበረባት እና ያለ ፕላን ያደገችውን አዲስ አበባ የመጣችበትን አካሄድ ለመቀየር ውሳኔ በማሳለፍ ሕግና ሥርዓትን እንደገና በማሰብ ዳግም እየለማች ነው።
ኮሪደር ልማቱ ሰው በነፃነት የሚንቀሳቀስበት፣ የሚኖርበት፣ የሚዝናናበት፣ የቱሪዝም መስሕብ እና የውበት ከተማ እንዲሆን እና ዘላቂ የሆነ ልማትን ለማረጋገጥ የመጣ የልማት ሞዴል ነው። ሞዴሉን በሌሎች ከተሞችም ላይ በተመሳሳይ በመተግበር ከተሞችን የልማት ማዕከላት ማድረግ ይገባል። ተገቢ የቤት አቅርቦት የተሟላባቸው ከተሞችንም ከመፍጠር አንጻር መንግሥት የፋይናንስ ተቋማትንም በማገናኘት እየሠራ ነው።
የዝናብ ውሃ ማስወገጃ መሰረተ ልማቶች በሚገባ ባለመኖራቸው በአንዳንድ አካባቢዎች ሁልጊዜ በጎርፍና ደራሽ ውሃ የመጠቃት ሁኔታዎች ይታያሉ። የመብራት፣ የፍሳሽ ማስወገጃ፣ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ጨምሮ ሌሎችም ሰፋፊ ችግሮች ነበሩባት። እነዚህን ሁሉ ችግሮች በመለየት በዘርፍ ደረጃ የከተማ አስተዳደሩም ይሄንን በመስራት አሁን በግልጽ የታየውን ለውጥ እያመጣ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፦ በአዲስ አበባና በአንዳንድ የክልል ከተሞች በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ የሚገኘው የኮርደር ልማቱ ከመሰረተ ልማት፣ ከጽዳት፣ ከተሜነትን ከማጎልበት አኳያ ምን ፋይዳ አለው?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ፦ በመዲናዋ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የኮሪደር ልማቱ፣ ከተሞች እንዴት ውበታቸውን አጉልተው ማሳየት እንደሚችሉ ማሳያ ነው። አዲስ አበባ በኮሪደር ልማቱ በድጋሚ እየለማች ነው። ተገቢ የሆኑ የተሽከርካሪ መንገዶች፣ የእግረኛ መሄጃዎች፣ የፍሳሽ እና የቆሻሻ ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ መስመር፣ የመብራትና የቴሌ መስመሮች በሙሉ በተናበበ መልኩ እየተሠሩ ናቸው። ዘላቂ የሆነ የተቀናጀ የመሠረተ ልማት ፕላን እንዲመጣ አድርጓል። በኮሪደሩ በግራና ቀኝ ደግሞ ኪነ ሕንፃ ጥበባቸው የተጠበቀ የሚያምሩ ሕንፃዎች እንዲመጡ፣ ቅይጥ የሆነ እና በአንድ ሕንፃ ሁሉም አገልግሎት ያለበት ሞዴል ተግባራዊ መሆን ጀምረዋል። ቢሮ ያለበትና እዚያው የሚሠራበት፣ የሚነገድበት፣ የሚኖርበት የሚለው ሃሳብ ተግባራዊ እየተደረገ ነው። የኮሪደር ልማት የከተማ ዲዛይን አንዱ ሞዴል ነው። ሌሎች ሀገራትም ይሄንን ተግባራዊ አድርገዋል።
በመዲናዋ ሰው በነፃነት የሚንቀሳቀስበት፣ የሚኖርበት፣ የሚዝናናበት፣ የቱሪዝም መስሕብ እና የውበት ከተማ እንዲሆን እና ዘላቂ የሆነ ልማትን ለማረጋገጥ የመጣ የልማት ሞዴል ነው። ከተማዋ አሁን ይበል በሚያሰኝ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ይሄንንም በማጠናከር ለሚቀጥለው ትውልድ ጭምር የመኖሪያ፣ የመነገጃ፣ የማምረቻ፣ የሥራ ፈጠራ፣ የቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን ማድረግ ተገቢ ነው።በዚህ ረገድ የሚታዩት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች በክልል ከተሞችም ተጀምረዋል። ይህም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
ይህ እንቅስቃሴ ወደ ሀዋሳ፣ ባህርዳር፣ ሻሸመኔ፣ መቀሌ፣ ጎንደር፣ ሆሳዕና፣ ሶዶ ከተሞች ሁሉ መስፋፋት መቻል አለበት። ወደ ክልል ከተሞችም እንዲሰፉ ማድረጉ ከተሞቻችን የስራ ፈጠራ ማዕከላት፣ የመናፈሻ ማዕከላት እንዲሆኑ የሚያግዝ ነው። ይህም የከተሞቻችንን ትሩፋት ማህበረሰቡ እንዲጠቀም ከማድረግ አንፃር የጎላ ሚና አለው። በመሆኑም ይሄንን አጠናክሮ መስራት የሚጠበቅ ነው። የሀገራችንን ልማት እድገት እና ብልፅግና ለማረጋገጥ በፕላን የተመሰረተ ከተሜነት ያስፈልገናል። የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ከክልል፣ ከዞን እና ከወረዳ መንግሥታት እና አስተዳደሮች ጋር በመሆን መስራት ይኖርበታል።
የኮሪደር ልማቱ እንቅስቃሴዎች ሕዝቡ ከከተሞቹ ትሩፋት እንዲጠቀም፣ ከተሞቹ እንዲያድጉ፣ የሥራ ፈጠራ ማዕከላት፣ የመናፈሻ ማዕከላት እንዲሆኑ ያግዛሉ። በሌሎች ከተሞችም ሁለተኛ ዋና ከተማ፣ ሦስተኛ ዋና ከተማ በሚል የቱሪዝም፣ የንግድ፣ የማምረቻ፣ የመናፈሻ ማዕከላት እንዲሆኑ የየራሳቸውን ሚና ሊጫወቱ ይገባል።
አዲስ ዘመን፦ ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ እናመሰግናለን።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም