አዲስ አበባ:- አካል ጉዳተኞችን በተመ ለከተ በመንግሥት በኩል ተነሳሽነቱና ፍቃደኝነቱ ቢኖርም አሁንም በሚፈለገው ደረጃ ትኩረትና እንክብካቤን እያገኙ አለመሆኑ ተገለፀ።
“የሁሉም አካል ጉዳተኞች በጎ አድራጎት ማህበር” ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ገብረመድህን ገብረሥላሴ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት ኢትዮጵያዊያን አካል ጉዳተኞችን በተመ ለከተ መንግሥት የሕግ ማእቀፎችን በማውጣት እየሠራና ለሚሠሩትም ደን ብና መመሪያዎችን በማስቀመጥ ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ ቢሆንም አሁንም የአካል ጉዳተኞችን ችግር በአግባቡ መፍታት አልተቻለም፡፡
ለምሳሌ በአገራችን አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ የመሰረተ ልማት ሥራዎች እንዲከናወኑ በሕጎችና መመሪያዎች ላይ ቢሰፍርም በአተገባበሩ ላይ ችግሮች ይታያሉ። በየመንገዱ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያላደረጉ ቁፋሮዎችና ግንባታዎች፤ የመንገድ ዳር ምልክቶች አለመኖር፣ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ያልሆኑ የህንፃ መሠረተ ልማቶች፣ ወዘተ አሁንም ያልተቀረፉ ችግሮች ናቸው፡፡
በሌላም በኩል የትምህርት፣ የሥራ ዕድልና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ያልሆኑ በርካታ አካል ጉዳተኞች በአገሪቱ እንደሚገኙም ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ገብረ መድህን ይናገራሉ።
እስካሁን ድረስ ከቤት ያልወጡ፤ በልመና ተግባር ላይ የተሰማሩ፣ የማህበ ራዊም ሆነ ሌሎች አገልግሎቶች ተጠ ቃሚ ባለመሆናቸው በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ አካል ጉዳተኞች አሉ የሚሉት የማህበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ መንግሥትም ሆነ በዘርፉ ለመሥራት የተሰማሩ ያገር ውስጥና የውጭ አገር ድርጅቶች እነዚህን ወገኖች ከቤት ሊያወጧቸው፣ በአገሪቱ በሚገኙት ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ተሳታፊና ተጠቃሚ ሊያደርጓቸው ይገባል በማለት ተናግረዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለፃ አካል ጉዳተኞች ከማህበረሰቡ ጀምሮ እስከ መንግሥ ታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ድጋፍና እንክብካቤ ከተደረገላቸው፣ ስልጠና ካገኙና የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው እንደማንኛውም ሰው ሠርተው ራሳቸውን፣ አገራቸውንና ማህበረሰቡን መጥቀም ይችላሉ፤ ለዚህም የተለያዩ ሰዎችን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።
“የሁሉም አካል ጉዳተኞች በጎ አድራጎት ማህበር” በተለያዩ ምክንያቶች የአካል ጉዳት በደረሰባቸው ወገኖች መካከል ምንም አይነት ልዩነት ሳይፈጥር፤ ማየት የተሳናቸው፣ መስማት የተሳናቸው. . . ፤ ህፃናት፣ አረጋዊ፣ ወንድ፣ ሴት ሳይል ሁሉንም በአንድነት በማየት ለሁሉም እኩል አገልግሎቶችን ይሰጣል ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ በዚህ አሠራሩም በርካቶችን ወደ አምራች ዜግነት በመቀየር ከራሳቸውም አልፈው አገራቸውን እንዲጠቅሙ ማድረጉንም ተናግረ ዋል።
ይህ በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ መብቶች ለማስከበር፣ እነዚህኑ ወገኖች በተመለከተም የሚስተዋለውን የተዛባ አመለካከት በማስወገድ የጉዳተኞቹን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረ ጋገጥና የአኗኗር ሁኔታቸውን ለማሻሻል በማሰብ በተወሰኑ አገር ወዳድ ሰዎች በ2006 ዓ.ም የተመሰረተው ይህ በጎ አድራጎት ማህበር አካል ጉዳተኞችን በማብቃትና ራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግ ላበረከተው አስተዋጽኦ፤ በተለይም በድህነት ቅነሳው በኩል ላከናወናቸው ተግባራት ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ምስጋና እንዳገኘና የተለያዩ ድጋፎችም እንደተደረጉለት ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2011
ግርማ መንግሥቴ