ስፖርትን ለታላቅ የበጎ አድራጎት ሥራ የተጠቀመ ተቋም

ዓለም የተራቀቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በየቀኑ እየተመለከተች ባለችበት በዚህ ዘመን፣ መከራዋና ሰቆቃዋም እየበዛ ነው። በየቦታው የሚፈጠሩ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች ሕዝቦቿን ለስቃይና መከራ መዳረጋቸውን ቀጥለዋል። እነዚህ ችግሮች ከሚፈጥሯቸው ማኅበራዊ ቀውሶች መካከል አንዱ የጎዳና ተዳዳሪነት ነው። የጎዳና ተዳዳሪነት በኢትዮጵያም ተንሰራፍቶ የሚታይ ማኅበራዊ ቀውስ ነው። በኢትዮጵያ በ11 ዋና ዋና ከተሞች ከ89ሺ በላይ ጎዳና ተዳዳሪዎች እንዳሉና ከእነዚህም ውስጥ ከ55ሺ በላይ የሚሆኑት በአዲስ አበባ እንደሚገኙ ከአራት ዓመታት በፊት ይፋ የተደረገ መረጃ ያሳያል፡፡

ችግሩን ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶችም ስር ነቀል ለውጥ ማስመዝገብ አልቻሉም። በችግሩ ምክንያት የሚፈጠሩ ቀውሶች ቤተሰብን፣ ህብረተሰብንና ሀገርን ብዙ ዋጋ እያስከፈሉ ነው። ይህ አደገኛ ችግር ያሳሰባቸው በጎ አሳቢ ዜጎች፣ ችግሩ ከዚህ የበለጠ ቀውስ እንዳያስከትል በየጊዜው የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ይስተዋላል። የበጎ አድራጎት ተቋማትን በማቋቋም የሚከናወኑ ምግባረ ሰናይ ተግባራት ከእነዚህ እንቅስቃሴዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

በኢትዮጵያ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ምግባረ ሰናይ ዓላማዎችን አንግበው የተቋቋሙና የሚንቀሳቀሱ በርካታ የበጎ አድራጎት ተቋማት አሉ። እነዚህ ተቋማት የተቸገሩ ወገኖች ድጋፎችን እንዲያገኙ በማድረግ ድጋፍ የተደረገላቸው ዜጎች የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው በማስቻል ሞራልና ማኅበራዊ ፍትሕ የሰፈነበት ማኅበረሰብና ሀገር ለመገንባት ቀላል የማይባል ሚና ይጫወታሉ።

እነዚህ የበጎ አድራጎት ተቋማት በተለያዩ መንገዶች የሚመሰረቱ ሲሆን፣ ዓላማቸው በተለያዩ ምክንያቶች የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ ከችግሮቻቸው እንዲላቀቁ መርዳት ነው። ለአብነት ያህል ለስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የተሰባሰቡ ግለሰቦች በስፖርት አካልንና አዕምሮን ለመገንባት ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ስፖርታዊ መሰባሰባቸውን የተቸገሩ ወገኖችን ለመርዳት ሲጠቀሙበትም ይስተዋላል። በዚህ መንገድ ተመስርተው የብዙ ዜጎችን ሕይወት የታደጉ በጎ ተግባራትን የሚያከናውኑ የበጎ አድራጎት ተቋማት አሉ።

ከእነዚህ ተቋማት መካከል አንዱ ከአምስት ዓመታት በፊት የተመሰረተው ‹‹ጳጉሜን አምስት (፭)›› የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው። የ‹‹ጳጉሜን አምስት (፭)›› የበጎ አድራጎት ድርጅት መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ማስተር ኤርሚያስ ገሰሰ እንደሚገልፁት፣ ድርጅቱ ሕጋዊ እውቅናና ፈቃድ ያገኘው በ2011 ዓ.ም ቢሆንም፣ እሳቸው የበጎ አድራጎት ሥራ መሥራት የጀመሩት ግን የማርሻል አርት ስልጠና መስጠት ከጀመሩበት ከ1995 ዓ.ም አንስቶ ነው።

ሥራውን እንዲጀምሩ ካነሳሷቸው ምክንያቶች አንዱ እሳቸው ያጠኑት የስፖርት ዓይነት፣ ከማርሻል አርት ጥበቦች መካከል አንዱ የሆነው፣ ጅት ኩን ዶ (Jeet Kune Do) እንደሆነ ይገልፃሉ። ‹‹ይህ የማርሻል አርት ክዋኔ ተፈጥሯዊ ጥበብን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል (ራስን ማወቅ፣ መግለፅና መሆን) የሚያስተምር ነው ይላሉ።

‹‹እነዚህን ነገሮች የተገነዘበና የተረዳ ሰው ከራሱ አልፎ ለራሱና ለሌላው ዜጋ ያስባል። እኔ የማስተምረው የተማሪ ስብስብ ብዛትና ያለው አቅም ከፍተኛ ነው። ይህን ስብስብ አዎንታዊ በሆነ መልኩ እንዴት ለሀገር ጥቅም ማዋል በሚቻልበት ላይ አሰብኩ። ከሕፃናት እስከ አዋቂዎች ብዙ ተማሪዎች ስለነበሩ ተማሪዎቹን በማሰባሰብ ይህን ኃይል ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም ማድረግ ወሳኝ ተግባር ነበር። ስብስቡ ጉልበት፣ እውቀትና ሙያ ያለው በመሆኑ ምን ብናደርግ ነው ለሀገር ጥቅም ልናውለው የምንችለው ብዬ አስብ ነበር።

ጎዳና ላይ የሚኖሩት ወገኖች እጅግ አሳዛኝ በሆነ ሕይወት ውስጥ ነበሩ። በየዕለቱ በጎዳናዎች ላይ የምናያቸው ጎዳና ተዳዳሪዎች የብዙ ችግሮቻችን መገለጫዎች ናቸው። የጎዳና ተዳዳሪዎቹን ከስፖርቱ ሰልጣኞች ጋር በማቀናጀትና ድጋፍ በማድረግ ከችግራቸው ማውጣት እንደሚቻልም አመንኩ። ይህን ሃሳብ ለሰልጣኞቹ ሳቀርብላቸው ሰልጣኞቹ ሃሳቤን በደስታ ተቀበሉት። ወቅቱ የትንሳዔ በዓል የደረሰበት ጊዜ ስለነበር፣ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለጎዳና ተዳዳሪዎች ድጋፍ በማድረግ የበጎ አድራጎት ሥራውን ጀመርን›› በማለት ስለበጎ አድራጎት ሥራቸው አጀማመር ያስታውሳሉ።

ስለድርጅቱ ስያሜ ሲስረዱ ደግሞ፣ ‹‹ጳጉሜን በአዲሱና በአሮጌው ዓመት መካከል የምትገኝ ድልድይና የተስፋ ወር ናት። ከዚህ በተጨማሪም ጳጉሜን ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ብቸኛዋ የ13 ወራት ፀጋ ባለቤት እንድትሆን ያስቻለች ልዩ መለያ ናት። እኛም እንደ ጳጉሜን ድልድይ ሆነን ወጣቶቹ ከአስከፊው የጎዳና ተዳዳሪነት ሕይወት ተላቀው ወደ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ እንዲሸጋገሩ ድጋፍ እናደርጋለን በሚል እሳቤ እንዲሁም የጳጉሜን ልዩ መገለጫነት እንደ መታሰቢያ ለመጠቀም በማሰብ የድርጅቱ ስያሜ ‹ጳጉሜን አምስት (፭)› እንዲሆን ተደርጓል›› በማለት ያብራራሉ።

‹‹ጳጉሜን አምስት (፭)›› የበጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ትኩረቱ ጎዳና ላይ የሚኖሩ ወጣቶች ናቸው። እነዚህን ወጣቶች ከጎዳና ላይ በማንሳት ቤት ተከራይቶ መጠለያ፣ ምግብ፣ አልባሳት፣ የቤት ቁሳቁስና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን የማቅረብ፤ የሥነ ልቦና ስልጠና የመስጠት፣ የትምህርትና የሥራ እድሎችን የማመቻቸት አገልግሎቶችን ይሰጣል። ቀደም ሲል ድጋፍ የሚያደርገው ወጣቶቹ ባሉባቸው አካባቢዎች (በጎዳናዎች ላይ) ነበር።

‹‹ጳጉሜን አምስት (፭)›› እስካሁን ባከናወናቸው የበጎ አድራጎት ሥራዎች አማካኝነት ከ10ሺ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደቻለ ማስተር ኤርሚያስ ይናገራሉ። ‹‹የመጠለያ፣ የምግብና የአልባሳት አቅርቦት፣ የትምህርት፣ የማዕድ ማጋራት፣ የሥራ እድል ፈጠራና የሥነ ልቦና ስልጠና አገልግሎቶችን ሰጥቷል። በድርጅቱ ድጋፍ የተደረገላቸው ወጣቶች በተፈጠረላቸው የሥራ እድል አማካኝነት የሙያ ክህሎታቸውን አሳድገዋል። በመንፈሳዊ ሕይወታቸውም (እንደ የእምነታቸው) በጣም ጠንካራ የሆኑ ወጣቶች አሉ። በድርጅቱ ድጋፍ ለተሻለ ሕይወት የበቁ ወጣቶችን በመሸለም፣ ሌሎች የጎዳና ተዳዳሪዎችም ተስፋ እንዲኖራቸውና እንዲበረታቱ እናደርጋለን›› በማለት ያብራራሉ። ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ቤት ተከራይቶ ለ30 ልጆች ቋሚ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በቀጥታ ከድርጅቶች የምናገኘው ቋሚ ድጋፍ የለም። የድርጅቱ መርህ ‹‹የራስን ችግር በራስ አቅም መፍታት›› ነው። ዓላማውና መነሻው እንደሌሎች ድርጅቶች ከውጭ ተቋማት የሚገኝን ገንዘብ ለመጠቀም አይደለም። ድርጅቱ ገንዘብ የሚያገኘው በተቻለ አቅም ከመንግሥት አካላት ጋር በመቀናጀት በተለያዩ አካባቢዎች (መንገዶች ላይ) በመዘዋወር ስለድርጅቱ ገለፃ በማድረግ ለጋሾችን ድጋፍ እንዲያደርጉ በመጠየቅ፣ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ አካላት በሚያደርጉት ድጋፍ እንዲሁም ከአባላት በሚሰበሰብ መዋጮ ነው።

‹‹ትያትር ቤቶች የአንድ ቀን ገቢያቸውን እንዲሰጡን በማድረግ ገቢ እናገኛለን። እኔ ተማሪዎችን የማሰለጥንበት ስፖርት ቤት ማስ ስፖርት አዘጋጅቶ ቲሸርት ይሸጣል፤ ከሽያጩ የሚገኘው ገቢ ለበጎ አድራጎት ድርጅቱ ገቢ ይሆናል። በአጠቃላይ ገንዘብ የምናገኘው በሀገር ውስጥ ከምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ነው። አርቲስቶች፣ ደራሲያን፣ ስፖርተኞች፣ ጋዜጠኞችና ሌሎች ባለሙያዎች የበጎ አድራጎት የድርጅቱ የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ሆነው ይሰራሉ›› በማለት ስለድርጅቱ የገንዘብ ምንጭ ያስረዳሉ።

‹‹ጳጉሜን አምስት (፭)›› የበጎ አድራጎት ድርጅት ሥራዎቹን ሲያከናውን ስለሚያጋጥሙት ችግሮችም ማስተር ኤርሚያስ ያስረዳሉ። ‹‹መንግሥት ለበጎ አድራጎት ሥራዎች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎችንና አሠራሮችን ቢዘረጋም፣ በየደረጃው ያሉ አንዳንድ የመንግሥት አካላት ለሥራዎቹ ተባባሪ የማይሆኑባቸው ጊዜያት አሉ። ለአብነት ያህል ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራዎችን በምናከናውንበት ወቅት አንዳንዶቹ ተቋማትና የሥራ ኃላፊዎች ፈቃድ ይሰጣሉ፤ አንዳንዶቹ ግን ሥራውን እንዳናከናውን ይከለክላሉ። ድጋፍ የሚደረግላቸው ግለሰቦች የግል ፀባይም ሌላው ችግር ነው። ግለሰቦቹ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ወደ ጎዳና ወጥተው አስከፊ ሕይወት ያሳለፉ በመሆናቸው አስተሳሰባቸውን ለመቀየር ጊዜ ያስፈልጋል። አንዳንድ ጊዜ ብዙ ገንዘብ፣ ጊዜና ጉልበት አውጥተን ወደ መደበኛ ሕይወት ለመመለስ ብዙ የደከምንባቸው ግለሰቦች ተመልሰው ወደ ጎዳና ሊወጡ ይችላሉ›› ይላሉ። የመጠለያ ችግር ሌላው ተግዳሮት እንደሆነም ይናገራሉ።

‹‹ጳጉሜን አምስት (፭)›› የበጎ አድራጎት ድርጅት ላከናወናቸው ምግባረ ሰናይ ተግባራት ከቦሌ ክፍለ ከተማና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እውቅናዎችንና ሽልማቶችን አግኝቷል። ‹‹ድርጅቱ የራሱ ግቢ ኖሮት ሴቶች በባልትና ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ (እንጀራ፣ ሽሮ፣ ቆሎ፣ ቅመማ ቅመም … እንዲያዘጋጁና የገበያ እድል ተመቻችቶላቸው ምርቶቻቸውን በየቤቱ እየዞሩ እንዲያከፋፍሉ…)፣ ወንዶቹ ደግሞ በብሎኬት ማምረት ሥራ ላይ እንዲሰማሩ እንዲሁም ድርጅቱ የራሱ ማዕከል ኖሮት ወጣቶቹ በማዕከሉ ውስጥ የከተማ ግብርና ሥራዎችን በመሥራት የገቢ ምንጭ እንዲያገኙ የማድረግ እቅድ አለው›› በማለት ስለድርጅቱ እቅዶች ይናገራሉ።

ማስተር ኤርሚያስ የበጎ አድራጎት ተግባራት ከዕለታዊ ርዳታ ተሻግረው በግለሰቦች ሕይወትና በማኅበረሰብ ገፅታ ላይ ዘላቂ ለውጥ እንዲያስገኙ ኅብረተሰቡ፣ የበጎ አድራት ተቋማት፣ ድጋፍ ፈላጊዎችና መንግሥት የየራሳቸው ኃላፊነቶች እንዳሉባቸው ያስገነዝባሉ።

እሳቸው እንደሚሉት፣ ህብረተሰቡ በተናጠል የሚያደርገውን ድጋፍ ተቋማዊ በሆነ መልኩ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንዲያበረክት መበረታታት አለበት። በተናጠል የሚደረጉ ድጋፎችን በኅብረት በማድረግ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች በተሻለ አቅም ተደራሽ ማድረግ ይቻላል። በተናጠል የሚደረጉ ድጋፎች ዕለታዊ/ የአጭር ጊዜ ፋይዳ ቢኖራቸውም ዘላቂ መፍትሔ መሆን አይችሉም፡፡

ድጋፍ የሚደረግላቸው አካላት ደግሞ ድጋፍ አድራጊ ግለሰቦችና ተቋማት መነሻ የሚሆን ድጋፍ ካደረጉላቸውና መንገዱን ካመለከቷቸው የራሳቸውን ጥረት ጨምረው መንገዱን ተከትለው ከችግሮቻቸው ለመውጣት መጣር አለባቸው።

መንግሥት ደግሞ የማኅበረሰብን ችግሮች ለማቃለል ለሚጥሩ የበጎ አድራጎት ተቋማት ክትትል በማድረግ ድጋፍ መስጠት ይኖርበታል። ብዙ ግለሰቦችና ተቋማት የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ጀምረው ሲያቋርጡ ይስተዋላል። ለዚህ ችግር አንዱ ምክንያት በመንግሥት አካላት በኩል የሚታየው የድጋፍና ክትትል ማነስ ነው። ስለሆነም የበጎ አድራጎት ተግባራት ድጋፍ የሚደረግላቸውን አካላት ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት በሚያስችል መልኩ እንዲሰሩ መንግሥት ተገቢውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You